>

የሮበርት ኢ.ሊ  ሐውልት ሲፈርስ:-  ኢትዮጵያ ውስጥ ቤት መፍረስ ካለበት ከአንድ ሚሊዮን በላይ ..... (አቻምየለህ ታምሩ)

የሮበርት ኢ.ሊ  ሐውልት ሲፈርስ:-

 ኢትዮጵያ ውስጥ ቤት መፍረስ ካለበት ከአንድ ሚሊዮን በላይ ባሮች የተፈነገሉበት የአባ ጅፋር ቤተ መንግሥት ነው! 

አቻምየለህ ታምሩ

እ.ኤ.አ. በ1861 ዓ.ም. በአሜሪካን አገር የተቀሰቀሰው የርስ በርስ ጦርነት መንስዔ የባርነት ሥርዓትን ለመልቀቅና የባሪያን  ነጻነት ለመስጠት ባለመፈለግ  በየአቅጣጫው ተቃውሞ መነሳቱ ነው። ጦርነቱ በዋናነት የተካሄደው በሰሜን የአሜሪካ የአንድነት ኃይልና በደቡብ የአሜሪካ ተገንጣይ የኮንፈደራል ኃይል መካከል  ሲሆን የርስ በርስ ጦርነቱ ባርነት እንዲወገድ በሚፈልጉ ሰሜንና ባርነት ሥርዓታዊ እንዲሆን በሚሹ ደቡብ አሜሪካኖች መካከል የተካሄደ ነበር። የባርያ ነጻነትን የማይፈቅዱት የደቡብ የአሜሪካ ክፍል ባሪያ አሳዳሪዎች የባርያ ሥርዓትን የሚቃወመው  አብርሐም ሊንከን ፕሬዝደንት ሆኖ ሲመረጥ በአላባማ ግዛት ሞንገመሪ ከተማ ላይ ታላቅ ስብሰባ አድርገው ጀፈረሰን ዴቪስ የሚባለውን ባርያ አሳዳሪ ፕሬዝደንት አድርገው በመምረጥ የባርያ ሥርዓታቸውን  ተገንጥለው ለማስቀጠል “ኮንፌደረት እስቴት ኦፍ አሜሪካ” ብለው የራሳቸውን አገር በመሰየም መደቡ ቀይ የሆነ ባንዲራ አዘጋጅተው ራሳቸውን ማስተዳደር ጀመሩ። የአብርሐም ሊንከንን ውሳኔም በመቃወም እ.ኤ.አ. በሚያዚያ 12 ቀን 1861 ዓ.ም. የርስ በርስ ጦርነቱን ጀመሩ።
የተገንጣዩ የደቡብ “ኮንፌደረት እስቴት ኦፍ አሜሪካ” ፕረዝደንት ሆኖ የተመረጠው የጀፈርሰን ደቪስ  አዝማች ጀኔራል ሮበርት ኢ.ሊ. ነበር። በጣም ታዋቂ የሆኑት  ሁለቱ የሰሜኑ ክፍል አዝማቾች ደግሞ ጀኔራል  ዩልየስ ግራንት እና ጀኔራል ሸርማን ነበሩ። ለሁለት ዓመታት የተካሄደው የርስ በርስ ጦርነት የተጠናቀቀው በፔንሲልቫኒያ ጌትስበርግ እ.ኤ.አ. ሐምሌ 3 ቀን 1863 ዓ.ም. በተደረገው ጦርነት የደቡቡ ኮንፈደሬት ጦር ሠራዊት አዛዥ ሮበርት ኢ.ሊ. የሚመረው ጦር በድል ከተመታና ወደ ትውልድ ቦታው የኮንፌደሬት ዋና ከተማ  ወደነበረችው ወደ ቨርጂኒያ ሪችመንድ ከሸሸ በኋላ በጦርነቱ መቀጠሉ ጥቅም የሌለው መሆኑን ተገንዝቦ  ለባሮች ነጻነትና እኩልነት ይታገል ለነበረው ለአሸናፊው የሰሜን  የአንድነት ኃይል እጁን ሲሰጥ ነው።
የቨርጂኒያ ክፍለ ሀገር አስተዳዳሪው ዲሞክራቱ  ራልፍ ኖርትሃም  ከሰሞኑ በአሜሪካ ግዛቶች የተቀሰቀሰውን ሕዝባዊ ተቃውሞ ምክንያት በማድረግ የባሮችን እኩልነት ባለመቀበል  አሳፋሪውን የባርነት ሥርዓት ለማስቀጠም  የኮንፈደሬት ጦር ሠራዊትን እየመራ ለሁለት ዓመታት  ለባሮች ነጻነትና አኩልነት ይታገሉ የነበሩ የሰሜን  አሜሪካ የአንድነት ኃይሎችን የወጋውን የባሪያ አሳዳሪውን የጀኔራል ሮበርት ኢ.ሊ.ን ሐውልት እንዲወገድ መወሰኑን ተከትሎ  ገዳ የሚባለው የባሪያ አሳዳሪዎች ሥርዓት አቀንቃኞቹ ኦነጋውያን  “የጀኔራል ሮበርት ኢ.ሊ.ን ሐውልት ከተነሳ የምኒልክ ሐውልትም መነሳት አለበት” የሚል አዲስ ዘመቻ ጀምረዋል።
ኦነጋውያን በዳግማዊ ምኒልክ ጥላቻ ጥንቢራቸው የዞረና  የማይድን የዝቅተኛነት በሽታ ተጠቂ የሆኑ ግብዞች ስለሆኑ ባሪያ አሳዳሪው ጀኔራል ሮበርት ኢ.ሊ. እና በዋናነት በኦሮሞ የአካባቢ ገዢዎች ይካሄድ የነበረው የባሪያ ንግድ እንዲጠፋ አዋጅ የደነገጉት  ባሪያ ነጻ አውጭው ዳግማዊ ምኒልክ ተቃራኒ ሰዎች እንደሆኑ እንኳ የማያውቁ የማንነት ቀውስ ያደደባቸው የእውቀት ጾመኞች ናቸው።
ባሪያ አሳዳሪውና የባሪያን እኩልነት የማይቀበለው አሜሪካዊው ጀኔራል ሮበርት ኢ.ሊ. ኢትዮጵያ ውስጥ ወደረኛ ይፈለግለት ከተባለው የሚቀርበው በምስራቅ አፍሪካ ወደር የማይገኝላቸው ባሪያ ነጋዴ ለነበሩት ለጅማው ንጉሥ ለአባ ጅፋር እንጂ  “ይድረስ ካባ ጅፋር ከጃንጃሮ ወዳንተ አገር የመጣውን ጋላ እንግዲህ ከእጄ ከገባልኝ ብለህ ጭቡ አድርገህ ባርያዬ ነህና አንተንም ልበድልህ፣ ልጅህንም አምጣና እንደከብት ልሽጠው ፣ ልለውጠው አትበል። ይህን ያህል ዘመን አባቶቻቸው ከአባቶችህ፣ ልጆቹ ካንተ ጋር አብረው ኑረው ባሪያ ሊባሉ አይገባም። ባደባባይም ባርያዬ ነው እያልክ አትሟገት። የሰው ባርያ የለውም። ሁላችንም የእግዚአብሔር ባርያዎች ነን።” የሚል የእኩልነት አዋጅ ከአዲስ አበባ  በባሪያ ንግድ ክብረ ወሰን ወደተቀዳጁት  ወደ አባ ጅፋር የላኩት አጼ ምኒልክ አይደሉም።
ስለዚህ የባሪያ አሳዳሪው ጀኔራል ሮበርት ኢ.ሊ. ሐውልት ስለፈረሰ ኢትዮጵያ ውስጥም  ሐውልት ይፍረስ ከተባለ መፍረስ ያለበት እንደ አብርሐም ሊንከን ባሪያን በአዋጅ ነጻ ያወጡት የዳግማዊ አጸ ምኒልክ ሐውልት ሳይሆን ከአንደ ሚሊዮን በላይ ባሮች የተፈነገሉበትና  በምስራቅ አፍሪካ ወደር የማይገኝለቱ የባሪያ ነጋዴ የሆነው የአባ ጅፋር ቤተ መንግሥት ነው።
አባ ጅፋርን በ1904 ዓ.ም. በሚኖርበት ጅማ ሄዶ የጎበኘው ፊታውራሪ ተክለ ሐዋርያት ተክለ ማርያም አባ ጅፋር «ከአንድ ሚሊዮን በላይ የአካባቢውን ሕዝብ በባርነት ሽጦ እንደጨረሰ» ኦቶባዮግራፊ [የሕይወቴ ታሪክ] በሚል ባዘጋጀው የታሪክ መጽሐፍ ውስጥ አስፍሯል።
ሌላም ማስራጃ አለን። በ1916 ዓ.ም. ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት [League of Nations] አባል ለመሆን ባመለከተችበት ወቅት በእንግሊዝ መንግሥት ከፍተኛ ተቃውሞ ቀርቦባት ነበር። የኢትዮጵያን መንግሥት የአባልነት ማመልከቻ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት [League of Nations] ለማስገባት ወደ ጀኔቫ የተላከው ቡድን መሪ የነበሩት ራስ ናደው አባ ወሎ በፈረስ ስማቸው «አባ መብረቅ» እንግሊዝ ኢትዮጵያ የመንግሥታቱ ማኅበር አባል እንዳትሆን የተቃወመችበትን ምክንያት ለንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ በላኩት የቴሌግራም መልዕክት፤
«እንግሊዝ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሐን የዘገቡትንና በሱዳን፣ በኬንያ፣ በኤደንና በግብጽ ባሉት የቅኝ ግዛት መንግሥቱ በኩል የሰበሰበውን ማስረጃ በማያያዝ በደቡብ ኢትዮጵያ እየተካሄደ ስለነበረው የባርያ ንግድ ሁኔታ፤ በተለይም የጂማው አባጅፋር በከፋ፣ በማጂ፣ በጊሚራና በጉራፈርዳ ሕዝብ ላይ እየካሄዱት ያለው መጠነ ሰፊ የባሪያ ንግድ ለማኅበሩ የፖለቲካ ኮሚሲዮንና ለጠቅላላ ጉባኤ በማቅረብ አባል እንዳንሆን ከፍተኛ ተቃውሞ አቅርቦብናል» ሲሉ አስረድተዋል።
ለዚህ የራስ ናደው አባ ወሎ ቴሌግራም የአልጋ ወራሽ ተፈሪ መኮንን መንግሥት አፋጣኝ ምላሽ ሰጠ። ኢትዮጵያ ውስጥ በአባ ጅፋር አማካኝነት የሚካሄደው የባርያ ንግድ ባጭር ጊዜ ውስጥ ጨርሶ እንዲታገድና የሰው ልጅ መብት በመላው የአገሪቱ ግዛት እንዲከበር የአልጋወራሽ ተፈሪ መንግሥት ለመንግሥታቱ ማኅበር ቃል በመግባት ኢትዮጵያ ያቀረበችው የአባልነት ጥያቄ ተቀባይነት አግኝቶ ከመስከረም 17 ቀን 1916 ዓ.ም. ጀምሮ ኢትዮጵያ የመንግሥታቱ ማኅበር 57ኛ አባል ሆና መመዝገቧ በይፋ ታወጀላት።
አባ ጅፋር ጅማን ያስፋፉው  በአካባቢው የነበሩ እንደ የምና ጌራ አይነት ነገዶችን በመውረርና በማጥፋት የተረፈውን ሕዝብ ደግሞ ባሪያ አድርጎ  በመሸጥ ነበር። አባ ጅፋር ባሪያ አድርጎ የሸጠው ኦሮሞን ጭምር ነበር። ለዚህ ማስረጃ ይሆን ዘንድ ከታች የታተመውን የዳግማዊ ምኒልክ ደብዳቤ መመልከት ይቻላል። ዳግማዊ ዐጤ ምኒልክ አባ ጅፋር ሰውን ባሪያ እያሉ እንዳይሸቱ በተደጋጋሚ ትዕዛዝና ማስጠንቀቂያ ከዚያም እስከካሰር ድረስ ደርሰው ነበር። ከዚህ በተጨማሪም ዳግማዊ አባ ጅፋር ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ በ1881 ዓ.ም. ኩሎና ኮንታን፤ በ1886 ዓ.ም. ወላይታንና በ1889 ዓ.ም. ካፋን ወደ ማዕከላዊ መንግሥት አስተዳደር መልሰው ባስገቡ ጊዜ አባ ጅፋር የዘመቻው ቀዳሚ ተካፋይ ነበሩ።
ከአንድ ሚሊዮን በላይ የጅማን አካባቢ ሕዝብ ባሪያ አድርገው የሸጡትና የምስራቅ አፍሪካው ታላቁ የባሪያ ነጋዴ አባ ጅፋር ልጆች ነን የሚሉን ኦነጋውያን ናቸው እንግዲህ  የባርያ ሥርዓትን ለመልቀቅና የባሪያን  ነጻነት ለመስጠት ባለመፈለግ  ጦርነት የከፈተው የጀኔራል ሮበርት ኢ.ሊ ሐውልት ሲፈርስ ስላዩ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያዊ በባርነት የሸጠው የአባ ጅፋር ቤተ መንግሥት ተቀምጦ አባ ጅፋር የባሪያ ንግዱን እንዲያቆም፤ ፈንግሎ  በባርነት ሰንሰለት ያሰራቸውን የልዩ ልዩ  ነገዶች ባሮች እንዲለቅና ባሮች ነጻ እንዲወጡ አዋጅ ያወጡት የዳግማዊ አጼ ምኒልክ ሐውልት ይፍረስ የሚሉን!
ባጭሩ  የባርነት ሥርዓትን ለመልቀቅና የባሪያን ነጻነት ለመስጠት ባለመፈለግ  ሁለት ዓመታት ተዋግቶ  በስተመጨረሻ ላይ የተማረከው ጀኔራል ሮበርት ኢ.ሊ. ኢትዮጵያ ውስጥ የሚመሳሰለው የባርያ ንግድ አላቆምም በማለቱ እስከመታሰር  የደረሰውና ከአንድ ሚሊዮን በላይ ባሮችን የሸጠው የምስራቅ አፍሪካው ታላቅ የባሪያ ነጋዴ አባ ጅፋር እንጂ   ባሪያ ነጻ አውጭውና “ደሀው እወደደው እተመቸው ቦታ ይደር” ያሉት ዳግማዊ ምኒልክማ የሚመሳሰሉት የባሪያ ነጻነትን ለማወጅ  ከጀኔራል ሮበርት ኢ.ሊ.  ጋር የተዋጋው አብርሐም ሊንከን ነው።
Filed in: Amharic