>
11:42 am - Tuesday January 26, 2021

ከታሳሪ ጋዜጠኞች፣ ጦማሪና አሕመዲን ጀበል ጋር በቂሊንጦ የነበረኝ ቆይታ [ጋዜጠኛ ኤሊያስ ገብሩ]

‹‹እኛ ታስረንም፣ በኢትዮጵያ ጋዜጠኝነት እና ጋዜጠኞች ላይ የሆነው ነገር እጅግ ቅስም ይሰብራል (It’s really heart breaking!)››
ጋዜጠኛ ተስፋለም ወልደየስ
‹‹እስር ደግም ነገር ነው›› ጋዜጠኛ አስማማው ኃ/ጊዮርጊስ
‹‹የነጻነት ትግል ላይ እንዳለሁ ያወኩት እስር ቤት ነው›› ጦማሪ ናትናኤል ፈለቀ
‹‹መጽሔቶች መታተም መቆማቸው ያሳዝናል፡፡ አማራጩ ምን ይሆን?››
አህመዲን ጀበል (የሙስሊሞች ጉዳይ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባል) 
—————————————————————————-
ከትናንት በስትያ፣ ሰኞ ነሐሴ 26 ቀን 2006 ዓ.ም በጣም የናፈቁኝን ታሳሪ ጋዜጠኞች እና ጦማሪያን ለመጠየቅ በማቀድ፣ ረፋድ ላይ ወደቂሊንጦ እስር ቤት አመራሁ፡፡ በቃሊቲ ወህኒ ቤት ዋና በር ጋር በታክሲ ሳልፍ፣ ጋዜጠኛ ርዕዮት አለሙ እና ኤዶምን ካሳዬ፣ ጦማሪ ማህሌት ፋንታሁንን፣ አቶ አንዷለም አራጌን፣ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋንና ሌሎች የማውቃቸውን እስረኞች በሀሳቤ መጥተው ነበር፡፡
ከታክሲ ተወርዶ ወደቂሊንጦ የሚወስደው መንገድ፣ አስፋልት ሆኖ ማግኘቴ በመጠኑም ቢሆን አስደስቶኛል፡፡ በፊት የቀድሞ የአውራምባ ታይምስ ጋዜጣ ባልደረባችንን ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬን ሰብሰብ በማለት ለመጠየቅ ወደቂሊኒጦ በጋሪ ተጭነን ስንሄድ ከአስቸጋሪ መንገዱ ላይ የሚቦነውን አቧራ አይጣል ነው፡፡ 
Tesfalem by Elias Gebruበከሰዓት በኋላ የመጠየቂያ ጊዜ፣ አነስተኛ ሰልፍ እና የተለመደ ፍተሻን አልፌ በአንድ ዞን ውስጥ ታስረው የሚገኙትን ጋዜጠኛ ተስፋለም ወልደየስ፣ አስማማው ኃ/ጊዮርጊስና ጦማሪ ናትናኤል ፈለቀን አስጠራኋቸው፡፡ ‹‹እስረኞች ስብሰባ ላይ ስለሆኑ ትንሽ ጠብቁ›› የሚል መልዕክት ከፖሊሶች አደመጥን፡፡ ከ15 ደቂቃ በኋላ ሶስቱም በአንድነት እኔ ወዳለሁበት መጠየቂያ ቦታ መጡ፡፡ ተስፋለም እና አስማማው በእጃቸው ተለቅ ባለ የፕላስቲክ ዕቃ ትኩስ ነገር እየጠጡ ነበር፡፡ በሽቦ ውስጥ አሳልፌ መጀመሪያ ተስፋለምን ጨበጥኩት፡፡ አስማማውን እየጨበጥኩት ባለበት ቅጽበት ተስፋለም ‹‹አንተ፣ አልተሰደድክም? ለምንድን ነው ያልተሰደድከው?›› በማለት በሳቅ የታጀበ ግን ጠንከር ያለ ጥያቄ አቀረበልኝ፡፡ አስማማው ፈጠን አለና ‹‹ተስፋለም፣ መጀመሪያ ሰላምታ ነው የሚቀድመው፡፡ ይሄ በኋላ መጠየቅ እና ማውራት የምንችለው ነገር ነው›› በማለት ተናገረው፡፡ ተስፋለምም ሳቅ እያለ ‹‹አይደለም፣ አይደለም …መጀመሪያ ሂሱን መዋጥ አለበት›› የሚል ምላሽ ለአስማማው ሰጠው፡፡ ….ናቲን ከጨበጥኩት በኋላ ‹‹ምን ይምጣልህ? ለስላሳ ወይስ ቡና?›› አሉኝ – በጋራ፡፡
‹‹ምንም አልፈልግም››
‹‹ለምን?›› 
‹‹እስከአሁን ቁርስ እንኳ አልበላሁም››
ተስፋለም በድጋሚ ‹‹ለምን?›› አለ፡፡
‹‹ጠግቤ ከበላሁ ብዙ እናገራለሁ፡፡ ስለዚህ እኔ ትንሽ እንድናገር፣ እናንተን ደግሞ ብዙ እንዳዳምጣችሁ ነው እስከአሁን ያልበላሁት›› ስላቸው ሶስቱም ሳቁ፡፡
‹‹ቡናችን አሪፍ ነው፤ በናትህ ጠጣ?›› ሲሉኝ ‹‹እሺ›› አልኳቸወ፡፡ ናቲ ሄዶ ያመጣልኝን ቡና ያዝኩና ከእነሱ ጋር ተመሳሰልኩ፡፡ 
…ከተስፋለም ባህሪ አኳያ አንድ ጥያቄ ጠይቆ መልስ ካልተሰጠው ጥያቄውን እንደማይተወው ከልጅነት ጀምሮ አውቃለሁ፡፡ ‹‹ቡናችንን እየጠጣህ የጠየኩህንም መልስልኝ›› አለኝ፡፡ በአሁን ወቅት የተፈጠረው ነገር ተከትሎ የሚሰማኝን እና ነፍሴ በስሜት ቋንቋ፣ በእውነት የምትለኝን በግልጽ ነገርኩት፡፡ የትምህርት ዕድል ኖሮ፣ ከሀገር ውጭ ተምሮ በመመለስ፣ በአቅሜ ለሀገር የሚጠቅም ሥራ መስራት እንደምሻ ተስፋለም ከድሮም ያውቃል፡፡ …ነገር ግን፣ አሁን ነጻ ፕሬሶች ላይ በተፈጠረው ሁነት እና መንግሥት ፕሬሶቹ እንዲዳፈኑ፣ እንዲሁም ጋዜጠኞች እንዲሰደዱ የቀለሰው መንገድ በጣም እንዳናደደኝ ጨምሬ ለተስፋለም አስረዳሁት፡፡ 
[በሀገራቸው ላይ የሚወዱትን የጋዜጠኝነት ሥራ መስራት እንዳይችሉ ተደርገው፣ ትናንትም ሆነ ዛሬ በተለያዩ ጫናዎች ሳቢያ ከሀገር ወጥተው የሚገኙ አቅም ያላቸውን ጋዜጠኞች ባሰብኩ አዝናለሁ፡፡ በሀገር ውስጥ ኖረንም የምንወደውን ሙያ በአግባቡ መስራት ያልቻልን ጋዜጠኞችንም እመለከትና ተስፋ ባልቆርጥም በቁጭት መብስለሰሌ አልቀረም፡፡ የዛሬዋ ኢትዮጵያ በተለይ በጋዜጠኝነት ሕይወት ውስጥ ተኩኖ ስለነገ ማለም እና ማቀድ እጅግ አዳጋች ነው – ምን እንደሚፈጠር ማወቅ ስለሚከብድ!] 
…ሶስቱም በግል ፕሬሶች ላይ በተፈጠረው ነገር አዝነዋል፡፡ በተለይ አስማማው የሆነ ነገር ተሰምቶት ለተወሰኑ ደቂቃዎች ወደመሬት አቀርቅሮ ተከዘ፡፡ የተሰማውን ደስ የማይል ስሜት በውስጡ ለመያዝ እንጂ ለእኛ ሊያጋራን አለመፈለጉን ተረድቼዋለሁ፡፡ 
Journalist Tesfalem by Elias Gebiru 1….አራታችንም በየተራ ስለሀገራቸው ያለፈ እና ወቅታዊ የጋዜጠኝነት የሙያ ሁኔታ፣ ስለስደት ጥቅም እና ጉዳት፣ ‹‹እስር ለውጥ አምጥቷል ወይስ አላመጣም›› በሚሉ ርዕሰ ጉዳዮችና ለችግሮቹ ‹‹መፍትሄ ይሆኑ ይሆናል›› ባልናቸው ጉዳዮች ላይ ከ30 ደቂቃ በላይ ደስ በሚል ሁኔታ ሃሳቦችን ተለዋውጠናል፡፡ በመሃል በመሃል የነበሩ ክርክሮችም መሳጭ ነበሩ፡፡ ይህቺን ክርክር “mini editorial meeting” ብያታለሁ፡፡ በስሜት ውስጥ ሆነን፣ ድምጻችንን ከፍ ስንነጋገር ከጎን ያሉ ተጠያቂዎችንና ጠያቂዎችን ትኩረት መሰረቁም አልቀረ፡፡
‹‹እናንተ ግን እንዴት ናችሁ?›› አልኳቸው፡፡ ‹‹እንደምታየን በጣም ደህና ነን፡፡ እስሩንም ለምደነዋል፡፡›› በማለት በፈገግታ መለሱልኝ፤ ሳቃቸው ደስ ይላል፡፡ አንድ ላይ በመሆናቸው ደስተኞች ናቸው፡፡ …አስከተልኩና ‹‹ከተስፋለም ጋር፣ ያኔ ልጅ እያለን፣ ሁለታችንም አንዲት ልጅን በዓይን ፍቅር ወድደናት ነበር›› አልኳቸው – አስማመውንና ናቲን፡፡ መካከላቸው ሆኖ ትከሻቸውን አቅፏቸው የቆመውን ተስፋለምን አዩትና ሳቁ፡፡
ሳቅ ቅርቡ የሆነው ናቲ ‹‹አሁን ቀሽት ጨዋታ መጣ›› አለ፡፡ ተስፋለም ‹‹አንተ ረስቼው ነበር፤ አስታወስከኝ›› አለኝ፡፡ ‹‹እና የማን ሆነች?›› በማለት ሁለቱ ጥያቄያቸውን ሰዝንዘረው አንዴ እኔን አንዴ እሱን ማየት ጀመሩ፡፡ …ያኔ፣ ተስፋለም እኔን ተደብቆ እሷን ለማየት እና ለማግኘት ይሄዳል፡፡ እኔም እሱን ተደብቄ እንደዛው፡፡ ብዙ ቀናት በድብብቆሽ ተጓዝን፡፡ አንድ ቀን ግን ሳይታሰብ፣ ሶስታችንም አንድ ቦታ ላይ ተፋጠጥን፡፡ …እኔና ተስፋለም ያለፈው የልጅነት ትዝታን በማስታወስ፣ ሳቃችንን በውስጣችን አፍነን፣ ናቲና አስማማውን በዝምታ አለፍናቸው፡፡ ዋይ! ከተስፍሽ ጋር በጨዋታ፣ በቁምነገር፣ በመማማር፣ በክርክር፣ …ደስ የሚል የልጅነት ሕይወት አሳልፈናል፡፡
በእስር ላይ ሆኖም ጥያቄ መጠየቅ የማያቆመው ተስፋለም፣ ‹‹ተቃዋሚ ፓርቲዎች እንዴት ናቸው?›› ሲል ሌላ ጥያቄ ሰነዘረ፡፡ በአሁን ወቅት ያሉ አዳዲስ መረጃዎችን አጠር አድርጌ ነገርኩት፡፡ የአንድነት እና የመኢአድ ውህደት እስከአሁን አለመፈጸሙን ከማውቃቸው ምክንያቶቹ ጋር ገለጽኩለት፡፡ አንድነት ፓርቲ ውስጥ ውስጣዊ ሽኩቻ መፈጠሩን፣ ይህንንም ተከትሎ የበፊት ሥራ አስፈጻሚ አባላት በኢንጂነር ግዛቸው ሽፈራው አመራር ደስተኛ ባለመሆን በገዛ ፈቃዳቸው ከለቀቁ በኋላ ሌሎች በቦታቸው መተካታቸውንም ስነግረው ‹‹ዳንኤል ተፈራም ለቀቀ?›› በማለት ሌላ ጥያቄውን አስከተለ፡፡ ‹‹አዎ፣ ከሥራ አስፈጻሚ አባልነት ራሱን አግልሏል›› አልኩት፡፡ ‹‹እንደጋዜጠኛ ሳይሆን እንደኢትዮጵያዊ ዜጋ ዳንኤል ጎበዝ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ለዚህች ሀገር ፖለቲካ ያስፈልጋታል ብዬ ተስፋ የምጥልበት ልጅ ነው፡፡›› በማለት በጣም ማዘኑን ተናገረ፡፡
Ahmedin Jemil by Elias Gebriru….የሙስሊሞች ጎዳይ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ የሆነው አሕመዲን ጀበል ጠያቂዎቹ ያመጡለትን ምግብ ወደክፍሉ ለማድረስ እየሄደ እያለ ‹‹አህመዲን›› ብሎ ተስፋለም ጠራው፡፡ አየን፡፡ በርቀት ሰላም አልኩት፡፡ ‹‹ተመልሼ እመጣለሁ›› ብሎ ከአፍታ በኋላ መጣ፡፡ ሞቅ ያለ ሰላምታ ተለዋወጥን፡፡ ጥንካሬ፣ ፈገግታና ግርማ ሞገስ በግልጽ ይንቀባርቅበታል፡፡ ከወራቶች በፊት ቃሊቲ ካየሁት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ሳገኘው ነው አህመዲንን፡፡ ‹‹ከመያዛችሁ በፊት የሰጣችሁንን ቃለ-ምልልስ አስታወስክ›› አልኩት፡፡ ‹‹አዎ አለኝ›› ፈገግ እያለ፡፡ እነአህመዲን በፖሊስ ከመያዣቸው አንድ ቀን ቀደም ብሎ፣ ካሉበት ቦታ ሆነው ፍትህ ጋዜጣ ላይ ለእኔ እና ለኃይለመስቀል በሸዋምየለህ ነበር ሰፊ ቃለ-ምልልስ የሰጡን፡፡ ይህንን ወቅታዊ ዘገባ አጠናቅረን ህትመት ከገባን በኋላ ከአቶ መለስ ሞት ጋር በተያያዘ የሰራነው የዜና ዘገባ በፌዴራል አቃቢ ሕግ የጋዜጣው ህትመት እንዳይሰራጭ ለማድረግ የእግድ ክስ በፍርድ ቤት አቅርቦ ተቀባይነት ካገኘ በኋላ በወቅቱ 30ሺህ ኮፒ የታተመችው ፍትህ ጋዜጣ እንድትቃጠል ሲደረግ፣ የእነ አህመዲን ጀበልና ሁለት የኮሚቴው አባላት የመጨረሻ ቃል ለአንባቢን መድረስ ሳይችል ቀርቷል፡፡ ይህ ዛሬም ድረስ ያሳዝነኛል፡፡
አህመዲን ‹‹ሕትመቶች ቆሙ አይደለ?›› በማለት ጠየቀኝ፡፡ ‹‹አዎን›› አልኩት፡፡ 
‹‹ቅዳሜ ፋክት አልወጣችም?›› 
አልወጣችም፡፡ 
‹‹መጽሔቶች መታተም መቆማቸው ያሳዝናል፡፡ አማራጩ ምን ይሆን?›› በማለት ጥያቄውን በአዘኔታ ገለጸ፡፡ አህመዲንን ብዙ ጠያቂዎች እየጠበቁት ስለነበረ ‹‹ተጫወቱ›› በማለት በድጋሚ ሰላምታ ሰጠን፡፡ ፈገግታ እና ጥንካሬው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋን አስታወሰኝ፡፡ ‹‹አይዞን!›› አልኩት፡፡ በእጁ የእሺታ ምልክት ሰጠኝና ሄደ፡፡ 
ወደጋዜጠኞቹ እና ጦማሪያኑ ተመለስኩ፡፡ ‹‹እናንተ ለድምጽ አልባዎች ድምጽ የነበረችሁ ልጆች ብዙ ሀሳብ፣ የመስራት አቅም፣ ብቃትና ተነሳሽነት እያላችሁ እዚህ እስር ቤት ሳይችሁ በጣም እያዘንኩ ነው፡፡›› አልኳቸው፡፡ ‹‹እንግዲህ ምን ታደርገዋለሁ፡፡ ከእኛ በላይ የምታሳዝነን ግን ሀገራችን ነች፡፡›› የሚል ተቀራራቢ ምላሽ ሰጡኝ፡፡
በመጨረሻ፣ ‹‹እስኪ ለሚያከብሯችሁ፣ ለሚወዷችሁ፣ ለሚያደንቋችሁ …ሰዎች በሙሉ የየራሳችሁን አጠር ያለ መልዕክት ንገሩኝ›› የሚል ጥያቄ አቀረበኩላቸው፡፡
ናቲ ፈጠን ብሎ ‹‹እኔ ሕገ-መንግሥቱን አከብራለሁ፡፡ እሱም ከለላ ይሆነኛል ብዬ በማመን ነበር ስንቀሳቀስ የነበረው፡፡ ከእስር በኋላ ግን ሕጉ ከላላ ሊሆነኝ እንዳልቻለ ተረድቻለሁ፡፡ በምርመራ ወቅት ከመርማሪዎች ጋር መግባባት በጣም አዳጋች ነበር፡፡ አንተ ሥራህን እየሰራህ ስትጓዝ ‹‹መስራት የምትችለው እስከዚህ ድረስ ብቻ ነው›› ብሎ የሚወስንብህ አካል አለ፡፡ …‹የነጻነት ትግል ላይ እንዳለሁ ያወኩት እስር ቤት ነው፡፡›› አለኝ፡፡
ተስፋለም ደግሞ እንዲህ በማለት ቀጠለ፡- ‹‹እኛም ታስረንም፣ በኢትዮጵያ ጋዜጠኝነት እና ጋዜጠኞች ላይ የሆነው ነገር እጅግ ልብ ይሰብራል (It’s really heart breaking!)፡፡ የጋዜጠኝነት ታሪክን በአሜሪካም ሆነ በአውሮፓ በተለያዩ ችግሮች ውስጥ አልፎ ነው ለዚህ የደረሰው፡፡ በሀገራችን ገና ለማደግ ዳዴ እያለ ያለ ነጻ ፕሬስን በእንጭጩ እንዲቀር ማድረግ ተገቢ አይደለም፡፡ የተለያዩ አመለካከቶች በሚዲያ መንሸራሸር አለባቸው፡፡ ያ እንደሀገር ይጠቅመናል እንጂ አይጎዳንም፡፡ ‹አንድን አመለካከት ብቻ አንብቡ፣ ተመልከቱ!› ማለት ተገቢነት የለውም፡፡ የግል ፕሬሶች ከችግር የጸዱ ናቸው እንደማይባል ግልጽ ነው፡፡ ነገር ግን ችግሮች ያሏቸውን ነገሮች በማጉላት በዘጋቢ ፊልም አማካኝነት የግል ፕሬሶችን ለማሳጣት መሞከር በጣም አሳዛኝ ነው፡፡ በኢቴቪ (አሁን ኢቢሲ ተብሏል) ሕትመት ዳሳሳ ላይ እነታደሰ ሚዛን ያቀረቡትን ፕሮግራም ተመልክቼ እፍረት ተሰምቶኛል፡›› ካለ በኋላ … 
‹‹የተሰደዳችሁ ጋዜጠኞች ስለእናንተ ይሰማኛል፤ አዝኛለሁ፡፡ ባላችሁበት ሀገር ሁለትም ሶስትም ሆናችሁ በመሰባሰብ ከሙያችሁ ሳትርቁ ጋዜጠኝነትን ብትሰሩ እና ለወገናችሁ ሚዛናዊ ሥራዎችን ብታቀርቡ በጣም ደስ ይለኛል፡፡ ከተሰደደም በኋላ የግል ኑሮውን ብቻ ለመቀየር የሚንቀሳቀስ ጋዜጠኛም አይጠፋም፡፡ ከሀገር ከተሰደዱ በኋላ የጋዜጠኝነት ሥራ ውስጥ ገብተው መስራት የቻሉትን ጋዜጠኞች እንደጥሩ ምሳሌ እወስዳቸዋለሁ፡፡ እባካችሁ፣ በሙያችሁ ለመሥራት ጣሩ! እኔም በበአንድ ወቅት ኡጋንዳ ውስጥ የጋዜጣ ስራን ሞክሬው እውቃለሁ፡፡ 
በሌላ በኩል ደግሞ በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ ውስጥ በሀገራችሁ የምትገኙ ጋዜጠኞችን አከብራችኋለሁ፣ አደንቃችኋለሁ፡፡ በሙያችሁ መስራት የምትችሉበት ሁኔታ እንዲፈጠር ከልብ እሻላችኋለሁ፡፡››
አስማመውም ተከታዩን አከለ፡- ‹‹እኔ ጋዜጠኛ እንጂ ታጋይ አይደለሁም፡፡ በተቻለ አቅም ሚዛናዊ ሥራዎችን ከባልደረቦቼ ጋር ‹‹በአዲስ ጉዳይ›› መጽሔት ላይ ስሰራ ቀይቻለሁ፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ የተወሰነ ወገን ስራህን አይቶ ‹‹ጥሩ ነው፣ በርቱ›› ሲልህ፣ አንዳንዱ ደግሞ ያለበቂ ምክንያት ‹‹የጭቆና አራዛሚዎች›› በማለት ይፈርድብሃል፡፡ በመንግሥት በኩል ደግሞ እንደ ጥፋት ሃይል ተቆጥረህ በአዲስ ዘመን ገጽ 3 ላይ ተደጋጋሚ ውንጀላዎች በተለያዩ ጊዜያቶች እየቀረቡብን ሁሉንም ችለን ሰርተናል፡፡ በዘላቂነትም ለመስራት አልመን ነበር፡፡ እንግዲህ የሆነውን አይተናል፡፡ …በእኔ በኩል እስር ደግም ነው እለላሁ፡፡ እስር መጥፎ ነገር እንዳለው ሁሉ ጥሩ ነገርም አለው፡፡ ብዙ ነገር ታያለህ፣ ትረዳለህ፣ ታሰላስላለህ፣ ለሀገርህ ይበልጥ ታስባለህ፡፡›› 
የጋራ ቃላችን ነው በማለት ደግሞ ሶስቱም እንዲህ የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ ‹‹ከታሰርን ጀምሮ እስከአሁን ድረስ ስለእኛ ያሰባችሁ፣ በተለያዩ ነገሮች ከጎናችን የቆማችሁ፣ በአካል በታሰርንባቸው ቦታዎች እና በፍርድ ቤት ድረስ በመገኘት የጠየቃችሁን እና ያበረታታችሁን በሙሉ፣ በአካል ከእኛ እርቃችሁም ስለእኛ ለምታስቡ በሙሉ እጅግ የከበረ ምስጋና ሰጥተናችኋል፡፡ እናመሰግናችኋለን፡፡ እናከብራችኋለን፡፡ እኛ ደህና ነን፤ በርትተናል!›› 
….ጸሐያማ የነበረው የቂሊንጦ አከባቢ አየር በአንዴ ወደዝናብ ተቀየረ፡፡ ፖሊሶች ለሁሉም ተጠያቂዎችና ጠያቂዎች ‹‹ጨርሱና ተሰነባበቱ›› የሚል ትዕዛዝ ሰጡ፡፡ ከሶስቱም ጋር መሰነባበበታችን ግድ ሆነ፡፡ ናቲ እንደኔው ሁሉ የሊቨርፑል ደጋፊ በመሆኑ ‹‹ዘንድሮ ባላቶሊ አለ፤ ድሉ የእኛ ነው›› አልኩት፡፡ እጄን በእጁ ገጨት አደረገና ‹‹cheers! ግን ቸልሲ ከአጀማማሯ አልተቻለችም፤ አስፈሪ ነች›› አለኝ በፈገግታ ተሞልቶ፡፡ ከሁለት ሰዓታት ቆይታ በኋላም ቻው ብዬ ተለየኋቸው፡፡
መውጪያው በር ላይ ደርሼ ወደኋላ ዞሬ ስመለከታቸው ተስፋለም ዝናቡን ለመከላከል የሹራብ ጃኬት ኮፍያውን ጭንቅላቱ ላይ አድርጎ እሱም ዞሮ እኔን ሲያየኝ አይን ለአይን ተገጣጠምንና ዳግም ቻው ለመባባል እጃችንን ከፍ አድርገን አውለበለብን፡፡ 
ከቂሊንጦ መልስ ወደሳሪስ ታክሲ ለመያዝ ቆምኩ፡፡ ዝናቡ ይወርዳል፡፡ ጉርድ ሸሚዜ በዝናቡ ርሷል፡፡ አንዲት ቆንጆ ሙስሊም (እስረኛ ጠያቂ) ከጎኔ ሆና በዠንጥላዋ ነካ አደረችኝና ‹‹በጋራ እንጠቀም፤ ቁመትህ ረዥም ነው፡፡ ያዘው›› አለችኝ፡፡ መልካምነቷ አስገረመኝ፡፡ አብረን ታክሲ ያዝን፡፡ ዝናቡ በጣም ከባድ ነው፡፡ የቴዲ አፍሮ አዲሱ ዘፈን ‹‹ሰባ ደረጃን›› እየሰማን ሳሪስ ደረስን፡፡ ሰዓቴን አየሁት 11፡00 ሰዓት አልፏል፡፡ ‹‹ከነጋ ምግብ አልበላሁም፤ በጣም ርቦኛል፤ አብረን እንብላ›› አልኳት፡፡ … በጨዋታም ሂደት በሙስሊሞች የመብት ጥያቄ ላይ ጠንካራ አቋም ያላት ወጣት ሆና አገኘኋት፡፡ 
የተከበራችሁ ወዳጆቼ ሰላም ሁኑልኝ!

Filed in: Amharic