>

ሁሉንም የነፃነት መንገዶች የባሰ ቅርቃር ውስጥ ላለመክተት ከሰመመኑ የነቃ ትውልድ እንፍጠር!!! " (አሰፋ ሀይሉ)

ሁሉንም የነፃነት መንገዶች የባሰ ቅርቃር ውስጥ ላለመክተት ከሰመመኑ የነቃ ትውልድ እንፍጠር!!! “

አሰፋ ሀይሉ
 
* «የኢትዮጵያ ጠላት ያ አካል ወይም ይሄ አካል አይደለም: በተግባር የተገለጸ ቁርጥ አቋም የሌለው ወላዋይ ሁሉ እንጂ…!!! 

ኢትዮጵያ ውስጥ አሁንም በትክክል «ተቋም» ተብሎ ሊጠራ የሚችል ተቋም የለም፡፡ በዓይን ምልክት ሊሾሙ ሊሻሩ (ካስፈለገም ሊፈርሱ) የሚችሉ አጨብጫቢ ከመሆን ውጭ ሌላ የህልውና አማራጭ የሌላቸው የስም ተቋማት ናቸው ያሉት፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ አሁንም በትክክል የወከለውን ሕዝብ ሃሳብ ሳያወላዳ የሚያራምድ ፓርላማ የለም፡፡
በአንድ አምባገነን ፓርቲ ቁንጥጫ ባስፈለገው አቅጣጫ የሚጠመዘዙ – ካስፈለገም ያለመከሰስ መብታቸው በአፍታ ተገፍፎ የሚታሰሩ፣ የሚፈቱ፣ የሚሾሙ፣ የሚሻሩ የፓርቲ ተላላኪዎች ናቸው «የተከበሩ የፓርላማ አባል» እየተባሉ ሲቆለጳጰሱ የሚኖሩት፡፡ አልፈርድባቸውም፡፡ ሥልጣኑም ክብሩም የላቸውም፡፡ በትክክል በሕዝብ ተመርጠው ይሁን ወንበር ያገኙት ወይስ ፓርቲያቸው ኮሮጆውን ገልብጦ የሚያውቁት ነገር የላቸውም፡፡
ብዙዎቹን ራሳቸውን ለማሻሻል የሻቱትን በተለያዩ ኮሌጆች ሳስተምራቸው ነበር፡፡ ስለ ማንነታቸውም (ስለ አስተሳሰባቸው፣ ስለ ትልማቸው፣ ስለሀገሪቱ ሁኔታ በግል ስለሚያስቡት ምልከታ) ለመረዳት ብዙ ሞክሬያሁ፡፡ ብዙም ነገር ለማስተዋል ሞክሬያለሁ፡፡ ብዙዎቹ ፍላጎቱና ቅንነቱ አላቸው፡፡ ግን «ቱል» ናቸው፡፡ ምንም አቅም የሌላቸው የፓርቲው መጠቀሚያ መሣሪያዎች፡፡ እና እያንዳንዳቸውን በተናጠል ስታያቸው ‹‹Helpless›› ናቸው፡፡ ረዳት የለሾች፡፡ ምንም ማድረግ የማይችሉ አቅመ ቢሶች፡፡ ቀርቦ ላየው እውነታውን ያሳዝናል በእውነቱ፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ፍርድ ቤቶቹ በፓርቲው ጥቅሻ በሚባረሩና በሚሰነብቱ ተሿሚ ዳኞች የተሞላ ነው፡፡ ዳኞቹም ቅንነትንና ሙያዊ ቀናዔነትን አላጡም፡፡ ግን በየት በኩል? ፖሊሱም ያው ነው፡፡ በፓርቲው ሰዎች የሚሾም የሚሻር – ካስፈለገም አፈር ድሜ የሚግጥ – አንገቱን የደፋ ፖሊስ የሞላበት ነው፡፡ ጤና ጥበቃ የሚባለው – በፓርቲው ቁጥጥር ሥር የዋሉ ሃኪሞች በሃኪሞች የተጠላ የበሰበሰ የፓርቲ አጀንዳቸውን በባለሙያው ላይ ሊጭኑ የሚርመሰመሱበት በባለሙያው ተጠልቶ የኖረ ‹‹የተተፋ›› ተቋም ነው፡፡ ተቃውሞውን ትንፍሽ ያለ በማግሥቱ ከሥራው ከሹመቱ ተባራሪ ነው፡፡
ባንኮች ተመሣሣይ ናቸው፡፡ ነጋ ጠባ በተለያዩ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችና ብሔራዊ ባንክ ስቃያቸውን የሚያዩ  – ሰጥ ለጥ ብለው ፓርቲውን እንደ ግል አዳኛቸው ቆጥረው የሚንቀሳቀሱ ተቋማት ናቸው፡፡ ሚዲያው በቀጥታ በፓርቲው ቁጥጥርና ምሪት ሥር የዋለ ነው፡፡ ድሮም፡፡ አሁንም፡፡ እና የትኛው ተቋም ነው ኢትዮጵያ ውስጥ በትክክል ተቋም ተብሎ ሊጠራ የሚችለው? ነፃ ተቋም የለም፡፡ የራሱን ሥነምግባር ለማስጠበቅ ፀንቶ የሚቆም ተቋም ይቅርና ተሰፍሮ የተሰጠውን ሥራ ራሱ ያለማንም ጣልቃ ገብነት ለመከወን የተፈቀደለት ገለልተኛ ተቋም በኢትዮጵያ ምድር አይታሰብም፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ነፃም፣ ገለልተኛም፣ የራሱን ሥራ በራሱ ለመሥራት የተፈቀደለትም አንድም ተቋም የለም፡፡
ነፃ ተቋም በሌለባት ኢትዮጵያ ለዚህ ነው የኮሮና ሰለባዎችን ቁጥር በትክክል ምን ያህል እንደሆነ ከተቋሙ ሰምተህ መደምደም የማትችልባት ሀገር የሆነችው፡፡ የሆነን አሃዝ ሰምተህ በሙሉ ልብህ የምታምነው ምንም ተቋም የለም፡፡ የኢኮኖሚና ፋይናንስ ተቋማቱ የሀገሪቱ ህዝብ በኑሮ አረንቋ መከራውን እየበላ ባለበት አስከፊ ኑሮ ውስጥ ሀገሪቱ በሁለት አሃዝ አድጋለች ተመንድጋለች የሚል ሪፖርትን ጠዋት ማታ የሚያዘንቡ ተቋማት ናቸው፡፡ ተቆጣጣሪው በተቆጣሪው መዳፍ ሥር የዋለባት ሀገር ብትኖር ኢትዮጵያ ናት፡፡
ሀገሪቱ ስላለችበት ሁኔታ የሚናገረውን መረጃ በትክክል አምነህ ልትቀበለው የምትችል ምንም አይነት ተቋም የለም በኢትዮጵያ ውስጥ፡፡ የዜጎችን እምነት ገደል የከተቱ ተቋማት ሌት ተቀን በተቆጣጠሩት ሚዲያ ለሕዝብ ስለሚያላዝኑ ብቻ – ለሩቅ ተመልካች «ቅቡልነት ያለው መንግሥት» በእውን ያለ እና ተግባሩንም እየከወነ ያለ መስሎ ይታያል፡፡ ነገር ግን የወሬ ፋብሪካ ነው ያለው፡፡ በሂትለር ፕሮፓጋንዳ ማሽን አምሳል የተቀረፁና በአንድ ፓርቲ የሌት ተቀን ቁጥጥር ሥር የዋሉ ተቋማት እንደ ምርት ፕሮፓጋንዳን እያመረቱ ለህዝብ የሚያሰራጩባት ሀገር ናት ኢትዮጵያ፡፡
እደግመዋለሁ በኢትዮጵያ ውስጥ እምነት ሊጣልበት የሚችል ምንም ነፃ ተቋም የለም፡፡ ለዚህ ነው የአውራው ፓርቲ አውራ ማፊያዎች ኮሮና ቫይረስ ምርጫውን ለማራዘም አሰናከለን ብለው ሲጮኹ – በሁሉም ዘንድ አመኔታ ለማግኘት ያልቻሉት፡፡ ዛሬ ኮሮና እያለ ምን ሲደረግ ምርጫ ይታሰባል – ብሎ ቡራ ከረዩ ሲል የሚታየው ወፈሰማይ ተንታኝና ባለሥልጣን – ነገ ፓርቲው በቃ ኮሮናው ቢኖርም ለአንዲት ቀን ምርጫ ማድረግ አይሳነንም – ቢል – ያው ወፈሰማይ አጨብጫቢ – እንኳን ምርጫን ተራራን መግፋት አይሳነንም ብሎ ሲያቾፈቹፍ ታገኘዋለህ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ተቋም የለም፡፡ ኢትዮጵያ የነፃ ተቋም ችጋር ላይ ነች፡፡ የነፃነት ረሃብ ላይ ነች፡፡ ይህንን የቅርቡን የነፃነት ጠላት መዋጋት የተሳነው ሕዝብ ነው – ሩቅ ያለችውን ግብጽን ተዋጋ ነው እየተባለ ያለው፡፡
በእኔ አስተሳሰብ ኢትዮጵያን ለመለወጥ ለተግባር የፈጠነ ሕዝብ መፈጠር አለበት! ወሬ ብቻ አይደለም ይሄን ያለንበትን የውሸት ድሪንቶ ከእግር እስከ ራሳቸው የተከናነቡ ተቋማት የሞሉበትን አዳፋ ታሪካችንን የሚቀይረው፡፡ በተግባር የተገለጸ ቁርጥ አቋም ነው ለውጥ የሚያመጣው፡፡ የኢትዮጵያ ጠላት ያ አካል ወይም ይሄ አካል አይደለም፡፡ ሕዝባችን ነፃ ተቋማትን ለመገንባትና ከነፃ ተቋማት ጎን ለመሰለፍ ያለው ዕውቀትና ቁርጠኝነት ዜሮ መሆኑ ነው – የችግሩ ሁሉ ምንጭ፡፡ ትናንት ወያኔ ሄደ፡፡ ዛሬ የወያኔ ቡችሎች መጡ፡፡ ነገ ደግሞ ሌላ መጣ፡፡ ከነገወዲያ ደሞ ሌላ ይሄዳል፡፡ ያ አይደለም ትልቁ ኢትዮጵያን ከገባችበት የሁሉን ፈላጭቆራጭ አምባገነን ቀንበር የሚታደገው ቁምነገር፡፡
ቁምነገሩ – ነፃ ተቋማትን ነፍስ ዘርተው ለማየት እና ተቋማቱን በነፍሱ ተወራርዶ ለመጠበቅ ሕዝብ ያለው ቁርጠኛ አቋም ነው፡፡ ኢትዮጵያን የሚቀይራት ብቸኛ ኃይል ይህ የሕዝብ ኃይል ብቻ ነው፡፡ ኢትዮጵያን ከገባችበት የኋላቀርነትና የአምባገነንነት ትብታብ አላቅቆ – ለዜጎቿ ፍላጎትና ህልውና ክብር ወደምትሰጥ፣ ወደ እድገት የምትገሰግስ ነፃነት የሰፈነባት ኢትዮጵያን ሊፈጥር የሚችለው ብቸኛው ኃይል – አሁን ከገባበት ወደር የሌለው የዳተኝነትንና የምንቸገረኝነት መንፈስ ተላቅቆ ነፃ ተቋማትን ለማነፅና በሕይወቱ ለመጠበቅ የሚተጋ ሕዝብ ብቻ ነው፡፡ ያ ህዝብ ገና አልተፈጠረም፡፡
አሁን ያለው የኢትዮጵያ ህዝብ ያንን እንዳያስብ ብዙ ለዓመታት የተሠሩ ሴራዎችና ቅርቃሮች ፕሮፓጋንዳዎች ግራማጋባቶች አዕምሮውን ጋርደውታል፡፡ ምናልባት የወደፊቱ ትውልድ አዕምሮውን ከፍቶ ኢትዮጵያ ሀገሩን ከነዚህ የዘመን ትብታቦች አላቅቆ ነፃ የሆነች ሀገርን ያተርፍ እንደሆነ የምናየው ይሆናል፡፡ ያም ሌላ ሁሉንም የነፃነት መንገዶች የባሰ ቅርቃር ውስጥ የሚከትት ሀገራዊ ክስተት ካልገጠመንና እንደ ሀገር እስከዚያ በሠላም ከኖርን ነው፡፡ የምመኘው ከሰመመኑ የነቃ ትውልድ እንዲፈጠር ብቻ ነው፡፡ ሌላ የምመኘውም የምለውም የለኝም፡፡
እናት ኢትዮጵያ – በአይበገሬ ልጆቿ ፀንታ – ለዘለዓለም ትኑር!       
ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ!
Filed in: Amharic