>

እንደምነው ዛፉ ...!!! (በእውቀቱ ስዩም)

እንደምነው ዛፉ …!!!

በእውቀቱ ስዩም

ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ አገሪቱን በልምላሜ ለማላበስ የሚያደርገው ጥረት እሚደነቅ ነው፤ ይህንን አረንጉዋዴ ዘመቻ ደግፌ  መዳፌ ወንፊት እስኪሆን  ሳጨበጭብ ቆይቻለሁ!!
የሰሞኑ  አልገባኝም!  ህልውናችን  ክንብል ድፍት ሊል ጫፍ ላይ  በሆነበት ጊዜ ላይ  ለችግኝ ተከላ ዘመቻ ህዝብን መጥራት አስፈላጊ  ነው?
አገራችን ማንም ያላገኘውን እድል አግኝታ በማባከን የሚደርስባት የለም !  ታሪኳ እንደዚያ ነው!  ለኮሮና  ያሳየነው ንቀት አንዱ ማሳያ ይመስለኛል፤  ባለፈ ነገር ላይ መወቃቀስ ስለማይጠቅም ነው እንጂ ብዙ እምለው ነበረኝ!
ለማንኛውም አሁን መንግስት፤
1)ለህክምና  አርበኞች የሚያስፈልጋቸውን ስንቅ እና ትጥቅ እያቀረበ   ነው?
 2)  የምግብ እጥረት በሚከሰትበት ጊዜ   ለህዝቡ የሚነዛው ምግብ  በጎተራው እያጠራቀመ ነው ?
3. ለኮሮና ቫይረስ መዳኒት ወይም ክትባት ቢገኝ ኢትዮጵያ የምታገኝበት መንገድ አስቦበታል? ‘፤  በቸርነቱ የሚደርስልን የአለም የጤና ድርጅት በትራምፕ ንፍገት ምክንያት ቺስታ ሆኗል!  መንግስት ይሄንን ጉድለት የሚሞላበት ነገር አዘጋጅቷል?
መልሱ አዎ ከሆነ ይመቸው! ካልሆነ  ግን  ለዚህ ጣጣ መፍትሄ ሳያገኙ  የችግኝ ዘመቻ ላይ ጉልበት መጨረስ አያዋጣም እላለሁ:: ወይራ ተከላው ከስምንት ወር በሁዋላ  ይደረስበታል  ! እስከዚያ  ግን በህይወት መቆየት አለብን ‘  እህል የሚደርስ የፍልሰታ እኔ እምሞት  ዛሬ ማታ “ ይላሉ ባልቴቶች ሲተርቱ!
በመጨረሻም፤  ድሮ በዘመነ ወረሼህ የነበረች አንዲት አሚና ከዙረት ወደ አገሯ ስትመለስ  ያንጎራጎረችው እንዳይደርስብን እመኛለሁ!
“አስቲ ወደ አገሬ ልዝለቅ ወደ አፋፉ
ሰውስ አልቋልና እንደምነው ዛፉ “
Filed in: Amharic