>

ትዝታ ወ ጉባ...!!! (ወሰን ሰገድ ገ/ኪዳን)

ትዝታ ወ ጉባ…!!!

ወሰን ሰገድ ገ/ኪዳን

ግብፆች ጊዜ ለመግዛት፣ ለማደናቀፍ እንጂ ለመስማማት እንደማይፈልጉ ሳይታለም የተፈታ ሐቅ ነው። ነገር ግን ግብፆች  ማወቅ ያለባቸው  ግድቡ በኢትዮጵያውያን ገንዘብ እየተገነባ  መሆኑን ብቻ አይደለም። ግድቡ እየተገነባ ያለው ከአስር ሺህ በላይ የኢትዮጵያ ልጆች በየቀኑ በሚያፈሱት ነጭ ላብ መሆኑን ነው። ላብ ደግሞ ከደም ይስተካከላል..!
እንደመግቢያ
የሆቴሉ በር በኃይለኛው ተንኳኳ። “ተነስ! ተነሽ! ተነሱ!” የሚል ድምፅ ከኳታው ጋር አስተጋባ። እንደመባተት ብዬ እየተጨናበስኩ የሞባይሌን ሰዓት አየሁ።
ለ11 ሰዓት ሩብ ጉዳይ ይላል። ሊነጋ ነው። እንደምንም ብዬ  ራሴን ከመኝታ ውስጥ አላቀቅኩ። የሆቴላችን ውስጥ ጥሪ አሁንም ቀጥሏል። “ቶሎ በሉ ውጡ እንጂ!” ይላል ቀስቃሹ። ሁላችንም እንቅልፋችንን ባለመጨረሳችን እየተነጨነጫነጭን ከያደርንበት ክፍል ወጣን።
ቀኑን ሙሉ ስንጓዝ ነው የዋልነው። ጉዞአችን ምቾት አልነበረውም። በዚያ ላይ ጉዞው ረዥም ነው። ከ650  ኪሎ ሜትር በላይ ተጉዘን ነው ለአዳር አሶሳ ከተማ ያረፍነው።
ከያደርንበት ክፍል ብንወጣም ውጪው እንደ ጨለመ ነው። ለሊቱ እየነጋ ያለ አይመስልም።ይዞን የመጣው አውቶብስ አፉን ከፍቶ ይጠብቀናል። እንደየአመጣጣችን ገብተን ቦታ ቦታችንን ያዝን።
ሾፌሩ አውቶብሱን ቀሰቀሰው ። ሰዓቴን አየሁ። ከለሊቱ 11 ሰዓት ይላል። ጉዞው ተጀመረ። ዛሬም ከ200  ኪሜ  በላይ  መጓዝ ይጠበቅብናል። መዳረሻችን ጉባ ነው፦ ታላቁ ሕዳሴ ግድብ ወደተፀነሰበት ምድር።
 ❶
አሶሳ ከተማን ለቀን ጥቂት ኪሎሜትር እንደተጓዝን ጥርጊያ አባጣ ጎርባጣ፣ ጥርጊያ መንገድ ገባን። እንዲያም ሆኖ አውቶብሱ እያዘገመም፣ እየነጠረም፣ ሲመቸው እየከነፈ ወደፊት መምዘገዘጉን ቀጥሏል።
ትናንሽ መንደሮች ጥቀርሻ ለብሰው ወደኋላ ሲሮጡ ይታየኛል። ለአንድ ሰዓት ያህል ጨለማው አለመግፈፉ ገርሞኛል። በአውቶብሱ መስኮት ወደ ውጪ ለማየት  ሞከርኩ። በአሻጋሪ የተራራው አድማስ ላይ ልትከት ያለችው ጨረቃ ፍም ያጋተች ትመስላለች።  ቅላቷ አመድ ውስጥ  እንደተተወ ፍም ዓይነት ነው። የተራራውን ጫፍ አስውባዋለች።
ባሻገር ተራራ ቢታይም የምንሄደው ሽቅብ አይደለም፤ ቁልቁል ነው፤ የምንምዘገዘግ  ነው የሚመስለው። ወደ ጉባ መሄድ ማለት ወደ ታች መንከባለል እንደማለት ነው። ምክንያቱም ጉባ ስምጥ ሸለቆ ውስጥ ነው የሚገኘው። ይህንን እያሰብኩ ነው ዕንቅልፍ የወሰደኝ።
 ❷
እኔ ብቻ አይደለሁም። አብዛኛው ተጓዥ ያላለቀ ዕንቅልፉን ለማጣጣት በየወንበሩ ለሽ ብሏል። በድንገት ግን ያልተጠበቀ የጭብጨባ ድምፅ ተሰማ።
“ሄይ ሄይ!…ነቃ ነቃ! ዕቃችሁን ይዛችሁ ውረዱ!”
“ደረስን እንዴ?”
“አልደረስንም….ከዚህ በኋላ 20 ኪሎሜትር ያህል ይቀራል፤  እዚህጋ ውረዱ ፍተሻ አለ..” አለ የተጓዡ ቡድን መሪ።
ወረድን።
በርከት ያሉ የመከላከያ ሠራዊት የጥበቃ አባላት በጥንቃቄ እያዩን ነው።
“….ኮምፒውተር፣ ካሜራ፣ ሞባይል፣ ሌላም ዓይነት ኤሌክትሮኒክስ መሳሪያ የያዛችሁ እዚህጋ አስመዝግቡ” አለ፦ አንዱ መኮንን።
“ጋዜጠኞች መሆናችሁ ስለተነገረን እንጂ ምንም ዓይነት ኤሌክትሮኒክስ መሳሪያ አናስገባም” አለ ሌላኛው ወታደር። እና ፍተሻቸውን ቀጠሉ። ሁላችንም በየተራ እስክንፈተሽ ድረስ አካባቢው መቃኘት ቀጥሏል። የፍተሻው ኬላ መግቢያ በር እንዲህ የሚል መልዕክት በጉልህ ተፅፏል፦
“…ድሮ ዓባይ ይጠጣ ነበር አሁን ግን ሊበላ ነው፤”
 ❸
መፈክሩ ልብ ያሞቃል፤ የአካባቢው ሙቀት ደግሞ ልብ ያቀልጣል። ገና ከአሁኑ ላብ ያጠምቀን ጀምሯል።
ከፍተሻ በኋላ ተመልሰን አውቶብሳችን ውስጥ ገባን። እኛን ለመምራት የመጣው ፓትሮል መኪና ወደፊት መጓዙን ቀጥሏል። የእኛ አውቶብስ ፓትሮሉን እንዲከተለው ታዟል።  (ፓትሮሉ ባይኖር በየኪሎ ሜትሩ በተጠንቀቅ የቆሙት ወታደሮች ያስቆሙናል)
ፓትሮሉ በጥርጊያው መንገድ ላይ እየተጠማዘዘ፤  እንደጉድ እንደ ጉድ እያቦነነ ይከንፋል። የእኛ አውቶብስ ጎማ የሚረግጠው አቧራ ሽቅብ ይጅመለመላል።
ከፍተሻ ጣቢያ ከተነሳን በግምት ከ25 ደቂቃ በኋላ ቅልጥ ያለ ዘመናዊ መንደር ውስጥ ገባን። ይህ ጉባ ነው! አባይ ወደሱዳን ሊወጣ 20 ኪሎሜትር ሲቀረው የሚያዝበት ጉባ! የሕዳሴው ግድብ እምብርት! ቅልጥ ያለው መንደር፣ የሰራተኞች መኖሪያ እና የቢሮዎች መገኛ ነው።
  ❹
ከመኪናችን ወርደን አንድ ዘመናዊ ጎጆ እንድንገባ ተደረገ። እዚህ ጎጆ ውስጥ ገለፃ ይሰጣል። ገለፃው በግድቡ ንድፍ እና አሰራር ላይ ያተኮረ በካርታ የተደገፈ ነው። ነጭ ሄልሜት ያጠለቁ እና ብርቱካናማ ጃኬት የለበሱ ናቸው ኢትዮጵያዊ መሃንዲሶች ናቸው ገለፃ የሚሰጡት። ወጣቶች ናቸው፤ አንደበተ ርቱዕ መሀንዲሶች።
ኮራሁ! “ይህ ትውልድ ጀግና ነው” አልኩ ገለፃቸውን እየሰማሁ።
ከገለፃ በኋላ የሚሰራውን ለማየት እንዲመቻችሁ ብለው ይዘውን ወጡ፦ ወደ መስክ። ጉዞው በመጣንበት አውቶብስ ነው። ጉዞው ወደ ላይ ነው፦ በቅርብ ወደ አለ ተራራ ላይ።
ይገርማል!
እዚያው ጉባ ሆነን፤ እዚያው ግድቡ የሚሰራበትን ቦታ ከከበቡት አንዱ ተራራ ላይ ቆመን ወደ ታች የምናየው እንቅስቃሴ “እጅግ አንሶ”፤ “ደቃቅ ሆኖ” ነው የሚታየው።
የግድቡ ሥራ ሁለት ተራሮችን ነው የሚያገናኘው። በሁለቱ ተራሮች መሃል የ 1.8 ኪሎ ሜትር ርዝመት አለ። በዚህ የ1.8 ኪሎ ሜትር ላይ ለግንባታ ሥራው ወዲያና ወዲህ የሚመላለሱት ዶዘሮች፤ ገልባጭ መኪኖች፤ እና ሌሎች ትላልቅ ማሽኖች ሁሉ የሕፃናት መጫወቻ መኪኖች ያህል አንሰው ነው የሚታዩት። እዛው ሆነን፣ እዛው አንዱ ተራራ ላይ ቆመን ግድቡ የሚሰራበት ሥፍራ የሚንቀሳቀሱት ሰራተኞች “የጆተኒ መጫወቻ ሰዎች” ነው የሚመስሉት። እዚያው ሆነን ቁልቁል የምናየው ጥድፊያ የንቦች በረራ ነው የሚመስለው።
 ❻
ይገርማል!
እዚያ ቦታ ቆመን ወደታች ያየነው ለ15 ደቂቃ ያህል ነው። ቢሆኑም አልቻልንም፦ ሙቀቱን። ቀደም ብሎ ተነግሮናል። የጉባ ሙቀት ከ40 – 50 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ይደርሳል።
እዚያ ያለው ሙቀት ሙቀት ብቻ አይደለም፤ እሳት ነው ማለት ይቻላል። ከላይ እሳት ይዘንባል፤ ከስር ደግሞ የሚፋጅ ወላፈን ይጋረፋል።
የኢትዮጵያ ልጆች ግን በዚህ መሃል ሥራ ላይ ናቸው። ከላይ እናታቸውን ፀሐይ እየነደነደለው፣ ከታች ወላፈኑ እግራቸውን እያንገረበገው ሥራ ላይ ናቸው።
እኛ ግን አልቻንም፤ ልብሳችንን እያወለቅን ነው። መጀመሪያ ቲሸርታችንን አወለቅን። በመጨረሻ በውስጥ ከናቲራ ቀረን። አሁንም አልቻንም፤ ሙቀቱ ይፋጃል፤ ያንገረግባል።
“እነዚህ የሀገሬ ልጆች ግን፣ ንዳዱን እንዴት ቻሉት?” ስል ራሴን ጠየቅኩ። በዚያው ቅፅበት ነበር አጠገባችን የሚቆፍር ስካባተር ያየሁ። ኦፕሬተሩ ወደፊት ወደኋላ እያለ ተራራውን ይምሳል። ፈርጣማ እጆቹ በላብ ርሰዋል። ጠቅላላ ሰውነቱ በላብ  ተዘፍቋል ማለት ይቻላል።
እሱ ብቻ አይደለም። ከ10 በላይ የኢትዮጵያ ልጆች ሥራ ላይ ናቸው፦  ላብ ብቻ ሳይሆን፣ ደም እያላባቸው። እኛ ግን አልቻልንም፦ ንዳዱን።
ይኼንን መሰሉን የሀገሬን ልጆች ትጋት በአርምሞ እየታዘብኩ ሳለ ነው፦ ለምሳ ወደ አንድ አዳራሽ የተወሰድነው።
እዚያ ደግሞ ሌላ ገራሚ ትዕይንት ነበር የጠበቀን። ከ30 በላይ የሕዝብ ማመላሻ አውቶብሶች ለምሳ እየገቡ ነው። በዚያው ቅፅበት ምሣ በልተው የጨረሱ ከ30 በላይ አውቶብሶች ወደ ሥራ እየተመለሱ ነው።
ምክንያቱም በጉባ ሠማይ ሥር እረፍት ብሎ ነገር የለም። ፋታ የለም። የብርሃን ናፍቆት ያነደዳቸው የሀገሬ ልጆች ካለ ዕረፍት እየሰሩ ነው፦ በትጋት። እኛ ጎብኚዎቹ ግን ደክሞና፤ ዕረፍት ናፍቆናል/ ዕረፍት ናፍቆን ነበር።
ይህንን ዕውነት በጉባ ሰማይ ሥር ያየሁት የዛሬ አምስት ዓም ታህሳስ 12/2007 ነበር። Ethiopian Enviroment Journalist Asosation /EEJA/ ነበር የጉብኝት ፕሮግራሙን ያዘጋጀው። ያኔ የግድቡ ሥራ 40 % ያህል ደርሶ ነበር። እነሆ ከ5 ዓመት በኋላ 73 % ደርሷል ተብሏል።
መውጫ
ዛሬ “ጉዞ ትዝታ ወ ጉባ”ን ያስታወሰኝ የግብፅ አቋም ነው። ግብፅ፤ ስምምነት ላይ ሳንደርስ ኢትዮጵያ ግድቡ ውሃ መያዝ የለበትም አለች አሉ።
አልገረመኝም፤
ትናንትና  የግብጽ የውኃ ሐብትና መስኖ ሚኒስቴር ቃል ፈቂ አሕመድ “ልዩነቱ በአጭር ጊዜ ይጠባል ማለት አስቸጋሪ ነው” ብለው ነበርና። ግብፆች ጊዜ ለመግዛት፣ ለማደናቀፍ እንጂ ለመስማማት እንደማይፈልጉ ሳይታለም የተፈታ ሐቅ ነው።
ነገር ግን ግብፆች አንድ ነገር በትክክል ማወቅ አለባቸው። ማወቅ ያለባቸው ግድቡ በኢትዮጵያውያን ገንዘብ እየተገነባ ያለ መሆኑን ብቻ አይደለም። ግድቡ እየተገነባ ያለው ከአስር ሺህ በላይ የኢትዮጵያ ልጆች በየቀኑ በሚያንጠባጥቡት ላብ ነው።እያንዳንዱ የግድቡ እርከን የተቀጣጠለው፣ እያንዳንንዱ የግድቡ እርከን የተላቆጠው የተያያዘው በሃገሬ ልጆች የላብ ደም  መሆኑን ነው።
በየዓመቱ፣ በየቀኒኑ ከ10 በላይ የሀገሬ ልጆች የሚያፈሱት ላብ፣ በጦር ሜዳ ከሚፈስ ደም የላቀ እና የደመቀ መሆኑን ጠንቅቀው ማወቅ አለባቸው። ይኼንን ከደም በላቀ ላብ የተገነባን  ግድብ ዳር ከማድረስ የሚመልሰን ኃይል እንደሌለ ማወቅ አለባቸው።  ግድቡ ገንዘብ፣ ጊዜ፣ እና ከደም የላቀ ላብ የፈሰሰበት ነውና።
በአጭሩ፤ ከአባይ ባለቤትነታችን ባሻገር፤ ገንዘባችንን፣ ደማችንን እና ላባችንን የከፈልንበት ነው። በተከፈለበት ጉዳይ ደግሞ ወደኋላ የሚመለስ የለም!
ይኸው ነው።
Filed in: Amharic