>

ከአሳቱ መካከል! (አለማየሁ ማሞ)

ከአሳቱ መካከል!

አለማየሁ ማሞ

አንድ ሰው ሞተ። ሚሊዮኖች ለተቃውሞ ተነሡ። አሜሪካ ይህች ናት። የጆርጅ ፍሎይድን አሰቃቂ ሞት ተከትሎ በየቦታው የነደደው እሳት ንብረት ብቻ ሳይሆን ይህንን ተንከሊስ የሆነ ቫይረስ አቃጥሎ እንዲያልፍ ስጸልይ ነበር። በርግጥም አሜሪካ እሳት በእሳት ሆናለች። እሳት የሚተፉ አንደበቶች በአሳት በሚጋዩ መኪኖችና ንብረቶች ታጅበው አየሩን ሸፍነዋል።
እሳት ይፈትናል። ያነጥራልም። አንዳንዶች ሲከስሉ ጥቂቶች ደግሞ ነጥረው ይወጣሉ። ከነደዱት የዓለም የንግድ ማዕከል ሕንፃዎች መካከል ሕያዋንን የታደጉ በወቅቱ ብሔራዊ ጀግኖች ተብለው እንደነበር ያስታውሷል። አሁንም እሳቱ የነደደላቸው ወይም የነደደባቸውን ሁለት ሰዎች ማለትም ትራምፕና ታሚካን በምሳሌነት ላሳያችሁ። ለትራምፕ እሳቱ መከራ ነው የሆናቸው። በኮረና ምክንያት የተዳፈነውን ኢኮኖሚ እንዴት ነፍስ እንደሚዘሩበት አስበው ሳይጨርሱ በየከተማው የሚነደው እሳት ይለበልበው ገባ። እሳቸው ደግሞ ይህንን ሊያበርዱ “ ዝርፊያ ከተጀመረ ተኩሱም ይጀመራል” ብለው ጻፉ። ለካ ይህች ጥቅስ ጦሰኛና ታዋቂ አባባል ኖራለች። የተናገራትም በሲቪል መብቶች ትግል ዘመን የነበረ ዘረኛ የፖሊስ አዛዥ ነበር። በዚህም ሌላ የተቃውሞ እሳት ተነሣባቸው። “እኔ ይህንን ታሪክ አላወቅሁም” ሲሉ በአደባባይ አስተባበሉ። የመጀመሪያው ሳያንስ እሳቱን ማብረዱ አላዋቂ ነኝ የሚል ውድ ዋጋ አስከፈላቸው።
በተቃራኒው ከዚህ እሳት ትንታግ ሆነው ብቅ ካሉት መካከል ደግሞ ዐይኔ የገባችው ጥቁር አሜሪካዊቷ አክቲቪስት ታሚካ ማሎሪ ነች። ዝናዋ አገር አዳርሷል። ሙሉ ንግግርዋ ዩቲዩብ ላይ የለም። ምናልባትም ሌላ እሳት ያስነሣል ብለው አግደውታል። እዚሁ ፌስቡክ ላይ ከተቀነጨበው ንግግርዋ ውስጥ ግን እነዚህ ኃይለ ቃላት ይገኙበታል። “ፖሊሦቹን ክሰሷቸው። አሜሪካ ለሁሉም ዘር የነፃ ሕዝቦች አገር ነች ካላችሁ ያንን በተግባር አሳዩን። ለጥቁሮች ነፃ አገር እንዳልሆነች እኛ እናውቃለን። ደግሞም ሰልችቶናል።  ስለ ዘረፋ አታውሩልን፤ ዘረፋውን ከናንተ ነው የተማርነው። አሜሪካ መጀመሪያ ነባር ባለርስቶችን ቀጥሎም ጥቁሮችን ስትዘርፍ ኖራለች። ከናንተው ነው የተማርነው። እንድናሻሽል ትፈልጋላችሁ? እንግዲያው መጀመሪያ እናንተው ተሻሻሉ”።
Filed in: Amharic