>

አቶ ሽመልስ "አንድም ጋዜጠኛ…" የሚሏትን ቃል መቼ ይሆን የሚያቆሟት? [ጋዜጠኛ ኤሊያስ ገብሩ]

(‹‹ፕሬስ ከተጀመረ ጀምሮ የተሰደዱ ጋዜጠኞችን በሙሉ፣
በአንድ ቅርጫት ውስጥ አይክተቱ›› እልዎታለሁ፤ ስህተት ነውና!)
——————————————————–

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሚኒስትር ደኤታ የሆኑት አቶ ሽመልስ ከማል የኢትዮጵያ የግል ፕሬስ እና በዚያ የሚሰሩ ጋዜጠኞች ላይ ችግር ሲከሰት እና ይህንንም ተከትሎ ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጡ ወይም ጉዳዮቹን ተከትሎ ከተለያዩ ሚዲያዎች ለዘገባ ጥያቄ ሲቀርብላቸው በሚሰጡት ምላሽ ውስጥ ‹‹አንድም ጋዜጠኛ…›› የምትል ቃል ከአፋቸው አትጠፋም፡፡ ቃሏን ሁሌም በሰማኋት ቁጥር ፈገግ ታስደርገኛለች – ሁሌም ያው ስለሆነች፡፡

ምሳሌ ላቅርብ፣ በጸረ-ሽብርተኝነት አዋጁ አማካኝነት ክስ ከቀረበባቸው ከእነጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ ጀምሮ እስከእነተስፋለም ወልደየስ፣ አስማማው ኃይለጊዮርጊስና ኤዶም ካሳዬ ድረስ ተጠርጥረው ሲያዙ ‹‹ከጋዜጠኝነት ሙያው ጋር የታሰረ አንድም ጋዜጠኛ የለም››፣ ‹‹በጻፈው ጽሑፍ የታሰረ አንድም ጋዜጠኛ የለም›› ብለው ነበር፡፡
ዛሬም ለንባብ በበቃው ‹‹አዲስ አድማስ›› ጋዜጣ፣ በፊት ለፊት ገጹ ላይ ‹‹መንግሥት አንድም የተሰደደ ጋዜጠኛ የለም አለ›› በሚል ርዕስ ፍትህ ሚኒስትር በስድስት መጽሄቶች እና አንድ ጋዜጣ ላይ ክስ መመስረቱን እና ማተሚያ ቤቶች በተለያየ ምክንያት የግል ሕትመቶችን አናትምም በማለታቸው ተከትሎ ሰፋ ያለ ዜና ቀርቦ ነበር፡፡ አቶ ሽመልስ በመንግሥት በኩል ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተው ነበር፡፡ ሚኒስትር ደኤታ፣ አንድም የተሰደደ ጋዜጠኛ እንደሌለ አስታውቀው ‹‹በሙያው ምክንያት በደረሰበት ጫና አንድም የተሰደደ ጋዜጠኛ የለም›› ብለዋል፡፡ ‹‹በሀገሪቱ የፕሬስ ሥራ ከተጀመረ አንስቶ አንድም የተሰደደ ጋዜጠኛ የለም፤ …አሁን ተሰድደናል የሚሉ ግለሰቦች ሙያውን የኢኮኖሚ ጥገኝነት መጠየቂያ እያረጉት ነው …፡፡›› ሲሉም አክለዋል፡፡
‹‹በሀገሪቱ የፕሬስ ሥራ ከተጀመረ አንስቶ አንድም የተሰደደ ጋዜጠኛ የለም፡፡›› በሚለው የአቶ ሽመልስ ምላሽ ላይ ጉንጭ አልፊ ክርክር ውስጥ መግባት አልፈልግም፡፡ ምክንያቱም በሙያቸው ምክንያት ጫና ደርሶባቸው ከኢትዮጵያ የተሰደዱት ጋዜጠኞች እንግዲህ ዓለም ይቁጠራቸው፡፡ ለጋዜጠኝነት ሙያ በቂ እውቀት፣ ችሎታ፣ ተሰጥኦና አቅም ኖራቸው ወደሃገራቸው መመለስ ዘወትር እየናፈቁ፣ ነገር ግን ሳይችሉ ቀርተው በስደት ዓለም የሚኖሩ ክብር የምሰጣቸው ወገኖቼ አሉ፡፡ [ከተወሰኑት ጋር ጥሩ ቀን በሀገራችን መጥቶ አብሬያቸው ብሰራ ብዬ እሻለሁ፡፡] ቤተሰቦቻችውን በትነው እና ትተው፣ ዘመድ፣ ጓደኞቻቸውን፣ የሚወዷትን ሀገርና ቢሰሩት የሚሹትን ሙያ ትተው በየሀገሩ ተበታነው በሚኖሩ ኢትዮያውያን ጋዜጠኞች ምንም ሳይደርስባቸው መሰደዳቸውን በጅምላ ጠቅልሎ መናገር ተገቢ አይመስለኝም፡፡ ለእነዚህ ወገኖቻችን ሞራልም መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡
‹‹በሀገሪቱ የፕሬስ ሥራ ከተጀመረ አንስቶ አንድም የተሰደደ ጋዜጠኛ የለም፡፡›› ብሎ ሁሉንም በአንድ ቅርጫት ውስጥ ማስቀመጥ በየትኛም ቀመር ቢኬድ እውነትነት የለውም፡፡ በታሪክ ፊትም ያስገምታል፤ ያስወቅሳል፡፡ ስህተት ነው ብዬ አምናለሁ!
‹‹…አሁን ተሰድደናል የሚሉ ግለሰቦች ሙያውን የኢኮኖሚ ጥገኝነት መጠየቂያ እያረጉት ነው›› የሚለውም የአቶ ሽመልስን መልስ በአንክሮ ሳሰላስለው ሚዛን የማይደፋ ሆኖ ባላገኘውም አንድ ከህሊናዬ የማልክደው ሀቅ ግን አለ፡፡ ጫና ደርሶባቸው እና ክሱ በቀጥታ መጥቶባቸው ‹‹በሀገር ቤት ብንሆን ምን ይገጥመን ይሆን? ምንስ እናገኛለን? ምንስ እንሰራለን…›› በማለት በሀገራቸው መስራት ፈልገው መስራት ሳይችሉ ቀርተው ከሀገር የተሰደዱ እንዳሉ ሁሉ፣ ኮሽ ያለውን ነገር ተከትከውና ይሄንን አጋጣሚ ተመርኩዘው (በቀጥታ እነሱ ላይ ያነጣጠረ አደጋ ወይም ስጋት ሳይኖር) በፍርሃት ከሀገር የወጡም እንዳሉም እረዳለሁ፤ ይህ የግል እምነቴ ነው፡፡ (በዚህ ሀሳብ መስማማትም አለመስማማትም መብት ነው፤ አከብራለሁ)
…ሲጀምር የጋዜጠኝነት ሙያ በምቾት ቀጠና ውስጥ ተኩኖ የሚሰራ ዘርፍ አይደለም፤ ብዙ ፈተናዎችን መጋፈጥ የግድ ይላል፡፡ በዚህ ወር እንኳ በሶሪያ ምድር ሁለት አሜሪካዊ ጋዜጠኞች ሞትን ያህል፣ ያውም አንገታቸው እንደሚቀላ እያወቁ ለሙያቸው ሲሉ ጽዋውን ቀምሰዋል፡፡ አንባገነን መንግሥታቶች በተፈራረቁባት እንደኢትዮጵያ ባሉ ሀገራት የጋዜጠኝነት ሙያ በብዙ ፈተና የታነቀ መሆኑን በቅድሚያ ማወቁ ተገቢ ይመስለኛል፡፡
ከዚህ አኳያ አሁን የተሰደዱት በሙሉ የኢኮኖሚ ጥገኝነት መጠየቂያ አለማድጋቸውን አቶ ሽመልስ ጠፍቷቸው አይመስለኝም – እንዲህ ማለት አለብኝ ካላሉ በስተቀር፡፡ ለነገሩ፣ አቶ ሽመልስ ከላይ የጠቀስኳትንና የሚወዷትን ‹‹አንድም …›› የምትለዋን ቃል ለመተው ካልወሰኑ በስተቀር ነገም ሌላ ነገር ሲፈጠር ይህቺን ቃል በድጋሚ መጠቀማቸው አይቀርም፡፡ ለነገሩ የቀድሞው ኢቴቪ በዜና እወጃው ላይ ‹‹በዚህ ጉዳይ ያነጋገርናቸው “አንዳንድ” የአዲስ አበባ፣ የባህርዳር፣ የናዝሬት፣ የሐዋሳ … ከተማ ነዋሪዎች …›› ይለን የለ?

(ኢትዮ ሪፈረንስ  ሙሉው የኣዲስ ኣድማስ ዘገባ ቀጥሎ ይገኛል)

መንግስት አንድም የተሰደደ ጋዜጠኛ የለም አለ

ክስ ያልተመሰረተባቸው ጋዜጦችና መፅሄቶች የሚያትምልን አጣን አሉ
“ማተሚያ ቤቶች አናትምም ማለታው ሊያስመሰግናቸው ይገባል” አቶ  ሽመልስ ከማል

ፍትህ ሚኒስቴር በ6 የግል ሚዲያ ተቋማትና ባለቤቶቻቸው ላይ ክስ መመስረቱን ተከትሎ  16 የሚደርሱ አሳታሚዎችና ጋዜጠኞች አገር ለቀው የወጡ ሲሆን መንግስት በበኩሉ፤ አንድም የተሰደደ ጋዜጠኛ እንደሌለ አስታወቀ፡፡
የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሽመልስ ከማል በተለይ ለአዲስ አድማስ በሰጡት ቃለ ምልልስ፤ በሙያው ምክንያት በደረሰበት ጫና አንድም የተሰደደ ጋዜጠኛ የለም ብለዋል፡፡
“በአገሪቱ የፕሬስ ስራ ከተጀመረ አንስቶ አንድም የተሰደደ ጋዜጠኛ የለም” ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ አሁን ተሰደናል የሚሉ ግለሰቦች ሙያውን የኢኮኖሚ ጥገኝነት መጠየቂያ እያደረጉት ነው እንጂ መንግስት በጋዜጠኞች ላይ ምንም ዓይነት ክስ አላቀረበም ብለዋ -፡ ክሱ በአሣታሚዎችና ባለቤቶች ላይ የቀረበ መሆኑን በመጠቆም፡፡
ተሰደዱ የተባሉት ጋዜጠኞች የጋዜጠኝነት ስነ ምግባር ያላቸው አይደሉም ያሉት አቶ ሸመልስ፤ “ያልተከሰሰ ሰው ምን አገኘኝ ብሎ ነው የሚሰደደው?” ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ ለኢኮኖሚ ጥገኝነት ሲል ከአገር የወጣ ሁሉ ተሰደደ ሊባል እንደማይችልም አስረድተዋል፡፡
በሌላ በኩል ክስ ያልተመሰረተባቸው አንዳንድ የግል ፕሬሶች የሚያትምላቸው ማተሚያ ቤት በማጣት ከገበያ ውጪ ለመሆን መገደዳቸውን የገለፁ ሲሆን መንግስት በበኩሉ፤ በአታሚዎችና አሣታሚዎች መሃል ጣልቃ መግባት እንደማይችል አስታውቋል፡፡
ዘወትር ማክሰኞ የሚወጣው “ኢትዮ ምህዳር” ጋዜጣን ጨምሮ ከሁለት ሣምንት ህትመት በላይ መዝለቅ ያልቻለው “ቀዳሚ ገጽ” ጋዜጣ እንዲሁም “ማራኪ” እና “ቆንጆ” የተሰኙ መጽሔቶች ቀድሞ የሚያሳትሙባቸው ማተሚያ ቤቶች የተለያዩ ምክንያቶችን በማቅረብ አናትምም እንዳሏቸው ጠቁመው ሌሎች ማተሚያ ቤቶችም ሊያትሙላቸው እንዳልቻሉ ገልፀዋል፡፡
የ“ኢትዮ – ምህዳር” ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ስለ ጉዳዩ ሲያብራራ፤ ከሁለት ሣምንት በፊት ትወጣ የነበረችውን ጋዜጣ ሙሉ ስራ አጠናቆ ሁልጊዜ ወደሚያሳትምበት ማተሚያ ቤት ቢልክም ማተሚያ ቤቱ ምክንያቱን በግልጽ ሳይናገር ማተም አልችልም እንዳለው ጠቁሞ፤ በሌሎች የግል ማተሚያ ቤቶች ቢሞክርም ተመሳሳይ ምላሽ ማግኘቱን ተናግሯል፡፡
አንዳንድ ማተሚያ ቤቶች “ማሽን ተበላሽቶብናል፣ መንግስት በምናትመው ጉዳይ ተጠያቂ ሊያደርገን ይችላል” የሚሉ ምክንያቶች እንዳቀረቡላቸው የገለፁት የህትመቶቹ ባለቤቶች፤ “በሙያችን ሠርተን ለማደር ተቸግረናል” ሲሉ አማረዋል፡፡
በማተሚያ ቤት በኩል የገጠማቸውን ችግር አዲስ በተቋቋመው “ዋቢ የግል ፕሬስ አሳታሚዎች ማህበር በኢትዮጵያ” በኩል ለሚመለከተው የመንግስት አካል አቤቱታ ማቅረባቸውን የጠቆሙት አሣታሚዎቹ፤ ምላሹን በመጠባበቅ ላይ እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡
የአሣታሚዎች ማህበር ሊቀመንበር አቶ አማረ አረጋዊ በበኩላቸው፤ ችግራቸውን ለመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሽመልስ ከማል ማሳወቃቸውንና በጉዳዩ ላይ ለመወያየት ሚኒስትሩ ምቹ ጊዜ እስኪያገኙና ጠርተው እስኪያነጋግሯቸው እየጠበቁ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሚኒስትር ዲኤታ አናትምም አሉ ስለተባሉት ማተሚያ ቤቶች ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ፤ የትኛውም ማተሚያ ቤት ለትርፍ የተቋቋመ የንግድ ኩባንያ መሆኑን ጠቁመው፤ “ከጋዜጣ ህትመት ይልቅ ሌላ ስራ ያዋጣናል ካሉ ያንን መምረጥ መብታቸው ነው፤ መንግስት ጣልቃ ገብቶ ማተም አለባችሁ ወይም ለምን ታትማላችሁ የማለት መብት የለውም” ብለዋል፡
ዜጐች በንግድ የመዋዋል መብታቸው የተጠበቀ ነው ያሉት አቶ ሽመልስ፤ ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤትም ቢሆን አትራፊ የልማት ኩባንያ ስለሆነ የሚያዋጣውን ራሱ ነው የሚያውቀው ብለዋል፡፡
“የአክራሪነት አጀንዳ ወይም ከህብረተሰቡ ባህልና ወግ ያፈነገጡ ሃሳቦች ያለውን ጽሑፍ ማተም አልፈልግም ካለ መብቱ ነው” ያሉት ዴኤታው፤ በዚህ ጉዳይ ላይ መንግስት ጣልቃ ገብቶ ምንም ሲል እንደማይችል ተናግረዋል፡፡

Filed in: Amharic