>

የወጋየሁ ንጋቱ 76ኛ ዓመት የልደት መታሰቢያ (ልዑል ዓምደጽዮን ሠርፀድንግል)

የወጋየሁ ንጋቱ 76ኛ ዓመት የልደት መታሰቢያ

ልዑል ዓምደጽዮን ሠርፀድንግል

ተወዳጁን ‹‹ፍቅር እስከ መቃብር›› የተረከው ዝነኛውና ተወዳጁ ተዋናይ ወጋየሁ ንጋቱ የተወለደው ከዛሬ 76 ዓመታት በፊት (ግንቦት 28 ቀን 1936 ዓ.ም) ነበር፡፡
ወጋየሁ ከአባቱ ከአቶ ንጋቱ ብዙነህና ከእናቱ ከወ/ሮ አምሳለ በየነ ግንቦት 28 ቀን 1936 ዓ.ም. አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ተወለደ፡፡ ወጋየሁ እናቱና አባቱ ጋብቻ ከፈጸሙ በኋላ ልጅ ሳይወልዱ ቆይተው ስለነበር በስለት ያገኙት ልጅ እንደነበር ይነገራል፡፡ (‹‹ፍቅር እስከመቃብር›› ልብ ወለድ ላይ ያለው በዛብህም የስለት ልጅ መሆኑን ልብ በሉ)
የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን የተማረው በስዊድን ሚሲዮን ት/ቤት ሲሆን፤ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ በተፈሪ መኮንን ት/ቤት አጠናቋል፡፡ በት/ቤት ቆይታውም በርካታ ድራማዎችንና ሌሎች የኪነ-ጥበብ ስራዎችን እንደሰራና በት/ቤቱ ማኅበረሰብ ዘንድም ተወዳጅ እንደነበረ ታሪኩ ያስረዳል፡፡
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን እንዳጠናቀቀም ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመግባት በወቅቱ ‹‹ኪነ ጥበብ ወትያትር›› ይባል ወደነበረው የአሁኑ ‹‹የባህል ማዕከል›› ገብቶ ከጓደኞቹ ከነአባተ መኩሪያ እና ደበበ እሸቱ ጋር እንቅስቃሴ ማድረግ ጀመረ፡፡
የትወና፣ የዝግጅትና የፅህፈተ-ተውኔትን መሠረታዊ እውቀት ተምሮ ‹‹ሮሜዮና ጁሌት››፣ ‹‹ጠልፎ በኪሴ››፣ ‹‹የከርሞ ሰው››፣ ‹‹መድሃኒት ቀምሰዋል››፣ ‹‹ዳንዴው ጨቡዴ››፣ ‹‹የዋርካው ሥር ምኞት›› እና ‹‹ላቀችና ድስቷ›› በተባሉ የትርጉምና ወጥ ተውኔቶች ላይ አብይ ሚናዎችን ይዞ በመጫወቱ ተደናቂ ሆነ፡፡
በ1959 ዓ.ም. ከደበበ እሸቱ ጋር ወደሀንጋሪ ቡዳፔስት ተልኮ የሥነ-ተውኔት ሙያን ለሁለት ዓመታት አጥንቶ ተመለሰ፡፡ ከሀንጋሪ እንደተመለሰም በሬዲዮና በቴሌቪዥን አጫጭር ተውኔቶችን ማቅረብ ቀጠለ፡፡ በተለይም በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ለተመልካች እንግዳ የሆኑ ‹‹አስማተኛው››፣ ‹‹ቁንጫ››፣ ‹‹ባሉን››፣ ‹‹ቀለም ቀቢው››፣ ‹‹የተዘጋ በር›› እና ሌሎች ተውኔቶችን እያቀረበ ተደናቂነትን አተረፈ።
ወደ ሐገር ፍቅር ትያትር ቤት ከተዛወረ በኋላም የትያትር ክፍሉ ኃላፊ፣ አዘጋጅ፣ ተዋናይና እንዲሁም በሙያው ለመስራት የሚፈልጉ ወጣቶችን በማስተማር ሁለገብ አገልግሎት ሰጠ፡፡ ከዚህ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ሬዲዮ ተዛወረና በመዝናኛ ፕሮግራም አቅራቢነትና በዜና አንባቢነት ሲሰራ ቆየ፡፡
ብሔራዊ ትያትር ከገባ በኋላም ‹‹የበጋ ሌሊት ራዕይ››፣ ‹‹ትግላችን››፣ ‹‹ደመ መራራ››፣ ‹‹ደማችን››፣ ‹‹ሀሁ በስድስት ወር››፣ ‹‹ሞረሽ››፣ ‹‹አፅም በየገፁ››፣ ‹‹ፀረ-ኰሎኒያሊስት››፣ ‹‹እናት ዓለም ጠኑ››፣ ‹‹የአዛውንቶች ክበብ››፣ ‹‹ዋናው ተቆጣጣሪ››፣ ‹‹ፍርዱን ለእናንተ››፣ ‹‹ጴጥሮስ ያቺን ሰዓት››፣ ‹‹ክራር ሲከር››፣ ‹‹ሀምሌት››፣ ‹‹ሊየር ነጋሲ››፣ ‹‹የድል አጥቢያ አርበኛ››፣ ‹‹ዘርዓይ ደረስ››፣ ‹‹ገሞራው››፣ ‹‹አሉላ አባነጋ›› እና ‹‹እናት ነሽ›› በተሰኙ ስራዎች ላይ አብይ ሚናዎች እየወከለ ተጫውቷል፡፡
ወጋየሁ ከተውኔት አዘጋጅነቱና ተዋናይነቱ በተጨማሪ በመጽሐፍት ትረካዎቹም ይታወቃል፡፡ በተለይ ደግሞ ክቡር ዶ/ር ሀዲስ ዓለማየሁ የፃፉትን ‹‹ፍቅር እስከ መቃብር››ን የተረከበት መንገድ የሚዘነጋ አይደለም፡፡ ለዚህም ደራሲው ክቡር ዶ/ር ሀዲስ ዓለማየሁም ‹‹ፍቅር እስከመቃብርን እኔ ጻፍኩት፤ ወጋየሁ ነፍስ ዘራበት፤ እኔ ከፃፍኩት ይልቅ አንተ በህዝቡ አዕምሮ የሳልከው ይበልጣል›› በማለት ለወጋየሁ የትረካ ብቃት ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡
ከ‹‹ፍቅር እስከ መቃብር›› በተጨማሪ የብርሃኑ ዘሪሁን ሶስት መፅሐፍት (ማዕበል የአብዮት ዋዜማ፣ ማዕበል የአብዮት መባቻ እና ማዕበል የአብዮት ማግስት) እንዲሁም የገበየሁ አየለ ‹‹ጣምራ ጦር›› ከተደራሲያን አዕምሮ የማይጠፉ ናቸው፡፡
ሰአሊ እሸቱ ጥሩነህ ‹‹መላ አካሉ ቋንቋው›› በሚል ርዕስ የወጋየሁ የሰውነት፣ የቁመት፣ የፊት፣ ቅርጽ ሁኔታ ላይ ጠለቅ ያለ ሂሳዊ ጽሁፍ አቅርበዋል። ታዋቂው ሀያሲ ስዩም ወልዴም ‹‹ገጸ ብዙ ጠቢብ›› ብሎ የወጋየሁን ሁለገብ የተዋናይነት ብቃት አብራርቶ ጽፏል።
ረዳት ፕሮፌሰር ሀይማኖት ዓለሙ ወጋየሁ ለመድረክ የተፈጠረ መሆኑን መስክረዋል። አርቲስት ፍቃዱ ተክለማርያም በበኩሉ ወጋየሁ ከእርሱ በኋላ ለሚመጡ ተዋናዮች እውቀቱን ለማካፈል ፍጹም የማይሳሳ እነደነበር ተናግሯል።
ወጋየሁ በ1966 ዓ.ም እንደ ፀረ-አብዮተኛ ተቆጥሮ ለጥቂት ጊዜያት ታስሮ ተፈትቷል፡፡ በ1977 ዓ.ም. ከባህል ሚኒስቴር ሠራተኞች መካከል ‹‹ምሥጉን ሠራተኛ›› ተብሎ ተሸልሟል፡፡
ወጋየሁ ወደመጨረሻው የህይወት ዘመኑ በግልፅ አውጥቶ በማይናገራቸው ጉዳዮች ይበሳጭ እንደነበርና አብዝቶ የመጠጣት ችግርም አጋጥሞት እንደነበር ይነገራል። በመጨረሻም ኅዳር 6 ቀን 1982 ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ፡፡
[ማሳሰቢያ ፡ ‹‹አንተ›› እያልኩ የፃፍኩት ይህን ታላቅ የጥበብ ሳው ክብር ለመንፈግ ፈልጌ እንዳልሆነ ይታወቅልኝ!]
3). የሻዕቢያ መንግሥት መቐለ ከተማ ውስጥ፣ በአይደር ት/ቤት ተማሪዎች ላይ በአውሮኘላን ቦምብ በመጣል በርካታ ሕፃናትን የገደለው ከዛሬ 22 ዓመታት በፊት (ግንቦት 28 ቀን 1990 ዓ.ም) ነበር፡፡
ነፍስ ይማር!
4). አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በተለምዴ ሰይጣን ቤት እየተባለ በሚጠራው ትያትር ቤት በተፈጠረ ግፊያና መጨናነቅ 14 ሕፃናት የሞቱት ከዛሬ 20 ዓመታት በፊት (ግንቦት 28 ቀን 1992 ዓ.ም) ነበር፡፡
ነፍስ ይማር!
ምንጭ:-
           ፡ ልዩ ልዩ ጽሑፎች)
Filed in: Amharic