>

ዕንቁላል፣ ድንችና ቡና..!!! (ዲ/ን ዳንኤል ክብረት)

ዕንቁላል፣ ድንችና ቡና..!!!

(ዲ/ን ዳንኤል ክብረት)

ልጅቱ ሁልጊዜ እየመጣች ታማርራለች፡፡ኑሮ አልተሳካልኝም፣ አልሞላልኝም፣ ባሌ ያስቸግረኛል፣ ሥራ ቦታ ሰላም የለኝም፣ ጎረቤቶቼ ረበሹኝ፣ ሕመሙ በረታብኝ፣ ገንዘቤ አልበረክት አለ፤ ጓደኞቼ ያሙኛል፣ ልጆቼ  ይበጠብጡኛል፡፡ ስለ ሸረኛ፣ ስለ መጋኛ፣ ስለ ምቀኛ፣ ስለ መተተኛ የማትለው ነገር የላትም፡፡ አባቷ የተለያዩ ታሪኮችን እየጠቀሰ ሊመክራት፣ ሊያጽናናትና ሊያበረታት ሞከረ፡፡ እርሷ ግን ማማረሯን፣ መማረሯንም አላቆመቺም፡፡ እንዲያውም ምሬቷ ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ፤ ኑሮዋንም እየጠላቺው፣ ፈተናዋንም እየፈራቺው መጣች፡፡
አንድ ቀን መኖር አስጠልቷት፣ ችግሩና መከራም በርትቶባት፣ ምሬቷም ጫፍ ደርሶ መጣች፡፡ ‹‹በቃ ከዚህ በኋላ መኖር አልፈልግም፤ ይህንን ያህልስ እኔ ለምን እፈተናለሁ፤ ለምንስ ችግር ይበረታብኛል፤ ለምንስ ሁሉም ነገሮች ይጠሙብኛል፤ በቃ እኔ መኖር የለብኝም›› እያለች ታለቅስ ነበር፡፡አባቷ ምክሩ ሁሉ እንዳልሠራ፣ የነገራትንም ሁሉ እንደዘነጋቺው ተረዳ፡፡
‹‹ተከተይኝ›› አላትና ወደ ማዕድ ቤት ገቡ፡፡
ወንበር ሰጣትና እርሱ ወደ ምግብ ማብሰያው ሄደ፡፡ ኮመዲኖውን ከፈተና ዕንቁላል፣ ድንችና የተፈጨ ቡና ይዞ መጣ፡፡ እርሷ ግን ትዕግሥቷ አልቆ ነበር፡፡ በልቧም ‹‹እኔ ኑሮ መርሮኝ እርሱ ምግብ ሊጋብዘኝ ይፈልጋል›› ትል ነበር፡፡ ‹‹አባቴ ችግሬን አልተረዳውም ማት ነው፤ ርቦኝ የተነጫነጭኩ መሰለው›› አለች፡፡ ‹‹እኔ ምግብ አልፈልግም፣ ቡናም አልጠጣም፤ በቃ እንዲያውም እሄዳለሁ›› አለችው፡፡ ዝም አላት፡፡
ሦስቱ ምድጃዎች ላይ የሻሂ ማፍያዎችን ጣደ፡፡ በአንደኛው ላይ ዕንቁላሉን፣ በሌላው ላይ ድንቹን፣ በሦስተኛውም ላይ የተፈጨውን ቡና ጨመረው፡፡ ከዚያም ወደ ልጁ መጣና ከጎኗ ተቀመጠ፡፡ ‹‹ምን እየሠራህ ነው፤ የኔ ችግርና ምግብ ምን አገናኛቸው፤ ቤቴ ውስጥ ሞልቷልኮ፤ ሕጻን አደረግከኝ እንዴ፤ ዕድሌ ነው፣ አንተ ምን ታደርግ›› ትነጫነጫለች፣ ትቆጣለች፣ ታማርራለች፡፡ አባቷ ግን ዝም ብሎ ያዳምጣታል፡፡ ማልቀስ ጀመረች፡፡ ትከሻዋን እየደባበሰ ዝም አላት፡፡ ቃል ከአፉ አልወጣም፡፡
ውኃው መንፈቅፈቅ ጀመረ፡፡ አልፎ አልፎም ውኃው ከመክደኛው ወጥቶ እሳቱ ላይ ሲንጠባጠብ ‹ትሽ› የሚለው ድምጽ ይሰማ ነበር፡፡ አባቷ ድንገት ቆመ፡፡ ደንግጣ እንደተቀመጠች አቅንታ አየቺው፡፡ ‹‹በይ ተነሺ› አላት፡፡ ዘገም ብላ ተነሣቺ፡፡
‹‹ሦስቱንም የሻሂ ማፍያዎች ክፈቻቸው›› አላት፡፡
‹‹ለምን?›› አለች ግራ ተጋብታ፡፡
‹‹ግዴለም እሺ በይኚ››
መንቀር መንቀር እያለቺ ወደ ማንደጃው ሄደቺ፡፡
‹‹ሦስቱም ማፍያዎች ውስጥ ያሉትን ነገሮች አውጫቸው›› አላት፡፡ ዕንቁላሉንና ድንቹን በጭልፋ አወጣቺና ሰሐኖቻቸው ላይ አደረገቻቸው፡፡ ቡናውን ስኒ ላይ ቀዳቺው፡፡
‹‹እና ምን ይሁን?›› አለቺው ልጁ፡፡
‹‹ድንቹን ተጫኚው፣ ዕንቁላሉን ላጭው፣ ቡናውንም ቅመሺው››
‹‹ተመልከቺ፤ ድንቹ ውኃ ውስጥ ከመግባቱ በፊት ጠንካራ ነበረ፡፡ የፈላው ውኃ ግን ጠንካራውን ድንች ፈረካከሰው፡፡ ዕንቁላሉ የፈላው ውኃ ውስጥ ከመግባቱ በፊት ውጩ ጠንካራ ውስጡ ግን ፈሳሽና ስስ ነበረ፡፡ ውኃው ሲፈላ ግን ውስጡ ፈሳሽና ስስ የነበረው አስኳሉ ጠንካራ ሆነ፡፡ ቡናው ሲፈላ ቤቱን በመዓዛው ዐወደው፣ የአካባቢውንም ጠረን ቀየረው፤ ጣዕሙም ልዩ ሆነ፡፡
‹‹ሦስቱም በተመሳሳይ ማፍያ በተመሳሳይ ዓይነት እሳት ነበር የተጣዱት፡፡ ችሀግራቸው አንድ ነው፤ ለአንድ ዓይነት ችግር የሰጡት ምላሽ ግን የተለያየ ነው፡፡ ድንቹ ጥንካሬውን አጣ፣ ዕንቁላሉ አስኳሉ ጠነከረ፣ ቡናው መዓዛውና ጣዕሙን ይበልጥ እንዲያወጣው አደረገው፡፡ ልጄ ያንቺም ችግር ያለው ከገጠመሽ ችግርና ፈተና አይደለም፡፡ ለገጠመሽ ችግርና ፈተና ከምትሰጪው ምላሽ እንጂ፡፡ የተለያዩ ሰዎች አንድ ዓይነት ፈተና ሊገጥማቸው ይችላል፤ እንዲያውም በኑሮው ውስጥ የማይፈተን ሰው የለም፡፡ ነገር ግን ሰዎች ለችግርና ለፈተና የሚሰጡት ምላሽ የተለያየ ነው፡፡
‹‹ፈተና አንዳንዱን እንደ ድንች ጥንካሬውን አጥቶ እንዲፈረካከስ ያደርገዋል፡፡ አንዳንዱን ሰው ደግሞ እንደ ዕንቁላሉ ውስጡን ያጠነክርለታል፤ ሞራሉን ገንብቶ፣ መንፈሱን ያበረታዋል፡፡ እሳት የብረትን ዝገት እንዲያስወግድ ፈተናም የአንዳንዱን የስንፍና ዝገት ያስወግድለታል፣ ውስጡን ጠንካራ ያደርግለታል፡፡ አንዳንዱ ደግሞ ችግርና መከራው፣ ፈተናና ስቃዩ ውስጣዊ መዓዛውንና ጣዕሙን እንደ ቡናው እንዲያወጣ ያደርገዋል፡፡ ውስጣዊ ችሎታውን፣ ዕምቅ ዐቅሙን፣ የተዳፈነ ተሰጥዖውን፣ ለሌሎች ሊተርፍ የሚችል ጸጋውን ያወጣለታል፡፡
‹‹ውሳኔው በእጅሽ ላይ ነው ልጄ፤ ችግር እንዳይመጣ፣ ፈተናም እንዳይኖር፣ መከራም እንዳይገጥም ተግዳሮትም እንዳይደርስ ማድረግ አይቻልም፡፡ ራስን ወይ ድንች፣  ወይ ቡና ወይም ደግሞ ዕንቁላል ማድረግ ግን ይቻላል፡፡››
ልጁ ጉንጩን ስማው አንገቷን እየነቀነቀች ወጣች፡፡ ውስጧም ‹ዕንቁላል፣ ድንችና ቡና› ይል ነበር፡፡
Filed in: Amharic