>

" ዴክሳሜታዞን የተሰኘውን መድሃኒት ለኮቪድ 19 ህሙማን እንዲሰጥ ተወሰነ!!!" (የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ)

” ዴክሳሜታዞን የተሰኘውን መድሃኒት ለኮቪድ 19 ህሙማን እንዲሰጥ ተወሰነ!!!”

የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ

   መድሃኒቱ ከቫይረሱ የሚፈውስ አይደለም!


ሰሞኑን በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን መረጃው እየተሰራጨ የሚገኘውና የኮቪድ 19 ህሙማንን ለማከም ያገለግላል የተባለው መድሃኒት፤ በአገራችን ጽኑ ህሙማንን ለማከም አገልግሎት ላይ እንዲውል ተወሰነ።
የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ ትናንት የተናገሩት፤ ሚኒስቴር መ/ቤቱ ለኮቪድ 19 ህሙማን የሚውለውን ዴክሳሜታዞን የተሰኘውን መድሃኒት በተመለከተ በእንግሊዝ መንግሥት የተካሄደውን ጥናትና ሪፖርት በዝርዝር ተመልክቶታል። እንደ ሚኒስትሯ ገለጻ፤ የህክምና ጉዳዮች አማካሪ ቡድንና የጤና ባለሙያዎች አማካሪ ምክር ቤት የሰጠውን ምክረ ሀሳብ መሰረት በማድረግ፣ መድሃኒቱ ኦክስጂን ወይም የመተንፈሻ መሳሪያ እገዛ ለሚያስፈልጋቸው የኮቪድ ህሙማን ጥቅም ላይ እንዲውል ተወስኗል። ህክምናውን አስመልክቶ ዝርዝር መመሪያ በቅርቡ እንደሚወጣም ሚኒስትሯ አስታውቀዋል።
በሌላ በኩል፤ መድሃኒቱን በተመለከተ የሚወጡ መረጃዎች በአብዛኛው ህብረተሰቡን የሚያዘናጉና የተሳሳቱ እንደሆኑ የጤና ባለሙያዎች ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል:: ባለሙያዎቹ እንደሚናገሩት፤ መድሃኒቱ በበሽታው በፅኑ የታመሙና የቬንትሌተር ወይም የኦክስጅን እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች ጥቅም ላይ ቢውል የማገገም አቅምን አፋጥኖ የሞት መጠንን ሊቀንስ ይችላል እንጂ ከቫይረሱ ለመፈወስ የሚያስችል አይደለም ብለዋል።
የህብረተሰብ ጤና ባለሙያውና የኮቪድ 19 በሽታ መከላከል ኮሚቴ ውስጥ በመስራት ላይ የሚገኙት ዶ/ር ሰለሞን ወርቁ እንደሚያስረዱት፤ ዴክሳሜታዞን የተባለው መድሃኒት ከ50 ዓመታት በፊት ጀምሮ አገልግሎት ላይ ሲውል የነበረና ለበርካታ በሽታዎች ህክምና ሲያገለግል የቆየ ነው። መድሃኒቱ ቫይረሱን ለመግደል የሚችል ሳይሆን በጽኑ ህመም ውስጥ ያሉ የኮሮና ታማሚዎችን የማገገም አቅም በማፋጠን ሞትን ለማስቀረት የሚያስችል ነው። መድሃኒቱ በኮሮና ሳቢያ የሚከሰተውን ሞት በመቀነስ ረገድ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው ሲሆን ከሀኪም ትዕዛዝ ውጪ በማንኛውም የኮሮና ታማሚ ሰው ቢወሰድ ጉዳቱ የከፋ እንደሚሆን ዶ/ር ሰለሞን ገልፀዋል።

የኮሮና ቫይረስ መድሃኒት አልተገኘለትም፤ ቫይረሱ አሁንም ገዳይነቱን እንደቀጠለ ነው ያሉት የህክምና ባለሙያው፤ በአሁኑ ወቅት ያለን ብቸኛ አማራጭ በበሽታው ከመያዝ ራስን መከላከልና አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ ብቻ ነው ብለዋል። መድሃኒቱ የኮቪድ 19 ጽኑ ታማሚዎች ሆነው በቬንትሌተር ድጋፍ የሚተነፍሱትን ሰዎች የሞት መጠን በአንድ ሶስተኛ (34 በመቶ) የሚቀንስ ሲሆን ኦክሲጅን ብቻ የሚፈልጉ ታማሚዎችን የሞት መጠን ደግሞ በአንድ አምስተኛ (20 በመቶ) ይቀንሳል ብለዋል። በእርግጥ ይህ ቀላል ነገር አይደለም፤ በተለይ እንደኛ ላሉ ታዳጊ አገሮች መድሃኒቱ ትልቅ ጠቀሜታ ይኖረዋል። ነገር ግን መድሃኒቱ ለሁሉም የኮቪድ 19 ታማሚዎች የሚሆንና ሙሉ በሙሉ ከቫይረሱ ለመፈወስ የሚረዳ አለመሆኑን ህብረተሰቡ ሊገነዘብ ይገባዋል ሲሉም አሳስበዋል።
መድሃኒቱ በባህሪው የበሽታ መከላከል አቅምን ከፍ የሚያደርጉ ሴሎች የሚመረቱበትን መጠን ዝቅ እንዲል የሚያደርግ ሲሆን ይህ ለጽኑ ህሙማን ጥሩ ውጤት የሚያመጣ ቢሆንም በፅኑ ያልታመሙ ሰዎች ሲወስዱት ግን የበሽታ መከላከል አቅምን በማዳከም ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል ሲሉ ባለሙያው ያስጠነቅቃሉ።
የድንገተኛና ጽኑ ህሙማን ሀኪሙ ዶክተር ተስፋዬ ታሪኩ በበኩላቸው፤ መድሃኒቱ በአሁኑ ወቅት በአገራችን በስፋት የሚገኝና ቀደም ሲል አንስቶ ከአፍንጫ ጀምሮ እስከ ሳምባ ድረስ ለሚያጋጥሙ አለርጂዎችና የአስም በሽተኞች ህክምና ሲውል የቆየ መሆኑን ገልጸው፤ አሁን በዚህ በሽታ በጽኑ ለተያዙ ህሙማን ጥቅም ላይ እንዲውል መወሰኑ የሚያስደስት ቢሆንም መድሃኒቱ መወሰድ ያለበት ግን በሀኪም ምክርና እርዳታ ብቻ ሊሆን እንደሚገባው አስምረውበታል።
መድሃኒቱ ቫይረሱን ለማዳን ሳይሆን ከሞት የመዳን እድልን ከፍ ለማድረግ ብቻ የሚረዳ መሆኑን ህብረተሰቡ ተገንዝቦና ከአጉል ተስፋ ተቆጥቦ፣ በሽታውን በመከላከል ላይ ትኩረት እንዲያደርግ ባለሙያው አሳስበዋል።
መድሃኒቱ ረዘም ላለ ጊዜ ከተወሰደ የጉሉኮስ ቁጥሮችን በመጨመር የስኳር በሽታን የሚያባብስ ሲሆን የአጥንት መሳሳት፣ ጭንቀትና ድብርትንም ሊያስከትል እንደሚችል ዶ/ር ተስፋዬ ገልፀዋል።
ዴክሳሜታዞን ኦክስጂንና የመተንፈሻ መርጃ መሳሪያ በሚያስፈልጋቸው የኮሮና ቫይረስ ህሙማን ላይ የሚያጋጥምን ሞት የሚቀንስ የመጀመሪያው መድሃኒት መሆኑን ሰሞኑን የገለፀው የዓለም ጤና ድርጅት፤ ነገር ግን በፅኑ ያልታመሙ ሰዎች መድሃኒቱን መውሰድ እንደሌለባቸውና ከወሰዱ ግን ለከፋ አደጋ እንደሚዳረጉ አስጠንቅቋል

Filed in: Amharic