>

ጃዋር የአብይን ምዝበራ አጋለጠ! (አሰፋ ሃይሉ)

ጃዋር የአብይን ምዝበራ አጋለጠ!

አሰፋ ሃይሉ

የጃዋር ሲራጅ መሀመድ የማለዳ የትዊተር መልዕክት እንዲህ ይነበባል፡-
‹‹ ባለፈው ሣምንት የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተጻፈውን `መደመር` የተባለ መጽሐፍ ለመግዛት በህገወጥ መንገድ 3.4 ሚሊየን ብር ወጪ ስለማድረጉ ማስረጃውን አውጥተናል፡፡ አሁን ደሞ መጽሐፉን በተለያዩ እርከኖች ለማስተማር 5.6 ሚሊየን ብር ወጪ ስለመደረጉ ማስረጃ ተልኮልናል (ይኸው ተመልከቱት)›› 
ሲጀመር ጀምሮ – ደሃ – በቀን 20ና 30 ብር አጥቶ – በልቶ ጠግቦ በማያድርባት ሀገር – በመጀመሪያ ደረጃ ይሄን ‹‹መደመር›› የተሰኘ አርቲ ቡርቲ የፕሮፓጋንዳ መጽሐፍ በሚሊዮኖች ኮፒ ለማሳተም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከቻይና መንግሥት የገንዘብ እርዳታ ተደረገለት ተባለ፡፡ እንዴ? ይሄ ነገር ሙስና አይሆንም ወይ? ቢያንስ ለሙስና በር አይከፍትም ወይ?
በወያኔ ዘመን የመከላከያ ሚኒስትር የነበረው ስዬ አብርሃ በሙስና የተከሰሰው በምን ሰበብ ነበር? በመንግሥት ሥልጣን ያገኘኸውን ተሰሚነትህን ተጠቅመህ ለወንድምህ ከውጭ ዕቃ እንዲያስመጣ ድርጅቱን አግባብተሃል (ስለ ወንድምህ መልካም አስተያየት ሰጥሃል) በሚል ነበር፡፡ የቻይና መንግሥትስ የአብይ አህመድን መጽሐፍ ያሳተመለት በምን የግል ትውውቅ ነው? ጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ለግሉ መጠቀሚያ በማድረግ አይደለም ወይ?
“አይ.. በግሌ ከዢን ፒንግ ጋር ባለኝ ትውውቅ ነው ቻይና ሚሊዮኖች ብሮችን ለመጽሐፌ ህትመትና ሽያጭ የዘረገፈችልኝ” ቢል እንኳ ቅቤው – እንዴ! ይሄን ያህል ከፍ ያለ ሥጦታስ የተቀበለ መሪ – ውሎ አድሮ ቻይናን በተመለከተ ሀገሪቱ በምትከተለው ፖሊሲና ውሳኔ ላይ ያ የበላበት እጁ ተጽዕኖ አያስከትልበትም ወይ? የአንድ ሀገር መሪስ – ሀገሩን፣ ፓርቲውን፣ ወዘተ ሳያስፈቅድ – ከሌላ ሀገር ስጦታና እርዳታ በግሉ ይቀበላል ወይ? ይሄ ነገር ለሀገር ክብረ-ነክ፣ ለአሠራርስ ብልሹ አሠራር አይደለም ወይ? በየትኛውስ ሰዓትና አጋጣሚ ነው – አንድ ጠቅላይ ሚኒስትር በግሉ ስለሚያሳትመው መጽሐፍ – አንድን የውጭ መንግሥት ወይም የውጭ መንግሥት መሪ – እንደ አጀንዳ አንስቶ ሊጠይቅ፣ ሊለምን፣ ሊያግባባ አሊያም ሊቀበልና ሊደራደር የሚችለው? ከዚህ በላይ የመንግሥትን ሥልጣን ለግል ማዋል ማለትስ ሌላ ምን የተለየ ትርጉም አለው?
ሲቀጥል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጻፈውን መጽሐፍ እንደ ስብከተ ወንጌል በየሃገሩ፣ በየደብሩ ለመስበክና ለማስተማር – የመንግሥት አካላትና ባለሥልጣናት ኃላፊነት ተቀብለው በመላ ሀገሪቱ ተፍ ተፍ ሲሉ ማየት አያስቅም ወይ? መደመር የተባለውን መጽሐፍ ለኢትዮጵያ ሕዝብ እናሠለጥናለን ተብሎ በየክልሉ ከፍተኛ በጀት እየተመደበ ካድሬዎችንና የመንግሥት ሠራተኞችንና የሥራ ኃላፊዎችን እየሰበሰቡ ለቀናት የአንድ የኢህአዴግ ባለሥልጣን መጽሐፍ ለማስተዋወቅ ‹‹ሀገራዊ ሥልጠና›› ብሎ መስበክ – በዘመናዊት ኢትዮጵያ – አያሳፍርም ወይ? አያሳዝንም ወይ?
የሰውየው መጽሐፍስ ለመሆኑ በመንግሥት የፀደቀ የመንግሥት ፖሊሲ ዶኪመንት ነው? ወይስ የአንድ ግለሰብ ከውልደቱና ከልጅነት ሰፈሩ እስከ መንበረ ቡራኬው ሄድኩበት ያለውን የተረከበት፣ ተረድቼዋለሁ ያለውን የለፈፈበት፣ ባጠቃላይ የግለሰብ ሀሳብ የተንጸባረቀበት መጽሀፍ? ምንድነው መጽሐፉ ይሄን ያህል በሀገርና በህዝብ ገንዘብ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ፈስሶ የእነ ሌንጮ ባቲ ልዑካን ቡድን አሜሪካ ሀገር ድረስ ሄዶ ከስቴት ስቴት እየዞረ ስለ ‹መደመር› መጽሐፍ እንደ ክርስቶስ ወንጌል የሚሰብከው? እንዴት ህግ አለ በሚባልበት ሀገር እና ጤነኛ የመንግሥት ባለሥልጣኖች ባሉበት ሀገር እንዲህ ይደረጋል?
እና ይሄ ጃዋር ያወጣው መረጃ – ሁላችንም በቀላሉ አስበን በግልጽ ማወቅ የምንችለውን ነገር – በተጨበጠ ማስረጃ አስደግፎ እውነትነቱን ከማረጋገጡ በስተቀር – ይፋ ያደረገው ይዘት ምንም አልገረመኝም፡፡ በጣት የሚቆጠሩ ሚሊዮኖች ብሮች ብቻም አይደለም፣ አይሆንምም የአብይን ‹‹መደመር›› በሀገር ደረጃ ለመስበክ የወጣው፡፡ ይሄ ጃዋር በማስረጃ አስደግፎ ያጋለጠው 3.4 ሚሊየን እና 5.6 ሚሊየን – በድምሩ የ9 ሚሊየን ብር ወጪ እኮ – የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ ብቻ ያወጣው ወጪ ነው፡፡ በየሌሎቹስ ክልሎች? የፌዴራል መንግሥቱስ? በየሀገሩ የሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎችና ቆንሲላ ጽ/ቤቶችስ? ከዚህ በላይ የመንግሥትን ሥልጣን ለግል መጠቀሚያ ማድረግ ከወደየት ይገኛል???
ከአብይ አህመድ አሊ የማደንቅለት ትልቁ ነገሩ – የመንግሥት ሥልጣን የቱን ያህል የግል ዝናንና ክብርን መነገጃነት መዋል እንደሚችል – ታላቁን የሥልጣን ፖቴንሻል ጠንቅቆ የተረዳ እና ያንንም የሥልጣን ጥቅም ለግሉ ለማዋል ያለማወላዳት ሌት ተቀን ታትሮ የሚተጋ የመሆኑ ነገር እጅግ እየገረመኝ ሁሉ ነው የሚደንቀኝ! ምናልባት ሀገሪቱን በሙሉ እንደ ግል ንብረታቸው ከሚቆጥሩት ከንጉሡ ዘመን በኋላ እንደዚህ እንደ አብይ አህመድ የመንግሥትን ሥልጣን እንዳሻው ለግሉ መጠቀሚያ ያደረገና ለማድረግ ሌት ተቀን የሚሠራ መሪ በኢትዮጵያ ታሪክ አጋጥሞ የሚያውቅ አይመስለኝም!
በነገራችን ላይ ጃዋር ሲራጅ መሀመድ የቱንም ያህል ደም-የጠማው አክራሪ ፋሺስት መስሎ ቢታየን – እውነቱን እንዲህ በአደባባይ ሲያጋልጥ ግን – ለዚሁ ተግባሩ አለማመስገንና አለማድነቅ ይከብዳል! ቢያንስ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሀብት እንዴት ባለ መልኩ ለግል ዝናና ክብር በቋመጡ በወቅቱ የኢትዮጵያ ‹‹ቡችላ አምባገነኖች›› እጅ ገብቶ መጫወቻ እና መዘባበቻ እንደሆነ የሚያሳየን እቅጭ ስዕል አለ፡፡ (የወያኔዎቹን ‹‹ቡችላ አምባገነኖች›› አጠራር ወድጄዋለሁ!)፡፡ እቅጩን ማስረጃ ነው ያቀረበው ጃዋር፡፡
እና ጃዋርን የቱንም ያህል በሌሎች ነገሮቹ ቢኮነን ስለዚህ የሀገርና የወገን ሀብት ለግለሰቦች ጥቅም ሲባክን ያሳየው መቆርቆርና ይሄንኑም በማስረጃ የማጋለጥ ተግባሩ ግን አለማመስገን ንፉግነት ይመስለኛል! ግን ቀጣዩ ጥያቄ – የወያኔ ሥልጣን ወራሽ – እና የኢህአዴግ የመጨረሻው ባለአደራ – ዶክቶር አብዪ አህመዶ – ጃዋር መሀመዶን – በዚህ አኳኋኑ – ይለቀዋል ወይ? የሚለው ይመስለኛል! ከኛ የሚጠበቀው ማየት ብቻ ይመስለኛል!
አይ መደመር…!  ይሄ የመደመር ነገር… ገና ብዙ ጉድ ሳያሳየን ይቀራል? ጊዜ መስተዋት ነው! ቀጣዩ የትዕይንቱ ክፍልም አጓጊ ነው! “ጊዜ ሰጥቶን ሁሉን ለማየት ያብቃን” – የስንብት ቃሌ ነው!
እኩል ይሆናል 
 
“አስከበረን ስንል ሀገሬ ተዋርዶ፣
በየቀኑ ሀዘን እለት እለት መርዶ፡፡
በሜንጫና ጥይት ሰርክ እየቀነሰው፣
ስንት ቀርቶ ይሆን ከተደመረው ሰው፡፡”
           – ገጣሚ ሙሉቀን ሰ.
ቸር ዋሉ አቦ! መልካም ጊዜ! 🥀
Filed in: Amharic