>

ቤት ተቀመጡ ተባልን፤ የኤሌክትሪክ ኃይል ግን የለም (ከይኄይስ እውነቱ)

ቤት ተቀመጡ ተባልን፤ የኤሌክትሪክ ኃይል ግን የለም

ከይኄይስ እውነቱ

በወረርሽኙ ምክንያት አብዛኛውን የመንግሥት ሠራተኛ ጨምሮ የግድ አስፈላጊ ለሆነ ጉዳይ ካልሆነ በቀር ኅብረተሰቡ በቤቱ በመቈየት ራሱን ከወረርሽኙ እንዲከላከል ከጤና ባለሙያዎች በተደጋጋሚ ምክር ተሰጥቷል፡፡ አገዛዙም ለዚሁ ዓላማ ሕጎችን አውጥቷል፡፡ ታዲያ ይህንን ምክርና ትእዛዝ ተግባራዊ በማድረግ ራሱንም ሌሎች ወገኖቹንም ለመጠበቅ ሲል በቤት ተወስኖ የሚገኘው የኅብረተሰብ ክፍል በቤት ውስጥ ቆይታው ከአገዛዙ ቢያንስ የኤሌክትሪክ ኃይልና የውኃ አቅርቦት ሊሟሉለት ይገባል፡፡ 

ሰሞኑን በተለይም በአዲስ አበባ ቂርቆስ ክ/ከተማ የተወሰኑ ወረዳዎች በተደጋጋሚ የኤሌክትሪክ ኃይል እየተቋረጠብን በችግር ውስጥ እንገኛለን፡፡ ምክንያቱ ከየትኛውም ክፍል አልተነገረንም፡፡ ብልሽትም የለም፡፡ እንዲያው ዝም ብሎ ክረምቱን ሰበብ ለማድረግ ካልተፈለገ በቀር፡፡ ወደሚመለከተው ድርጅት ስንደውል፣ አገርን ወክሎ ባለቤት ከተባለው መ/ቤት ፕሮጀክቱ የቻይኖች ነው፤ እኛ አልተረከብነውም እነሱን (ቻይኖቹን) ጠይቁ የሚል የሚገርም መልስ ተሰጥቶናል፡፡ ይህ በመላው አ.አ. በቻይና ድርጅት ለዓመታት ሲንከባለል የቈየው ፕሮጀክት ባንዳንድ ክ/ከተሞች ሥራው ተጠናቅቆ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ ቢያንስ ከ6 ወራት በላይ ሆኖታል፡፡ በኤሌክትሪክ አገልግሎት ክፍያ ላይ አንድ መቶ ፐርሰንት ጭማሪ ተደርጎ ክፍያው አብዛኛውን የኅብረተሰብ ክፍል እያንገዳገደ ባለበት ሰዓት ይባስ ብሎ አገልግሎቱን ማቋረጥ ምን የሚሉት ነው?

ኤሌክትሪክ ከሌለ ምግብ በምን እናብስል? ከቴሌቪዥን፣ ከራዲዮ፣ ከኢንተርኔት መረጃ እንዴት እናግኝ? ቤት ውስጥ ሥራቸውን የሚያከናውኑ የመንግሥትም ሆኑ የግል ድርጅቶች ሠራተኞች ሥራቸውን እንዴት ያከናውኑ? ልጆችስ ትምህርታቸውን እንዴት ይከታተሉ? ቀኑ ጨለማ ሆኖ ማነው ቤት ውስጥ የሚቀመጥ?

ኧረ ሰውን ባትፈሩም ባታፍሩም፣ እምነት ካላችሁ እግዚአብሔርን ፍሩ!

Filed in: Amharic