>
5:13 pm - Wednesday April 19, 1944

እነሆ እውነቱ....!!! (ኤርሚያስ ለገሰ ዋቅጅራ)

እነሆ እውነቱ….!!!

ኤርሚያስ ለገሰ ዋቅጅራ

 

እኛ ስነግርህ አንተ ስትሰድበን! አንቺ ስትሞልጪን ከረምክ(ሽ)፣
ራሱን “የለውጥ ሃይል” ብሎ የሚጠራው ቡድን በተረኛ ባለሃብቶች ሙርከኛ (State Capture) ሆኗል ብለን ነገርንህ። አላመንከንም(ሽም)። አልፈህ ሄደህ “ለውጡን አደናቃፊ” የሚል ማዕረግ ሰጠኸን(ሽን)። ቀጥለን የመንግስት ባለስልጣናት የተደራጀ ዘራፊና ሌባ የሆኑ የሀብት ማማ ላይ የወጡ ባለሃብቶች ጉዳይ አስፈፃሚ ሆነዋል አልንህ። ምሳሌ ጥቀስ ብለህ ስታብጠለጥለን ደግሞ ኦቦ ድንቁ ደያስ ብለን ነገርንህ። የውሸት ዜና ብለህ ባደራጀኸው ሃምሳ ሳንቲሞች ወረድክብን። አስወገዝከን። ይወገሩም አልክ። አልሽ።
ጊዜ ያወጣዋል ብለን ድንቁ ደያስና ኔትወርኮቹ ከኢትዮጵያ ሱሴ፣ ከንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት ባጫ፣ ከጃዋር መሃመድ ጋር በመሆን የንግድ ባንኩን አጥንት እንደጋጡት ገለጥንልህ። አሁንም “ፌክ ኒውስ” በሚል ስድብ በሚኒሊክ ጊዜ እንደ ደነቆረው ሰው ሆንክብን። “ኢትዮጵያ ሱሴ” እንዴት ተነካብን ብለህ አገር ይያዝልኝ አልክ። ተንደርድረህ ከለውጥ አደናቃፊነት ወደ “ሁከት ጠማቂነት” የደረጃ እድገት ሰጠኸን። በዛም ሳትወሰን በስታሊናዊና ኮሚኒስታዊ አጠራር ተጠቅመህ “የሕዝብ ጠላት” አልከን። የጭብጨባህ አጃቢዎች ጐርፍ ሆነው ዘመቱብን። ተናዳፊና ያልተገራ የቃላት እሩምታቸው ዘግናኝ ነበር። እንትፍ! እንትፍ! የሴጣን ጆሮ ይደፈን ብለን በጉንበሳ ባናሳልፈው ኖሮ ሰቅጣጭ ነበር። እርግጥ ቢገባቸው ኖሮ የህዝባችንን አበሳ እያራዘሙት ነበር።
እኛም የእርከን ጭማሪውን በፀጋ ተቀብለን አሁንም ባለቃልቻው ድንቁ ደያስ የራሱ እስር ቤትና ገራፊ እንዳለው ነገርንህ። በደረቅ ቼክ በርካቶችን ጉድ እንደሰራ ጨመርንልህ። እንደ ሶደሬ ያሉ የህዝብ ንብረቶችን በህገ ወጥ መንገድ መቆጣጠሩን አክለን አጫወትንህ። እንደ አባዱላና ብርሃኑ ፀጋዬ የመሳስሉ ባለስልጣናት ጭውቴ ውስጥ አሉበት አልንህ። አንተ እቴ! ምን ገዶህ! ማህተብ አልቦ አይደለህ! የአንተ መነጽር እንደሆነ ሁሉንም ነገር የሚያየው በመደገፍና መደመር ሌንስ ነው። ቄጠማ ስለሆንክ ትደገፋለህ። ራስን ሆነህ መኖር ስላቃተህ ትደመራለህ። ጀንበር ትወጣለች። ትጠልቃለች። አንተ ግን የአደራ እቃ ነህ። እንዳስቀመጡህ የምትገኝ።
ዛሬ ደግፎ የደመረህ ዋልታ ቴሌቭዥን ድንቁ ደያስን ሰማይ አንስቶ ምድር ሲያፈርጠው ከማንም ቀድመህ አዳማቂ ሆንክ። ወስላታ ባህሪህ አይኑን በጨው አጥቦ መጣ። ደያሳም ብጤ ነህ። ያው! በአዱ ገነት ቋንቋ ደያስ ሽሮ ነው። ሽሮ የሚደነፋው ደግሞ እንጀራ እስከ ቅርብ ነው።
ያም ሆነ ይህ እኛም “ለጠላቴ ምርቃት” የሚለውን የገጣሚ ታገል ሰይፉ ዘመን ተሻጋሪ ግጥም በህሊናችን እያውጠነጠንን ቀጣዩን ምዕራፍ ወደ ማሰብ ተሸጋገርን። አንተም በመደመር ምጽዋት ያገኘኸውን ደያስ ግድግዳ ተደግፈህ ብላ።
Filed in: Amharic