>

የሐምሌ ወር ፖለቲካ...!!! (ዮሀንስ አምበርብር)

የሐምሌ ወር ፖለቲካ…!!!

ዮሀንስ አምበርብር

* ..   ግብፅ በፍሊስጤም ጉዳይ ላይ ድምጿን እንዳታሰማ የሚፈልገው የአሜሪካ መንግስት ይህንን ለማሳካት ኢትዮጵያ  የያዘችውን የውኃ ሙሊት እቅድ እንድታራዝም ይፈልጋል በመሆኑም ስምምነት ሳይደረስ የግድቡ ሙሊቱ እንዳይጀመር ያሳስባል!!!
*      *      *
ግብፅ በፍልስጤም ጉዳይ የአረብ አገራትን በማስተባበር እና በመምራት እስራኤል ላይ ጦርነት ከጀመረች በኋላ (አንዳንድ መረጃዎች ሽንፈት ሌሎች ደግሞ አሸንፋ ሳለ ይላሉ) እርግጡ ባልታወቀ እና ያስተባበረቻቸውን የአረብ ሀገራት ሳያውቁ አሜሪካ ባመቻቸው የካምፕ ዴቪድ ስምምነት ከእስራኤል ጋር እርቅ ካወረደች አርባ ዓመታት አለፉ። ግብፅ ስምምነቱን በመፈረሟ ከአረብ ሀገራት ሊደርስባት የሚችልን ጥቃት መመከት እንድትችል እና በአባይ ውኃ ላይ ያላትን ፍላጎት አሜሪካ እንድትከላከል የጎንዮሽ ስምምነት አደረጉ። ይሁን እንጂ ስምምየቱን የፈጸሙት የግብፁ ፕሬዝዳንት ከጥቂት ቆይታ በኋላ ስምምነቱን በተቃወሙ ኃይሎች ተገደሉ።
ዛሬ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ትራምፕ እስራኤልን የሚጠቅም የመካከለኛው ምስራቅ የሰላም ሀሳብ (Middle East Peace Plan) ይዘው ሲቀርቡ የግብፅን ድጋፍ በዋነኝነት ተማምነዋል። ግብፅም በኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ፖለቲካ ለገጠማት እራስ ምታት ፈውስ ይሆነኛል ብላ ተቀብላዋለች። ይህንን ጉዳይ ለመቀልበስም ፋይሉን ለፕሬዝዳንት ትራምፕ በማቅረብ የካምፕ ዴቪዱን ስምምነት ፈጽሙ እኛም የፍልስጤምን ጉዳይ ጆሮ ዳባ እንላለን ያለች ይመስላል።
እስራኤል ከፍልስጤም ጋር በይገባኛል የምትሟገበትን የዌስት ባንክ ግዛት በኃይል ወደ ራሷ ግዛት ለማዘዋወር ቀን በቆረጠችበት ወቅት እንኳን ከግብፅ መንግስት የሚሰማ የጓላ ድምጽ የለም። ከግብፅ ይልቅ የተመድ የፀጥታ ምክር ቤት እና መቀመጫውን በአሜሪካ ያደረገው Human Rights Watch እና ሌሎች የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች እየጮኹ ይገኛሉ።
ጩኸቱን ከምንም ያልቆጠሩት እስራኤል እና አሜሪካ የዌስት ባንክን የተወሰነ ግዛት በኃይል ወደ እስራኤል ለማዘዋወር የቆረጡበትን ቀን July 1 2020 እየጠበቁ ይገኛሉ። ኢትዮጵያም የህዳሴ ግድቧን የመጀመሪያ ምዕራፍ ሙሌት ለማካሄድ በዚሁ ወር ቆርጣለች።
ግብፅ በፍሊስጤም ጉዳይ ላይ ድምጿን እንዳታሰማ የሚፈልገው የአሜሪካ መንግስት ይህንን ለማሳካት ኢትዮጵያ በዚህ ወር የያዘችውን የውኃ ሙሊት እንድታራዝም ይፈልጋል በመሆኑም ስምምነት ሳይደረስ የግድቡ ሙሊቱ እንዳይጀመር ያሳስባል።
ሱዳን ከገባችበት የኢኮኖሚ ቀውስ ለመውጣት የነደፈችውን የኢኮኖሚ ፕሮግራም የሚጠይቀውን የፋይናንስ ፍላጎት ለመመለስ ኃያላኑ የሱዳን የኢኮኖሚ ማነቃቂያን ለመደገፍ የሚችሉበትን መንገድ ሊወያዩ በዚሁ የሐምሌ ወር ቀጠሮ በመያዛቸው ምክንያት ሱዳንም ግድቡን በተመለከተ የአሜሪካ ወይም የሌሎቹ ሀገራትን እና የግብፅን ፍላጎት የሚጻረር አቋም ማራመድ አዳግቷታል።
ኢትዮጵያ የግድቡ ሙሊትን በሐምሌ ወር ካልጀመረች የግድቡን ሙሊት ለማካናወን የቀጣዩ ዓመት ሐምሌ ወር መጠበቅ የግድ ይላታል። በዚሆ ጊዜ ውስጥ ግብፅም የፍልስጤምን ጉዳይ እንዳልሰማ ሆና በያዙኝ ልቀቁኝ የተቃውሞ መግለጫ ኃጥያቷን ታጥባለች። ይህ ባይሳካ እንኳን የሚገጥማትን የፖለቲካ ቀውስ ለማለፍ የአንድ ዓመት ጊዜ በቂ ነው። ወይም ሌላ ማዘናጊያ ፖለቲካዊ ጉዳይ ትፈጥራለች። አልያም ይፈጠርላታል ወይም ታገኛለች። ኢትዮጵያም የውሳኔዋን ውጤት ትቀበላለች። በቀጣዩ ዓመትም ግድቡን ስለመሙላቷ እርግጠኛ መሆን አትችልም።
ኢትዮጵያ የግድቡን የውኃ ሙሌት በያዘችው እቅድ መሠረት በሐምሌ ወር ብታከናውን ግን የቀደመ እቅዷ አካል እንጂ ሌላ ነገር ሊባል አይችልም። ይህን በማድረጓ ፍልስጤም ላይ የተያዘው እቅድ ቢጨናገፍ አይመለከታትም ፤ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታ ምክር ቤትም እየተቃወመው የሚገኝ እቅድ በመሆኑ እንዲሁም በህዳሴ ግድብ ላይ ያላት ፍላጎት ፍትሐዊ በመሆኑም አትከስርም። ግብፅም በፍልስጤም ላይ የፈጸመችው ዳግመኛ ክህደት በህዝቦቿ እና በተቀረው ሙስሊም ዓለም ስለሚጋለጥ አቅም አይኖራትም።
ኢትዮጵያ ከእስራኤል ጋር ያላት ሀይማኖታዊ እና ባህላዊ ቀረቤታ እንጂ ፖለቲካዊ ትስስር የላትም። ከዛ ይልቅ በፍልስጤም ጉዳይ ላይ በተመድ ስብሰባ ላይ ያንጸባረቀችው አቋም ለፍልስጤም ራስ ገዝ አስተዳደር ያላትን ድጋፍ ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ በመሆኑ በሐምሌ ወር ግድቡን መሙላቷ ተጨማሪ ድጋፍ ከሙስሊሙ የዓለም ማህበረሰብ ያስገኝላት እንደሆነ እንጂ አያስወቅሳትም።
Filed in: Amharic