>

ጠ/ሚ ዶ/ር አቢይ ማስመሰል የማያውቅበት ቋሚ ጠባዩን ልንገርህ! (ዳግማዊ ጉዱ ካሣ)

ጠ/ሚ ዶ/ር አቢይ ማስመሰል የማያውቅበት ቋሚ ጠባዩን ልንገርህ!

ዳግማዊ ጉዱ ካሣ


 

“Why do people lie?” በሚል መሪ ጥያቄ አንዳንድ እውነታዎችን ከአንዳንድ ምንጮች መዳሰስና ወደ እናንተ ማድረስ ፈልጌ ሳለ ኢንተርኔት ተቋረጠብኝ፡፡ እኔው ከማውቀው ተነስቼ ትንሽ ልጓዝበት ነው፡፡

በርግጥም  “ሰዎች ለምን ይዋሻሉ?” ከባድ ጥያቄ ነው፡፡ መልሱም እንዲህ በቀላሉ የሚገኝ አይመስልም፡፡ 

እንደምገምተው ውሸት ወይም ሀሰት መናገር ከመጥፎ ስብዕና ጋር የተቆራኘ ነው፡፡ ሀሰተኛ ሰው ሃይማኖት የለውም፡፡ ለምን ቢባል “ዋሽ” ወይም “ሀሰትን ተናገር” የሚል የምናውቀው የሃይማኖት ተቋም የለምና፡፡ በክርስትናው ከሆነ ከአሠርቱ ትዕዛዛት አንዱ ነው፡፡ ለእውነት ሲባል አንገታቸውን ለሠይፍ፣ ደረታቸውን ለጦር የሰጡ አባቶችና እናቶች እንዲሁም ወንድሞችና እህቶች እንደነበሩ ገድሎችና ድርሣናት ይዘግባሉ፤ መጽሐፍ ቅዱስም ስለእውነት ብዙ ብዙ ብሏል፡፡ ብሂላችን ሳይቀር በብዙ ትርክቶች “እውነትን ተናግሮ እመሸበት ማደር፤ የተናገሩት ከሚጠፋ የወለዱት ይጥፋ፤ እውነትና ንጋት እያደር ይገለጣል፤ ስንቅና ውሸታም እያደር ይቀላል፤…” ሲል እውነት የመናገርን ሞራላዊ ግዴታ በግልጽ ያሳያል፡፡ አንድን ህግ መጣስ ደግሞ ለሌላኛው አቀባብሎ ስለሚተውህ ቀጣዩንና ቀጣዮቹንም ጭምር ያላንዳች ይሉኝታና ሀፍረት ትደረማምሳቸዋለህ፡፡ ለምሣሌ አንድ ነገር ሰርቀህ ሳለ ስትጠየቅ “አልሰረቅሁም” ነው የምትለው፡፡ ታማኝ ሌባ ብሎ ነገር የለምና “አዎ፣ ሰርቄያለሁ” የሚል ሰው ማግኘት የሚቻል አይመስለኝም፡፡

በቀደሙ ዘመናት ባህላችን እንደዛሬው ሳይሆን በአብዛኛው እውነትን እንድንናገር ተኮትኩተን እናድግ ነበር፡፡ በዚህ ዘመን ግን ከላይ እስከታች ሀሰትን መናገር እንደጽድቅ እየተቆጠረ በተቃራኒው እውነትን መናገር ግን ዘብጥያ የሚያወርድ ወንጀልና ቡና የማያጠራራ ነውር እየሆነ ነው፡፡ ይህ እኛነታችን በመንግሥት ደረጃ ግዘፍ ነስቶ መሪያችን የሀሰት ጣቃ ሲሆን ደግሞ ይታያችሁ፡፡ ሃይማኖትም መንግሥትም ከመሪዎች ጋር በጽኑ ይያያዛሉና የሁሉም ዘርፍ መሪዎች ዋሾ ከሆኑ ትውልዱም ዋሾነትንና በየትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው መሰላል እየተንጠላጠለ የራሱን ብልጥግና ማረጋገጥን ብቻ ዋና ትኩረቱ ስለሚያደርግ ለሀገርና ለዜጋ የሚፈይደው ነገር እስከዚህም ነው ወይም ከናካቴው ላይኖርም ይችላል፡፡

በዚህ መልክ ክርስቲያን ነኝ የሚለው መሪያችን “በሀሰት አትመስክር” የሚለውን መሠረታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል በተደጋጋሚ በመሻር የሚስተካከለው እንደሌለ በሃቅ መመስከር ይቻላል፡፡ በዚህ የማያወላውል ቋሚ ባሕርዩም ሊወደስ ይገባዋል – መጥፎም ቢሆን፡፡

ዛሬ ጧት የግዛው ለገሠን አንድ ግሩም ጽሑፍ ፌስቡክ ላይ ሳነብ የተረዳሁትም ይህንኑ የጠ/ሚኒስትራችንን የማይለወጥና ዕድገት ብሎ ሲያልፍ የማይነካው የመዋሸት ባሕርይ ነው፡፡ በዚህ ሰው መመራት በበኩሌ እጅግ ያሳፍረኛል፡፡ እርግጥ ነው – በሌላ በኩል በንባብ፣ በትምህርትና በልምድ ያዳበረው ዕውቀቱ፣ የንግግሩና የአነጋገር ለዛው (ይዘት አላልኩም!)፣ የሚያሳያቸው “አክሮባቶቹ”ና የትወና ብቃቱ ያስደንቁኛል፡፡ እነዚህ ሁሉ ግን በርሱ ላለማፈር አልረዱኝም፡፡ አዝናለሁ፤ እሱም ያሳዝነኛል፡፡ እንዲህ ፍዳውን የሚበላው ይቺም ሥልጣን ሆና እሷን ለማስጠበቅ እንደሆነ ይገባኛል፡፡ ለነገሩ ለሥልጣን የሚቋምጥ ሰው ኅሊናውን ለሥጋዊ ፍላጎቱ በመሸጥ በሥነ ልቦና መስክ እንደሚጠቀሰው pathological liar የመሆን ዕድሉ ሰፊ ነው – ለምድሩ እንጂ ለሰማዩ ደንታ የለውም፡፡ አለዚያ ሥልጣኑን የሚቀራመተው ቀበሮና ተኩላ የትዬለሌ ነው – ሊያውም በዘርና በጎሣ በተበጣጠቀች ሀገር፡፡ የመለስ ልጅ አቢይም የተከተለው የአባቱን መርኅ መሆኑ ይህን የፈጠጠ እውነታ ያሳያል፡፡ “ዱባ ካላበደ ቅል አይጥልም” ይባላልና ከዘንዶ ሆድ ወጥቶ ዕርግብ እንዲሆን ከጠበቅህ ሞኙ አንተ እንጂ አስመሳዩ አቢይ ሊሆን አይችልም፡፡ እንደኔ ኢትዮጵያን መምራት ያለባት ማንም ይሁን ማን ዕድሜው/ዋ በትንሹ ከ60 ዓመት  የማያንስና በቀደመው ኢትዮጵያዊ የአብሮነት ጨዋ ባህልና ወግ የተገራ መሆን አለበት፡፡ በዚህ መስመር የመጣ ሐጎስ ይሁን ደቻሳ ወይም ዘበርጋ  ይሁን ኦባንግ ግዴለኝም ብቻ ሳይሆን ምርጫየም ነው፡፡ 

ሰዎች ለተለያዩ ጉዳዮች ለውሸት ይጋለጣሉ፡፡ ያጣውን ለማግኘት፣ ያገኘውንም ላለማጣት አንድ ሰው ሊዋሽ ይችላል፡፡ ራሱን ለመካብ ወይም ሌላ ሰው ለማዋረድ ሊዋሽ ይችላል፡፡ የሠራውን መጥፎም ይሁን ደግ ሥራ እንዳይታወቅበት ለመደበቅ ሲል ሊዋሽ የሚችልም አለ፡፡ በፍርድ ቤት ከቅጣት ለመዳንና ለመሳሰለው ሁሉ ይዋሻል፡፡ መዋሸት ስንል በደምሳሳው የሆነን እንዳልሆነ፣ ያልሆነን እንዳሆነ አድርገን ለአንድ ዓላማ ወይም ለአንዳች ጥቅም መናገር ማለት ነው፡፡ በዚህም እንዋሽ በዚያ ውሸት ምን ጊዜም ያው ውሸት ነው፡፡ ሀሰት መናገር ሰውን ግምት ውስጥ የሚያስገባ፣ በዚያ ሰው ላይ የሚኖረንን ወይም ያለንን አመኔታ የሚሸረሽርና እስከወዲያኛው የሚያቆራርጥ ነው፡፡ ለምሣሌ አቢይ አህመድን መቼም ላምን አልችልም፡፡ እኔና እሱ ባለንበት አንድ ክፍል እኔ ውስጥ ሆኜ እሱ ውጭ ሆኖ “እሳት!እሳት!” ቢል  እነዳታለሁ እንጂ ቃሉን ከቁብ ቆጥሬ ደንግጬ የምወጣ አይመስለኝም፡፡ የውሸታም ሰው መጨረሻ ይህ ነው – እውነት ቢናገር እንኳን የሚያምነው አይኖርም – ልክ እንደዚያ በአንድ የዱሮ አማርኛ መጽሐፍ ውስጥ እንዳለው ውሸታም እረኛ፡፡

ግዛው ያነሳቸው ነጥቦች ብዙ ናቸው፡፡ ግን የጠሚውን ከብርቱካን ሚዴክሳ ጋር የነበረ “ንትርክ” ቁልጭ አድርጎ አስረድቶናልና  ያን ጽሑፍ ማየት ስለሰውዬው የግነት ዘይቤ አጠቃቀምና የውሸት አጣጣል ይበልጥ ይረዳል፡፡ ክርስቶስ “አፌን በምሣሌ እከፍታለሁ” እንዳለ ጠሚውም አፉን የሚያሟሸውና የሰዎችን (ማለትም የጅል ተከታዮቹን) አፍ የሚያስከፍተውም በውሸት ትርክት ነው – ሰው እንዴት በሀሰት ያመልካል ግን? መለከፍ እኮ ነው፡፡ የዚህ ልጅ እውነት በጣም ጥቂት ነው – ሊያውም ሳት እያለው መሆን አለበት እውነትን የሚናገረው፡፡ በተለይ ከሰኔ 16 ቀን 2010 የመስቀል አደባባዩ መጥፎ ክስተት በኋላ ያለውን አብዛኛውን ነገሩን ስንከታተል የሚገርም ቅጥፈትና አዛኝ ቅቤ አንጓችነት በገሃድ የሚስተዋልበት ንግግር ነው የሚያሰማው፡፡ ለነገሩ የጳጳሱን እጅ ሲሳለምና የኢማሙን ሙስባሃና ኪታብ ሲስም እኮ ነው ነገሩ ያለቀው፡፡ አቢይ ብዙ ሰው ነው፡፡ ግን የአቢይ ብዙ ሰዎች ዐይንና ናጫ በመሆናቸው በውስጡ ሲተረማመሱበት ለብስናትና ግሣት ይዳርጉታል፡፡ ብስናትና ግሣቱ ደግሞ ሽታውም፤ መልኩም፣ ወርድና ቁመቱም የተለያዬ እንደመሆኑ ደሴ ላይ የሚያበሰናውና ባሌ ላይ የሚያገሣው ከአንድ ሰው መውጣታቸውን እየዘነጋ ክፉኛ አስጨነቀን፡፡ ዛሬንስ እንዲህ ሆነ፡፡ ነገስ? አንድዬ ይሁነን! ከባድ ችግር ውስጥ ነን፡፡ እንደዱሮው ወዲህ ወዲያ እንሄዳለን፣ እንሸሻለን እንዳንል ዓለም ራሷ እንደኳስ ተወጥራ ሁለ ነገሯ ዞሮባት ኤሎሄ እያለች ነው፡፡ አንድዬ መፍትሔውን በቶሎ ያምጣልን፡፡

ስንቱን አንስተን ስንቱን እንጥላለን እንጂ የዚህ ብላቴና ውሸት እንኳን ለራሱ ለሰውም ይተርፋል፡፡ ሆዳሙ ንጉሡ ጥላሁን የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ተፈትተዋል ብሎ በሚዲያ የተናገረው አቢይ በል ብሎት እንጂ ከራሱ እንደማይሆን ጥርጥር የለውም፡፡ ውሸታም ደግሞ ነገን ፈጽሞ አያስባትም፤ ምናልባት ለነገ እደርሳለሁ ብሎ አያምን ይሆናል – አላውቅም፡፡ ግን የመጣለትን መቀደድና መተርተር ነው እንደጣቃ፡፡ ሲነጋ ደግሞ ለሌላ ዙር ውሸት ይዘጋጃል፡፡ ምን ይሉኝን ቀቅለው በልተዋታልና ሃጃቸው አይደለችም፡፡ “ውሸታም!” ብትላቸው “አይ አንተ ሞኝ! እንዲህ ካልተሆነ ሥልጣን ይጸናል ብለህ ነው?” እያሉ በማሾፍ ይስቁብሃል፡፡ ለዚህ ነው እነአቢይ ውሸት የማያልቅባቸውና መዋሸትም የማይሰለቻቸው፡፡ ጉድ ነው! 

በአመራር ደረጃ እንዲህ ያለ ቅሌት ሲያጋጥም ከባድ ችግር ነው፡፡ “እህል ቢያንቅ በውኃ ይዋጣል፤ ውኃ ቢያንቅ በምን ይዋጣል?” ይባላል፡፡ ሌላም አለ፡፡ “ሰውነት ቢያብጥ በምላጭ ይበጣል፤ ምላጭ ቢያብጥ በምን ይበጣል?” እንላለን፡፡ አቢይ ከዋሸ፣ ንጉሡ (ጥላሁን) ከዋሸ፣ ፓትርያርኩ ከቀጠፈና ከ…፣ ካህኑ ከሞሰነና ከቀጠፈ፣ …. ተራው ዜጋ እንዴትና ለምን እነሱን አይከተል? ማን፣ ምንና ለምንስ ይፈርድበታል? ህግን አስፈጻሚው አካል፣ ሃይማኖትን መሪው አበው ወእመው ራሳቸው ጠፍተው ህግን የሚያስከብርና ሃይማኖትን የሚያስጠብቅ ከየት ይምጣ? ችግር እኮ ነው እናንተዬ፡፡ ተያይዞ ገደል ማለት እንደዚህም አይደለ ታዲያ? መዳረሻችን ወዴት ይሆን? አለቃው ሲቀደድ የሚያይ ምንዝር ምን ሊማር ነው ከርሱ? አባትና እናት ተያይዘው ከጠፉ ልችጆስ ለምን እሱን ተከትለው በጥፋት መንገድ አይነጉዱ? ከየት ያዩትን ደግነትና ቅንነት ይተገብራሉ? በተመሳሳይ ሁኔታ በዋልጌዎችና በሀሰተኞች የሚመራው መንግሥት ተብዬውስ ህግን ለማውጣት፣ ለመተርጎምና ለማስፈጸም የሞራል ብቃቱን ከየት ያገኘዋልኝ? ይህ ጊዜ ሲያልፍ የሚወራው መብዛቱ! – ለደረሰበት፡፡ 

 አንድ ሰው ትንቃለህ፤ ሁለት ሰው ትንቃለህ፤ አሥር ሰዎችን አልተማሩም ወይም ሞኞች ናቸው ብለህ ችላ ልትል ወይ ልትንቅ ትችላለህ፡፡ 115 ሚሊዮን ሕዝብ ለመናቅ ግን ሞራሉ ከየት ይመጣል? እጅግ እጅግ የሚገርመኝ ነገር ይህ ነው፡፡ በበኩሌ አንድ መቶ ብር የገዛሁትን ሳልቫጅ ሸሚዝ እቤቴ ስገባ 150 ገዛሁት ብዬ ከዋሸሁ (ለቀልድም ቢሆን) ሲኮሰኩሰኝ ነው የሚያድር፡፡ ስለዚህም መዋሸቴን ዘንግቼው እውነቱን ከማፍረጤና ትዝብት ውስጥ ከመውደቄ በፊት ወዲያውኑ “ውሸቴን ነው!” ብዬ አስተባብላለሁ፡፡ ወ/ሮ ብርቱካን “ምርጫው ካልተዛወረ ኃላፊነቴን እለቃለሁ ብለው ስልኩን ጆሮየ ላይ ጠረቀሙብኝ!” የሚል ቃና ያዘለ ቱሪናፋ “ፓርላማ” ላይ መናገር ግን እንኳን እኛን የፓርላማ አባላት ተብዬዎቹን ራሳቸውንም የሚያሳምን አይደለም፡፡ ልቀጥልልህ – “አሜሪካና ካናዳ ኮሮና የያዘው ሰው ስልክ ሲደውል ‹እስኪያቅትህ ድረስ እቤትህ ራስህን አስታም› ይሉታል፡፡ እኛ ግን” አለ ቅቤ አንጓቹ ጠ/ሚ “እኛ ግን ወዲያው ነው አምቡላንስ ልከን ወደ ሀኪም ቤት የምንወስደው፡፡ ይህም ለዜጎች አሳቢነታችንን ያሳያል፡፡”  እንደአካሄድ ግሩም ነው – ግን በጨው ደንደስ በርበሬ መወደስ የለበትምና እሱን ለማግዘፍ የነሱን ለ“ዜጎቻቸው አለማሰብ” በገሃድ ማጋለጥ ነውር ነው፡፡ ስለራስ ብቻ መናገር፡፡

ለማንኛውም ነገሩ ግን ወዲህ ነው፡፡ አለቃ ገ/ሃና “ያቺ ሌላ ይቺ ሌላ” ያሏትን እዚህ ላይ ማስታወሱም ተገቢ እንደሆነ ግንዛቤ ይወሰድልኝ በኢሕአዲግኛ ቋንቋ፡፡ ‹ግልጸኝነት› ጥሩ ነው፡፡

ይህ ራስን ካለማወቅ ወይም ለራስ ከፍተኛና ያልተገባ ግምት ከመስጠት የሚመነጭ ብዥታ ነው፡፡ አሜሪካንና ኢትዮጵያን ማወዳደር ከመነሻው መቀናጣት ነው፡፡ የአንድን ዜጋ ሬሣ ከጠላት ወረዳ ለማስለቀቅ ብቻ በሺዎች የሚቆጠሩ እስረኞችን እየፈቱ ሬሣውን በሀገሩ በክብር የሚቀብሩ ሀገራትና (በሕወት ያለውን ትተን ማለት ነው) ሽዎች ምሥኪን የቤት ሠራተኞች የሀገሬ ኤምባሲ ነው ብለው “ኤምባሲያቸው” በር ላይ ከሞት አስጥሉኝ ሲሉ ሰሚ የሚያጡ፣ አምባሳደሩን ጨምሮም በሙያ ብቃት ሳይሆን በዘርና በጎሣ የተመደቡ፣ በሥራ ሰዓትም ንግድና ተዝናኖትን በአሥረሽ ምቺው የሚያጧጥፉ ጉደኛ ዲፕሎማቶች ያላት ሀገር በዜጎች አያያዝ ለውድድር ማቅረብ ከእውነት ጋር መላተም ነው፡፡ በዚያም ላይ ሥራ የሌለው ሰው፣ ሰው በመሆኑና ዜጋ በመሆኑ ብቻ ደሞዝ የሚከፈለው ዜጋ ያለውን ሀገርና ሥራ ያለው ሰው ራሱ በሚከፈለው እዚህ ግባ የማይባል መናኛ ደሞዝ መኖር የማይችልባትን መናጢ ድሃ አገር ማወዳደር ከሥር መሠረቱ ድንቁርና ካነሰው ዕብደትን መደረብ አግባብ ነው፡፡ ሲቀጥል በሦስት ወራት ውስጥ ብቻ 113 ሽህ ሟችና ከሁለት ሚሊዮን ሃያ ሰባት ሽህ በላይ በቫይረስ ተጠቂ ያለባትን ሀገር በዚሁ ጊዜ ውስጥ ዛሬን ጨምሮ 32 ሟችና ሁለት ሽህ ሦስት መቶ ገደማ ተጠቂ ይዞ ለውድድር መንጠራራት ቆዳን ለማዋደድ ሲባል ሰማይን እንደመቧጠጥ የሚቆጠር የጅል ሥራ ነው፡፡ እግዜር አይበለውና በወር መቶና ሁለት መቶ ሽህ ተጠቂና በቀን ሁለትና ሦስት ሽህ ሟች ቢገጥመን ራሱ እነአቢይ በሄሊኮፕተር ተሳፍረው እግር አውጪኛቸውን በአንዱ አቅጣጫ እንደሚጠፉ መገመት አይከብድም፡፡ ወንድሞቼና እህቶቼ ጉራ ለማንም አልበጀም፤ አይበጅምም፡፡ እርግጥ ነው “ለአፍ አቀበት የለውም”፡፡ እንዴት ነው የሚቀልድብን ይህ ልጅ ግን? ኧረ ግዴላችሁም የምትቀርቡት ሰዎች ምከሩት! እንዴ? የሚናገረውን ይወቅ እንጂ፡፡

አላስችልህ ስላለኝ እንጂ በአርምሞ እንደመቀመጥ ያለ ጠቃሚ ነገር የለም በተለይ አሁን፡፡ ግን ተከትቦ መቀመጡም መልካም ነው፡፡ ma74085@gmail.com

Filed in: Amharic