>
5:13 pm - Friday April 18, 7828

የሱሌማን ደደፎ ነገር ...!!! (አቻምየለህ ታምሩ)

የሱሌማን ደደፎ ነገር …!!!

አቻምየለህ ታምሩ

ሱሌማን በሽምግልና ዘመኑ እንኳ ኦነግና ወያኔ በወጣትነቱ የጫኑትን የፕሮፓጋንዳ ጭነት ለመመርመር የሚያስችል ጥሞና ማግኘት አልቻለም። ሁላችንን ወክሎ በተሰየመበት ወንበር ላይ ተቀምጦ ጭምትነት መለያ ባሕሪው የሆነውን የአምባሳደርነት ካባ አውልቆ የአንድ ወገን የፈጠራ ታሪክ ቱቦ ሆኖ አረፈው። የጥላቻ ብሔርተኛ ስትሆን ስነ ምግባር፣ ሞያ፣ ኅሊናና ሃይማኖት አይገቱህም…!
 
ሱሌማን ደደፎ  በወዶ ገብነት የወያኔ አገልጋይ የሆነው ወያኔ ሻዕብያን ተከትሎ አዲስ አበባ ሳይገባ ገና ጫካ ሳለ  ከ1983 ዓ.ም. በፊት ነበር። ቦረና ተወልዶ ያደገው ሱሌማን ደደፎ ወያኔ ትግራይን ከኢትዮጵያ ለመገንጠል ይታገል በነበረበት ወቅት ትግራይ ምድር ደጋ ተምቤን በሚባል ወረዳ ሀገረ ሰላም ተብሎ በሚጠራ ገጠር ውስጥ ይገኝ በነበረ የወያኔ ሬዲዮ ጣቢያ በአማርኛ ቋንቋ የፕሮፓጋንዳ ቅስቀሳ ያካሂድ ነበር። በሳምንት ሶስት ጊዜ ይተላለፍ በነበረው የአማርኛ ፕሮግራም “እናት አገር ወይም ሞት” ብሎ ሕይዎቱን ሰጥቶ የአገሩን አንድነት ለማስጠበቅና ገንጣዮችን ለመደምሰስ የዘመተው የኢትዮጵያ ጦር ወያኔንና ሻዕብያን እንዳይወጋ ይቀሰቅስ ነበር። ለተገንጣዮች ይህን ሲያደርግ የነበረው ሱሌማን ዛሬ ዳግማዊ ምኒልክን የአገር ዳር ድንበር የሸረሸሩ ጦሰኛ አድርጎ ሊያቀርባቸው ሲነሳ  ትንሽ እንኳ አይሰቀጥጠውም።
የኢትዮጵያ ጦር ተገንጣዮችን እንዳይወጋ ለቀሰቀሰበት ውለታው ወያኔ ሻዕብያን ተከትሎ አዲስ አበባ እንደገባ ሱሌማንን በአገዛዙ ሚዲያዎች በጋዘጠኛነት እንዲሰራ መደበው። ሱሌማን ወያኔ የሰጠውን ኃላፊነት  በትንሽ ጊዜ ውስጥ በትጋት በመወጣቱ  ብዙ ሳይቆይ “የኢትዮጵያ ሬዲዮ የፕሮግራሞች ኃላፊ”  ተደርጎ በበረከት ስምዖን ሹመት ተሰጠው። በዚህ ኃላፊነቱ ላይ እንዳለ አለቃው እና የፕሬስ መምሪያ ኃላፊ የነበረው የሻዕብያው ሰላይ ተስፋዬ ገብረ አብ ስላልወደደው ከድርጅቱ አባረረው። ከዚህ በኋላ ተስፋዬ ባባረረው በሳምንቱ በምልጃ ወደ ሬድዮ ፋና ተመድቦ መስራት ጀመረ። በዚህ መልክ በፕሮፓጋንዳ ሰራተኛነት ሲሰራ ቆይቶ ኦሮምያ ወደሚባለዉ  “ክልላዊ መንግሥት” ዝውውር አድርጎ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሆኖ ተሾመ። ከምርጫ 97 ማግስት ደግሞ በናይጀሪያ የኢትዮጵያ አምባሰደር ሆኖ ተሾመ። ከዚያም ወደ ጅቡቲ  ተዛውሮ አምባሳደር ሆኖ ነበር።
ዐቢይ አሕመድ ጠቅላይ ሚኒስትር እንደሆነ  ከወሰዳቸው ተቀዳሚ እርምጃዎች ውስጥ በወያኔዎች ተይዘው የነበሩትን ቁልፍ ቁልፍ ቦታዎች በኦሕዴድ ሰዎች ማስያዝ ነበር። በዚህ መሰረት በወያኔው ስዩም መስፍን ተይዞ የነበረውን በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደርነት ቦታ  ለኦሕዴዱ ሱሌማን ደደፎ ተሰጠ።
ይህ በሆነ በሳምንቱ ሱሌማን በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆኖ የተመደበበትን የአንድ ወር እንኳን ደመወዝ ሳይበላ ድርጅቱ ኦሕዴድ በጡረታ ማስወገዱን ቃል አቀባይ የነበረው አዲሱ አረጋ  በሰበር ዜና ነገረን። በእርግጥ አዲሱ አረጋ በሰበር ዜና የነገረን የሱሌማንን ከድርጅቱ መወገድ ብቻ አልነበረም።  በዐቢይ አሕመድ ሊቀመንበርነት ይመራ የነበረው ኦሕዴድ ከዛሬ ሁለት ዓመት በፊት  ከድርጅቱ በጥሮታ ማሰናበቱን በሰበር ዜና  የነገረን ወያኔን ለ27 ዓመታት ሲያገለግሉ የነበሩ 17 የኦሕዴድ ከፍተኛ ባለስልጣናትን  ነበር። ከነዚህ ኦሕዴድ በጥሮታ ካሰናበታቸው 17ቱ  የኦሕዴድ  ከፍተኛ ሹማምንት መካከል  ከሱሌማን ደደፎ በተጨማሪ  እነ አባዱላ ገመዳና  ግርማ ብሩም ይገኙበታል።
ስዩም መስፍንን ተክቶ በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆኖ በተሾመ በሳምንቱ ከድርጅቱ በጥሮታ የተባረረው ነባሩ የኦሕደድ አመራር ሱሌማን  ደደፎ በጥሮታ ከተሰነበተበት  አንድ ወር እንኳን ሳይቆይ  የቤት ልጅ ስለሆነ  በጓሮ በር  ተመልሶ በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ  የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር  ሆኖ በዐቢይ አሕመድ እንደገና ተሾመ።
ሱሌማን ደደፎ ከላይ በቀረበው አኳኋን ለበርካታ አመታት የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆኖ በተለያዩ አገራት እየተዘዋወረ ብዙ የአለም አገራትን ታሪክ የማየት እድል ቢገጥመውም ተሞክሮና ልምድ ሊያገኘው የሚገባው እውቀት ግን የፕሮፓጋንዳ ሰራተኛ በነበረበት ወቅት የተጫነውን  የውሸት ክምር እንዲያራግፍ ሊያግዘው አልቻለም። ሱሌማን በሽምግልና ዘመኑ እንኳ ኦነግና ወያኔ በወጣትነቱ የጫኑትን የፕሮፓጋንዳ ጭነት ለመመርመር የሚያስችል ጥሞና ማግኘት አልቻለም። ሁላችንን ወክሎ በተሰየመበት ወንበር ላይ ተቀምጦ ጭምትነት መለያ ባሕሪው የሆነውን የአምባሳደርነት ካባ አውልቆ የአንድ ወገን የፈጠራ ታሪክ ቱቦ ሆኖ አረፈው። የጥላቻ ብሔርተኛ ስትሆን ስነ ምግባር፣ ሞያ፣ ኅሊናና ሃይማኖት አይገቱህም።
በጥላቻ አእምሮው የዞረ ብሔርተኛ ዘመን ቢቀየር፣ አለም ቢያልፍ ባሕሪውን ሊቀይር አይችልም። ብሔርተኛ የፈለገው ቢሰለጥን፤ በየትኛውም የኃላፊነት ደረጃ ይሰየም ሕልሙ በጥላቻ ከጎለመሰበት መንደር አያልፍም። በጥላቻ ያበደ ብሔርተኛ ህግጋትን ያከብራሉ፣ መብት ይጠብቃሉ፣ ለሞያ ተገዢ ይሆናሉ ተብሎ አይታሰብም። በጥላቻ ያበደ ብሔርተኛ ጥላቻውን እንዳያራምድ የሚያደርግ አለማዊ ሕግ ቢኖር እንኳን የበለጠ መጥላት እንዲችል አድርጎ ይቀይረዋል።
የሮበርት ኢ.ሊ. ሐውልት ይፍረስ መባሉን ተከትሎ  የዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ ሐውልትም እንዲፈርስ ኦነጋውያን ለጀመሩት የጥላቻ ዘመቻ “የሮበርት ኢ.ሊ. ሐውልት ሲፈርስ ኢትዮጵያ ውስጥ ሐውልት መፍረስ ካለበት ከአንድ ሚሊዮን በላይ ባሮች የተፈነገሉበት የአባ ጅፋር ቤተ መንግሥት ነው!” በሚል ርዕስ የጻፍሁትን መልስ ያነበበው ሱሌማን ደደፎም  በሁላችን ስም አምባሳደር መሆኑ ሳያስጨንቀው ኦነጋውያን የከፈቱትን የጥላቻ ዘመቻ በይፋ  የተቀላቀለው “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ” እንዲሉ የጥላቻ ብሔርተኛ ስለሆነ  የተሸለመው ኃላፊነት  ከጎለመሰበት የጥላቻ ፖለቲካ ስለማይበልጥበት ነው።
ኦነጋውያን ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክን የጭካኔ ቁንጮ፣ ጥቁር እባብ፣ የዱር አውሬ እና የአፍሪካ ሂትለር አድርገው የፈጠሩትን ታሪክ ሳይመረምሩ ሲደግሙ የሚውሉት እየጋቱ ያሳደጉትና ለማሰብ ፍቃደኛ ያልሆነው “የቁቤ ትውልድ” የሚሉት ብቻ ሳይሆን ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ እንደገና አንድ ያደረጓትን አገር ወክለው አምባሳደር የሆኑና ጥርሳቸውን የጨረሱ አዛውት ኦሕዴዶች ጭምር መሆናቸው ኦሕደድና ኦነግ ምንና ምን እንደሆኑ በግልጽ የሚያሳይ ይመስለኛል።
ወጣቶቹም ሆነ አዛውንቶቹ የጥላቻ ደቀመዝሙራን የሚያውቁት የተጫኑትን የዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ ፈጸሙት ተብሎ የተነገራቸውን የፈጠራ ‹ጭካኔ› እንጂ ዳግማዊ ምኒልክ በአዋጅ ያስቀሩትን ‹አባቶቼ› የሚሏቸው አባዱላዎች ለዘመናት ሲፈጽሙ የኖሩትን የዘግናኝ ግፍና ጭካኔ ታሪክ ባለቤት መኾናቸውን ከቶ አያውቁም።

 

የሩቁን ዘመን የዐይን ምስክሩን የአባ ባሕረይ ‘ዜናሁ ለጋላ’ን፣ በተመሳሳይ ዘመን የተጻፈውን የዐፄ ሠርፀ ድንግል ዜና መዋዕል፣ ፖርቱጋላዊው የዐይን ምስክር ማኑኤል አልሜዳህ እየተዘዋወረ ከጎበኘ በኋላ በጉዞ ማስታወሻው ያሰፈረውን እና የግራኝ አሕመድ ወረራ ማብቂያ አካባቢ ወደ ኢትዮጵያ የመጣው የፖርቱጋል አምባሳደር ጆን ቤርሙዴዝ በዐይኑ አይቶ በመዘገበው ታሪክ ውስጥ የምናገኘው የኦሮሞ አባ ዱላዎች፣ አባ ገዳዎች እና ሉባዎች ያደረሱትን ሰብዓዊ ጥፋትና ቁሳዊ ውድመት ለጊዜው አቆይተን፣ የቅርቡን ዳግማዊ ምኒልክ በአዋጅ ያስቀሩትን የአባ ዱላዎች ግፍና ጭካኔ፣ የእጅና የጡት ቆረጣ፣ የንጹሐንን ዐይን እንደ ሙጀሌ እያወጡ እና ብልትና እግር እየቆረጡ ይዝናኑ የነበሩበትን የጭካኔ ታሪክ ብቻ ወስደን ሐውልት በመገንባት ለግፉአን መታሰቢያ እናቁም ቢባል የሐውልቱ ብዛት ከኢትዮጵያ የቆዳ ስፋት ይተርፋል።
“ተው ማነህ ተው ማነህ የተኛ ሰው አለ ትቀሰቅሳለህ” የሚል የኢትዮጵያ ብኂል አለ። እነ ተስፋዬ ገብረ አብ የጫኗቸውን ጭነት እንደ እውቀት ተቀብለው ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክን የጭካኔ ቁንጮ አድርገው የሚያቀርቡ ግብዞች አባቶቻችን በሚሏቸው ጦረኛ አባ ዱላዎችና አባ ገዳዎች ተነግሮ የማያልቅ ግፍና መከራ የተፈጸመበት በጣም ከፍተኛ ሕዝብ አለና ተዉ የተኛ ሰው አትቀስቅሱ፤ ያ ቢነሳ ደግ አይደል እንላለን! የነ ተስፋዬን ፈጠራ እያመነዠኩ ጭፍጨፋ የሚል ጸብ አጫሪነት እየደጋገሙ ሲጭሩ የሚውሉ ግብዞች ‹አባ ገዳዎች ለተፈጸመው ጭካኔ ሁሉ መታሰቢያ ይቁም› የሚል የእውነተኛ ተበዳዮች ሀገራዊ እንቅስቃሴ እንዲፈጠር እየሰሩ መኾኑን ልብ ያሉት አይመስልም።
ተስፋዬ ገብረ አብ ፈልስሞ እንካችሁ ያላቸውን ሸቀጥ ሳይመረምሩ ተቀብለው የአኖሌ ትርክትን እንደ ጭፍጨፋ ታሪክ ለሚቆጥሩ ትላልቅ ሕጻናት፣ አባቶቻችን ከሚሏቸው አባገዳዎች መካከል አንዱ የኾነው የጎማው አባ ገዳ፣ የሰዎችን እጅና እግር ሲቆርጥ፣ አንፍጫ ሲፎንን እና ዘግናኝ የጭካኔ ተግባሮችን ሲፈጽም መኖሩን ያውቁ ዘንድ ታሪኩን እነሆ ጋብዣቸዋለሁ። ባለታሪኩ አባ ዱላ የጎማ ገዢ የነበረ ሲኾን ስሙ አባ ዱላ አባ ረቡ ይባላል። የአባ ረቡ ግዛት ጎማ “5ቱ የጊቤ አካባቢ ግዛቶች” ከሚባሉት መካከል አንዱ ነበር። የጎማው አባ ዱላ አባ ረቡ ከታች የቀረበውን ጭካኔ ሲፈጽም የኖረው ዳግማዊ ምኒልክ ሳይወለዱ በአያታቸው በንጉሥ ሣህለ ሥላሴ ዘመን ነበር።
የአባ ረቡን ጭካኔ በጉዞ ማስታወሻቸው ከመዘገቡ የምዕራብ ሀገር ተጓዦች መካከል እግሊዛዊው ሻለቃ ኮርንዋሊስ ሐሪስ አንዱ ነው። ሻለቃ ሐሪስ እ.ኤ.አ. 1840ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ ወደ ኢትዮጵያ የመጣው ከሸዋው ንጉሥ ከሣህለ ሥላሴ ጋር የንግድና የወዳጅነት ስምምነት ለመፈራረም በእንግሊዝ መንግሥት የተላከውን ልዑክ እየመራ ነበር። ሻለቃ ሐሪስ ጎማን ጨምሮ በደቡቡ የኢትዮጵያ ክፍል ያደረገውን ጉብኝት ጨርሶ ወደ አገሩ ከተመለሰ በኋላ እ.ኤ.አ. በ1844 ዓ.ም. በሦስት ቅጽ ባሳተመው «The Highlands of Ethiopia» መጽሐፉ ሦስተኛው ቅጽ፣ ገጽ 60 ላይ ስለ ኦሮሞው የጎማ ገዢ ስለ አባ ዱላ አባ ረቡ የጭካኔ ተግባር የሚከተለውን ጽፏል፡-
“The cruelties practiced by the chief of the Góma are almost incredible. Offenders are deprived of hands, nose, and ears; and their eyes having been seared with a hot iron, the mutilated victims are paraded through the market place for the edification of the populace. The sight of all prisoners taken in war is similarly destroyed; and a stone having been tied about the neck, they are thrown by hundreds into a river formerly styled Daama”
ሻለቃ ሐሪስ በዚህ ምስክርነቱ አባ ረቡ የሚፈጽመው ጭካኔ ለማሰብ የሚከብድ ዘግናኝ መኾኑን ነግሮናል። የሰዎችን እጅ፣ አፍንጫና ጆሮ እየቆረጠ፣ ዐይናቸውን በጋለ ብረት እያፈረጠ የሚዝናና sadist እንደኾነ ምስክርነቱን ሰጥቷል። የአባ ረቡ ጭካኔ በዚህ አያበቃም። እጃቸውን የቆረጣቸውን፣ አፍንጫቸውን የፎነናቸውን እና ጆሯቸውን የጎመዳቸውን፣ ዐይናቸውን በጋለ ብረት ያፈረጣቸውን ሰዎች ‘እኔን ያየህ ተቀጣ’ የሚል መልዕክት ‹ተጽፎባቸው› በገበያ መሀል ያሳልፋቸዋል። ወረራ ፈጽሞ በምርኮ የያዛቸውን ምስኪኖች ደግሞ መቶ መቶውን እያቆራኘ አንገታቸው ላይ ድንጋይ ያስርባቸውና ዳባ ተብሎ ወደሚጠራው ጥቅል ወንዝ ከተራራ ላይ ይወረመራሉ።
በጎማ ይፈጸም የነበረው ይህ ጭካኔ የቆመው ለዐፄ ምኒልክ የገበረው የጎማው የመጨረሻው ጨካኝ ገዢ አባ ቦካ በአዋጅ እንዲተው ከተገደደ በኋላ ነው። እንዲህ ዓይነቱ በዘመኑ የዐይን ምስክር የተመዘገበ በአባ ዱላዎች ሲፈጸም የነበውን የሰዎችን እጅ፣ አፍንጫ እና ጆሮ መቁረጥ፣ ዐይናቸውን በጋለ ብረት እያፈረጡ ማውጣትና መቶ መቶ እያደረጉ ከተራራ ላይ ድንጋይ አሸክሞ  ወደ ወንዝ  እየጣሉ በጭካኔ ይዝናኑ የነበሩ ጨፍጫፊዎች ልጆች ሰውና ርስት የገበሩ ተበዳዮች ዝምታ በጅቷቸው ይህን የመሰለውን ግፍና ጭካኔ በአዋጅ ያስቀሩትን ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክን በተጫኑት የፈጠራ ታሪክ  እየተመሩ ጨፍጫፊ ሊያደርጓቸው ይቃጣቸዋል።
ባጭሩ ኢትዮጵያ ውስጥ በተለይም ኦሮሞ በብዛት በሚኖርበት አካባቢ ተመዝግቦ የምናገኘው በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተፈጸመው የጭካኔ ታሪክ ቢኖሮ ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ የፈጸሙትን የጭካኔ ታሪክ ሳይሆን ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ በአዋጅ ያስቀሩትን የአባ ዱላዎች ጡት የመቁረጥ፣ ዐይን የማፍረጥ፣ አፍንጫ የመፎነንና እጅ የማሳጠር ሥርዓትና ወግ ታሪክ ብቻ ነው። ሳይመረምሩ እንደወረደ የሰለቀጡትን የተስፋዬ ገብረ አብን ፈጠራ እውቀት በማሳከል ዳግማዊ ምኒልክን የጭካኔ መለኪያ ባሮሜትር አድርገው በጩኸትና  ለማሳመር በሚሞክሩት የተስፋዬ ገብረ አብ የአእምሮ ፈጠራ ሲያቀርቡ የሚውሉት ኦነጋውያን ኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጸመ በማስረጃ ሊቀርብ የሚችል ግፍ ቢኖር ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ ያስቀሩት የአባ ረቡ አይነት የኦሮሞ አባ ዱላዎች ያካሄዱት ጭፍጨፋ፣ ዘግናኝ ጭካኔ፣ ገዳ በሚባለው ሥርዓታቸው እየተመሩ በንጹሐን ላይ ሲፈጽሙ የኖሩትን የአረመኔ ተግባር እንጂ የአኖሌ ትርክት አይነት የዐፄ ምኒልክ ታሪክ በዘመኑ በተመዘገበ የታሪክ ማስረጃ ሊያቀርቡ እንደማይችሉ ስለሚያውቁ ነው።
ሱሌማን ብሔርተኛነት በሚሰጠው ድፍረት እየተመራ  ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ የዓባይ ውኃ እንዳይገደብ ለእንግሊዞች እንደፈረሙ፤ ከሱዳን ጋርም የሚያናቁረን የድንበር ጉዳይ የዳግማዊ ምኒልክ ጦስ እንደሆነ ጽፏል። ሱሌማን የሚያውቀው ያገኘውን ጸረ ዐፄ ምኒልክ  የሆነ የፈጠራ ታሪክ  ሁሉ ሳይመረምር ስለሆነ  ይህን ያህል ትላልቅ ክሶች ሲያቀርብ  ኃላፊነት እንደሚሰማው ሰው ተጠያቂነት ቢመጣብኝ ላቀርበው የምችለው ማስረጃ ያስፈልገኛል ብሎ ትንሽ እንኳን  ለመመርመር አልሞከረም። ለመሆኑ ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ አባይን በሚመለከት  ከእንግሊዝ ጋር ሱሌማን እንደነገረን ምንም አይነት ግድብ እንዳይሰራ ተፈራርመዋልን? ከሱዳን ጋርስ ተናቆርንበት ያለው የድንበር ጉዳይ በዐፄ ምኒልክ የተፈጠረ ነውን? እስኪ ዶሴው ይውጣና ይመርመር።
ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ ከእንግሊዝ ጋር እ.ኤ.አ. በ1902 ዓ.ም.  የአባይን ወንዝና የጣናን ሐይቅ እንዲሁም የኢትዮጵያና ሱዳንን ድንበር አስመልክተው የተፈራረሙት ስምምነት አምስት አንቀጽ ያለው ነው። የመጀመሪያው አንቀጽ በኢትዮጵያና ሱዳን መካከል ያለውን ድንበር በሚመለከት ሲሆን ስምምነቱ እንደሚከተለው ነው፤
“በሱዳንና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን ድንበር ሁለቱ መንግሥታት ወደው ከዚህ የውል ደብዳቤ ጋራ ካሉት ሁለት ካርታዎች ላይ በቀይ ቀለም ተመልክቷል። ይህም የተመለከተው ከኮር ኦምሀጀር አንስቶ ገላባት ድረስ፤ ከገላባት እስከ ነጭ ዓባይ፣ ባሮ ወንዝ፣ ፒቦር ወንዝ፣ አኮቦ ወንዝ  እስከ  በሚሌ ድረስ፤ ከመሊሌ አንስቶ እስከ 6ኛው  ማዕረግ (ዲግሪ)ና ከ35ኛው ማዕረግ(ዲግሪ) መገናኛ ድረስ ነው።”
ዳግማዊ ዐፄ  ምኒልክ የተስማሙት ይህን  የኢትዮጵያና የሱዳን ድንበር  ይዘን ወደ መሬት ስንወርድ በዛሬዋ ኢትዮጵያ የሄደብን እንጂ እሳቸው ለሱዳን የሰጡት መሬት የለም። ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ ባደረጉት ስምምነት መሰረት ዛሬ ኤርትራ የሆነው ኦምሃጀርና  ዛሬ የሱዳን አካል የሆነው ገላባት የኢትዮጵያ  ነበር። ወደ ደቡቡ ክፍል ስንሄድም ድንበራችን ዛሬ ደቡብ ሱዳን ውስጥ የሚገኙት ቲቦርና መሊሌ የሚባሉት ወንዞች ነበሩ።  ባጭሩ ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ ከእንግሊዝ ጋር እ.ኤ.አ. በ1902 ዓ.ም.  ባደረጉት ስምምነት የኢትዮጵያ ድንበር አድርገው የተፈራረሟቸው ወንዞችና ወረዳዎች የዛሬዋ ኢትዮጵያ ውስጥ ሳይሆን ሱዳን ውስጥ ነው ያሉት። ይህ የሚያሳየው ዳግማዊ ምኒልክ በስምምነታቸው ለኢትዮጵያ ያደረጉት መሬት ዛሬ የኢትዮጵያ ክፍል አለመሆኑን እንጂ የኢትዮጵያን መሬት አሳልፈው በመስጠት  ዛሬ ጦስ ለተባለው ነገር ምክንያት አለመሆናቸውን ነው። በሌላ አነጋገር ዳግማዊ ዐፄ  ምኒልክ የኢትዮጵያ አድርገውት ሱሌማን ባለሥልጣን የነበረበት የወያኔ አግዛዝ ለሱዳን የሰጠው እንጂ ዳግማዊ ምኒልክ ለሱዳን የሰጡት የኢትዮጵያ መሬት እንደሌለ ስምምነቱ ይነግረናል።
ዳግማዊ ምኒልክ የዓባይን ወንዝ አስመልክቶ የተፈራረሙት የስምምነት  ሶስተኛው አንቀጽ የዛሬዎቹ ለመፈረም ቀርቶ አጀንዳ ለማድረግ የማይደፍሩት የሚያስደንቅ ስምምነት ነው። የስምምነቱ ሶስተኛው አንቀጽ እንዲህ ይነበባል፤
“ጃንሆይ ዳግማዊ ምኒልክ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ ከጥቁር ዓባይና ከባሕር ጣና፤ ከሶባት ወንዝ ወደ ነጭ ዓባይ የሚወርደውን ውኃ ከእንግሊዝ መንግሥት ጋር አስቀደሞ ሳይስማሙ ወንዙን ከዳር እስከ ዳር የሚደፍን ሥራ እንዳይሰሩ፤ ወይም ወንዝ የሚደፍን ሥራ ለማሰራት ለማንም ፍቃድ እንዳይሰጡ በዚህ ውል አድርገዋል።”
ከዚህ የስምምነት አንቀጽ መረዳት እንደሚቻለው ጃንሆን ዳግማዊ ምኒልክ ከእንግሊዝ መንግሥት ጋር የተዋዋሉት ከእንግሊዝ መንግሥት ጋር ሳይስማሙ ዓባይን ሙሉ በሙሉ የሚያስቆም ስራ እንዳይሰሩ እንጂ ዓባይን እንዳይገድቡ ያደረጉት ስምምነት የለም። በስምምነቱ መሰረት ጃንሆን ዳግማዊ ምኒልክ ዓባይን ሙሉ በሙሉ  እስካላቆሙ ድረስ ወንዙን ከእንግሊዝም ጋር ሳይስማሙ መገደብ ይችላሉ። በስምምነቱ የተከለከለው ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ  ከእንግሊዝ ጋር ሳይስማሙ ወንዙን ሙሉ በሙሉ የሚያስቆም ስራ እንዳይሰሩ  ብቻ ነው። በሌላ አነጋገር በስምምነቱ  መሰረት ጃንሆይ ዳግማዊ ምኒልክ 99% የሚሆነውን የዓባይን ውኃ  የማንንም ስምምነት ሳይጠይቁ  መገደብ ይችላሉ። ይህን አይነት ስምምነት የተስማሙትን  ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ ነው እንግዲህ ሱሌማን ደደፎ ሲባል የሰማውን ሳያጣራ እየደገመ ምኒልክ  በዓባይ ላይ ምንም አይነት ግድብ እንዳይሰራ ተስማምተዋል የሚለን።
ዛሬ ዳግማዊ ምኒልክን የሚወቅሱት ባለጌዜዎች ግን  እንኳን 99% የሚሆነውን የወንዙን ውኃ ማንንም ሳያስፈቅዱ ሊገድቡ ቀርቶ የኢትዮጵያ ድርሻ የሆነውን ማለትም 85% የሚሆነውን የዓባይን ውኃ እንኳ ኢትዮጵያ ይገባታል ብለው ደፍረው የመደራደሪያ ነጥብ አድርገው ማቅረብ የማይችሉ ዞምቢዎች ናቸው።
ዳግማዊ ምኒልክ ያልፈረሙትን እንደፈረሙ አድርጎ ሲወቅስ የሚውለው ሱሌማን እስቲ  የሚወክለው አገዛዝ ሞራሉና ወኔው ካለው ዳግማዊ ምኒልክ እ.ኤ.አ. በ1902  ስለ ዓባይ ወንዝ ከእንግሊዝ ጋር የተስማሙትን ስምምነት ዛሬ በመድገም ኢትዮጵያ ማንንም ሳታስፈቅድና ከማንም ጋር ሳትስማማ ወንዙን ሙሉ በሙሉ እስካላቆመች ድረስ ማለትም 99% የሚሆነውን የዓባይን  ውኃ መገደብ እንችላለን ይበሉና እንያቸው እስቲ? ጉብዝና የሚባለው በዚያ ዘመን የነበሩት ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ 99% የሚሆነውን የዓባይ  ውኃ ማንንም ያሳስፈቅዱ እደሚገድቡ የተስማሙትን ስምምነት ዛሬ መድገም እንጂ ኦነግና ወያኔ አምርረው በሚጠሏቸው ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ ላይ ያመረቱን ፈጠራ ታሪክ ሳይመረምሩና ሳያጣሩ መድገም አይደለም። ሱሌማንም ጎበዝ ከሆነ ሲባል የሰማውን ሳያጣራ ከመድገም የያዘውን ቁልፍ የአምባሳደርነት ስልጣን ተጠቅሞ ዳግማዊ  ምኒልክ የተፈራረሙት ስምምነት የዓባይን ውኃ ሙሉ በሙሉ ለመገደብ ሲያስቡ ካልሆነ በስተቀር እስከ 99% የሚሆነውን የወንዙን ውኃ ለመገደብ የማንንም  ፍቃድ ለመጠየቅ እንዳልተፈራረሙ ለአረብ አገራት  ያስረዳ።

∧ከላይ የታተሙት ዶሴዎች እንግሊዛዊው ሻለቃ ሐሪስ  በኢትዮጵያ የነበረውን ጉብኝት አጠናቅቆ ወደ አገሩ ከተመለሰ በኋላ እ.ኤ.አ. በ1844 ዓ.ም. ባሳተመ መጽሐፉ የመዘገበው  ኢትዮጵያ ውስጥ  ሲፈጸም የነበረው  የጉማ ንጉሥ ዘግናኝ ግፍና ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ በአዋጅ የቀረው በአባ ገዳዎች ይፈጸም የነበረው ጭፍጨፋ፣ እጅና ጡት የመቁረጥ፣ ዐይን ማፍረጥ፣ አፍንጫ መፎነንና ዘግናኝ ታሪክ ነው የሚያሳይ ሲሆን የተቀሩት ገጾች ደግሞ ዳግማዊ ምኒልክ ባልዋሉት የሚወቀሱበት እ.ኤ.አ. በ1902 ዓ.ም.  ከእንግሊዝ ጋር የአባይን ወንዝና የጣናን ሐይቅ እንዲሁም የኢትዮጵያና ሱዳንን ድንበር አስመልክተው የተፈራረሙት ስምምነት አንቀጾችን የያዙ ናቸው።

Filed in: Amharic