>

የህዳሴ ግድቡ ወርዶ ወርዶ የአንድ ግለሰብ ፕሮጀክት ሆኖ ነበር፤ ይህም ለትልቅ ውድቀት ዳርጎታል!!! አምባሳደር አለማየሁ

 

የህዳሴ ግድቡ ወርዶ ወርዶ የአንድ ግለሰብ ፕሮጀክት ሆኖ ነበር፤ ይህም ለትልቅ ውድቀት ዳርጎታል!!!

አምባሳደር አለማየሁ ተገኑ የቀድሞ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር፣ በሩሲያ የኢትዮጵያ ልዩ መልዕክተኛና ባለ ሙሉ ስልጣን አምባሳደር
ሀብታሙ ስጦታው
* ‹‹የህዳሴ ግድቡ በወቅቱ የቦርድ ሰብሳቢ አድራጊ ፈጣሪነት ለከፍተኛ ኪሳራ ተዳርጓል›› 

‹‹የህዳሴ ግድቡ ግንባታ በወቅቱ ቦርድ ሰብሳቢ በነበሩት ዶክተር ደብረፂዮን ገብረሚካኤል አድራጊ ፈጣሪነት በፍጥነት ተዳክሞ ለከፍተኛ ኪሳራ ተዳርጓል›› ሲሉ የቀድሞው የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትርና፤ በሩሲያ የኢትዮጵያ ልዩ መልዕክተኛና ባለ ሙሉ ስልጣን አምባሳደር አለማየሁ ተገኑ አስታወቁ፡፡
አምባሳደር አለማየሁ ተገኑ በተለይ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንዳስታወቁት ፣ የህዳሴ ግድቡ አቶ መለስ በህይወት እስከነበሩበት ጊዜ ድረስ በየወሩ ይገመገም የነበረ ሲሆን ከእርሳቸው ህልፈት በኋላ በየወሩ መገምገሙ ቀርቷል፡፡
የወቅቱ የቦርድ ሰብሳቢ በክላስተር አደረጃጀት በሁለት ወር አንድ ጊዜ እንዲታይ ብለው አቅጣጫ ማስቀመጣቸውን አስታውሰው ፣ ሰብሳቢው አሠራሩን ተግባራዊ ሳይደርጉ መቅረታቸውንም አመልክተዋል። በዚህ ሁኔታ የህዳሴ ግድቡን ፕሮጀክት የመብራት ኃይል ቦርድ አካልም ይገመግመው እንዳልነበር ጠቁመዋል:: ፕሮጀክቱን በሚመለከት በየጊዜው ለቦርዱ ጥያቄ እናቀርብ ነበር ያሉት አምባሳደር አለማየሁ፣ ቦርዱም ገምግሞ ወደ ውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የግምገማውን ውጤት አይልክም ነበር ብለዋል፡፡ የዘርፉ ባለቤት ብንሆንም ተገልለን ነበር፤ ሪፖርትም ከመብራት ኃይል እየወሰድን ጉድለቶቹን እንናገር ነበር ሲሉም ተናግረዋል::
እንደ አምባሳደሩ ገለጻ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከመብራት ኃይል የሚያገኘውን መረጃ ይዞ እንደ ዘርፍ መግለጫ በሚሰጡበት ወቅት እንኳን ‹‹ምን አግብቷችሁ ነው መግለጫ የምትሰጡት›› በማለት በቦርድ ሰብሳቢው በኩል ቁጣ ይደርስባቸው እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ በዚህ ሁኔታም ፕሮጀክቱ ከህዝብ ፕሮጀክትነቱ ወርዶ የአንድ ግለሰብ ፕሮጀክት ሆኖ እንደነበር አመልክተዋል። ይህም የግድቡን ግንባታ ለውድቀት ከመዳረጉ ባለፈ ‹‹በአገራችን ታሪክ የሚያሳዝን ድርጊት ሆኖ አልፏል›› ብለዋል፡፡
በወቅቱ የህዳሴ ግድቡ ሥራና ውሳኔዎች በሰብሳቢው ውሳኔ ስር የነበሩ መሆናቸው ትክክል እንዳልሆነ ለቦርድ አባላት ቢነገርም የቦርድ አባላትም ፕሮጀክቱን እንደማይገመግሙ ማስታወቃቸውን አመልክተው፤ ግንባታው በአካል ባለመገምገሙ ብቻ ትልቅ ውድቀት እንደነበር ገልጸዋል። በወቅቱ የነበረውን ቦርድ ችግሮች በሚገባ ለማየት አሁን የተቀየረው ቦርድ በአጭር ጊዜ ያመጣውን ለውጥ ማየት አሳማኝና በቂ ነው ብለዋል።
“ፕሮጀክቱ በአሁኑ ወቅት ከግለሰብ እጅ ወጥቶ ወደ ህዝባዊነቱ ተመልሷል፡፡ አገግሞና የኮንትራት አስተዳደሩም ተለውጦ አስደናቂ ለውጥ በማምጣት ዳግም አገራዊ ተስፋ ፈጥሯል” ብለዋል፡፡
‹‹አቶ ኃይለማርያም በወቅቱ በጠሩትና በገመገሙት ስብሰባ ላይ ፕሮጀክቱ መዘግየቱ መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡ ሳሊኒም ሜቴክ ባልሠራቸው ሥራዎች ምክንያት የራሱን ሥራ መሥራት እንዳልቻለ በግምገማው ላይ ተነስቷል፡፡ በዚህ ወቅትም ቢሆን ለሥራው መጓተት ዋናው ምክንያት ሜቴክ እንደሆነ ተረጋግጧል፡፡ ቦርዱም ዕርምጃ እንዲወሰድ አቅጣጫ ቢቀመጥም ማስተካከል ሳይቻል ቀርቷል›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የሚያሳዝነው ፕሮጀክቱ ምንም ለውጥ ሳይመጣ በሜቴክ በኩል ይሠራሉ የተባሉት ሥራዎች ሳይሠሩ ቦርድ ሰብሳቢው ለሜቴክ ሽፋን በመሆን ፕሮጀክቱ ‹‹ባለህበት ሂድ›› ሆኖ እንዲቀር ትልቅ በደል በሀገርና በህዝብ ላይ መሠራቱን አመልክተዋል፡፡
በግድቡ ግንባታ ሂደት ሜቴክ ሥራውን በጊዜ ባለመጨረሱ ሲቪል ሥራውም ቆሞ ነበር ያሉት አምባሳደሩ፣ ለዚህ ችግር ተጠያቂው ሜቴክ ሆኖ ሳለ ቦርድ ሰብሳቢው ዕርምጃ ከመውሰድ ይልቅ ለሜቴክ ሽፋን በመሆን አልፈውታል፡፡ ከዚህ ውጪም ቦርዱ ዕርምጃ ሊወስድባቸው የሚገቡ ሥራዎች ኖረው ሳይተገብራቸው የቀረ ብዙ ናቸው ብለዋል፡፡ አሁን ያለው ለውጥ ባይመጣ ሜቴክን ይዞ የመቀጠል አቋማቸው የፀና እንደነበር አቶ አለማየሁ አመልክተዋል፡፡
በጉዳዩ ዙሪያ የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የቀድሞው የህዳሴ ግድብ ግንባታ የቦርድ ሰብሳቢ የነበሩትን ዶክተር ደብረፂዮን ገብረሚካኤልን በስልክ ለማግኘት ያደረግነው የተደጋገመ ጥረት ስልካቸው ዝግ በመሆኑ ሳይሳካ ቀርቷል። የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊንም ለማናገር ያደረግነው ጥረትም በስልካቸው አለመሥራት ምክንያት ሊሳካ ያልቻለ ሲሆን፤ በጉዳዩ ዙሪያ በቀጣይ የሚሠጡን ምላሽ ካለ የምናስተናግድ መሆኑን እንገልጻለን።
አዲስ ዘመን ሰኔ 11/2012
Filed in: Amharic