>

“ጦር አውርድ...!!!” ( በዕውቀቱ ሥዩም )

“ጦር አውርድ…!!!

 በዕውቀቱ ሥዩም

… ከዘመናት ባንዱ ዘመን የሀበሻ መዲና በነበረችው አክሱም በጐረቤቶቿ በኑብያና በየመን ሰላም ነገሠ … ይልቁንም በአክሱም ብልፅግና ሰፈነ፤ ሁሉም እንጀራና ወይን ጠገበ።
ከጥቂት ዓመታት በኋላ ከተመሰገኑት ያክሱም ሊቃውንት አንዱ ንጉሡ በተገኙበት ጉባኤ ‘ልቦናዬ ያሳየኝን ልናገር’ አሉ።
ተፈቀደላቸው።
“ግርማዊ ጃንሆይ” አሉ ባማረ ድምፃቸው … “ግርማዊ ጃንሆይ አክሱም የምትገኝበት ሁኔታ ለረጋው ሕሊናየ ሥጋት ፈጥሮብኛል፤ ይሄ ሥጋት ደግሞ ቀስ በቀስ ወደ ወገኖቼ መጋባቱ አይቀርም።”
“ምንድን ነው የሥጋትህ ምንጭ?” አሉ ንጉሡ።
ሊቁ ማብራራት ጀመሩ።
“እንደምናየው በመንግሥታችን ሰላም አለቅጥ ሰፍኗል … የባሩድ መዓዛ ከሸተተን ብዙ ዘመን ሆነን … የሽለላ የፉከራ ዜማዎቻችን ተዘነጉ። እረኞቻችንን ስሟቸው … በዜማዎቻቸው ውስጥ የብልግናና የፍቅር እንጂ የጉብዝናና የጀግንነት ስንኝ አይገኝም። ጋሻዎቻችን በተሰቀሉበት ድር አደራባቸው … ጦሮቻችን ዶልዱመዋል … ፍላጻዎቻችን ዛጉ … ነጋሪቶቻችን ዳዋ ዋጣቸው … ሰላም ልማዶቻችንና ትውፊታችንን አጠፋብን። ሕንፃ ያለ ጡብ ያለ ጣሪያ ሕንፃ እንደማይሆን እኛም ያለ ነውጣችን ያለ ሽለላችን ያለ ድላችን እና ያለ ሽንፈታችን እኛ አይደለንም።
“ግርማዊነትዎ እንደሚያውቁት አንበሳ ከሚዳቋ ጋር ተኝቶ ማየት ለጊዜው የሚያስደስት ትዕይንት ሊሆን ይችላል። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ግን ይሰለቻል። የሁሉም ዓይን አንበሳው ሚዳቆዋን ሲያሳድዳት … ሰብሮም ሲገነጣጥላት ለማየት ይናፍቃል።
“ጃንሆይ … ‘እርግቦች በሰገነቶቻችን ላይ ሰፍረዋል፤ የዘንባባ ዛፎች በጓሮአችን በቅለዋል’ ብለው የሚያዘናጉትን አይስሟቸው! … ብርቱ መንግሥት ከርግቦች ላባ ፍላፃ ያበጃል … ከዘንባባዎች ዝንጣፊ የጦር ሶማያ ይሰራል።
“ለራሳችን ብርቱዎች ነን ብለን እንጃጃላለን … ካልታገሉ ሀቅንም ማወቅ አይቻልም። ጐረቤቶቻችን ከፈገግታቸው ባሻገር ምን እያሴሩ እንደሆኑ አናውቅም። የጐረቤቶቻችን በር ተዘግቷል … በዚህ ምክንያት በእልፍኛቸው ውስጥ ምን እየተሰራ እንደሆነ አናውቅም … የጐረቤቶቻችንን ልክ አለማወቅ በቤታችን ላይ ሥጋት እንዲያንዣብብ አድርጓል።
📜📜📜
“ጃንሆይ! የምንኖረው ፈተና በሌለበት ዘመን ነው። ፈተና የሌለበት ዘመን የተፈጥሮን ሕግ ያዛባል። እስቲ ጐረምሶቻችንን እይዋቸው! … እንደ ሴት ዳሌና ጡት ማብቀል ጀምረዋል … በምትኩ ፂማቸውን ካገጫቸውና ከከንፈራቸው ጠርዝ አርግፈዋል … መዳፎቻቸው ከሐር ጨርቅ ይለሰልሳሉ … እግራቸውን ዘርግተው የባልቴት ተረት በመተርተር ጊዜያቸውን ያጠፋሉ … የደም ቀለም አያውቁም!
“አያቶቻችን ፍላፃ የወጠሩባቸው ደጋኖች የሴት ልጆቻችን የጥጥ መንደፊያ ሆኑ … ስለዚህ የምንለብሰው ሸማ በውርደት አድፏል። ይሄን እድፍ ከደም በቀር የሚያነፃው ምን አለ?”
ንጉሡ ከመኳንንቱ ጋር ይሄን አድምጠው፣ “ታዲያ ምን ይሻላል?” አሉ።
“ኑብያዎችን ለምን አንወጋም?” አሉ ሊቁ።
“ኑብያዎች ምን አደረጉን?”
“ሁለታችንን በሚለየው ድንበር ላይ ዋርካ ተክለዋል!”
“እና ቢተክሉስ?”
“ዋርካዎች እየሰፉ በመጡ ቁጥር የኛን መሬት መውሰዳቸው አይቀርም!”
“እና ምን ይሻላል?”
“እናቅምሳቸው!” አሉ ሊቁ።
“እንበላቸው!” አሉ መኳንንት።
“በሏቸው” አሉ ንጉሡ።
ሁኔታዎች ተቀያየሩ።
ሴቶች ቆሎ በማመስ ጭብጦ በማሰናዳት ተጠመዱ። ወንዶች ኢላማ ልምምዱን አጣደፉት። አሮጌ ጋሻዎች ከተሰቀሉበት ወረዱ። ደጋኖች ተወለወሉ። ፍላፃዎች ተሳሉ። የጐበዞች አረማመድ ተለወጠ። የእረኞች የፍቅር ዘፈን አንደበታቸው ላይ ሟሟ።
የደም ቃና ያላቸው ዜማዎች መስኩን ዱሩን ጋራውን ሞሉት። የአክሱም ባንዲራ ከእንቅልፏ ተቀሰቀሰች።
📜📜📜
ጥቂት ወራት አለፈ።
ከወደ ኑብያ ግድም ደብዳቤ መጣ።
“ዛቲ ጦማር ዘተፈነ ወ ትኀበ ንጉሠ አክሱም …
… የየመን ሊቃውንት አንድ መረጃ ነገሩን … እናንተ አክሱሞች በኛ ላይ ሠራዊት ልታዘምቱ እንደተሰናዳችሁ ሰምተን አዝነናል። ይሁን እንጂ የጠባችን ምክንያት በድንበሮቻችን ላይ የተተከሉት የዋርካ ዛፎች መሆናቸውን በማወቃችን ለሰላም የሚበጀውን አድርገናል። ከዛሬ ጀምሮ ዋርካዎች እንዲቆረጡ ትእዛዝ አስተላልፈናል … ይቅርታ አድርጉልን!”
              – የሚታይ ማህተም
ደብዳቤው ከደረሳቸው በኋላ ንጉሡ ሊቁን አስጠሩ።
“ምን ይሻለናል? ኑብያዎች ሳንወጋቸው ዋርካዎችን ቆረጡ! እንግዲህ ምን ሰበብ እንፈጥራለን?” አሉ በቅሬታ።
“ግርማዊ ሆይ!” አሉ ሊቁ “የሰማነው ዜና በእውነቱ የሚያስቆጣ ነው። እንደሚያውቁት ሠራዊት ለማደራጀት ብዙ ገንዘብ ብዙ ጉልበት ብዙ ጊዜ ፈጅተናል። ጐበዞቻችንን ከሙያቸው አፈናቅለን አስታጥቀናቸዋል። ሴቶቻችን ቡሃቃቸውን አሟጠው ስንቅ ሰርተዋል። ይሄ ሁሉ ያለ አንዳች ተግባር ብላሽ መሆን የለበትም ጃንሆይ!” አሉ በመማፀን ድምፅ።
“ታድያ ምን አድርግ ነው የምትለኝ?”
“የዘመቻችንን እቅድ ሰልሎ ለኑብያዎች የነገራቸው የየመን መንግሥት ነው።”
“እናስ?”
“በዚህ ምክንያት የመኖች የኛን ሉዐላዊነት ደፍረዋል። ስለዚህ ለምን ዘመቻውን ወደ የመን አናዛውረውም?”
አማራጭ አልተገኘም።
በማግስቱ አዋጅ ተነገረ፤
“ጠላታችን ወደሆነው ወደ የመን ሀገር ዝመቱ። በዚያ ሕያው የሆነውን ሁሉ ፍጁ! … ከተሞቻቸውንም ወደ ፍርስራሽ ለውጡ! …”
ድርሰት – በዕውቀቱ ሥዩም
ምንጭ – “በራሪ ቅጠሎች”። 1996 ዓ.ም። ገጽ 76-81።
Filed in: Amharic