>
5:13 pm - Saturday April 19, 6623

ደራሲው ዲፕሎማቱ  ብላቴን ጌታ ኅሩይ  ወልደ ሥላሴና  በጥረት የተገኘ ታላቅነታቸው!!! (ታደለ ገድሌ ጸጋየ (ዶ/ር)

ደራሲው ዲፕሎማቱ  ብላቴን ጌታ ኅሩይ  ወልደ ሥላሴና  በጥረት የተገኘ ታላቅነታቸው!!! 

ታደለ ገድሌ ጸጋየ (ዶ/ር)

       በኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ ታሪክ ታላቅና ግዙፍ አስተዋጽኦ ያላቸው ደራሲ፤ታሪክ አዋቂ፤የታወቁ ዲፕሎማት፤በቤተ ክህነት ትምህርትና በቋንቋ የተካኑ፤ ባለቅኔ፤ገጣሚ፤የዘመናቸውን ዕውቀት የቀሰሙ ምሁር፤ በአኗኗራቸው  በምሳሌነት የሚታዩና ሠርተው የማይደክሙ ኢትዮጵያዊ ናቸው ፡፡እኒህ ሊቅ ብላቴን ጌታ ኅሩይ  ወልደ ሥላሴ ይባላሉ፡፡ ከአባታቸው ከአቶ  ወልደ ሥላሴና ከእናታቸው ወይዘሮ ወለተ ማርያም ዜና የተወለዱት ግንቦት 1 ቀን 1871 ዓ ም በቀድሞ አጠራሩ በመርሐ ቤቴ አውራጃ በታች ቤት ወረዳ ረመሸት ቀበሌ ደን አቦ ገዳም በተባለ ሥፍራ ሲሆን ያረፉት ደግሞ መስከረም 9 ቀን 1931 ዓ ም እንግሊዝ አገር ባዝ በተባለው ቦታ በስደት ላይ እያሉ ነው:: ብላቴን ጌታ ኅሩይ ለቤተ ሰቦቻቸው የመጀመሪያ ልጅ ሲሆኑ አባትና እናታቸው ከእርሳቸው ቀጥሎ በተከታታይ ሁለት ሴት ልጆችን ወልደዋል፡፡ሲወለዱ የወጣላቸው ስም ገብረ መስቀል የሚል ነው፡፡ ምናልባትም የክርስትና ስማቸው ሊሆን ይችላል፡፡ይህም የመስቀል ባሪያ አገልጋይ፤ ጽሙድ እንደማለት ነው (ካፕላን፡2007፤21)፡፡
        ክቡር  ብላቴን ጌታ ኅሩይ  የተወለዱበትን የደን አቦ ገዳም ቤተ ክርስቲያን ያሠሩትና የበላይ ጠባቂ ሆነው ያስተዳድሩት የነበሩት የዳግማዊ ምኒልክ የቀድሞ  ሁለተኛ ሚስታቸው ወይዘሮ ባፈና ነበሩ፡፡በዚህ ረገድ ወይዘሮ ባፈና የብላቴን ጌታ ኅሩይን አባት አቶ ገብረ ሥላሴን የገዳሙ አስተዳዳሪና የቤተ ርስት ሹም አድርገው አስቀምጠዋቸው ነበር፡፡አቶ ገብረ ሥላሴም ሸዋ ውስጥ በመርሐ ቤቴ አገሪት በተባለች ቦታ መንዝ ውስጥ ቢያድጉም ቤተ ሰቦቻቸው ከወሎ አማራ ሳይንት የመጡ ናቸው፡፡እናም አባታቸው እናታቸውን ያገቡት የ40 ዓመት ጎልማሳ እያሉ ሲሆን ወይዘሮ አመተ ማርያም ዜና በመንዝ ጠል በተባለው ቦታ የማደሬ ቤተሰብ ተወላጅ ናቸው፡፡ከሸዋው ንጉሥ ከሣህለ ሥላሴ እናት ከወይዘሮ ዘነበወርቅ ጋርም ወይዘሮ አመተ ማርያም ይዛመዳሉ፡፡
       ከዕለታት አንድ ቀን አቶ ወልደ ሥላሴ የገዳሙን ካህናትና ዲያቆናት ግብር ለማብላት ዝግጅት ባደረጉ ጊዜ የገዳሙ አለቃ ለጊዜው በቦታው ላይ ባለመገኘታቸው ካህናቱ በረሀብ ይንገላታሉ፡፡ ይህንን ያስተዋሉት የቤተ ርስቱ ሹም አቶ ወልደ ሥላሴ የገዳሙ አለቃ የድርሻቸው ምግብ ተቀምጦላቸው አገልጋይ ካህናቱ እንዲመገቡ ያደርጋሉ፡፡በመኻል የደብሩ አለቃ  ድግስ እየተበላና እየተጠጣ ከች ይላሉ፡፡ በዚህ ጊዜ በቁጣ ንግግር « በቃ የገዳሙ ባህል ፈረሰ ፡፡እንዴት እኔ ሳልመጣ  ሌሎቻችሁ ማእድ ትቆርሳላችሁ? ይህንን የሚያደርግ መቼም ወልደ ሥላሴ እንጂ ሌላ አይደለም፡፡ ወይዘሮ ባፈና  ያልተማረ ጨዋ ሾመው ይኸው ይጫወትብናል » በማለት ከተናገሩ በኋላ ወደ ካህናቱ ዞረው « እንዴትስ በሌለሁበት ግብር ትበላላችሁ?» በማለት ይገስጹዋቸዋል፡፡
       አቶ ወልደ ሥላሴም ጠቡንና ክርክሩን ያበረድሁ መስሏቸው « ካህናቱ በደጅ ቆመው በፀሐይ ሙቀት ስለተጉላሉ እርስዎም እንደደረሱበት  ገብተው ግብር እንዲቀመጡ ያደረግሁ እኔ ነኝ፡፡ የእርስዎም ፋንታ በክብር ተቀምጦዋል፡፡ እና እባክዎን ይቀመጡና ይጋበዙልን » በማለት በትሕትና ይለምኗቸዋል፡፡የደብሩ አለቃ ግና ባለመረጋጋት ነገሩን አክርረው « ካልተማረ መሐይም ምን ይጠበቃል? ቆይ ለወይዘሮ ባፈና ነግሬ ከሹመትህ ባላሽርህ እኔ ሰው አይደለሁም» ብለው የተቀመጠላቸውን ምግብ  መኮምኮምና ጠላቸውንም መጎንጨት ይጀምራሉ፡፡ አቶ ወልደ ሥላሴም በደብሩ አለቃ ንግግር ተበሳጭተው ነበርና «መቼም እኔ ከእንግዲህ ተምሬ አልደርስም፡፡ልጀ እንደኔ እንዳይሰደብ እርሱን ማስተማር አለብኝ  »በማለት ወሰኑ(ኅሩይ ኢትዮጵያ ታሪክ 1999፤10) ፡፡
       በዚህ ዓይነት ልጃቸው ገብረ መስቀል የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ለመማር እንዲችሉ በሰባት ዓመታቸው አባታቸው መርሐ ቤቴ ሥላሴ ወስደው ከነስንቃቸው ጭምር ለመምህራኑ አስረክበዋቸዋል፡፡የመጀመሪያው መምህራቸውም ደብተራ ሥነ ጊዮርጊስ ይባላሉ፡፡በሁለት ዓመት ውስጥ በግእዝ ለማንብባና ዳዊት ለመድገም ችለዋል፡፡ከችሎታቸው የተነሣም ኅሩይ ለአባታቸው ጠቃሚ ልጅ ሆነው ታዩ፡፡በዚህም ልጃቸው በበለጠ እንዲማር ከፍተኛ ፍላጎት ስለአደረባቸው ኅሩይ 10 ዓመት ሲሆናቸው በዘመኑ ታላቅ ወደነበረው ስሬ መድኃኔዓለም መንፈሳዊ ትምህርት ቤት  ወስደው አስገቡዋቸው፡፡ በዚህ ዓይነት የቤተ ክህነቱን ልዩ ልዩ ከፍተኛ ትምህርት ሲማሩ ቆይተው በዜማ ትምህርት እስከመምህርነት ደረጃ አጠናቀቁ፡፡የመጻፍንም  ልምድ ከተለያዩ ዕፀዋትና ጥላሸት ቀለም በጥብጠው ከሚገለብጡት ከብራና መጻሕፍት ቀለማት ለማወቅ ችለዋል፡፡ስሬ መድኃኔዓለም በትምህርት ከሚያተጉዋቸው አባታቸው ጋር በነበሩበት የመጀመሪያ ዓመታት ከፍተኛ የሆነ የምግብ ችግር ደርሶባቸዋል ( ሞልቪየር 1997፡3)፡፡በኋላ ግን ችግራቸውን የተረዱትና የስሬ መድኃኔ ዓለም የበላይ ጠባቂ የነበሩት  ወይዝሮ ፀሐየ ወርቅ ዳርጌ ቋሚ የሆነ ጥቂት የምግብ አቅርቦትና ጥቂት ዓመታዊ የኪስ ገንዘብ መድበውላቸው ነበር፡፡
       በዚህ ዓይነት አባትና ልጅ  አብረው ለሁለት ዓመታት ከቆዩ በኋላ ወልደ ሥላሴ ወደ ታላቁ ገዳም ደብረ ሊባኖስ ሄደው በምንኩስና መኖር ጀመሩ፡፡በኋላ በ53 ዓመታቸው እንደገና ወደ ልጃቸው ዘንድ ተመለሱ፡፡ወላጅ እናታቸው ልጃቸውን ኅሩይን አንድ ጊዜ እስከሚማሩበት ቦታ ድረስ ሄደው ቢጠይቋቸውም በኋላ ሊያገኙዋቸው አልቻሉም፤ ጠፉባቸው፡፡የአባ ወልደ ሥላሴም ጤና እየታወከ በመሄዱ እንደገና ወደ ደብረ ሊባኖስ ወርደው ጸበል ሲጠመቁ ከቆዩ በኋላ ልክ ኅሩይ 13 ዓመት ሲሞላቸው ዐረፉና እዚያው ደብረ ሊባኖስ ተቀበሩ፡፡ኅሩይ የአባታቸውን መቃብር ለማየት ወደ ደብረ ሊባኖስ በሄዱበት ሰዓት የአባታቸውን የንስሐ አባት አግኝተው ያባታቸውን ኑዛዜ ነገሩዋቸው፡፡ ይኸውም  ለኅሩይ በዚህ ዓለም ላይ ያለው ሀብት ትምህርት ስለሆነ ጠንክሮ ይማር፤ የማወርሰው ሀብትና ንብረት ስለሌለኝ ወደ ትውልድ ሀገራችን እንዳይመለስ የሚል ነው፡፡ከአባታቸው በተቀበሉት ኑዛዜ መሠረትም ኅሩይ የቤተ ክህነቱን ልዩ ልዩ የትምህርት ዓይነት አጠናቅቀው በዜማ ትምህርት እስከ መምህርነት ደረጃ ደርሰዋል፡፡ከዚህ ደረጃ ላይ የደረሱትም ብዙ ችግሮችን በመቋቋም ነው፡፡
       ቀደም ሲል ይረዱዋቸው የነበሩት ወይዘሮ ፀሐየ ወርቅ ዳርጌ በሀገራችን በ1881 ዓ ም የተከሠተውን የከብት እልቂት ተከትሎ ረሀብ ስለ ገባ ለኅሩይ ይሰጡዋቸው የነበረውን የምግብና የኪስ ገንዘብ ድጋፍ ያቋርጡባቸዋል፡፡ አሁን የግድ ራሳቸውን ለማኖር ሲሉ በአደረጉት ጥረት ያያ በተባለው ቦታ የቤተ ክርስቲያን መሬት  ያስተዳድር ከነበረ አርሶ አደር ድጋፍ ለማግኘት ቻሉ፡፡በዚህ ጊዜ ኅሩይ በዲቁና ማዕርግ ሲያገለግሉ  የራሳቸው መተዳደሪያ የሆነች መሬትም አግኝተው ስለነበር ኑሯቸው ከሞላ ጎደል ጥሩ ሆነላቸው፡፡የተለያዩ የጽሕፈት ሥራዎችን በክፍያ ለሰዎች ይጽፉ ነበር፤እንዲያውም በዚህ ዓይነት ገቢያቸው ስለአደገ ፈረሰኛ ባይሆኑም አንድ ፈረስ ገዝተው ነበር፡፡ በዚህ ሁኔታ ስማቸው እየታወቀ ስለሄደ የሰላሌው ገዥ ደጃዝማች በሻህ ውረድ ጸሐፊ አስፈልጓቸው ነበርና ኅሩይን በጸሐፊነት ቀጠሯቸው፡፡ብዙም ሳይቆዩ የራስ መኮንን ወልደ ሚካኤል ዋና ጸሐፊ ለሆኑትና አዳበርጋ አጠገብ ሲኖ ከተባለው ቦታ ለሚኖሩት  ቀኛዝማች መቅረጭ አገልጋይ ሆኑ፡፡ኅሩይ በጸሐፊነት ባይቀጠሩም ቀኛዝማች መቅረጭ ችሎታቸውን ተመለከቱና የሆነው ፍሬ እያሉ ይጠሯቸው ነበር፡፡ከዚህም የተነሣ የመንግሥት ግብር በሚሰበሰብበት ሰዓት ኅሩይ ዋና ንብረት መዝጋቢ ሆነው ያገለግሏቸው ስለነበር በቀኛዝማች መቅረጭ ዘንድ እጅግ ተወዳጅ ሆኑ  (ዝኒ ከማሁ 1997፡3)፡፡
       ቀጥሎ ወደ አዲስ  አበባ እንጦጦ ራጉኤል ደብር መጥተው የመጻሕፍትን ትርጓሜ በዘመኑ ከነበሩ ሊቃውንት ዘንድ በመማር አጠናቀቁ፡፡በእንጦጦ የነበሩ አንድ ሊቅ መምህራቸው ስማቸውን በጠየቋቸው ጊዜ ገብረ መስቀል መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ሊቁም «ጎንደር በነበርሁ ጊዜ አስተማሪየ ስለወደዱኝ ኅሩይ እያሉ ይጠሩኝ ነበር፡፡ ወደ  አዲስ አበባ   ስመለስ ግን በቀድሞ ስሜ እየተጠራሁ ነኝ፡፡ስለዚህ አንተ የቀለም ቀንድ ስለሆንህና  በምግባርህም የተወደድህ በመሆነህ ኅሩይ የተባለውን ስሜን ትጠራበት ዘንድ ሸልሜሃለሁ» ይሏቸዋል፡፡በ1901 የራጉኤል የደብር አለቃና የዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ የጽሕፈት ሚኒስትር ጸሐፌ ትእዛዝ ገብረ ሥላሴ ወልደ አረጋይ ስለ ኅሩይ ዝና ከደብሩ ሊቃውንት ስለሰሙ ኅሩይንበጣም፡አቀረቧቸው፤ኅሩይንና፡ጓደኞቻቸውን፤በምሁርነታቸውናበብሩህነታቸው፤በትጋታቸው፤ በታማኝነታውና በመልካም ሥነ ምግባራቸው ፈጽሞ ወደዷቸው፤ አከበሯቸውም፡፡
       ከዳግማዊ ምኒልክ ፊት አቅርበውም አሸለሟቸው፡፡ዳግማዊ ምኒልክም የኅሩይን ልጅነት አይተው« እንዲያው ለቁጥር ማሙያ ከሊቃውንቱ ጋር አቅርበህ አሸለምከው እንጂ ገና ልጅ ነው፡፡ምን ሊያውቅ ይችላል ? ቢሏቸው  ጸሐፌ ትእዛዝም ‘ጃንሆይ እድሜው ነው እንጂ እውቀቱ ትልቅና ዘሊቅ ነው ’ብለው በመመስከር ንጉሠ ነገሥቱን አሳመኗቸው፡፡ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ኅሩይ በቤተ ክህነቱና በቤተ መንግሥቱ እየታወቁና እየገነኑ ስለመጡ ተወዳጅነታቸው በሁሉም ሰው ዘንድ ታወቀ፡፡
       ብላቴን ጌታ ኅሩይ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን የታወቁ ፖለቲከኛና በቤተክህነቱም ከፍተኛ ምሁር የነበሩ ሰው ናቸው፡፡ኅሩይ በጥንታዊና ዘመናዊ ትምህርት የተቀረጹ ሰው ነበሩ፡፡   ለዘመናዊ ትምህርትም ከአላቸው ጉጉት የተነሣ በኋላ ላይ አዲስ አበባ ስዊድን ሚሽን ትምህርት ቤት ገብተው የውጭ አገር ቋንቋ ማለት እንግሊዝኛ መማራቸው ስለውጭ ሀገራት የነበራቸውን አሰተሳሰባቸውን በበለጠ አሳድጎላቸዋል፡፡በተጨማሪም ከዶክተር ቻርለስ ማርቲን ወይም ከሐኪም ወርቅነህ ጋር ግንኙነት መመሥረታቸው ስለውጭ ሀገር ያላቸውን ዕውቀት ከፍ አድርጎላቸዋል፡፡ከእንግሊዝኛ በተጨማሪ በዐረብኛም የተለያዩ የትምህርት ዓይነቶችን ለመማር ጥረት አድርገዋል፡፡
       ነገር ግን በወቅቱ ኅሩይ እስላም ሆነ የሚለውን አሉባልታ ስለሰሙ የዐረብኛ ትምህርታቸውን ለማቆም ተገድደዋል፡፡ ቀጥለው ከፈረንሳይ የከብት ሕክምና ባለሙያዎች ፈረንሳይኛን ለመማር ችለዋል፡፡በተለይ የኅሩይን  ዕውቀት በበለጠ ያሳደገላቸው በተደጋጋሚ ወደ ውጭ ሀገራት ሲያደርጉት የነበረው ጎዞ ነው፡ለማለት ይቻላል፡፡ለአብነትም እኤአ በ1911 ከደጃዝማች በኋላ ልዑል ራስ ካሣ ኃይሉ ጋር በእንግሊዙ ንጉሥ በጆርጅ 5ኛ በዓለ ንግሥ ላይ ለመገኘት መቻላቸውና  በተደጋጋሚም ከኢትዮጵያ መንግሥት  ልዑካን ጋር እንግሊዝ ሀገር ደርሰው መመለሳቸው፤እኤአ በ1949 በመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ዘአሊያንስ ተብለው ይታወቁ የነበሩት  የቃልኪዳን ( የኅብረት ኃይሎች ) ስለአሸነፉ አሜሪካንን እንኩዋን ደስ አለሽ ለማለት ወደዚያው መጓዛቸው፤እኤአ በ1920 እና በ1923 ወደ ኢየሩሳሌም ማቅናታቸው፤እንደገና እኤአ በ1924 እና 1931 ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ጋር ወደ አውሮፓና ወደ ቻይና ደርሰው ለመመለስ በመቻላቸው፤ ለጥቂት ጊዜያትም በጃፓን የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሙሉ ሥልጣን ሚኒስትር( አምባሳደር) ሆነው መሥራታቸው ስለውጭ ሀገራት እድገትና ሥልጣኔ ይበልጥ ለማወቅ አስችሏቸዋል፡፡
       እኤአ በ1914/15 የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እንዲሆኑ በር የከፈተላቸው ራሳቸው የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ብለው ስም በአወጡለት መሥሪያ ቤት ዋና ጸሐፊና ኃላፊም ሆነው መሥራታቸው ነው፡፡እኤአ ከ1916 ጀምሮ የዲሬክተር ጀኔራልነት ማዕርግ አግኝተው አገልግለዋል፡፡እኤአ ከ1920-21 ድረስ ደግሞ የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ምክትል ከንቲባ ሆነው ሠርተዋል፡፡ቀጥሎ በዋና ኃላፊነትና በብላቴን ጌታ ማዕርግ የልዩ ፍርድ ቤት ዳኛ በመሆን አገልግለዋል፡፡ልዩ ፍርድ ቤቱ ይመለከትና ይመረምር የነበረው ርእሰ ጉዳይ የአገር ውስጥና የውጭ አገር ዜጎችን ክስ ነው፡፡«ብላቴን ጌታ» የሚለው ስመ ማዕርግ  ኅሩይ ከሚለው ስማቸው ጋር ተወራራሽነት አለው፡፡  ብላቴን ጌታ  ኅሩይ እኤአ በ1927 በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዲሬክተር ጀኔራል ሆነው ተሾመዋል፡፡
       ብላቴን ጌታ ኅሩይ በትዳር ሕይወታቸውም መልካም አርዓያ ስለነበሩ ከባለቤታቸው ወይዘሮ ሐመረ እሸቴ ስድስት ልጆን ወልደዋል፡፡በርካታ የልጅ ልጆችንም አፍርተዋል፡፡ቤተሰባቸውንም በእግዚአብሔር ሕግ መሠረት በፍቅር ይመሩና ያስተዳድሩ ነበር፡፡ሞልቪየር እንደጻፈው ብላቴን ጌታ ኅሩይ  በዚያች በድህነታቸው ዘመን ለማግባት የፈለጉት የጸሐፌ ትእዛዝ ገብረ ሥላሴን ልጅ ነበር፡፡ ግን አልፈቀዱላቸውም፡፡ለዚህም ነው ወደ ትውልድ ሀገራቸው ሔደውና ቆንጆይቱን ወይዘሮ ሐመረን አፈላልገው ያገቡት፡፡ በድርሰት ረገድ ከ21 በላይ የተደነቁ መጻሕፍትን ደርሰዋል፡፡ሥራዎቻቸው ሁሉ ትሕትናን፤ትክክለኛነትን፤ምግባረ ሠናይነትንና  ሞራልን ከፍ አድርገው የሚያሳዩ ናቸው፡፡
       ብላቴን ጌታ ኅሩይ  ከጻፉዋቸው መጻሕፍት ውስጥ ኢትዮጵያና መተማ የዓፄ ዮሐንስ  ታሪክ ባጭሩ(1910 ዓ ም)፤ ወዳጄ ልቤ 1955 ዓ ም ፤ዳግማዊ ቴዎድሮስ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ 1955 ዓ ም፤የልዕልት ወይዘሮ መነን መንገድ በኢሩሳሌምና በምስር1915ዓ ም፤መጽሐፈ ቅኔ 1918 ዓ ም፤ዋዜማ 1926 ዓ ም፤በኢትዮጵያ የሚገኙ በግእዝና በአማርኛ ቋንቋ የተጻፉ የመጻሕፍት ካታሎግ 1920፤የኢትዮጵያ ታሪክ ከንግሥት ሳባ እስከ ታላቁ የዓድዋ ድል 1999 ዓም፤ድርሳኖች 1983፤ማኅደረ ብርሃን ሀገረ ጃፓን1924፤ዓ ም፤የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ ታሪክ1871-1931ዓ፡ም፡በባሕሩ ዘውዴ የሚሉት ይጠቀሳሉ፡፡ከሥራዎቻቸው ውስጥ አብዛኞቹ በታሪክ፤በግለ ታሪክ‹መዝገበ ቃላት፤በጉዞ ማስታወሻሳዎችና በልቦለድ ላይ ያተኮሩ ናቸው፡፡ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎቻቸውም ዓለማቀፋዊ ዝናን አትርፈውላቸዋል፡፡
       ይህም እኤአ በ1929 እና በስደት እንግሊዝ አገር እንደነበሩ የጀርመን ኦሪየንታል ማኅበረሰብ የክብር አባል እስከመሆን አስችሏቸዋል፡፡በኢጣሊያ ወረራ ምክንያት በስደት እንግሊዝ አገር እንደነበሩም በኦሪየንታል ጥናትና ምርምር ተቋም በኋላ የኦሬንታልና የአፍሪካ ጥናት ትምህርት ቤት በተባለው የግእዝና የአማርኛ መምህር ሆነው ሠርተዋል፡፡ የአገልግሎታቸው ዋጋ ከፍ እያለ በመሄዱም እኤአ ከሚያዚያ 19/1931 ጀምሮ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው አገልግለዋል፡፤ በተጨማሪም በ1937 ዓ ም ለተቋቋመው የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር የመጀመሪያው ሊቀ መንበር ሆነው ሠርተዋል፡፡  ብላቴን ጌታ ኅሩይ በኢጣሊያ ወረራ ወቅት  ንጉሠ ነገሥቱ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በማይጨው ጦርነት ስለተሸነፉ ወደ ስደት መሄድ የለባቸውም ከሚሉት ወገኖች የነበሩ ሲሆን በኋላ ግን ንጉሠ ነገሥቱን ተከትለው ወደ እንግሊዝ ሄደዋል፡፡
       ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በጀኔቫ የዓለም መንግሥታት ማኅበር ስለ ኢትዮጵያ የግፍ ወረራ ሲገልጹ እርሳቸውም ከንጉሠ ነገሥቱ ጎን ሳይለዩ የመከራውና የስደቱ ተካፋይ ነበሩ፡፡ እዚያም የሕይወታቸው ፍጻሜ ሆኗል፡፡መስከረም 9 ቀን 1931  ዐርፈው መስከረም 10 ቀን 1931 ዓ ም በባዝ ከተማ ሉግዘምበርግ በተባለው ቦታ በተከናወነው የቀብራቸው ሥነ ሥርዓት ላይ ንጉሠ ነገሥቱ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር «ታላቅ ነህ ሳልልህ ብቀር ሥራዎችህ ቀድመውኝ ይናገራሉ» ብለዋል፡፡ ቀጥለውም«ይህ የአዳም ልጆችን ወግ ሲቀበል የምታዩት ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ በሀገራችን ሥርዓት በመልካም አያያዝ ያደገ ፤ከኢትዮጵያም ከፍ ከአሉት ሊቃውንት የሚቆጠር ነው፡፡ብልኃቱንና ትጋቱንም ለመልካም ሥራ የሚያገለግሉ መሣሪያዎች ስለአደረጋቸው በመንግሥታችን ሥራ ለመመረጥና ወደ ታላቁ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ለመድረስ ችሏል፡፡በጊዜውም የጻፋቸው መጻሕፍት ከፍተኛ ባሕርዩን የሚገልጹ  ይልቁንም በቤተ ክህነትና በታሪክ ዕውቀት በዓለም ሊቃውንት ዘንድ የታወቀና የተከበረ አደረጉት ፡፡ለምታውቁት ሰው ከታሪኩ ከዚህ የበለጠ ልነግራችሁ የሚያስፈልግ አይመስለኝም » የሚል ምስክርነት ሰጥተዋል፡፡የእግዚአብሔር መልካም ፈቃዱ ሆኖ ሀገራችን ለነጻነት ከበቃች ዐፅሙን  ለሀገሩ ዐፈር እንደሚያበቁ ንጉሠ ነገሥቱ ቃል የገቡ ሲሆን በቃላቸው መሠረት ከነጻነት በኋላ የብላቴን ጌታ ኅሩይ ዐፅም ከባዝ የመቃብር ቦታ ፈልሶና በመስከረም 11 ቀን 1940 ዓ ም አዲስ አበባ ገብቶ በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ቤተ ክርስቲያን በክብር እንዲያርፍ ተደርጓል፡፡
       ብላቴን ጌታ ኅሩይ ለሀገራቸው እድገትና መሻሻል የራሳቸውን አሻራ ጥለው ያለፉ ታላቅ ምሁር ስለነበሩ በትውልድ ዘንድ ለዘለዓለም ሲታወሱ ይኖራሉ፡፡ለስማቸው ማስታወሻ እንዲሆንም መኖሪያ ቤታቸው የሳይንስ አካዳሚ  ሆኖ በማገልገል ላይ ይገኛል፡፡
Filed in: Amharic