>

የልጅ ተክሌና የጅሉ አማች ምስስሎሽ (ዳግማዊ ጉዱ ካሣ )

የልጅ ተክሌና የጅሉ አማች ምስስሎሽ

ዳግማዊ ጉዱ ካሣ 


አንዳንድ ጊዜ አለመናገር ከመናገር የሚሻልበት ጊዜ አለ፡፡ “አፍ ሲከፈት ጭንቅላት ይታያል” የሚለውን ነባር ብሂል ይዘን ወደ ጣሊያን የቀደመ አንድ ታሪክ ጎራ ብንል እንዲህ ያለ ሃይማኖታዊና ሞራላዊ ስህተት በግልጽ የተስተዋለበት አጋጣሚ እናገኛለን፡፡ እርሱም ጣሊያን ኢትዮጵያን ልትወር በተነሣች ጊዜ የወቅቱ የሮማ ጳጳስ ወራሪውን የጣሊያን ጦር “ይቅናህ” ብለው ባርከው በጸሎት የሸኙበትን ሁኔታ ለመግለጽ በጊዜው አንድ አስተዋይ ተቺ ቆየት ብሎ ይመስለኛል ሌላ አጋጣሚን ተመርኩዞ ከተናገረው የምንገነዘበው እውነታ ነው፡፡ ተቺው “አቡኑ ዝም ማለት በሚገባቸው ጊዜ ተናገሩ፤ መናገር በሚገባቸው ጊዜ ግን ዝም አሉ” የሚል ግሩም ሂስ ለታሪክ ድርሣናት አብቅቷል፡፡

እኔ ልረዳው ባልቻልኩት ሥነ ልቦናዊ ደዌ የሚሰቃየው የካናዳ ቶሮንቶው ራሱን “ልጅ ተክሌ” ብሎ መጥራት የሚያስደስተው ጎልማሣ የሕግ ምሁር ብዙውን ጊዜ የሚጽፋቸውንና የሚናገራቸውን ስመለከት ከእንደልቡነትም ባለፈ ወፈፌ ነገር ይመስለኛል፡፡ የዚህ ዘመን ሰዎች – እኔንም ጨምሮ – በብዙ ነገር አንጎላችን በመመታቱ ይመስለኛል አንዳንዶቻችን ዘባራቂ፣ አንዳንዶቻችን ዘርፍጤ፣ አንዳንዶቻችን እንዳሻው …ነገር ነን፡፡ የዚህ ሰውዬ ጉዳይ ግን በጣም እያሳሰበኝ ነው – ከብዙዎቻችን ባሰ(በት)፡፡ ምናልባት ይሄ ብዙዎችን በጨካኝ ሽመሉ የሚነርተው የ“ከኔ በላይ ዐዋቂ ላሣር፣ ከኔ በላይ ትልቅ ሰው ለውርርድም አይገኝ…” ዓይነቱ የ‹megalomania› ሥነ ልቦናዊ ልክፍት ይህን ሰው ሳያጠቃው አልቀረም፡፡ ሲናገር ራሱ ልክ እንደዚያ የትግራይ ክልል የሽማግሌ ቅሌታም – የእንጨት ሽበት ነው የምትሉት – እንደዚያ ገብረኪዳን ደስታ የተባለ የአእምሮ በሽተኛ፤ ተክሌም ከቃላቱ በበለጠ የሰውነት እንቅስቃሴው ብዙ ይናገራል፡፡ ጅንን ሰውነቱ ብቻውን የሚናገረው ሽሙጥና ምጸት ሌላ ነው፡፡ እንደዚህ ያለ መለሳዊና ወያኔያዊ ስብዕና መላበስ አለመታደል ነው፡፡ እንደነዚህ ያሉ ስብዕናዎች ተሰሚነት ያለው ቦታ ላይ ሲቀመጡ ብዙዎችን ያሳስታሉ፡፡ ሚዲያን ሲቆጣጠሩ ወዮ ለምስኪኖች፡፡ የዚህ ሰውዬ ወንድሞች ጃዋርና ልደቱ ኢትዮጵያን እያመሱ የሚገኙትም ከርቸሌ መገኘት ሲገባቸው የዘመኑ ከፋፍለህ ግዛ የዘረኞች የፖለቲካ ጫጉላ ውስጥ ስለሚገኙ የሚጨክንባቸው ባለመኖሩ ነው፡፡ ያሳዝናል፡፡ የነዚህ ሰዎች ጀምበር እስክትጠልቅ እንዲሁ እየቆሰልን መቆየታችን ነው፡፡

አንድ ሞኝ አማች ነበረ፡፡ እንደለመድከው ዘርፍጤ በለኝ እንጂ እነግርሃለሁ፡፡ ልጁ ከነሚስቱና ከነዘመዶቹ ለቅልቅል ይሁን ለመልስ ተጠርቶ እሚስቱ እናት ቤት ውስጥ አመሻሽ ላይ ተገኝቷል፡፡ መብሉና መጠጡ ቀርቦ ቤቱ ሁከታ በሁካታ ሆኗል፡፡ ሁሉም ሲጫወትና ሲያውካካ ግና ሙሽራው በዝምታ ተውጦ የሌሎችን ጨዋታ ይከታተላል፡፡ ይህን የልጁን ሁኔታ የታዘቡት የሙሽሪት እናት “ልጄ፣ ምነው ዝም አልክ? ተጫወት እንጂ!” ቢሉት በጅልኛ የአነጋገር ለዛ አንደበቱን እየጎተተ (እናንተም ጎተት አድርጉልኝማ – ጎርነን አድርጉት ታዲያ…) “እናቴ ንግግርህ አር አር ይለኛል ብላ መክራኛለችና አልናገርም እማማ!” ይላታል፡፡ እናትም “ውይ፣ አፈር በበላሁት ልጄ! ለኔ ማር ነው – ተጫወት፤ ዝምታ እኮ ጥሩ አይደለም” ትለዋለች፡፡ የመናገር አረንጓዴ መብራት ያገኘው ጅል አማች ንግግሩን በደስታ ቀጠለ፤ “እሽ፣ ይች ልጅ የማናት?” ብሎ ጥያቄ አንድን ሰነዘረ፡፡ እናትም “አፌ ቁርጥ ይበልልህ! እንዲያ ነው እንጅ … እሰይ የኔ ልጅ! … የኔ የእናትህ ናት” አለችና መለሰች፡፡ ሞኙ አማች ሴትዮዋ ድክም እስኪላት በወዘቱ ዳርና ዳር ተኮልኩለው የነበሩትን ሰባት ገደማ ልጆች ሁሉ የማን እንደሆኑ በተመሳሳይ ጥያቄና የአጠያየቅ ሥልትና ድምፀት ከጠየቀና ሴትዮዋም ልጆቹ የርሷ መሆናቸውን አንዳችም የመሰልቸት ስሜት ሳታሳይ ከነገረችው በኋላ ጅል አማች ሆዬ በመደነቅ “ሆ! ይሄን ሁሉ ልጅ የወለዱበት ‹እምብርትዎ› እንዴት ይሰፋ!” ብሏት እርፍ፡፡( ብልጤ ‹እንትን› ብዬ እቅጯን ልናገርልሽ ፈለግሽ? እረግ! አይሆንማ!)… ለማንቻውም “ወደሽ ከተደፋሽ …” እንዲሉ ነውና ትቻለው፡፡ ግን ምን ብላ ብትመልስለት ጥሩ ነው – “ውይ ልጄ፤ እውነትም ከአርም አር!”፡፡ አዎ፣ ያምርልኛል ብሎ ነገርን አለመላው ከመዘርፈጥ አንዳንዴ በርግጥም ዝምታ ወርቅ ነው፡፡ ማወቃችንንና መመራመራችንን በዚያም ከሰው መብለጣችንን የምንገልጥበት ምቹ የመሰለን አጋጣሚ የራሳችንን መቃብር አርቆ እንዳይቆፍር መጠንቀቅም ተገቢ ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ የመራቀቅ አባዜ ብዙዎችን ገደል ሲከት እታዘባለሁ፡፡ ጀብድ እሚያምረው በአንደበት ሣይሆን በጦር ሜዳ ነው፡፡ አቅል ጀባ ልጅ ተክሌ!

አንባቢ የፈለግኸውን ብትለኝ አልፈርድብህም፡፡ ለምን ቢባል ልጅ ተክሌ እንደኔ አላናደድህም፡፡ ዛሬ ጧት በፌስቡክ ካገኘሁት አንድ የተክሌ ትዕቢታዊ የደንቆሮ ንግግር ተነስቼ የመጣልኝ ነገር የዚህ ከፍ ሲል የጠቀስኩት ሞኝ አማች ንግግር ነው፡፡ ተክሌ ከሀብታሙ አያሌው ጋር ባደረገው ውይይት ግብጻዊ እንጂ ኢትዮጵያዊ አልመስልህ አለኝ፡፡ እናንተም እዩትና ዕርማችሁን አውጡ፡፡ ስለዚህ ተክሌም ሆነ ጃዋር ወይም ተስፋዬ ገብረባብ በምግባራቸውም ሆነ በአስተሳሰባቸውና አነጋገራቸው እንዲሁም አንዳንዶቹ በትውልድ ሐረጋቸው ኢትዮጵያውያን አይደሉምና በፍጥነት እጃቸውን ከኛ ያንሱ!

“ግብጽ ኢትዮጵያን ምንም አላደረገቻትም፤ አባይ ለግብጽ የኅልውና ጉዳይ ነውና ‹አሁንም ሞት ነው በኋላም ሞት ነው› ብለው በመዝመት ኢትዮጵያን ድባቅ መትተው ማሸነፍ አያቅታቸውም፤ አባይ ለኢትዮጵያ የኩራት (pride) ጉዳይ እንጂ ያን ያህል አስፈላጊዋ አይደለም፡፡ ለስንት ሽህ ዓመት ዝም ብለን የለቀቅነውን ወንዝ ለግብጽ ኅልውና ስንል ለ21 ዓመት ወደፊት ብንተውላት ምንም ማለት አይደለም፤ ችግሩን ለምደነዋል፤ አዲስ አይደለም፡፡ እንዲያውም ግብጽን ማፍቀር አለብን፡፡ ይበልጥ ማቅረብና ማፍቀር ይገባናል – ፈረንጆች love your enemy, make him closer … ይላሉ፡፡ እናም እኛም ግብጽን እናፍቅራት፤ ጠላታችን አይደለችም፡፡ በራሳቸው ኢንጂነሮችና በራሳቸው ደሞዝ ክፍያ ብናሠራቸውም እንችላለን፡፡ …” ምን ያላለው አለ፡፡ ተክሌ ክርስቶስንም መሰለኝ፤ የቲቤቱን ሎብሳንግ ራምፓንም መሰለኝ፡ ደላይላማንም መሰለኝ፤ ኦሾና ታኦንም ቡድሃንም መሰለኝ፡፡ ሉሲፈርንም መሰለኝ፡፡ ብቻ ያልመሰለኝ የለም፡፡ ቅዱስ ማነው እቴ እመ ብርሃንን “በምንት ንመስለኪ” ያለው ለካንስ ወዶ አልነበረም፡፡ ተክሌ ጥፍት ብሎ እንደከረመው በዚያው ጥፍት ቢል ነበር የሚሻለው እንዲህ ከሚጃጃል፡፡

ሃታኡ መሌ – የሆኖ ሆኖ ለማለት ፈልግቼ ነው በአዲሱ የአስተዳደር ቅኝት – ሃታኡ መሌ ልጅ ተክሌን ሀኪም ቤት ውሰዱት፡፡ ይህን ሰው የሥነ አእምሮ ሀኪም ይየውና የአንጎሉ ክሮች ተበጣጥሰው ሳያልቁ ይቀጣጥልለት፡፡ ይህን ልጅ ተክሌ ወደ ሸንኮራ ዮሐንስ ወይም ለብቃ ኢየሱስ ውሰዱና በዚህ ለራስ ከሚሰጥ ትልቅ ግምት የተነሣ ከሚፈጠር በሽታ ቶሎ እንዲድን ፈጥናችሁ ድረሱለት – አያያዙ ሌልኛ ነውና የሚተርፍም አይመስልም፡፡ “ግብጽ የኢትዮጵያ ጠላት አይደለችም” ብሎ የሚያምንና ለዚያም ሽንጡን ገትሮ የሚከራከር ኢትዮጵያዊ “ምሁር” ማግኘት እጅግ የሚደንቅ ነው፡፡ ይህ ሰው በርግጠኝነት በሽተኛ ነው ወይም እንደነጃዋር የግብጽ ተከፋይ ባንዳ ነው፡፡ ፍሉስ ከባድ መግነጢሳዊ ኃይል ነው(አለው) – ክርስቶስን በሠላሣ አላድ ያሸጠ ገንዘብ፣ የኤሣውን ብኩርና በእፍኝ ምሥር ያሸጠ ገንዘብ፣ … ምፅዋንና ሀሰብን በ200 ሽህ የሻቢያ ፎርጅድ ብር ለጄኔራል ጥላሁን ነው ኮሎኔል ማንትስ ያኔ በ80ዎቹ ያሸጠ ሶልዲ… እነዚህ ሮጠው ያልጠገቡ ጃዋርን መሰል ልጆች ስለገንዘብ፣ ለገንዘብና በገንዘብ እንዲህ አቅላቸውን ስተው አሣራቸውን ቢበሉ አይፈረድባቸውም፡፡ አትለከፍ ነውና አትፍረዱባቸው፡፡

ሌላው ሁሉ ቀርቶ ባስታወስኩት ቁጥር እንደቀውስ የሚያደርገኝን ነገር ልናገር፡- ከጠቅላላው የሀገሪቱ የሕዝብ ብዛት አሥር ከመቶ ክርስቲያን ካለባት ግብጽ ዘጠና ከመቶ ክርስቲያን ለሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ፓትርያርክ እየተሾመ ለሽዎች ዓመታት በሃይማኖታችን ሠርገው ገብተው የተጫወቱብን ለኔ የእግር እሳት ነው፡፡ ምን ነክቶን ይሆን? ማን ምን አዙሮብን ይሆን? ይህም ብቻ አይደለም፡፡ ጳጳሱ ወዳገሩ ሲመለስ በቁመቱ ልክ የወርቅ ጥፍጥፍ ይዞ ይሄድ ነበር አሉ፡፡ እሞኝ ደጃፍ ሞፈር እየተቆረጠ እኛ ግን በነሱ ትብታብ እየተጃጃልን አባይን በጭልፋ እንኳን እንዳንነካ መቼም በማይገባኝ አፍዝ አደንግዝ ታስረን ለብዙ ምዕተ ዓመታት ዘለቅን – ፍቺ የሌለው ዕንቆቅልሽ፡፡ ሌላው የሚገርመው ነገር ጳጳስ ቢያጡ እስላሙን ጀለብያውን አስወልቀው የጳጳስ ቀሚስ በማልበስና መስቀል በማስጨበጥ ልከውታል አሉ፡፡ መጫወቻ እኮ ነው አድርገውን የነበረው፡፡ ይህን ዓይነቱን አሳፋሪ ታሪካችንን ሳስበው ስለሀገራችን የሚባለውን ብዙውን ነገር ለመቀበልና በርሱም ለመኩራት ይቸግረኛል፡፡ የበዓሎቻችንን አበዛዝ፣ የማይምነታችንን ድንበር ማጣት፣ በሸርና በተንኮል፣ በሤራና በደባ የተጠመዱ የጠላቶቻችንን ልዑካን ለመቀበልና በነሱ ለመታዘዝ ያለንን ቅንነት፣ በዘርና በጎሣ፣ በሃይማኖትና በድንበር እርስ በርስ ተጠላልፎ ለመውደቅ የገባነውን ቃል ኪዳን ሳስበው ከኢትዮጵያ ወጥተህ ብረር ብረር ይለኛል፡፡ ግን ወዴት? ንገረኛ! ለምን ታክላላኛለህ? ወንድምህ አይደለሁ?

ma74085@gmail.com

 

ግልባጭ

  • ለአቶ ጌታቸው ረዳ 

  የትግራይ ዴሞክራሲያዊት ሪፓብሊክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር 

  መቀሌ 

  • ለጃዋር መሀመድ

የኦሮሚያ ዴሞክራሲያዊ ሪፓብሊክ ፕሬዝደንት

ፊንፊኔ

  • አቶ ልደቱ አያሌው

የኢፌዲሪ ዕጩ ጠ/ሚኒስትር የፀረ-ሙስና ኮሚሽን የበላይ ጠባቂ

አዲስ አበባ

 

(ህልመ-ከስት ቅጠል የበላሁ አልመስልም? ምን ታይቶኝ ይሆን ግን?)

Filed in: Amharic