>
5:13 pm - Thursday April 19, 0660

ደቡብ ክልል፤ የፌዴራሊዝሙ ስኬትና ውድቀት መበየኛ! (በፍቃዱ ዘ ሀይሉ)

ደቡብ ክልል፤ የፌዴራሊዝሙ ስኬትና ውድቀት መበየኛ!

በፍቃዱ ዘ ሀይሉ

በኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም ውስጥ የመጀመሪያው እና ጉልህ የማንነት ጥያቄ የተስተናገደው በደብብ ክልል ነው፤ ይኸውም የስልጤ ከጉራጌ ዞን መነጠል ነው። በወቅቱ “ጉራጌ አይደለንም፤ ስልጤ ነን” የሚለው የማንነት ሙግት ለፖለቲካ ውይይቱ እንግዳ ከመሆኑ የተነሳ በቅርብ ለማያውቁት በጣም አስደንጋጭ የነበረ ቢሆንም፥ በውጤቱ የፌዴራሊዝሙ ቀራጮች ኮርተውበት ነበር። ከዚህ በተለየ ፌዴራሊዝሙ መጀመሪያ የተፈተነበት አጋጣሚ እዚያው ደቡብ ክልል ውስጥ በወጋጎዳ ጉዳይ ነው። “ወጋጎዳ” የወላይታ፣ ጋሞ፣ ጎፋ እና ዳውሮ ቋንቋዎችን አዳቅሎ የትምህርት መጽሐፍትን ለማሳተም የተደረገው ሙከራ ነበር፤ በማኅበረሰቡ አባላት የዘውግ ቡድኖችን በአንድ ቅርጫት እንደመጨፍለቅ ሙከራ ተቆጥሮ በከፍተኛ ተቃውሞ ከሽፏል። ከዚያም በላይ እስከ ዛሬ የጥናት ርዕሰ ጉዳይ ሆኗል። ከዚያ በኋላ በክልሉ ውስጥ በርካታ የዞንነት እና የልዩ ወረዳነት ጥያቄዎች ተስተናግደዋል።
የሲዳማ ሕዝበ ውሳኔ ደቡብ ክልልን በሦስት መልክዓ ምድራዊ ግዛቶች ከፍሎታል። ጌዴኦ ዞንን ከሌሎች የደቡብ ክልሎች ጋር የሚያያይዘው የሲዳማ ዞን ነበር። በርካታ የክልሉ ዞኖች በምክር ቤቶታቸው የክልልነት ጥያቄን ቢያፀድቁም፣ የክልሉ መንግሥት ጥያቄያቸውን ወደ ምርጫ ቦርድ እስካልመራላቸው ድረስ ሕዝበ ውሳኔ አያገኙም። ይህ በእንዲህ እያለ ነው ገዢው ፓርቲ ክልሉን ወደ አራት የመክፈል ዕቅድ ይዞ የተነሳው።
የደቡብ ክልል ስለ ኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም ምን ይነግረናል? አሁን የክልሉ መንግሥት “ሳይንሳዊ ጥናት” አስደርጌ መፍትሔ አምጥቻለሁ እያለ ያለው ክልሉን ወደ አራት የመክፈል መፍትሔስ ያዛልቅ ይሆን?
“የትንሿ ኢትዮጵያ” ተሞክሮ
የደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥት (ደቡብ ክልል) “ትንሿ ኢትዮጵያ” በመባል የሚጠራው ከሃምሳ በላይ የዘውግ ቡድኖችን በአንድ ክልልነት ያቀፈ ክልል ስለሆነ ነበር። “ትንሿ ኢትዮጵያ” ውስጥ የሚሆነው የትልቋን ኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታም ነጋሪ ሊሆን ይችላል። ለዚህም ነው ሁለቱ የፖለቲካ ኃይሎች (የብሔር ፌዴራሊዝሙን የሚደግፉት እና የሚቃወሙት) ደቡብ ክልል ውስጥ እየሆነ ባለው ጉዳይ ከምንም በላይ ቀልባቸው የሚማረከው።
ለደቡብ ክልል የሠራ ፖለቲካዊ መፍትሔ በኢትዮጵያም የመሥራት ዕድሉ ሰፊ ነው። በደቡብ ክልል ያልሠራ ፖለቲካዊ መፍትሔ ደግሞ በትልቋ ኢትዮጵያም የመሥራት ዕድሉ ጠባብ ነው። ንፅፅሩን ቀለል አድርጎ ለማሰብ የክልልነት ጥያቄን ከክልሎች የመገንጠል ጥያቄ ጋር ማመሳሰል ነው፤ የእርስ በርስ ግንኙነቱም ይሁን ቀጣይ እርምጃዎቹ የሚፈጥሩት ተፅዕኖ ላይ ያለውን መሠረታዊ ልዩነት ግን አብሮ መረዳት ያስፈልጋል። ባጭሩ፣ የክልሎች ከኢትዮጵያ የመገንጠል ጥያቄ ታናሹ የክልልነት ጥያቄ ነው። የክልልነት ታናሽ ደግሞ ዞንነት፣ ልዩ ወረዳነት እያለ ይቀጥላል።
ጋንቤላንና ቤኒሻንጉል ጉምዝም ተመሳሳይ ባሕሪ አላቸው። ሌሎቹ ክልሎችም ከአንድ በላይ የዘውግ ቡድኖች አሏቸው። ነገር ግን፣ ክልሎቹ ውስጥ በሕዝብ ብዛት አንዱ ቡድን ከሌሎቹ የበለጠ ስለሆነ ሌሎቹ የመዋጥ ዕድላቸው ሰፊ ነው። በአማራ እና በትግራይ ክልሎች አናሳ ቁጥር ያላቸውን ብሔረሰቦች በልዩ ክልልነት የማስተናገድ ልምዱ አለ። ፌዴራሊዝሙ ከሚታማባቸው ነገሮች አንዱ በክልሎች ውስጥ ያሉ አናሳ ቁጥር ያላቸውን ማኅበረሰቦች ልዩ ዞን ከመስጠት የተሻለ መፍትሔ ማምጣት ባለመቻሉ ነው።
 
መከፋፈል እና መዋሐድ
የደቡብ ክልል ከሽግግር መንግሥቱ ወዲህ ሲዋሐድ እና ሲፈርስ ነበር የከረመው። በሽግግር መንግሥቱ በቁጥር የሚለዩ 14 ክልሎች ነበሩት፤ ቁጥሮቹን አሁንም ድረስ የሚጠቀሙባቸው አሉ። ከነዚህ ውስጥ ከክልል 7 እስከ 11 ያሉት ሕገ መንግሥቱ ሲፀድቅ ወደ አንድ ተዋሕደው የደቡብ ክልልን የመሠረቱ አምስት ክልሎች ነበሩ። ነገር ግን በደቡብ ክልል ውስጥ የመከፋፈል እና መዋሐድ ጉዳይ ሲነሳ ተጠቃሹ ይሄ ብቻ አይደለም። በአንድ ወቅት ሰሜን ኦሞ የነበረው ኋላ ላይ ወላይታ፣ ዳውሮ፣ ጋሞ፣ ጎፋ እና ባስኬቶ ሆኖ ተከፋፍሏል።
የዛሬ ዐሥር ዓመት ገደማ የኮንሶ፣ ቡርጂ፣ ደራሼ እና አማሮ ወረዳዎች ተዋሕደው ሰገኔን ፈጥረው ነበር። ይህ በቅርብ ጊዜ ለምናስታውሰው እና ብዙ ግጭት ያስነሳውና የኮንሶ ባሕላዊ ንጉሥ መታሰርን ያስከተለ ቁጣ አምጥቶ ነበር። የኋላ ኋላ ይህም ስላልጠቀመ ኮንሶ ከሰገኔ እንዲነጠል ተደርጓል። በተመሳሳይ ጋሞ ጎፋ ደግሞ በጋሞ እና ጎፋ ወረዳዎች እንዲከፋፈል ተወስኗል።
የደቡብ ክልል ብዙ ጊዜ እየተከፋፈሉ መልሶ የመዋሐድ መለስ ቀለስ፥ የአስተዳደር ችግሩ ዘላቂ መፍትሔ እንዳልተገኘለት አመላካች ነው። ችግሩ አሁን መንግሥት በጥናት ደርሼበታለሁ ያለው ‘የአራት ክልል መዋቅራዊ መፍትሔስ ምን ያህል ያዛልቃል?’ የሚለው ነው። በመሠረቱ ከዐሥር በላይ ዞኖች የክልልነት ጥያቄ ካቀረቡ በኋላ፥ በጥናት የቀረበ መዋቅር ለመቀበል ፈቃደኛ ይሆናሉ ተብሎ አይገመትም። የመጀመሪያው ቁም ነገር ሕዝባዊ ይሁንታ የሌለው መዋቅር መጫን መቼም ቢሆን ከቀውስ እንደይታደግ ማሰብ ነው።
በተለያዩ ምክንያቶች ምክረ ሐሳቡን ተስማምተው ተቀብለዋል ቢባል እንኳን፥ ክልሎቹ በተሰባበሩ ቁጥር ማዕከላዊው መንግሥት ላይ የሚያሳድረሩት ተፅዕኖ ይቀንሳል። ለምሳሌ ያክል ትልልቆቹ ክልሎች (ኦሮሚያ እና አማራ) ለአስተዳደር የቱንም ያህል የተመቸ መዋቅር ቀርቦ ወደ ሁለት ወይም ሦስት ተከፋፈሉ ቢባሉ ብዙዎቹ ይቃወማሉ። ምክንያቱም መከፋፈላቸው ማዕከላዊው መንግሥት ላይ የሚያሳድሩትን ተፅዕኖ ያሳንስባቸዋል። የደቡብ ክልል ዞኖች ግን ይህንን እያወቁም ቢሆን ክልልነትን ይመርጣሉ። ምክንያቱም ክልልነት የግዛቱ ባለቤት ያደርገናል ብለው ያስባሉ።
 
የክልሎች የግዛት ባለቤትነት ጉዳይ
የክልልነት፣ እንዲሁም የልዩ ዞንነት፣ እንዲሁም የልዩ ወረዳነት ጥያቄዎችን መበራከት ምክንያት የፈተሽን እንደሆነ የምናገኘው ቀላል መልስ ጠያቂዎቹ ክልልነትን (ወይም ልዩ ዞን እና ወረዳነትን) የሚረዱበትን የተለየ መንገድ መሆኑን እንረዳለን።
የፌዴራሉ እና የክልል ሕገ መንግሥቶች ከሞላ ጎደል ነዋሪዎቻቸውን በሙሉ እኩል ዕውቅና ይሰጣሉ። በልዩነት የቤኒሻንጉል ሕገ መንግሥት “የክልሉ መሥራቾች” በሚል የሰየማቸው የቋንቋ-ማኅበረሰብ አባላት አሉት፤ እንዲያም ሆኖ ሌሎቹም ነዋሪዎች እኩል መብት አላቸው ይላል። በተግባር ግን ክልሎች ባለቤት እንዳላቸው ነው የሚቆጠሩት። ከነርሱ ውጪ ያሉት በሙሉ እንደ መጤ ወይም እንግዳ ነው የሚታዩት። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ይህንን የተሳሳተ ግንዛቤ ለማረም ባንድ ወቅት “የአስተዳደር ወሰን እንጂ ማንኛውንም ኢትዮጵያዊ ከሌላው ክልል ለማገድ የተደረገ ድንበር አይደለም” በሚል ልዩነቱን ለማስረዳት ሞክረው ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ አስተያየታቸው እና ሌሎችም ያተረፉት ነገር ቢኖር “ፀረ-ፌዴራሊስት ናቸው” የሚል ቅጥያ ነው።
ፕሮፌሰር ክላፋም ‘ኮንትሮሊንግ ስፔስ ኢን ኢትዮጵያ’ በተባለው ጽሑፋቸው፣ “በአንድ ቡድን የተያዘ ግዛት፣ በሌላ አይያዝም” የሚል አስተሳሰብ እንዳለ ጽፈዋል። “ለረዥም ጊዜ የሰፈሩ እና ብዝኀዊ ስብጥር ባላቸው ሕዝቦች መካከል […] ግልጽ የግዛት መሥመር ተሰምሯል” ሲሉ ሐሳባቸውን ያጠናክራሉ። ወደ ታችኛው የመንግሥት አስተዳደሮች እርከን በወረደ ቁጥር ደግሞ ይህ አስተሳሰብ እና የልዩነት መሥመር እየጎላ ወርዶ ወረዳዎች እንደ “አግላይ የአንድ ዘውግ ምኅዳር” ይታያሉ። ይህ አስተሳሰብ የክልሎችን፣ የልዩ ዞኖችን፣ የልዩ ወረዳዎችን ጥያቄ ማለቂያ የሌለው ወራጅ ውኃ ያደርጋቸዋል።
 
ፌዴራሊዝሙ ለእነማን ነው የተሠራው?
ፌዴራሊዝሙ የተሠራው እና የሚሠራው ብዙ ሕዝብ ላላቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች ነው፤ ስለዚህ አነስተኛ ቁጥር ላላቸው ሕዝቦች አሥማሚ አስተዳደራዊ መዋቅር ማቅረብ በጣም ይቸግራል። የኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም ሥሪት እንደሚያመለክተው ከሆነ የሕዝብ ብዛት ላላቸው ብሔሮች የተሻለ የድርድር ዕድል ይሰጥና፥ አነስተኛ ቁጥር ያላቸውን ግን እንደ አጋር ይተዋቸዋል።
ክልልነት ጥቂት ቁጥር ላላቸው ብሔሮች ከሥም በስተቀር ፌዴራል መንግሥቱ ላይ ያላቸውን ተፅዕኖ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰው ነው የሚመጣው። የኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች ድርድር ከ60% በላይ የሚሆን የፌዴራል መንግሥቱን ሥልጣን ወይም ውሳኔ የሚያስገኝ ሲሆን፣ ደቡብ ክልል በሦስተኝነት ተጠቃሽ ነበር። የደቡብ ክልል ዞኖች ወደ ክልልነት በተቀየሩ መጠን ፌዴራል መንግሥቱ ውስጥ በተናጠል ማሳረፍ የሚችሉት ተፅዕኖ እንዲሁም የሚኖራቸው ውክልና እያሽቆለቆለ፣ የፌዴራሉ መንግሥት በሁለቱ ክልሎች የበላይነት ቁጥጥር ሥር እየዋለ ይመጣል።
የደቡብ ክልል ዘላቂ እና አስተማማኝ የአስተዳደር መዋቅር አለማግኘት ለፌዴራል መዋቅሩ ትንሽ ቁጥር ላላቸው ሕዝቦች የማይበጅ መሆኑን ለማስረጃ እማኝ ምስክር ነው። እንደ መፍትሔ ጠቅላላ የፌዴራል መዋቅሩ ላይ መነጋገር ሁነኛ መፍትሔ ነው። ነገር ግን ይህንን በሰከነ ሁኔታ ለማድረግ ከብሔርተኝነት ይልቅ የሰከነ ፖለቲካዊ ውይይት ለማድረግ መዘጋጀት ያስፈልጋል።
Filed in: Amharic