>
5:13 pm - Saturday April 19, 1473

ጣና በእነማን ? እንደምን ተገደለ? (ዴቭ ዳዊት)

ጣና በእነማን ? እንደምን ተገደለ?

ዴቭ ዳዊት
ጣና ማነው….? ችግሩስ ምንድነው? መፍትሔውስ….?
▪️የጣና ሐይቅ መነሻው አባይ ወንዝ ነው፣ መድረሻ ደግሞ ቪክቶሪያ ሐይቅ ነው፣
▪️ጣና ሐይቅ ከኢትዮጵያ አንደኛ ትልቁ ሐይቅ ነው፣ 84 ከ.ሜ. ርዝመት እና 66 ስፋት አለው። ባጠቃላይ 3,500 ካሬ ኪ.ሜ. (Square kilometers) ይሸፍናል። በዚህ ግዝፈቱ “የአፍሪካ ውኃ ታንከር” የሚል ስያሜ አግኝቷል።
▪️እዚህ ሐይቅ ላይ የሚገኘው “ደጋ ደሴት” ላይ የድሮ የኢትዮጵያ መሪዎች መቃብሮች ሲገኙ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ክርስትናን ለመጀመሪያ ያስተዋወቀው አቡነ ሰላማ መቃብርም በዚሁ ሃይቅ ይገኛሉ።
▪️የጣና ሐይቅን የሚመግቡ 3ቱ ዋና ዋና ወንዞች:-
ርብ ወንዝ፣ ጉማሬ እና መገጭ ወንዝ  በመባል ይታወቃሉ።
▪️የጣና ሃይቅ 1,454 ቶን አሳ በአመት ይመረታል።
▪️ጣና ሐይቅ ላይ ካሉት መርከቦች ትልቋ መርከብ “ጣናነሺ” ትባላለች።
▪️ጣና ሐይቅ ላይ በሃይለስላሴ ዘመን የተሰራው ግድብ “ጨረጨራ” ይባላል።
▪️ የሙሴ ጽላት ይገኝበታል የሚባለው ደጋ ስጢፋኖስ ደሴት አለ።
▪️ጣና ላይ ካሉት በርካታ ደሴቶች ትልቁ ደሴት “ደቅ” ይባላል።
▪️ጣና ሐይቅ ላይ ከ37 ደሴቶች ሲገኙ፣ 4 የትራንስፖርት ተርሚናሎች አሉ።
በነኝህ ደስቶች ከ15 ሺህ ሰዎች በላይ ይኖራሉ፣
ባጠቃላይ ከ2.5 ሚሊዮን  ሰዎች በላይ ኢትዮጵያውያን በሐይቁ ዙሪያ ኑሯቸውን መስርተዋል።
▪️ 21 የአሳ ዝርያ በውስጡ ይዟል።
▪️ የአባይና የጣና ውሃ ተለያይተው ወይም መስመር ሰርተው የሚታዩበት ቦታ “ደብረ ማሪያም ደሴት” ይባላል።
– ጣና መደፍረስ የሚጀምረው በወረሃ ሃምሌ አጋማሺ ጀምሮ ነው።
▪️ጣና በለስ 400 MW የሚያመነጭ የሀይል ማመንጫ አለ….!!
ይህን ሁሉ ታሪክና ሀብት የያዘ ብርቅዬ ሐይቅ ላይ ዛሬ ትልቅ አደጋ አንዣቧል። አደጋው መንፈሳዊም መንግታዊም አይደለም፣ ነገር ግን መንግስት እና ህዝብ ተባብሮ ካልዘመተበት ለአደጋው መስፋፋት አጋዥ ነን።
በሐይቁ ዙሪያ ያሉት ሀገር ወደድ ወጣቶች ቢጀምሩት ሁሉም እንደሚረባረብ ጥርጥር ባይኖረኝም፣ አሁን ባለው ነባራዊ ሆኔታ ግን ችግሩን ፖለቲካዊ እያደረግነው ያለን ይመስለኛል።
ወደድንም ጠላንም… መንግስት ይሄዳል ይመጣል፣ ፖለቲካም እንደዛው … ጣና ግን ትላንትም ነበር፣ ነገም የሚኖር ታዳሽ ሀብት ነው። ስለዚህ ብልፅግና፣ አብን፣ አዴፓ፣ ሙስሊም፣ ክርቲያን፣ ፕሮቴስታንት፣ ወጣት ሽማግሌ፣ አማራ፣ ኦሮሞ፣ ትግሬ… ሳንል በአንድነት ተባብረን ማጥፋት የዜግነት ግዴታችን ነው…!!
በጣና ሐይቅ የሚደረግ ማንኛውም የፖለቲካ ትርፍ ይቁም!!
ጣና ከፖለቲካ በላይ ነው፣ ጣና ክልል በላይ ነው። ጣና ከብሔር እና ከቡድን በላይ ነው። ጣና ከሀይማኖት በላይ ነው!!
ጣና መታደግ ራስን መታደግ ነው፣ ጣናን መታደግ ህይወትን መታደግ ነው፤ ጣናን መታደግ ተፈጥሮን ማዳን ነው!!
——
መንግስት ጣናን ለመታደግ ለምን ዳተኛ ሆነ???
/…እዚህም እዚያም “አብይ አህመድ ጣናን ለመታደግ ዳተኛ ሆነ፣ የፌደራሉ መንግስት እንዴት በጣና ዙሪያ ዝም ይላል” የሚሉ የዋሃን ድምፆች በተደጋጋሚ  ስሰማ ጣናን ከ16 ዓመት በፊት የሞት ፍርድ የፈረደበት ማን ሆነና ነው፥ ዛሬ የፌደራል መንግስቱ ዝም አለ የሚባለው? ወያኔ ትግሬ መራሹ የፌደራል መንግስት ከተላላኪው ብአዴን ጋር ሆነው መስሎኝ “ኤሌክትሪክ በማመንጨት” ሽፋን በወረቀት ላይ በጣልያኑ ሳሊኒ ከንስትራክሽን የተሰራውን ዲዛይን አስለውጠው ጣናን የወጉት?
 እርግጥ ነው ያንን ተከትሎ “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” ሆኖበት እምቦጭ ደግሞ ሐይቁን በፍጥነት ወደ ደረቅ መርዛማ መሬትነት እየቀየረው ነው። አብይ አህመድ የሚዘውረው የፌደራል መንግስት መፍትሔ ይሰጠኛል ብሎ የሚጠብቅ እሱ፥ “ተረኝነት የለም” ብለው የሚሰብኩ ፍርፋሪ ለቃሚ ውሉደ-ብአዴኖች አልያም የኦሮሙማ ፖለቲካን ያልተረዱ የዋሃን ይሆኑ እንደው እንጂ በተግባር ጠብ የሚል ነገር እንደማይኖር ልናረዳቸው እንወድዳለን። ደግሞስ አበዳሪ የናቀውን አሞሌ፣ባለዕዳ እንዲያከብረው መጠበቅ እንደምን ትክክል ሊሆን ይችላል? ብአዴንን በአይንህ ስር ታግሰኸው ስታበቃ፥መንግሥት አልባ መሆንህን ለ29 ዓመታት በተግባር እያሳየህ፥በልመናና ተማፅኖ ብአዴንም ይሁን የፋሽታዊው የኦሮሞ መንግስት ለጣና መልስ ይሰጥልኛል ብሎ መጠበቅ ከንቱ የቀን ቅዠት  ነው!!! ለማንኛውም ጣና እንዲህ እንደተወጋ ማስታወሱ ለመፍትሔው ማን መጠራት እንዳለበት ፍንጭ ይሰጥ ይሆናል። ችግሩን ፈጥረው ሲያበቁ፥ጆሮ ዳባ ያሉትን ልግመኞች ለመፍትሔ መጥራት ትርፉ ጉንጭን ማልፋት ነው። ያለው ብቸኛ አማራጭ ህዝባችን በስርዓቱ ላይ አምፆ መነሳት ብቻ ነው። ህልውናና መብትህን የምታስከብረው በክንድህ ብርታት ተባጥሰህ እንጂ በልመናና ተማፅኖ ሰዎች በችሮታ እንዲሁ እንዲያደርጉልህ በመጠበቅ አይደለም።
 ከአስራ አምስት ዓመታት በፊት “ይሙት በቃ!” የፖለቲካ ፍርድ ተወስኖበት የተገደለው ጣና!!!
 
ምናልባትም እኛ ራሳችንን እናውቀዋለን ከምንለው በላይ ጠላቶቻችን የግል ስማቸውን የማወቅ ያህል ጠንቅቀው ያውቁናል የሚል ጥርጣሬ አለኝ። በተለይ ከእኛ ጋር ውጊያን ማድረግ እንዴት እንደሆነ አሳምረው ተክነውበታል።
በዘመናት መካከል ተፈትኖ ውጤታማ የሆነ ስልት አላቸው፤ ይኸውም በባህርይው አዝጋሚ፣በለሆሳስ የተቃኘ ግን ደግሞ የማያቋርጥ ውጊያ /Gradual Warfare/ ነው። ይህ የውጊያ ስልት መጥፎ ጎኑ ጦርነት እየተደረገብህ እንደሆነ እንኳን የምትባንነው አንድም እጅግ በጣም ከረፈደ አልያም ውጤቱን ልትቀለብሰው ብትሞክር እንኳን አስቀድሞ አንተ ከመንቃትህ በፊት ሙሉ አቅምህን ገዝግዞ የጨረሰው በመሆኑ የአቀበት ላይ ውጊያ /Uphill battle/ ስለሚሆንብህ ነው።
በተለይ በወያኔ ትግሬ ከተፈፀመብን ጥፋት መካከል የአንዳንዶቹን ውጤት ማወራረድ የሚጠበቅብን ዛሬ ላይ በዚህ ትውልድ ብቻ ሳይሆን ነገና በመጪው ትውልድ ጭምርም ነው። የጣና መገደል የዚህ አንዱ ማሳያ /microcosm/ ነው።
የጣና ሐይቅ ዋነኛ ችግር እምቦጭ የሚባለው አረም ቢሆን ኖሮ “የአማራ ህዝብ ጊዜ የማይሰጥ የህልውና አደጋ ገጥሞታል” የሚለውን እምነት በጽኑ እንደሚያምን አንድ ግለሰብ “ጣና ታሟል አሉ” የሚለውን የድምፃዊያን ዳኜ ዋለንና ሰለሞን ደምሌን ዘፈን እያዳመጥኩ በጥቂት ጥረት መስተካከል የሚችል ጉዳይ ነው በሚል የማልፈው ይመስለኛል።
ነገር ግን ጣና ከአስራ አምስት ዓመታት በፊት “ይሙት በቃ!” የፖለቲካ ፍርድ ተወስኖበት የተገደለ፣ ዛሬ ጉሮሮው ላይ ሲር፥ሲር የምትል እስትንፋሱን ደግሞ ቧልተኛውና ዳተኛው ብአዴን/አዴፓ እንዲጨርሳትና ግብዓተ-መሬቱን እንዲያከናውን የተተወ መሆኑ ነው።
ጉዳዩን በአማራ ህዝብ ላይ ከተቃጡ የጅምላ ፍጅቶች ጎራ እንዲመደብ የሚያደርገው ደግሞ የጣና ሞት የሶስት ሚሊየን አማራዊያንን ህይወት የቀጥታ ሰለባ ከማድረግ አልፎ ጎንደርና ጎጃም የሚባሉ ቦታዎች ለሰው ልጅ መኖሪያነት ፍፁም ከማይመቹ ስፍራዎች ተርታ እንዲመደቡ የማድረግ እምቅ አቅሙ ነው። ይህም በአማራ ህዝብ ላይ በወያኔ ትግሬና ተላላኪዎቹ ከተፈፀመው የዘር ማጥፋት፣ የዘር ማጽዳት፣ የሜዲካል አፓርታይድ እና መሰል ጥፋቶች ጎን ለጎን በአማራ ህዝብ ላይ መጠነ ሰፊ የሆነ የስነ-ህይወትና ከባቢ ፍጅት /Ecocide/ ተፈጽሟል ብለን በድፍረት እንድንናገር ያደርገናል።
ለመሆኑ የስነ-ህይወትና ከባቢ ፍጅት /Ecocide/ ምንድነው?
የስነ-ህይወትና ከባቢ ፍጅት /Ecocide/ እንዲህ እና እንዲያ ነው ከማለታችን በፊት ከጣና ክስተት ጋር የሚመሳሰል አንድ አለማቀፍ ምሳሌን አንስቶ መመልከት ለአንባቢ የተሻለ ግንዛቤ ያስጨብጣል።
በ1960ዎቹ አካባቢ በዓለም ላይ በመሬት ከተከበቡ ባህሮች /Inland Seas/  መካከል በትልቅነት የአራተኛ ደረጃ ላይ የነበረው በቀድሞዋ ሶቭየት፥ በዛሬዎቹ ደቡባዊ ካዛክስታንና በሰሜናዊ ዩዝቤክስታን መካከል የሚገኘው የኤራል ባህር /Aral Sea/ ነው። በወቅቱ ይህ ባህር የጣና ሐይቅን ሰላሳ ሁለት /32/ እጥፍ ይሆናል። እሱም እንዲህ እንደ ዛሬው ጣና በክፉዎች እጅ ወደቀና የፖለቲካ ፍርድ ተላለፈበት፤ ይኸውም የሀገሪቱን የእዝ ኢኮኖሚ በበላይነት የሚመራው የኮሚዩኒስት ፓርቲው የላይኛው አመራር ወደ ባህሩ የሚገቡ “አሙ ዳሪያ” እና “ሲር ዳርያ” የተባሉ ወንዞችን ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ በመጥለፍ የጥጥ እርሻ በሰፊው እንዲካሄድ አደረገ። በዚህም ሳይወሰን በባህሩ መሃል ላይ ትገኝ በነበረችው “ቮዝሮዝዴንዬ” በተባለችው ደሴት ላይ ከኢትዮጵያ ሳይቀር ዝንጀሮዎችን እየወሰዱ በደሴቷ ላይ እጅግ ገዳይ የሆኑ የባዮሎጂካል የጦር መሣሪያዎችን በምስጢር የመሞከሪያ ስፍራ አደረጉት።
ለጊዜው ሶቭየት በጥጥ ምርት ራሷን ከመቻል አልፋ ለአለም ገበያ በሰፊው አቅራቢ ሀገር ብትሆንም በሂደት ግን ይህ በትልቅነቱ ከአለም አራተኛ የነበረ ባህር ለሰላሳ ዓመታት ያህል በአዝጋሚ ሞት ሲሰቃይ ኖሮ ሶቭየት ስትበታተን መጠኑ የመለስተኛ ሐይቅ ያህል ሆኖ ሲቀር በሶቭየት የመጨረሻው ዓመት ላይ ራሽያዎች ይባስ ብለው ከላይ በተጠቀሰችው ደሴት ላይ ሁለት መቶ ቶን የሚመዝን ለባዮሎጂካል ጦር መሣሪያነት የሚውል የአንትራክስ  ዕጭ /Weapon Grade Anthrax Spores/ ቀብረውበት ሄዱ።
ሶቭየት ስትበታተን የባህሩ አብዛኛው ክፍል የነበረው ቦታ “ካራካልፓክስታን” የሚባለው የዩዝቤክስታን ግዛት አካል ሆነ። በ1960ዎቹ የኤራል ባህር ይባል የነበረው  ዛሬ የኤራል በረሃ የሚባል ሲሆን ይህ በረሃ /የትናንቱ ባህር/ ለሰው ልጅ መኖሪያነት እጅግ አደገኛ ከሆኑ ስፍራዎች አንዱ ነው፤ በመሆኑም ከሁለት ሚሊየን በላይ የሚሆኑ ዩዝቤክስታናዊያን በተለያዩ ካንሰርና ተያያዥ በሽታዎች እየተጠቁ ያለዕድሜያቸው በአጭሩ እንዲቀጩ ምክንያት ሆኗል። ያደረሰውን የኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቀውስ ማንሳት እንዲሁ በከንቱ አንባቢን ማሰልቸት ነው የሚሆነው።
በፖለቲካዊ  “ይሙት በቃ!” ውሳኔ የጥጥ ማሳ ታላቁን ባህር ሲበላ፤ የባህሩም ሞት፥ በሚሊየን የሚቆጠሩ ህዝቦችን፣ በባህሩ ውስጥና በአጠቃላይ በአካባቢው የነበረውን የስነ-ህይወት ምህዳር ክፉኛ አመሳቀለው። እንግዲህ ይህ ሆን ተብሎ የሚደረግ የስነ-ህይወት ምህዳር ምስቅልናና በሰዎች ላይ የሚያስከትለው ለከት የለሽ ጥፋት ነው የስነ-ህይወትና ከባቢ ፍጅት /Ecocide/ የሚባለው።
ወደ ጣና ጉዳይ ስንመለስም ከላይ ሲታይ “የምዕተ ዓመቱን የዕድገትና የልማት ዕቅድ ለማሳካት” በሚል ሽፋን በልማት ስም “የጣና-በለስ የኃይልና የመስኖ ልማት አገልግሎት” አልያም “The Tana Diversion Program” /TDP/ በሚል የዳቦ ስም ከጣና ሐይቅ ላይ 12 ኪ.ሜ. በሚረዝም ሰው ሰራሽ ቦይ /Tunnel/ ከፍተኛ መጠን ያለው ውሃ በመውሰድ የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲያመነጭ ከተደረገ በኋላ ውሃው ወደ ጣና እንዳይመለስ ተደርጎ ከበለስ ወንዝ ጋር ይገናኛል። ከዚያም እስከ 140 ሺህ ሄክታር መሬት የሚሸፍን ለስኳር ምርት የሚውል የሸንኮራ አገዳ የመስኖ እርሻን እንዲያለማ ከተደረገ በኋላ የበለስ ወንዝ በሱዳን ድንበር አካባቢ ከአባይ ወንዝ ጋር ተቀላቅሎ ድንበር ተሻግሮ ይሄዳል።
ከላይ ሲታይ በስሱም ቢሆን ጤነኛ ይመስላል። ነገር ግን ጉዳዩን ከሁለት መሠረታዊ ነገሮች አንፃር ስንመዝነው የአማራ ህዝብ የምንጊዜም ጠላት የሆነው ወያኔ ትግሬ በአንድ ድንጋይ ብዙ ወፎችን የማርገፍ አላማ ይዞ የተነሳበት፤ በተለይም በልማት ስም ኢኮኖሚያዊ ትርፉን ከማግኘት ጎን ለጎን ተፈጥሮን እንደ መውጊያ መሳሪያ / Weaponization of Nature as an Offensive Tool/ በመጠቀም  ለአማራ ህዝብ ዘመን ተሻጋሪ የቤት ስራን ሰጥቶ ያለፈ ጉዳይ ነው።
ዛሬ ላይ አይናችን ህያው ምስክር በሆነበት ሁኔታ የጣና ሐይቅ በአስደንጋጭ ሁኔታ ሲደርቅ ስናይ እንዲሁም የአባይን ግድብ በመጠነኛ ወጪ በአማራ ምድር ላይ እንዳይሰራ የተደረገበትን ፖለቲካዊ ውሳኔ ስንታዘብና እንዲሁም ሌሎች የልማት እድሎች ሆን ተብሎ ሲነፈገው የኖረ ህዝብ እንደዚህ ላለው ዘመን ተሻጋሪ አካባቢያዊ ጠባሳን ለሚያስከትል እንቅስቃሴ /Stigmatized Activity/ ሲመረጥ ከጅምሩም ይህ የአማራ ህዝብ ለምን ዓላማ እንደታጨ ግልጽ ነው።
 የአማራን ህዝብና የአማራን ሀገር ለበለጠ ጥፋት እያዘጋጀ ያለው የዚህ ፕሮጀክት ውጤቶች ማለትም የኃይል ማመንጫውም ይሁን የመስኖ ስራ ፕሮጀክቱ ንብረትነቱ የፌደራል መንግስቱ መሆኑ ደግሞ ፈጣሪ ለህዝባችን የሰጠው ፀጋ በኢ-ፍትሐዊ መንገድ መበዝበዙ ሳያንስ የሚያስከትለውን ከባቢያዊ እና የአጠቃላይ የስነ-ህይወት ምህዳሩ ጥፋት ብቸኛ ገፈት ቀማሽ የሆነው የአማራ ህዝብ መሆኑ ነው።
ሲጀመር ይህ የጣና-በለስ ፕሮጀክት /”The Tana Diversion Program” /TDP// በቀላል የዲዛይን ስራ መስተካከል የሚችል ሆኖ ሳለ በእኔ እምነት ሆን ተብሎ በፖለቲካ ውሳኔ እንዲያ እንዲሆን በመደረጉ በሁለት ተመጋጋቢ ምክንያቶች በሐይቁ እና በዚያ ዙሪያ ላይ የስነ-ህይወት ምህዳሩ ላይ መዛባት /Ecological Imbalance/ እንዲፈጠር ተደርጓል።
1ኛ. የሐይቁ ተፈጥሯዊ የውሃ ፍሰት ሚዛን እንዲናጋ ማድረግ /Breaking the Water Balance/:- ይህ የሆነው የፕሮጀክቱ ባህርይ በራሱ ሙሉ በሙሉ ከሐይቁ ላይ ውሃን በመውሰድ ብቻ /Irreversible Consumption/ ላይ የተንጠለጠለ በመሆኑ ወደ ሐይቁ ከሚገባው ውሃ ይልቅ ከሐይቁ የሚወሰደው ውሃ በመብለጡ የሐይቁ መጠን በጣም ሊታይ በሚችል ሁኔታ ሊጠብ ችሏል። አሁን ባለው አያያዝም ከዚህ በላይ እየጠበበ ከመክሰም የሚያድነው የለም።
2ኛ. ከላይ ባየነው መንገድ እየደረቀና እየጠበበ የመጣው ሐይቅ “ዕድሜ ለብአዴን ይሁንና¡” በሁለት መሠረታዊ ምክንያቶች የብክለት ሰለባ ሆኗል።
2.ሀ. የሐይቁን መድረቅ ተከትሎ ውሃው ሲሸሽ በተፈጠረው ረግረጋማ ቦታ ላይ የሚሰራውና በከፍተኛ ሁኔታ ኖርዌይ ሰራሽ የሆነውን ግን ደግሞ በአውሮፓ እና አሜሪካ ለአገልግሎት እንዳይውል የታገደን ማዳበሪያ በሩዝ እና መሰል እርሻዎች ላይ በመጠቀም ከፍተኛ የሆነ የኬሚካል ብክለት ሲሆን /Pesticide–Intensive Farm/
2.ለ. ከመኖሪያ ቤቶችና ከሆቴሎች የሚወጡ ቆሻሻዎች ወደ ሐይቁ እንዲፈሱ መደረጋቸው /Household and Municipal Waste Disposal/ ሌላው የብክለት ምንጭ ነው።
እንግዲህ እነዚህ ሁኔታዎች ናቸው የጊዜ ቦምብ ሆነው ነገ የሶስት ሚሊየን አማራዊያንን ህይወት እና የመኖሪያ ስፍራ የቁም ሲኦል ሊያደርጉ እየተዘጋጁ ያሉት።
ሙይናክ በምትባለው የዩዝቤክስታን ከተማ ውስጥ “የሰው ልጅ እንዴት እንዲህ ሆኖ ይወለዳል?” ብለህ በድንጋጤ እስክትጠይቅ ድረስ ቀልብህን የሚገፍ ክስተት ስታይ የስነ-ህይወትና ከባቢ ፍጅት /Ecocide/ ማለት የመጨረሻ ውጤቱ በኑክሌር ከመመታት እንደማይተናነስ ትታዘባለህ። ታዝበህም አትቀር ነገር “Fools rush in where angels fear to tread.” የሚለው የአሌክዛንደር ፓፕ አባባል ኅሊናህን ሰቅዞ ይይዝሃል።
    “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ”
ከላይ ለማየት እንደሞከርነው የጣና-በለስ ፕሮጀክት /”The Tana Diversion Program” /TDP/ በሐይቁ ላይ የስነ ህይወት ምህዳር መዛባት /Ecological Imbalance/ ከፈጠረበት ምክንያት አንዱ የሐይቁን የውሃ ፍሰት ሚዛን ማናጋት /Breaking the Water Balance/ ሲሆን የእንቦጭ አረም በሀይቁ ላይ መከሰት ደግሞ ከአረሙ ባህርይ አንፃር የተጋረጠውን አደጋ በማፋጠን በኩል ነገሩን “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንዲሆን አድርጎታል።
ከቀን አንድ ጀምሮ በእምቦጭ ዙሪያ ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ እና የትንታኔ ስራ በተለያዩ ሰዎች በመሰራቱ ያንን ዛሬ እንደአዲስ ልናነሳው አይገባም። ከዚያ ይልቅ ይህን አደገኛ አረም ለመቆጣጠር ከመትጋት ይልቅ ዳተኛውና ቧልተኛው ብአዴን የሄደበትንና እየሄደበት ያለውን መንገድ መመልከት በቀጣይ ምን ቢደረግ ይሻላል? የሚለውን ለመወሰን ይረዳል።
  የብአዴን/አዴፓ ቧልቶች
ብአዴን በአማራ ምድር ላይ በህግ መታገድ ያለበት ድርጅት ነው የሚል አቋም ካላቸው ሰዎች መካከል ራሴን ከማገኝበት ምክንያት አንዱ ገና ከፍጥረቱ ጀምሮ ፀረ-አማራ ተላላኪ በመሆኑ ብቻ አይደለም። ይልቁን ባለችው አቅም እንኳን መወጣት ያለበትን ህዝባዊ ኃላፊነት መሸከም የማይችል፣ ቅቡልነት ያለው አመራር እንዲኖረው ሊያደርገው የሚችለውን ዝቅተኛውን የሞራል ልዕልና /The Moral Minimum for Legitimate Rule/ የሌለው ቀትረ-ቀላል ተላላኪና በህዝብ ጥቅምና ህልውና ላይ የሚቀልድ ድርጅት በመሆኑ ነው።
የእንቦጭ አረምን በተመለከተም ብአዴን የጣና ሐይቅ በጣና-በለስ ፕሮጀክት /”The Tana Diversion Program” /TDP/ እንዲገደል ከተደረገ በኋላ ቀሪ እስትንፋሱ ከማለቋ በፊት አፋጣኝና ዘላቂ ውጤት ያለው መፍትሔ ከመስጠት ይልቅ አይንና ጆሯችንን እስክንጠራጠር ድረስ ዛሬም ድረስ የቧልት ስራ ሲሰራ ነው የሚታየው።
  ቧልት ቁጥር 1. ሐይቁን ላልሰለጠኑ ተለማማጆች የመለማመጃ ላቦራቶሪ ማድረግ:-
በአማራ “ክልል” የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎችና በከተሞች የሚገኙ ብረት በያጆች ሌላ የፈጠራ ስራ የሌለ ይመስል “የእንቦጭ አረም ማስወገጃ ማሽን” ሰሩ የሚል ዜና በሳምንት አንድ ጊዜ መስማት በጣም የተለመደ ነው። እውነታው ግን ተሰሩ የተባሉት በሙሉ ውጤታማ አይደሉም!!!
እስኪ ክስተቱን ወደግል ህይወታችን መልሰን እንየው። ብንታመም የመጀመሪያ ስራችን የሚሆነው አቅማችን በፈቀደው መልኩ ጥሩ የሚባል ሐኪም ፈልገን እንታከማለን እንጂ “ቆይ ትንሽ ታገሰኝ። ለጊዜው ሀኪም አይደለሁም። አጥንቼ ሀኪም ከሆንኩ በኋላ አክምሃለው” ወደሚለን የእኔ ቢጤ ጨዋ ጋር አንሄድም።
በድጋሚ “ዕድሜ ለብአዴን ይሁንና¡” ጣና ግን ለዚህ አልታደለም። ይልቁን የጣና አዝጋሚ ሞት የብአዴን/አዴፓ የቧልት ማድመቂያ ነው የሆነው። ሲፈልግ “ለጣና ያሰባሰብኩትን ገንዘብ እስከዛሬ ጥቅም ላይ አላዋልኩትም” ብሎ እንደደህና ወሬ ያወራል፤ ሲብስም “አረሙን ለማጥፋት ተገዝተው የመጡት ጥንዚዛዎች ማደሪያቸው በነፋስና በዝናብ በመፍረሱ ተበተኑ” የሚል ዜና እያስነገረ፥ ሳንወድ በግድ “አለበለዚያውማ በዘዋል ልጅ ሊዳር!” እንድንል ያደርገናል።
 ቧልት ቁጥር 2. “ከእንቦጭ ነዳጅ /Bio-diesel/ እናመርታለን”
ይህ እ.አ.አ በ2012/2013 ዓ.ም. የተፈፀመ የብአዴን ታሪክ ነው። አንድ የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ተማሪ የነበረ በኋላም የአዋሳ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆነ ከዚያው ከደቡብ አካባቢ የመጣ ሰው ከጃትሮፋ ተክል ነዳጅ ማምረት የሚችል መጠነኛ የጎጆ ኢንደስትሪ ይሰራና ከአዕምሮ ፈጠራ መስሪያ ቤት የባለቤትነት ማረጋገጫና ከሳይንስና ቴክኖሎጂ መስሪያ ቤት ደግሞ ሽልማት ይበረከትለታል።
ይህን ዳር ቆሞ ሲታዘብ የከረመው ብአዴንም በአማራ መልሶ ማቋቋም ልማት ድርጅት /አመልድ/ አማካኝነት በወሎ /ከኦሮሞ ወረራ በፊት ቤተ-አማራ/ ባቲ ወረዳ ሶስት መቶ አርሶ አደሮችን አደራጀው ይልና ይህን የጃትሮፋ ተክል እንዲያመርቱ ያደርጋል። በዚህም ሳይወሰን ከላይ የጠቀስነውን የአዋሳ ዩኒቨርሲቲ መምህር የነበረውን የፈጠራ ባለሙያ ያነጋግርና ከጃትሮፋ ተክል ነዳጅ ማምረት የሚችለውን የጎጆ ኢንደስትሪ በባቲ ያስተክላል።
በሚሊየኖች የሚቆጠር ብር  አውጥቶ ሲያበቃ፥ “አደራጀሁ” ያላቸውን አርሶ አደሮች በአግባቡ መያዝ ባለመቻሉ ምክንያት የጃትሮፋ የባዮ ዲዝል ታሪክ የውሃ ሽታ ሆኖ ሲቀር ያቺ መጠነኛ የጎጆ ኢንደስትሪም ዛሬም ድረስ በባቲ እንደጅብራ ተገትራ ቀርታለች። የብአዴን ሌጋሲ እንግዲህ እንዲህ ነው።
ይህ ልምድና ታሪክ ያለው ቧልተኛው ብአዴን ነው እንግዲህ ከአንዳንድ ደፋር “ምሁር” ነን ባዮች ጋር ሆኖ በሌላ ትርክት “ከእንቦጭ ነዳጅ አወጣለሁ” የሚለን። እንቦጭ እንደጃትሮፋ ለቧልተኞች ጊዜ የሚሰጥ አለመሆኑን ብአዴን ጠፍቶት አይደለም። ይልቁን ብአዴን ቧልተኛ ብቻ ሳይሆን ዳተኛም ስለሆነ ጭምር ነው እንጂ!!!
በዚህ አጋጣሚ ወደ ድምዳሜያችን ከመሸጋገራችን በፊት አንድ ነገር ተናግረን እንለፍ።
በዚህ በጣና ሞት ላይ የቆመው የጣና-በለስ ፕሮጀክት /”The Tana Diversion Program” /TDP/ ላይ የመስኖ ፕሮጀክቱ ተጠቃሚ የሆኑት ንብረትነቱ የፌደራሉ መንግስት የሆነው የስኳር ፕሮጀክት ብቻ ሳይሆን ካሣ ተክለብርሃን የሚባለው ትግሬ የብአዴን አባል የክልሉ የኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ በነበረበት ወቅት ለወያኔ ትግሬ ባለስልጣናት እና ልጆቻቸው በወረራ ባደላቸው የምዕራብ ጎጃም የአማራ መሬት ላይ የአግሮ ኢንደስትሪ ባለሀብት የሆኑ ትግሬዎች ጭምር ናቸው።
ከነዚህም መካከል የስብሐት ነጋ ልጅ የሆነችው ህያብ ስብሐት ነጋ አንዷ ስትሆን በምዕራብ አማራ በአዊ ዞን በጃዊ ወረዳ አንድ ሺህ ሄክታር መሬት ያለውና ሰባ አምስት ሚሊየን ብር የመነሻ ካፒታል ያለው “ህያብ የግብርና ኢንደስትሪ” በመባል የሚታወቀው ድርጅት ባለቤት ናት።
መቼም ህዝባችንን የእኔ የሚለው መሪ ባለመኖሩ ይህ በምዕራብ አማራ የተፈፀመው የመሬት ቅርምት ለከት የለሽ ከመሆን አልፎ ከራሳቸው ባሻገር ገና የሀይስኩል ትምህርታቸውን እንኳን በአግባቡ ባልጨረሱ ልጆቻቸው ስም ሳይቀር የተፈፀመ መሆኑ ነው። ለዚህም ማሳያ የሚሆነን የስብሐት ነጋ ልጅ የሆነችው ህያብ ይህንን ከላይ የተጠቀሰውን መሬት በወሰደችበት ወቅት በጣልያን ሀገር ፓድዋ በሚባል ስፍራ የሀይስኩል ትምህርቷን እየተማረች ነበር። በዚሁ አጋጣሚ የስብሐት ነጋ የቅርብ ዘመድ የሆኑ ሰዎች ሆላንድ ከሚገኝ የአግሮ ኢንደስትሪ ድርጅት ጋር በማሴር በጤፍ ላይ የፈፀሙትን የስነ-ህይወት ዘረፋ /Bio-Piracy/ እንዳስፈላጊነቱ በሌላ ጊዜ እንመለከተዋለን።
ወደ ተነሳንበት ቁምነገር ስንመለስም መሬታችንን ተቀራምተው፣ የሐይቃችንን ህልውና አደጋ ላይ ጥለው እንዲሁም አጠቃላይ የስነ-ህይወትና ከባቢ ውድመት /Ecocide/ ፈጽመውብን ሲያበቁ አማራዊ ምድራችን የጭሰኛ መፍለቂያ /Peon Factory/ ሲሆን እያየን ጦርነት ውስጥ አይደለንም ልንል አንችልም።
ከዚያ ይልቅ እያስፈራኝ የመጣው ይህን መሰል እና ከዚህም በላይ የከፋ ስንት አስጨናቂ ጉዳይ ከብቦን እያለ አሁን፥አሁን የአማራ ጉዳይ ያገባናል ባዮች ጊዜና ኃይላቸውን የሚያጠፉበት ነገር እንቶ ፈንቶ በሆነ አጀንዳ እየሆነ ስናይ ያሳፍራልም፣ያሳዝናልም፣ ያሳስባልም።
እንዳስፈላጊነቱ በሌላ ጊዜ ይህንን ጉዳይ በግልጽ አውጥተን የምናነሳው ይሆናል። ይሁን እንጂ የአማራ ህዝብ ዙሪያ ገባውን የህልውና አደጋ ተጋርጦበታል ስንል ግን በእርግጥም መሬት የያዘ እውነትን መሠረት አድርገን ነው።
ቸር እንሰንብት።
Filed in: Amharic