>

ከህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ(ህወሓት) ማዕከላይ ኮሚቴ  የተሰጠ መግለጫ!

ከህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ(ህወሓት) ማዕከላይ ኮሚቴ  የተሰጠ መግለጫ!

የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ  ከግንቦት 15 እስከ 22 ቀን 2012 ዓ/ም ባካሄደው ስብሰባው በፍጥነት እየተለዋወጠ ያለው የዓለም፣ የአካባቢያችንና የሀገራችን ሁኔታ ጨምሮ የክልላችን ሰላምና ደህንነት፣ የኮረና ቫይረስ በሽታ ስጋትና የመከላከል ስራ፤ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ሂደት፣ የድርጅትና የመንግስት ስራ አፈፃፀም እንዲሁም በአስተዳደር በኩል እየመጡ ያሉት ለውጦች አስመልክቶ ሰፊ ውይይት አካሂዷል፡፡
ኮረና ቫይረስን ወይም ኮቪድ-19 ተከተሎ እየመጣ ያለውን አዲስ ዓለማዊ ሁኔታ የልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መስመር አስፈላጊነትንና ትክክለኛነትን የሚያረጋግጥ ነው፡፡ቀድመውንም ቢሆን የመንግስት ስልጣን ሽግግርን ለብቻ ተቆጣጥረህ ጠባብ ጥቅምህን ለማርካት፣ የህዝብ ተጠቃሚነትን ለአፍታ እንኳን ግድ የሌለው ጥገኛ የብልፅግና ቡድን በተፈጠረው አዲስ ዓለማዊ ሁኔታዎችና ፈተናዎች ራሱን አስተካክሎ በህዝባዊ ትግልና በህዝብ ልጆች መስዋእትነት በግንቦት 20 የተመዘገቡ አስደናቂ የዴሞክራሲና የልማት ድሎች አጠናክሮ ከማስቀጠል ይልቅ የጥፋት መንገድ አጠናክሮ ቀጥሎበታል፡፡
በጊዜያዊ ጥቅም ወይም  በጥላቻ  የዚህ ስርዓት መጠቀሚያ በመሆን ሙያቸውንና ስብእናቸውን አሳልፈው የሰጡ አካላት ከፊት በማሰለፍ  በግላጭ ህገ-መንግስቱን በመጣስ ስልጣን ላይ እንደሚቆይ  ይፋ ያደረገው የብልፅግና ቡድን ለማስመስል እንኳን ውሳኔ ይሰጣሉ የተባሉትን ተቋሞች የሚሉትን እስከምንሰማ ድረስ እንኳን ሊታገስ አልቻለም፡፡ በእንደነዚህ ዓይነት ወደ ጥፋት የሚምዘገዘገው የብልፅግና ቡድን የሚያስተዳድረው መንግስት ባላት ሃገር ሆነን መሰረታዊ ዓላማችንንና ልማታችንን ለማሳካትም ሆነ የገጠመንን የኮረና ቫይረስ ፈተና ለመመከት ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ሁሉም ሊገምተው የሚችል ነው፡፡
የ’ብልፅግና’ ቡድን ሉአላዊነትና  መሰረታዊ የሚባሉ የሀገር ጥቅሞች ለሽያጭ በማቅረብ፣ ህገ መንግስትንና ስርዓትን እንዲሁም ሁሉም ዓይነት ከፊቱ ላይ የቆሙትን ህጎችንንና ተገቢ የመንግስት አሰራሮችን በመጣስ ስልጣን ላይ ለመቆየት ከመወሰን አልፎ ስርዓትንና ህግን አክብረው በሄዱት አካላት ላይ ይፋዊ ጦርነት ወደ ማወጅ ተሸጋግሮ ይገኛል፡፡ የዚህ ቡድን ፉከራዎችና ሴራዎች በአካሄዳችን ላይ ይሁን በህዝባዊ ትግላችን ተጨማሪ ቁጭትና ወኔ ከመፍጠር አልፈው ሌላ ፋይዳ ያላቸው እንዳልሆኑ ግልፅ ቢሆንም ለጠባብ ፍላጎት ሲባል የሃገርና የመላ ህዝቦች ጥቅም ወደ ገደል ገፍትሮ ለመጣል ‘ብልፅግና’ ምን ያህል ዝግጁ እንደሆነ ለሁሉም ግልፅ ሆኗል፡፡
ይሁን እንጂ ወትሮም ቢሆን ህልውናውንና  ጥቅሙን በጠንካራ ክንዱና በትክክለኛ አስተሳሰቡ የተመሰረተ መሆኑን፤ ታሪኩንና ትግሉን በተጨባጭ አሳምሮ የሚያውቅ ህዝባችን፤ የጥገኞች ቀጣይ በርካታ ጥቃቶችን ተቋቁሞና የመመከት ተግባሩን አጠናክሮ መቀጠሉን አረጋግጠናል፡፡ ድርጅታችን ህወሓት ህዝባችን እያካሄደ ላለውን ፍንክች የማይል ቀጣይነት ያለው ትግል ከፍተኛ ክብርና አድናቆቱን ይገልፃል፡፡ ወደፊትም ሁኔታዎች በጥብቅ እየገመገምን የምናሳልፋቸው ውሳኔዎች በንቃት እንደሚከታተልና እንደሚፈፅም የትናንትም የዛሬም ታሪካችን ምስክር ነው፡፡ እያካሄድን ያለነው የተፋፋመ ትግል በሁሉም የሰላም፣ ልማትና ዲሞክራሲ አውዶች ተስፋ የሚያሰንቁና ለቀጣይ ድሎችም አመቺ ቦታ የሚፈጥሩ ውጤቶች እየተመዘገቡ ናቸው፡፡  ይህ በእንዲህ እንዳለ አሁንም ህዝባችንን ያላረካንባቸው በርካታ ጉዳዮች እንዳሉ አሳምረን የምንረዳው ዕውነታ ነው፡፡
ከህዝባችንና ከመሪ ድርጅታችን ፊት ለፊት መግጠም ከብረት ጋር መጋጨት የሆነባቸው ጥገኛ ቡድንና ተከታዮቹ በዋንኛነት በተቀናጀ የሚዲያ ዘመቻ የታገዘ ግልፅ ውሸት በመመስረትና ባንዳዎችን በማዝመት ውስጣዊ ሰላማቻንን በማደፍረስና ልማታችንን በማደናቀፍ ወደ ድቅድቅ ጭለማ ሊያስገቡን እየሰሩ መሆናቸውን ሁሉም በተለይ ደግሞ ህዝባችን የሚገነዘበው ጉዳይ ነው፡፡
በዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ ሆነን በአንድ እጃችን ሁለገብ የመመከት ስራዎቻችን እያጎለበትን በሌላም በኩል ፈጣን የልማትና የመልካም አስተዳደር ማስፈን፤ ህዝባችንንና መላ መዋቅራችንን እንዲሁም የሰላምና የልማት ወዳጅ የሆነ ኃይል ሁሉ ሊረባረብላቸው የሚገቡ ጉዳዮች መሆናቸው በማረጋገጥ የህወሓት ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ከሚያዝያ 23 እስከ 25/ 2012 ዓ/ም ባካሄደው ስብሰባው ያሳለፋቸው ውሳኔዎችንና አቅጣጫዎችን በማፅደቅና መሰረት በማድረግ የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ የሚከተሉትን ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡
1. የኮረና ቫይረስ መከላከል ስራ ከዚህ በፊት ሲደረግ እንደቆየው አዲስ ለውጦች፣ ተጨባጭ የክልላችን ሁኔታ እንዲሁም ሳይንሳዊ ማሳረጃዎችን መሰረት በማድረግ ህዝባችንን ለማዳን እየተከላከልን ኢኮኖሚያዊ ጉዳት በሚቀንስ መልኩ እየተገመገመ በጥብቅ እንዲመራ ተወስኗል፡፡
2. የ‘ብልፅግና’ ቡድን ከድሃ ጉሮሮ እና ልማት ቀምቶ ያልተቆጠበ ሃብት በማፍሰስ ሀገር ከጫፍ እስከ ጫፍ ለማበጣበጥ፤ በዶክሜንተሪ ፊልሞች የታገዘ ዘር የማጥፋት ጥሪ እንዲካሄድና ሁሉም መብቶች እንዲረጋገጡ እያደረገ ያለው ጭፍን ፀረ ህዝብና ስልጣንን በገንዘብ የመግዛት ተግባር እንዲቆም ብቻም ሳይሆን ከጥፋት መንገድ ወጥቶ በህገ መንግስት መሰረት የሚመለከተው ወገን ሁሉ ተሳትፎ ባረጋገጠ መልኩ እና ወደ ምክንያታዊ ውይይት እንዲገባ እንዲሁም ጨርሶ ሳይረፍድ ህገመንግስታዊ ስርዓት ከማፍረስ እንዲቆጠብ የህወሓት ማዕከላይ ኮሚቴ ያሳስባል፡፡
3. ሙሉ ዝግጅትና የህብረተሰቡን ጤና የመጠበቅ ስራ በመስራት በህገ መንግስት በተዘረጋው ስርዓት መሰረት ሁሉንም እኩል ማየት የሚችል ኃይል የሚመራው ሀገራዊ ምርጫ እንዲካሄድ የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ዳግም ያሳስባል፡፡
4. ምርጫ በሀገር አቀፍ ይሁን በክልል ደረጃ በሺዎች መስዋዕትነትና ከፍተኛ ዋጋ የተከፈለበት ህገ-መንግስታዊ ዋስትና ያገኘ መብት እንጂ ገደብ የለሽ የስልጣን ጥማት ያለው ግልገል አምባገነን የሚሰጠው ወይም የሚከለክለው ችሮታ አይደለም፡፡ የትግራይ ህዝብ ከድሮም ቢሆን ራሱን በራሱ የማስተዳደር መብቱን በመስዋዕትነቱ ያረጋገጠ፤ በማንኛውንም ሁኔታ በራሱ ላይ ይሁን በሌሎች ህዝቦች ላይ ባርነት እንዲነግስ የማይፈቅድ ህዝብ ነው፡፡
የትግራይ ህዝብ በመስዋዕትነቱ ያረጋገጠው መብት በማንኛውንም ጊዜ እና ሁኔታ ወደ ድርድር እንደማይቀርብና የዚህን መብት ተግባራዊነት ወደ ኋላ መመለስ የሚችል ማንኛውም ምድራዊ ፖለቲካዊ ኃይል እንደሌለ  የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አስምሮበታል፡፡ ስለዚህም የፌደራል ስልጣን በአምባገነናዊ አኳኋን ተቆጣጥሮ ያለው ኃይል በተለመደው አካሄዱ የህዝቦችን መብት እየደፈጠጠ መቀጠሉን አጠናክሮ እየገፋበት በመሆኑ ህዝባችን በመስዋዕትነቱ ያረጋገጠው እና የማንም ፈቃድ የማይጠይቅበት፤ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት በተግባር ለመተርጎም በክልላችን ምርጫ እንድደረግ እና ይህንን ለማድረግ የተጀመሩ ዝግጅቶች ለማድረግ የተጀመሩ ዝግጅቶች በህግ አገባብ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ወስኗል፡፡
የህወሓት ማዕከላይ ኮሚቴ በትግራይ ምርጫ እንዲካሄድ ሲወስን በ‘ብልጽግና’ ጥገኛ ባህሪ ምክንያት የተጀመረው ሕገ መንግስታዊ ስርዓት የማፍረስና ሃገር የመበተን ሂደት ወደ መጨረሻ ምዕራፍ እየደረሰ መሆኑን ይገነዘባል፡፡ አሁንም ቢሆን ሁሉም የኢትዮጵያ ብሄሮች ብሄረሰቦችና እና ህዝቦች የሀገራችንን ህገ መንግስት ያጎናፀፋቸው ራስን በራስ የማስተዳደር መብት እንዳያጡ ትግላቸው ማጠናከር እንደሚገባቸው ህወሓት ያምናል፡፡ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብም ይህንን ተገንዝቦ አዎንታዊ ሚና እንዲጫወት ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡
5. የ‘ብልፅግና’ ቡድን ምርጫ ላለማካሄድና የስልጣን ዕድሜውን ለማራዘም እየወሰዳቸው ካሉ ህገ ወጥ እርምጃዎችና ሴራዎች በተጨማሪ የድርጅታችን ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በትግራይ ክልል ህግና ስርዓት እንደሚቀጥልና ‘ብልፅግና’ ምርጫ ለማስቀረት እየሰራ በመሆኑ በትግራይ ደረጃ በህግ መሰረት ምርጫ ለማካሄድ ውሳኔ ባሳለፈበት ወቅት የብልጽግና መሪ አሁንም መሰረታዊ የህዝቦች ራስን በራስ የመወሰን መብት ክብር እንደሌለው በሚያሳይ መልኩ የጦርነት አዋጅ ይፋ አድርጓል፡፡ የትግራይ ህዝብ በፉከራና የጦርነት ነጋሪት መጉሰም እንደማይደነግጥና  መብቱን አሳልፎ እንደማይሰጥ የሚታወቅ ሃቅ ነው፡፡ ኃላፊነት በጎደለው አካሄድ እንዲሁም የ‘ብልፅግና’ ቡድን  እና መሪው የሚመጣ ማንኛውንም ጥፋት ብቸኛው ተጠያቂዎች ራሳቸው መሆናቸው መላው የኢትዮጵያ ህዝብና ዓለምአቀፉ ማህበረሰብ መገንዘብ ይገባቸዋል፡፡
6. በልማት ስራዎች፣ የዴሞክራሲ ባህል እና አስተዳደር የተጀመሩ ለውጦች በጊዜ የለንም መንፈስ በበለጠ ፍጥነት ተጠናክረው እንዲቀጥሉ በየደረጃው ያለው አመራር በከፍተኛ የኃላፊነት መንፈስ እንዲሰራው ተወስኗል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ መላው ህዝባችንና ሁሉም የመንግስትና የድርጅት መዋቅሮች ለርካሽ ዓላማቸው ሲሉ ከልማትና የዴሞራሲ ግንባታ ሃዲድ አውጥተው ወደ ብጥብጥና ጥፋት ሊያስገቡን የሚረባረቡ ብልጽግና ኃይሎች፣ አይዞህ ባዮችና እና ተላላኪዎቹ ለመመከት የተጀመረውን ትግል እንዲጠናከር ተወስኗል፡፡
7. የራስን ዕድል በራስ የመወሰንና ራስን በራስ የማስተዳደር መብት፣ የህዝባችን ደህንነትና ሰላምን የማረጋገጥ ጉዳዮች ላይ አብሮው ሊሰሩ ዝግጅ ከሆኑ የሀገራችንና የክልላችን የፖለቲካ ኃይሎች የተጀመረውን ዝምድና በፍጥነት ወደ ከፍተኛ ደረጃ እንዲሸጋገርና ትርጉም ያለው ለውጥ ሊያመጣ ወደሚችልበት የህዝባችን ደህንነትና የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ስራዎች እንዲገባ የህወሓት ማእከላይ ኮሚቴ ወስኗል።የህገ መንግስታዊ ስርአትንና መንግስትን አስፈላጊነትና ቀጣይነት በአግባቡ ተረድታችሁ ፣ይህን ለማረጋገጥ የድርሻችሁ ሀገራዊ ግዴታ እንደምትወጡ እና ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ እንቅስቃሰያችሁን አጠናክራችሁ እንደምትቀጥሉ የህወሓት ማእከላይ ኮሚቴ ያምናል።
የትግል ጥሪ፤
የተከበርክ የትግራይ ህዝብ፤የራስን ዕድል በራስ የመወሰንና ራስን በራስ የማስተዳደር መብቶች ለመናድ  ህገወጡ የ’ብልፅግና’ ቡድን  እየተከተለው ያለው የተቻኮለ አካሄድ እና የጦርነት አባዜ ሰላማዊና ህጋዊ ትግል በማካሄድ ለመመከት የትግራይ ህዝብ በተለይ ደግሞ የትግራይ ወጣቶች የትግል ዝግጁነታቸውና አደረጃጀታቸውንእንዲያጠናክሩ የህወሓት ማእከላይ ኮሚቴ ጥሪውን ያቀርባል።
ኮሮና ቫይረስ በህልውናችን ላይ እና በጀመርነው የመመከት እንቅስቃሰያችን ለያደርስ የሚችለውን ተፅእኖ በመረዳት፣ የባለሞያዎች ምክርና የመንግስት መመሪያዎች በጥብቅ በመተግበር፣ ህዝባችን ተገቢ ትኩረት በመስጠት እንዲመክተው ከከፍተኛ አደራ ጭምር ጥሪውን ያቀርባል።
ህልውናችን፣ሰላማችንና ልማታችን ለማረጋገጥ ደግሞ መላ ህዝባችን የሚያጋጥሙትን ችግሮች ተሸክሞ፣ምርቱና ምርታማነቱ ይበልጥ እንዲጠናክር በድጋሜ ጥሪያችንን እናቀርባለን።
የተከበራችሁ የድርጅታችን ህወሓት አባላት፣ በየደረጃው ያላችሁ አመራሮች፣አሁን ያለንበት መድረክ የሚጠይቀውን ፅናትና መስዋእትነት በውል ተገንዝባችሁ፣ህዝባችን ለማዳን በሚደረገው ሁለንተናዊ ትግል ግንባር ቀደም ድርሻችሁ እንዲትወጡና  አርአያነታችሁ አጠናክራችሁ እንድትቀጥሉ የህወሓት ማእከላይ ኮሚቴ ጥሪውን ያቀርባል።
የተከበራችሁ የክልላችን የህዝብ ማህበራትና ሲቪክ ተቋሞች፤ ዛሬም እንደትላንቱ ለሰላማችሁ፣ ለልማታችሁና ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ከናንተ በላይ ሊቆረቆር የሚችል ኃይል እንደሌለ ተገንዝባችሁ በመመከት እንቅስቃሴ በጠቃላይ፣ በተለይ ደግሞ ምርጫውን በድል እንዲጠናቀቅ በከፍተኛ ፍጥነት እንድቀጥሉ ጥሪያችንን እናቀርባለን።
የተከበራችሁ  የሀገራችን ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች፣ የአፈና፣የሰብአዊ መብት ጥሰቶች፣ ጭቆናና የተለያዩ በደሎች እንዲሁም ሁለንተናዊ ችግሮች የጀመራችሁት ትግል አጠናክራችሁ እንዲትቀጥሉ ጥሪያችንን እናቀርባለን። ለመሰረታዊ መብቶች፣ ፍትህና እኩልነት በምታደርጉት ትግል ህወሓት ዛሬም እንደትላንቱ ከጎናችሁ እንደሚቆም ያረጋግጣል።
የተከበራችሁ የሀገራችን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት፣ ህገ መንግስቱን ለመናድ የተጀመረውን እንቅስቃሴ  ሊያስከትለው የሚችል ሀገር የማፍረስና እልቂት በውል ተገንዝባችሁ፣ ይህ ተግባር እንዲቆም ታሪካዊ ኃላፊነታችሁ እንትወጡ ጥሪያችንን እናቀርባለን።
በህገ መንግስት መሰረት የተዋቀራችሁ የሀገራችን የክልሎችና ተቋሞች፣ ህዝብ የሚያስቀድምና ህገ መንግስቱን የሚያከብር መንገድ እንድትከተሉ እና ህገ መንግስታዊ ስርአት በመናድ ላይ ከመሳተፍ እንድትቆጠቡ ጥሪያችን እናቀርባለን።
የተከበራችሁ  የፖለቲካ ፓርቲዎች በተለይ ደግሞ በትግራይ ህግ አክብራችሁ የሚትንቀሳቀሱ  የፖለቲካ ፓርቲዎች  እና አስተዋፅኦ ያላችሁ ሀይሎች፤ አሁን ያለው ተጨባጭ  ሁኔታ  በጥሞናና በእውቀት በመመርመር የብልፅግና ቡድን የያዘው የጥፋት መንገድ  እንዲቆም ሀላፊነታችሁን እንዲትወጡ፣ ከህግና ከታሪክ   ተጠያቂነት ራሳችሁን እንዲታድኑ ጥሪ እናቀርባለን።
የተከበራችሁ የትግላችን አጋር፣ የጎረቤት ሀገሮች ህዝቦች በተለይ የኤርትራ ህዝብ ፤ አሁንም እንደ ትላንቱ የጋራ ችግሮቻችን ለመፍታት ትግላችንና ትብብራችን እንድናስቀጥልና ይበልጥ እንድናጎለብት ጥሪ እናቀርባለን።
የተከበራችሁ የዓለማቀፍ ተቋሞች በተለይ ደግሞ ኢጋድ፣ አፍሪካ ሕብረት እና የተባበሩት  መንግስታት ድርጅት፣ እንዲሁም ሌሎች የሚመለከታችሁ አካላት፤ በኢትዮጵያ በለውጥ ስም እየተካሄደ ያለው ዘግናኝ የሰብአዊ መብት ጥሰት፤ ህገ መንግስታዊ ስርአቱን የመናድና ሀገሪቱን የማፍረስ እንቅስቃሴ በጠራ መረጃ እና ዕውቀት እንዲሁም በከፍተኛ የኃላፊነት መንፈስ አወንታዊ ሚናችሁ እንድትወጡ ጥሪያችንን እናቀርባለን።
ዘልኣለማዊ ክብርና  ሞገስ ለጀግኖች ሰማእታት!
ድልና ድምቀት ለ29ኛው የግንቦት 20 ድል በዓል!
አሁንም መስመራችን አጥብቀን እንመክት!
ግንቦት 23/ 2012 ዓ/ም
መቐለ
Filed in: Amharic