>
5:13 pm - Friday April 19, 9247

ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ - ተወርዋሪው ኮከብ!!!    (ታደለ ገድባሕቲቱ)

ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ – ተወርዋሪው ኮከብ!!!

   ታደለ ገድባሕቲቱ

    ባለቅኔ፤ጸሐፌ ተውኔት ፤መምህር፤ አርበኛ፤ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባልና ፕሬዚደንት፤የቴአትር ደራሲና ታላቅ የሥነ ጽሑፍ ሰው ነበሩ፡፡ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ በሚያዚያ 23 ቀን 1887 ዓ ም ጎጃም ውስጥ  በታላቁ  ደብረ ገነት ኤልያስ ልዩ ስሙ ሙዛ ዐመድ ጎባ በተባለ ቀበሌ  ተወለዱ፡፡ ያረፉትም በ1939 ዓ ም በ52 ዓመታቸው  አዲስ አበባ ሲሆን ከሞቱ ዘንድሮ  75 ዓመት ሆኗቸዋል፡፡ የቀኝ ጌታ ዮፍታሔ አባት ቄሰ ገበዝ   ንጉሤ ወልደ ኢየሱስ ፤እናታቸው ወይዘሮ ማዘንጊያ ወልደ ኄር ይባሉ ነበር፡፡ ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ባባታቸውም ፤ በእናታቸውም  ፍጹም የካህን ዘር፤ የካህን ወገን ሲሆኑ  አባታቸው መሬት የተረፋቸውና የሞላቸው ፤ከታፈሩና ከተከበሩ ባላባቶች የተገኙ ባለጸጋ  ነበሩ፡፡ እናም ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ከባለጸጋ ቤተ ሰብ  በመወለዳቸው  በጥሩ እንክብካቤ ለማደግና ለመማር ችለዋል፡፡ዮፍታሔ የቀለም ትምህርት የጀመሩት ገና በሕፃንነት ዘመናቸው ነው፡፡በኢትዮጵያ  ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ዐራት ዓይነት የትምህርት ደረጃዎች አሉ፡፡እነርሰም ንባብ ቤት፤ ዜማ ቤት፤ ቅኔ ቤትና መጽሐፍ ቤት ናቸው፡፡
     ንባብ ቤት፤ሀ ለ ሐ መ ሰ–እያሉ የፊደል ዘሮችን  የመለየትና መልእክተ ዮሐንስን ፤መዝሙረ ዳዊትንና ሌሎችን– የመማርና የማወቅ ሒደት ነው፡፡ይኽም እንደ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሊታይ ይችላል፡፡(The School of Reading (ንባብ፡:ቤት “nəbab bet”) can be seen as an elementary school). ዜማ ቤት፣ማለት የቃል ትምህርት ሲሆን ትምህርቱን ለምሳሌም ውዳሴ ማርያምን– በሦስት ዓይነት ዜማ ( በግእዝ፤ እዝል፤አራራይ) እያዜሙ መንፈሳዊ መዝሙሮችን የሚማሩበትና ምልጣንም የሚያመለጥኑበት የትምህርት ክፍል ነው፡፡ ይኽም እንደ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ይታያል፡፡ (The School of Zema (ዜማ ቤት “Zema bet”)  is regarded as the education of spiritual relics or as a school of Sacred songs. Zema bet is the equvalent of the modern school system’s junior and senior high school). ቅኔ ቤት.ማለት  የግእዝ ንባብ  የሚተረጎምበትና ሰዋስው ወይም ግስ  የሚታወቅበት  ሰምና ወርቁን እያስተባበሩ ፤ ቤት እየመቱ ቅኔ የሚቆጠርበትና የሚዘረፍበት የቤተ ግጥም ቦታ ነው፡፡ ይኽም  በኮሌጅ ደረጃ ሊታይ ይችላል፡፡(The School of Qǝne (ቅኔ ቤት “Qǝne bet”)  is a school of poetry where the Qǝne teaching and learning process is going on. It is the equivalent of a college education).
    መጽሐፍ ቤት፤ መጽሐፈ ብሉይ፤ሐዲስ፤ሊቃውንትና መጽሐፈ መነኮሳት የሚተነተኑበትና የሚተረጎሙበት ክፍል ነው፡፡ይኽም ከዩኒቨርሲቲ ደረጃ  ጋር የሚመዛዘን ነው(The School of Commentary (መጽሐፍ  ቤት “Mӓśḥaf bet”)  has the status of a univesity, where different manuscripts are prepared, studied and interpreted in the form of commentary ). እናም  ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤን ፊደል ያስቆጠሯቸው መምህራቸውመሪጌታ አደላ ንጉሤ ይባላሉ፡፡እርሳቸውም የደብረ ገነት ደብረ ኤልያስ ቤተ ክርስቲያን የዜማ መምህር ነበሩ፡፡ዮፍታሔ ፊደል ቆጥረው፤ ዳዊት ደግመው፤ ንባብ ተምረው ጥሩ አንባቢ ከሆኑ በኋላ ጸዋትወ ዜማ ተማሩ፡፡ ጾመ ድጓና ምዕራፍ  ከተማሩ በኋላ  ወደ መምህር ገብረ ሥላሴ ቅኔ ቤት ገቡ፡፡ ብሩሕ አእምሮና ፈጣን ተዘክሮ ስለነበራቸው በ13 ዓመታቸው የቅኔ ዘራፊ ኾኑ፡፡መምህር ገብረ ሥላሴም ተቀመጥ በወንበሬ፤ ተናገር በከንፈሬ ብለው መርቀዋቸዋል፡፡በኋላም ድጓ ተምረውና የዜማ ትምህርታቸውን በደንብ አለዝበውና  በመምህር ገብረ ሥላሴም በቅኔ ተመርቀው በልጅነታቸው መሪጌታ ኾነዋል፡፡
   ዮፍታሔ የሚቀኗቸው ቅኔዎች የዋሸራን የሰምና ወርቅ ስልት የተከተሉ ናቸው፡፡ድጓ አስኪደው የቅኔና የዜማ መምህር እንደሆኑ እዚያው ደብረ ኤልያስ ሊቀ ጠበብት አይቼህ ዘንድ ገብተው ትርጓሜ መጻሕፍት መማር ጀምረው ነበር፡፡ የቁም ጽሕፈትም በደንብ ተምረዋል፡፡ እዚያው ደብረ ኤልያስ ገና 20 ዓመት ሳይሞላቸው ቀኝ ጌታ የሚል  የታላላቅ ሰዎችን ማዕረግ ያገኙትም በልጅነታቸው ቅኔና ድጓ ተምረው  ሊቅነታቸውን ስላስመሰከሩ ነው፡፡ከዚህም የተነሣ የንጉሥ ሚካኤል ወላጅ እናታቸው ኤልያሴ  ነበሩና  በ1906 ደሴ ላይ ሲነግሡ  ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ  ከማኅበረ ኤልያስ  ካህናት  ተወክለውና ስጦታና የእንኳን ደስ አለዎ መልእክት  ይዘው ወደ ደሴ ሔደው ከተመለሱ በኋላ ደብረ ኤልያስ ውስጥ ብዙም አልተቀመጡም፡፡ወላጅ አባታቸው እንደሞቱ እጅግ ቆንጆ የነበሩት እናታቸው እመት ማዘንጊያ ወንድ ያማልላሉ የሚል ሐሜታስለተሰማና በካህናቱም ዘንድ ቅኔ እየተዘረፈ  ወሬው በመዛመቱ  ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ደብረ ኤልያስ መቆየት አልፈለጉምና ወደ አዲስ አበባ መጡ፡፡አለቃ መንበሩ የነገሯቸውን ጠቅሰው ዶክተር ዮናስ አድማሱ ‘ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ  አጭር የሕይወቱና የጽሑፉ ታሪክ ( 2004 15) ’ በሚል እንደጻፉት ወደ አዲስ አበባ ከመምጣታቸው በፊት ደብረ ኤልያስ እያሉ የተቀኟቸው እልፍ አእላፍ  ቅኔዎች አልተገኙም፡፡
     እምትንበር በሕይወተ ሥጋ አብደረት ተመትሮ ከምትለዋ የመወድስ ሐረግ በስተቀር ፡፡( በሕይወት ከመኖር ይልቅ መቆረጥን መረጠች) እውቁ ባለቅኔ፤አርበኛውና ጸሐፌ ተውኔቱ የፍታሔ ንጉሤ   ባለቅኔው ዮሐንስ አድማሱ እንደሚለው  በኢትዮጵያ የሥነ ጽሑፍ ታሪክ እንደ ኮከብ ሲያበሩ የሚኖሩ ጥበበኛ ናቸው፡፡አፋጀሽኝ፤ እለ ቄጥሩ ፤ዕርበተ ፀሐይ—የተሰኙና ሌሎች በርካታ የተውኔትና  ድንግል ሀገሬ ሆይ፤ወላድ ኢትዮጵያ፤አጥንቱን ልልቀመው፤ጎበዝ አየን፤የባሕር ዳር ጨፌ፤ጎሐ ጽባሕ፤ሚጠተ  እስራኤል፤ንጉሥና ዘውዱ፤የእኛማ ሙሽራ፤ ዐይኔን ሰው አማረው፤—-የተሰኙ    ሥራዎችን አበርክተው ያለፉት ዮፍታሔ ንጉሤ በተለይ በኢጣሊያ ወረራ ወቅት ከወልወል እስከ ማይጨው የተዋጉ፤ከማይጨው እስከ ምዕራብ ወለጋ የተዋጉ፤ እስከ ሱዳን የተሰደዱና ዐርበኞችን በቀስቃሽ  ግጥሞቻቸው ሲያበረታቱና እስከ ነጻነት ሲታገሉ  የነበሩ  ገጣሚና ስመ ጥር ዐርበኛም ናቸው፡፡ በሀገራቸው በምዕራብ ወለጋና በሱዳን በስደት ሲዘዋወሩ   ኢትዮጵያ በኢጣሊያ መደፈርዋ ያስቆጫቸውና ያንገበግባቸው ስለነበር ከሥራዎቻቸው ውስጥ ጥንተ ሀገሬ ሆይንና አጥንቱን ልልቀመውን  እንጥቀሳቸው፡፡
ጥንተ ሀገሬ ሆይ ጥንተ  ተደንግሎ፤
ሕጻናቱ ታርደው ያንቺም ልብ ቆስሎ፤
ሕዝቡ ተሰደደ  አንቺን ተከትሎ፤
የሕጻናቱን ደም አዘክሪ ኵሎ፡፡
አስጨነቀኝ ስደትሽ፤
እመቤቴ ተመለሽ፡፡
–ሀገሬ ተባብራ ካልረገጠኝ እርካብ፤
ነገራችን ሁሉ የእንቧይ ካብ የእንቧይ ካብ፡፡
–አጥንቱን ልልቀመው መቃብር  ቆፍሬ ፤
ጎበናን ተሸዋ አሉላን ተትግሬ፤
ስመኝ አድሬያለሁ ትላንትና ዛሬ፤
ጎበናን ለአሞራ አሉላን ለጭሬ፡
ተሰባሰቡና ተማማሉ ማላ ፤
ጎበኛ ከሸዋ  ተትግሬም አሉላ (—)
      በሚሉ ወኔ ቀስቃሽ ግጥሞቻቸው  የኢትይጵያን አርበኞች ሲቀሰቅሱና የሀገራችን ነጻነት እስኪመለስ በብዕራቸው ሲታገሉ  የኖሩ ታላቅ ሊቅ ናቸው፡፡ለዛ ባለው ቋንቋና ምጡቅ በሆነ ሐሳብ  ውስጠ ወይራና ሰምና ወርቅ የአማርኛ ቅኔ በመግጠም  በሀገራችን ተወዳዳሪ ያልነበራቸውና የተወርዋሪ ኮከብ ተምሳሌት ተደርገው  የሚታዩት  ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ በሀገራችን የኪነ ጥበብ ዘርፍ ያበረከቱት አስተዋጽኦ ከታላቁ የወርቅ ወንበር ላይ እንዲቀመጡና ለዘለዓልም ሲታወሱ እንዲኖሩ አድርጓቸዋል፡፡ ዮፍታሔ የዜማ  ትምህርት ቤት ገብተው ትምህርታቸውን በሚገባ ስላጠናቀቁ እጅግ ተወዳጅ የሆኑ መዝሙሮችንና ዜማዎችን እየደረሱ በየትምህርት ቤቶች አሰራጭተዋል፡፡ደብረ ኤልያስ የጥበብ ማእከል( 1996፤41) ለዚህ ሁሉ ሥራቸው ሀገራችን  ሐውልት ልታቆምላቸውና በክብርም ልትዘክራቸው ሲገባ በልማት ምክንያት  ሐውልታቸው ሲፈርስ ፤  አዲስ አበባ የዐፅማቸው ማረፊያ የሚሆን ቦታ ስለከለከለቻቸው   ዐፅማቸው በሊስትሮ ሳጥን በበዓለ ወልድ ቤ/ ክ አንዲት ጥግ ላይ ተቀምጦ በአሳሳኝ ሁኔታ ይኖር ነበር፡፡ከጊዜ በኋላ ቅን ኢትዮጵያውያን ወደ ትውልድ ቀያቸው ደብረ ኤልያስ በመውሰድ ዐፅማቸውን በክብር አሳርፈዋል፡፡ የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበርም ለእውቁ ባለቅኔ፤አርበኛውና ጸሐፌ ተውኔቱ የፍታሔ ንጉሤ  በስማቸው ማስታወሻ ቴምብር ያሳተመላቸው ሲሆን የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ እንዲሁ በስማቸው የጉባኤ አዳራሽ ሰይሞላቸዋል፡፡
‘ኢትዮጵያ ሀገሬ ሞኝ ነሽ ተላላ፤
 የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ ’
 ከበርካታ ቅኔዎቻቸው ውስጥ ሦስቱን ጠቅሼ እሰናበታለሁ፡፡
1.ጉባኤ ቃና
ዓለም የምትጠፋበተን ቀን ከአብና ከልጁ በስተቀር ማንም እንደማያውቃት ያመሰጥራል፡፡
ለዛቲ ሰዓት ኢያእመርዋ መላእክተ ርቀት እሙንቱ፤
ዘእንበሌሁ ለአብ ወላዲ ወዘእንበለ ወልድ ባሕቲቱ፡፡
2ዋዜማ  (የስካርን አስከፊነት የሚገልጽ )
ቆመ የበርሜል ጠጅ  ውስተ ደብረ ማሕው ልብነ ሀገረ ስቃይ ወተድላ፤
ወወደይነ በበተራሆሙ አረቄ ወጠላ፤
በውስተ በርሜል ልብነ ምስትግቡዓ በቀል አተላ፤
እሳተ አራዳ ኮኛክ እሷው ተቃጥላ፤
አውዓየታ ለባቢሎን ገላ፡፡
3.መወድስ(የመንግሥታቱ ማኅበር ኢትዮጵያን ስለመበደሉ)
ምንተ ንግበር የዐመፃ ልጆች
ለእመ ዐረፍት ይእቲ ቃለ አፉነ ወስላታ፤
ወተድባበ ብሩር ልብነ ስታጫውተን ቆይታ፤
ንግበር ማዕጾሃ
ቃለ ጽድቅ ወቃለ ሐሰት ወአኮ ባሕቲታ፤
ወዲያና ወዲህ ስትንገላታ፤
በየበራችን ለትቁም የዝግባ ሳንቃ ይሉኝታ፤
በጀኔቭሂ አመ ተፀንሰ ዘኢትዮጵያ አለኝታ፤
የቱሞሮው እናት እሺ ነገ በብሂለ ኦራይት ወለደታ፤
ወእሽ ነገ እኅትነ በአፍተር ቱሞሮው ተቀበለታ፡፡
Filed in: Amharic