>

ጀግናው አርበኛ  ቢትወደድ አያሌው መኰንን ዋሴ !!! (አቻምየለህ ታምሩ)

ጀግናው አርበኛ  ቢትወደድ አያሌው መኰንን ዋሴ !!!

አቻምየለህ ታምሩ

ቢትወደድ አያሌው መኰንን በ፲፰፻፺፩ ዓ.ም ሕዳር ፳፯ ቀን  በቀድሞው ጎጃም ጠቅላይ ግዛት በባሕር ዳር አውራጃ በአቸፈር ወረዳ አሹዳ አቦ በተባለች ቀበሌ ከአባታቸው ከፊታውራሪ መኰንን ዋሴና ከእናታቸው ከወይዘሮ የውብዳር ንጉሤ የተወለዱ ጀግና አርበኛ ናቸው፡፡
በትምህርት ቤት ቆይታቸው የሥነ መንግሥት ትምሕርታቸውን በቅልጥፍናና በከፍተኛ ውጤት ካጠናቀቁ በኋላ አገራቸው ማገልገል የጀመሩት ገና የ፲፰ ዓመት ወጣት ሳሉ ልጅ ተብለው በጉልተ ገዥነት ሲሾሙ ነበር፡፡ በ፲፱፻፲፫ ዓ.ም. ልዑል ራስ ኃይሉ ተክለ ሃይማኖት የጎጃምን ጦር ይዘው ወደ ሰገሌ በዘመቱ ጊዜ ልጅ አያሌው መኰንንም በአባታቸው በፊታውራሪ መኰንን ዋሴ ስር ዘምተው ባሳዩት ብቃት ወደ ግዛታቸው ሲመለሱ ልዑል ራስ ኃይሉ ተክለሃይማኖት  የግራዝማችነት ማዕረግ ሰጥተዋቸዋል፡፡
ከዚያው ልዑል ራስ እምሩ ኃይለ ሥላሴ ጐጃምን ያስተዳድሩ በነበሩበት ጊዜ የግራዝማች አያሌውን አግልግሎትና ብቃት ተመልክተው አስቀድሞ ከሚያስረዳድሩት አድቤ ከተባለው ግዛት ሌላ በአቸፈር ወንድየና አሥራ ደብር ውስጥ የባሕር ዳር ሚካኤል አስተዳደር ተጨመሮላቸዋል፡፡
በ፲፱፻፳፰ ዓ.ም. ኢጣሊያ ኢትዮጵያ በግፍ በወረረች ጊዜ በልዑል ራስ እምሩ አዝማችነት ወደ ማይጨው ሲዘምቱ አባታቸው በሽምግልና ምክንያት በልዑልነታቸው ፈቃድ ግዛታቸውን እንዲጠብቁ ስለቀሩ ፣ ግራዝማች አያሌው ከራሳቸው ጦር ሌላ በአባታቸው እንደራሴ በመሆን ዘምተው ሽሬ ላይ ፫ ቀን ሙሉ ጦርነት በጀግንነት ተዋግተው ከፍተኛ ጀብድ ፈጽመዋል፡፡
ከዚያም  በአባቶቻቸው ዘመን በአድዋው ጦርነት በእግር የሚያውቁት ጠላት  በሰማይ በመምጣቱ  የጠላት ኃይል ስለበረታና በወራሪነት ሲገባ ከልዑል ራስ እምሩ ጋር ተመልሰው ልዑልነታቸውን ወደ ጎሬ ሸኝተው ከተሰናበቱ በኋላ  ከትውልድ ቦታቸው ገቡ  አቸፈር እንደገቡ ዝብስት በረሃን ማእከል አድርገው ለአርበኝነት የሚያደርጉትን ዝግጅት ጠላት ስለደረሰበት አባታቸውን ፊታውራሪ መኰንንና /ከአዴት/፤ የታናሽ እኅታቸውን ባል ግራዝማች በላይ ዓለሜን በባሕር ዳር ከተማ ሲያስር፤  ግራዝማች አያሌው ከሁለት ታናናሽ ወንድሞቻቸው [ከልጅ ይግዛውና ከልጅ እምሩ መኰንን] ጋር እንዲሁም ከዝብስት የታላቅ እኅታቸውን ባል ቀኛዝማች ገሠሠ መሹን ጨምሮ በአቸፈር ወረዳ ውስጥ ይስማላ ጊዩርጊስ ታሰሩ።
ፊታውራሪ አያሌው  ለሰባት ወር ያህል በጥብቅ  ከታሰሩ በኋላ በ፲፱፻፳፱ ዓ.ም በሐምሌ ወር በባሕር ዳር ከተማ የታሰሩት አባታቸውና የእኅታቸው ባል በግፍ መገደላቸውን እንደሰሙ ወዲያውኑ አብረዋቸው የታሠሩትን ወንድሞቻቸውን ይዘው በሚያስደንቅ ሁኔታ ከፋሽስት እስር ቤት ሰብረው በማምለጥ መውጫ መግቢያውን አጥርተው ወደሚያውቁት ዝብስት በረሃ ገብተው ከመታሰራቸው በፊት ደብቀውት የነበረውን የጦር መሣሪያ ከየቦታው በመሰብሰብ ከፋሽስት ጋር ስለሚያደርጉት ተጋድሎ ከወንድሞቻቸውና  ከግብረ አበሮቻቸው ጋር ሲመካከሩ ለጥቂት ሳምንቶች ያህል ቆዩ፡፡
ጠላትም ከወሕኒ ቤት ሰብረው ማምለጣቸው እንደተረዳ እሹዳ አቦ በሚበለው ቀበሌ የነበረውን የርሳቸውንና የአባታቸውን ቤትና ንብረት  በውሉ ከዘረፈ በኋላ ቤታቸውን አቃጠለው።  ግራዝማች አያሌውም ወዲያውኑ ጦር ሰብስበው ለሰባት ወር ታስረው ከነበሩበት አገር ይስማላ ላይ የነበረውን የጠላት ጦር አስከረም  ፫ ቀን ፴ ዓ.ም ገጥመው መግቢያና መውጫ በማሳጣት  ካምፑን አፈራርሰው ያከማቸውን የጦር መሣሪያና ማንኛውንም ንብረት በሙሉ ማረኩ።
ከዚህም ቀጥሉው መስከረም ፭ ቀን ፴  ዓ.ም ዳንግላ ከተማ በነበረው የፋሽስት ማእከል ላይ የተደረገውንና ፋሽስት ኢትዮጵያን ከወረረ ወዲህ  ብዙ ሰላቶዎችና ባንዶች ለመጀመሪያ ጊዜ ያለቁበትን ታላቅ ጦርነት የመሩት ግራዝማች አያሌው  መኮንን ናቸው። በዚሁ ዓመት ያቸፈር  ሕዝብ ተሰብስቦ በግፍ ለተገደሉባቸው አባታቸው ሙት ዓመትና ስለእርሳቸውም አገልግሎት ያቸፈር ገዥና ጦር መሪ እንዲሆኑ በሙሉ ድምጽ መረጣቸው፡፡ በነገራችን ላይ በወቅቱ  አቸፈር ይባል  የነበረው ግዛት  አንድ መቶ አሥራ አራት ደብቶችን  ያጠቃለለ ሲሆን በምሥራቅ ሜጫ፤  በደቡብ የኳኩራ፣  የባቻና የርምሃ ም/ወረዳ፤ በምዕራብ የበላያ ም/ወረዳ፣ ከቤገምድር ጠቅላይ ግዛት የጋዝጌ ም/ወረዳና  በሰሜን ከጣና ሐይቅና ከአለፉ ጣቁሳ ወረዳ ጋር ይዋሰን ነበር፡፡
ከዚህ በኋላ ግራዝማች አያሌው የሕዝቡን ድጋፍና መተባበር በማግኘታቸው በየጊዜው ከጠላት ጋር መግጠምና በአቸፈር  ውስጥ እየመጣ ካምኘ /የጦር ሰፈር/ ለመሥራት ከሚሞክረው ወራሪ ጋር ሁሉ  ያለዕረፍት በመዋጋት ያርበኝነት ትግላቸውን ቀጠሉ፡፡
በ ፲፱፻፴ዓ.ም በታህሳስ ወር ጠላት በወታደርና በመሣሪያ መደርጀታቸውን ስለአወቀ ከዳንግላ፤  ከቁንዝላና  ከወተት ዓባይ የነበረውን ጦር ይዞ በአይሮኘላይ እየተረዳ ዝብስት የነበሩትን ግራዝማች አያሌውን  ገጠማቸው፡፡
አባ ይርጋ አያሌውም  ከአቸፈር ጀግኖች ወንድሞቻቸው ጋር ሆነው በተፈጥሮዋ ለጠላት በማትመቸው በዝብስት ተራራ ሸንተረር ላይ በአይሮኘላን እየተረዳ የመጣውን የጠላት መድረሻ በማሳጣት ወደ መጣበት መልሰውታል። በዚህ ጊዜ ጠላት በኃይሉ የወሰደው ርምጃ ውጤት እንዳላስገኝነት ስለተረዳው ነገሩ በስብከት የሚያልቅ መስሎት አግባብቶ ለማሳሳት ሽማግሎችን ልኰ  ለመታረቅ ሞክሮ ነበር፡፡ ሆኖም ግራዝማች አያሌው በማር ተለተጠቀለለው የፉሺስት ስብከት ሳይታለሉ ውጊያቸውን ቀጠሉ፡፡
ግፈኛው ጠላት የግራዝማች አያሌው መጠንከርና ብዙ ወታደር ማደራጀት እንቅልፍ የነሳው ከመሆኑም ይልቅ ከግርማዊነታቸው ጋር መላላካቸውንና የጃንሆይን መልክተኞች  የሆኑትን እነ ደጃዝማች ከበደ ተሰማን እየተቀበሉ ማስተናገዳውን ይሰማ ስለነበረ ፣ በኃይል ተጠቅሞ ድል ማድረግና በሙሉ ሣምባው መተንፈስ ስለፈለገ ፲፱፻፴ ዓ.ም በጠቋሚ ተመርቶ ሌሊቱን ሲጓዝ አድሮ ሠራዊታቸውን ለዕረፍት አሰናብተው ጥቂት ሆነው በሰፈሩበት መንደር አምባ ጊዩርጊስ ላይ  ሳይታሰብ ደረሰና አደጋ ጣለባቸው፡፡
በተደረገው የጨበጣ ውጊያ እርሳቸውና ሁለቱ ወንድሞቻቸው 3ቱም በአንድነት ቆስለው እጃቸውን ለጠላት ሳይሰጡ በሚያስደንቅ ጀግንነት ተከላክለው ወደዝብስት በረሃ ገቡ፡፡
ከጠላት በተወረወረው ቦምብና በተተኰሰው ጥይት እግራቸውን የተመቱት ግራዝማች አያሌውና ወንድሞቻቸው በበረሃ ሆነው ቁስላቸው እስኪያገግም ድረስ ከቆዩ በኋላ በ፲፱፻፴፪ዓ.ም በየካቲት ወር እርሳቸውን አድኖ ለመያዝ ከተላከው የጠላት ጦር ጋር አዳምና ከተባለው መንደር ላይ ተጋጥመው ብዙ ጀግኖች ወንድሞቻቸው በጦሩ ሜዳ ላይ ተነባብረው ወደቁባዋሙ፡፡ እርሳቸውም ተቀምጠሉባት የነበረችው በቅሎ በጥይት ተመትታ ስትወድቅ ግራዝማች አያሌው ግን ምንም ሳይሆኑ በጠላት ላይ ብዙ ጉዳት አድርሰው ፋሽስትን ወደ መጣበት  መለሱት፡፡ በዚህ ጊዜ አብሯቸው የነበረ አንድ ወታደር በጨበጣ ውጊያ ከፋሽስቶች ጋር ግብግብ ገጥመው የማረኩትን ፋሽስት መሬት ለመሬት እየጎተቱ ወደ አምባ ጊዮርጊስ ሲወስዱ በመመልከቱ እንዲህ ብሎ ገጠመላቸው፤
ቤልጅግህ ዘበኛ ጓንዴህም ዘበኛ፣
የመጣውን ጠላት አንጥሮ ሲያስተኛ፤
አባይርጋ አያሌው አትጠመቅም ወይ አሁን አስመጥተህ፤
ካረመኔው ጋራ ተናክተህ ተናክተህ፡፡
አባ ይርጋ የግራዝማች አየሌው የፈረስ ስም ነው።
ከዚህ ጦርነት ቀጥሎ እረፍት ሳያገኙ ሚያዝያ ወር በ፲፱፻፴፩  ዓ.ም እርሳቸውን ለማሳደድ ከተላከው ጦር ጋር ጭቃ ወንዝ ላይ ተጋጥመው ብዙ ሰዓት ከተወጉ በኋላ ጠላት ሽንፈት ተከናንቦ  ወድ ወጣበት ጦር ሰፈር  ወደ ዳንግላ  በመመለስ  መከላከል ግድ ሆኖበታል፡፡ ይህን የግራዝማች አያሌውን ጀግንነት የተመለከተው ሕዝብ የጦር መሪ አድርጎ የሾማቸውን መሪውን  ቅጠል በመበጠስ በጭንቅላታቸው ላይ እየጣለ “ፊታውራሪ ብለን ሾመንዎታል” ያላቸውና የፊታውራሪነት ማዕረግ የሰጣቸው በዚሁ በ፲፱፻፴፩ ዓ.ም ነበር።
ጠላት ቆስለው ያልወደቁለትን ያቸፈር አርበኞች ጦር መሪ ፊታውራሪ አያሌውን  ተስፉ ሳትቆርጥ ተዋግታ ማጥቃት ስለተመኘች  በጥር ወር በ፲፱፻፴ ዓ.ም፤  እንዲሁም ግንቦት ፩ ቀን ከየጦር ሰፈሯ   ማለት ከቁንዝላ ከይስማላ ከወተት ዓባይ ከዳንግላና ከባሕር ዳር ተውጣጥቶ በመትረየስና በቦምብ እንደሁም በከባድ መሳሪያ የሚረዳ ጦር አዘመተች። ሆኖም ግን የመጣውን እግረኛና ፈረሰኛ የጠላት ጦር አዘና ከተባለው መንደር ከቦታው የተፈጥሮ አቀማመጥና ጫካው  ለጠላት አለመመቸት ጋር  ተደምሮ ፊታውራሪ አያሌው ባላቸው የተፈጥሮ ጀግንነት  ሲገሰግስ በመጣው ወራሪ ጠላት ላይ ብዙ ጉዳት አድርሰው ወደ የጦር ሰፈሩ እንዲመለስ አድርገውታል፡፡
ከዚህ ዘመቻ ቀጥሎም ጠላት ተስፉ ባለሙቁረጡ እንደገና ተጨማሪ እግረኛ ጦርና አውሮፕላን  ይዞ በ፲፱፻፴፪ ዓ.ም ዝብስት ላይ ገጥሟቸው በጀግንነት ተዋግተው በመመለስ የሕዝባቸውን ነጻነት ጠብቀዋል፡፡
የዝብስቱን ጀግና ካላሸነፈ ዕረፍት አለማግኘቱን የተረዳው  ኮሎኔል ቶሌሬ የተባለው የፋሽስት ጦር መሪ በዚሁ በ፲፱፻፴፪ ዓ.ም. ዝብስት ላይ ለ፫ኛ ጊዜ  ፊታውራሪ አየሌውን ገጥሟቸው የብዙ ወታደሩን ሬሣ ጥሎ ተመልሷል፡፡
ከዚያም ወዲህ ጠላት የብስጭት ጊዜው ሆኖ ለአርበኞችም የንጉሥ ነገሥታቸው መምጫ ሰዓት ተቃርቦ ዘናው በሰፊው ተሠራጭቶ ሞራላቸው በበለጠ የጠነከረበት ጊዜ ስለነበር ፊታውራሪ አያሌው  ጠላትን ንፉሳ ጊዩርጊስ ላይ ተጋጥመው ድል አድርገው መልሰውታል፡፡
በዚሁ ዓመት ለ ፪ኛ ጊዜ ንፉሳ  ላይ ከመጣው የጠላት ጦር ገጥመው መንገዱን ለውጦ እንዲመለስ ሰማድረግ በቆራጥነት ተዋግተው መልሰውታል፡፡
በ፲፱፻፴፪ ዓ.ም በጷጉሜ ወር ፊታውራሪ አያሌው መኮንን እነክቡር ደጃዝማች ከበደ ተሰማንና እና ኰሎኔል ሳንድፎርድን ዝብስት ላይ ለመቀበል በሚዘጋጁበት ሰዓት የእንግዶችን ከግርማዊ ጃንሆይ ተልኰ መምጣት ጠላት ሰምቶ ኖሮ ከየጦሩ ሰፈሩ ያለውን ጦር ሰብስቦ ዝብስት ላይ ለአራተኛ ጊዜ ገጥሞ ከባድ ውጊያ ከተደረገ በኋላ ምኞቱ ሳይሳካለት በመቅረቱ ጊዜያዊ የጫካ ቤታቸውን ብቻ በጣለው የአውሮፕላን ቦንብ አቃጥሎ ተመለሰ፡፡ ዝብስት ላይ በተደረገው ተደጋጋሚ ጦርነትና ፊታውራሪ አያሌው ባሳዩት ጀብድ የተደነቀ አንድ  በየጦርነቱ ሁሉ  ያልተለያቸው ተከታያቸው እንዲህ ሲል ገጠመ፤
ዝብስት መልካም አገር ዝብስት መልካም ቦታ፣
ታደባድባለች እንደጋለሞታ፤
ይርጋ መስረየስህን ማን አልከው ስሙን፣
ያለፉሽስት ሥጋ የማይቀምሰውን፡፡
ይህ ሁሉ ትግል ከተፈፀመ በኋላ  ለ፪ኛ ጊዜ ይስማላ ላይ መጥቶ የሰፈረው የጠላት ጦር በመከላከል ዕረፍት ስላጣ ካምቱን ለቆ በጌምድር ጠ/ግዛት ውስጥ አርፎ ከነበረው ጦር ጋር ሄዶ ስለተደባለቀ ተከታተሉትና ድኩልካን ከተባለው ቀበሌ ላይ ገጥመው እስከ ምሽጉ ድረስ በመግባት አውድመውት ተመልሰዋል።
ከዚያም ወዲህ በ፲፱፻፴፫ ዓ.ም ለ፪ኛ ጊዜ አለፉ ሻሁራ ላይ የሰፈረውን የጠላት ጦር በመግጠም ምሽጉን አፍርሰው ድል አድርገው ካባረሩ በኋላ ነጻ አድርገው ያስተዳድሩት በነበረው የአቸፈር ግዛታቸው ላይ  በሻሁራው ጦርነት ነጻ ያወጡትን አለፉን ደርበው  ማስተዳድር ጀመሩ። ባሕር ዳርን ለማስለቀቀ በተደረገው ዘመቻም ትልቁን ድርሻ የተወጣው የቢትወደድ መንገሻ ጀምበሬና  የፊታውራሪ አያሌው መኮንን ጦር ነበር። ከዚህ በኋላ ነበር ንጉሡ ወደ አገራቸው ሲመለሱ ከፋሽስት ነጻ በነበረው የነፊታውራሪ አያሌው መኮንን ግዛት አድርገው ደብረ ማርቆስ የገቡት። ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የኢትዮጵያን ምድር ረግጠው የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ምድር የሰቀሉበት ጎጃም ውስጥ የሚገኘው በላያ ከፋሽስት ነጻ የወጣው በፊታውራሪ አያሌው መኮንን ጦር ተጋድሎ ነበር።
ንጉሡም በሱዳን በኩል  አድርገው ጎጃም እንደገቡ የተበሏቸውና ወደ ደብረ ማርቆስ ሲያልፉ  ቡሬ ድረስ የሸኟቸው ፊታውራሪ አየሌው መኮንን ነበሩ።  ከዚህ በኋላ የአገር ግዛት ሚኒስትር መስሪያ ቤት በግንቦት ወር ፲፱፻፴፫ ዓ.ም  ተመስርቶ የአገር አስተዳደር ሲደለደል ፊታውራሪ አያሌው መኮንን ያገውምድር አውራጃ ገዥና የአቸፈር ወረዳ የበላይ አስተዳዳሪ ሆነው ተሾሙ፡፡
በ፲፱፻፴፭ ዓ.ም ደግሞ ደጃዝማች ተብለው ወደ አቸፈር ግዛታቸው ተመልሰው ከቆዩ በኋላ በ፲፱፻፵፪ ዓ.ም እንደገና ያገው ምድርና  የባሕር ዳር አውራጃ አስተዳዳሪ ሆኑ።  በ፲፱፻፵፫ ዓ.ም የቆላ ደጋ ዳሞት አውራጃ አስተዳዳሪ ሆነው በመሾም ፲፰ ዓመት ሙሉ በመልካም መግባባት አስተዳድረዋል።  በ ፲፱፻፵፫ ዓ.ም ደግሞ  የቢትወደድ ማዕረግ አግኝተዋል፡፡
ከዚያም በ፲፱፻፷፩ ዓ.ም ለ፫ኛ ጊዜ ያገው ምድር አውራጃ ገዥ ሆነው በመሾም እስከ በ፲፱፻፷፪ ዓ.ም መጨረሻ ድረስ ሠርተዋል፡፡
ቢትወደድ አያሌው ከዚህ በላይ በመጠኑ በተጠቀሰው አገግሎታቸው ከግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሰ የሚከተሉትን ሽልማቶች ተሸልመዋል፤
1. የአርበኝነት ሜዳይ ባለ ፬ ዘንባባ
2. የድል ኰከብ ሜዳይ
3. የኦሜድላ መታሰቢያ ሜዳይ
4. የቅዱስ ጊዮርጊስ የጦር ሜዳ ሜዳይ ባለ፫ ዘንባባ
5. የኢትዩጽያ የክቡር ኰከብ አዛዥ መኰንን ኒሻን
6. የኢትዩጽያ የክቡር ኰከብ ታላቅ መኰንን ኒሻን
7. የዳግማዊ ምኒልክ ታላቅ መኰንን ኒሻን
ዳሩ ግን ሰው ሆኖ ተፈጥሮ ምንም ጀግና፣  ደግ፣  አዋቂና በሰውም ዘንድ የተወደደና የተከበረው ቢሆን ከመሞት የሚቀር ባለመኖሩ ፣ ባደረባቸው ሕመም ምክንያት ባሕር ዳር በፈለገ ሕይመት ሆስፒታል ሲረዱ ቆጥተው በተመለዱ በ፸፪ ዓመታቸው ሐምሌ ፳ ቀን ፷፫ ዓ.ም ከዚህ ዓመት በሞት ተለይተዋል፡፡ ከዚህ አለም ማለፋቸው እንደታወቀ እስከሬኑ ዳንግላ ከተማ ወደሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ተወስዶ ጸሎተ ፍትሐት ሲደረግለት አድሮ ሐምሌ ፳፩ ቀን ፷፫ ዓ.ም የጐጃም ጠቅላይ ግዛት እንደራሴ  ክብር ደጃዝማች ደረጃ መኰንንና ምክትል እንደራሲው ክቡር ደጃዝማች ደረሰ ሽፈራው፣  የጠቅላይ ግዛቱ ሊቀ ጻጻስ ብፁዕ አቡነ ማርቆስ ፣ ያውራጃው ገዥዎችና ከፍተኛ ሹማምንት፤ በየጦሩ ሜዳ ያልተለያቸው በብዙ ሺህ የሚቆጠር የቢትወደድን የጀግንነት ሞያና  የጦር ሜዳ ውሎ እንዲሁም በአስተዳደር ዘመናቸው  የነበራቸውን  አዋቂነት በሽለላ፣  በፉከራና በእንጉርጐሮ  የሚገልጽ የአቸፈር አርበኛ፤  ለኀዘኑ ተካፉይ ለመሆኑ ከልዩ ልዩ አካባቢ የተሰበሰበው ቁጥሩ ከ፲ሺህ በላይ የሆነ ሕዝብ በተገኙበት  እስከሬኑ ከቤት ወጥቶ የጦር መሣሪያ በያዙ አርበኞች ታጅቦ ጥቂት እንደተጓዘ ከደብረ ማርቆስ የተላከው የክብር ዘበኛ ሠራዊት የክብር ሰላምታ ሰጥቶ ከተረከበው በኋላ ጉዞው ወደ አጉንታ ማርያም ቀጥሎ ከቤተ ክርስቲያኑ እንደደረሰ ጸሎተ ፍትሐቱ ተፈጽሞ ሠልፈኛው የመጨረሻ በጀኔራልነት ማዕረግ የክብር ሰላምታ ከሰጠ በኋላ የኀዘን ማርሽ አሰምቶ ሲጨርስ አጭር የሕይወት ታሪካቸው ተነቦ አስከሬኑ በተዘጋጀለት  የአርበኞች ሥፍራ በክብር አርፏል።
አስከሬኑም በክብር እንዳረፈ እንደራሴው ከግርማዊ ንጉሠ ነገሥት የተላከውን የኀዘን መግለጫ ቴሌግራም ለክብርት ባለቤታቸው እስረከበዋል፡፡ የቢትወደድ አየሌውን የሕይዎት ታሪክ፤ በተለይም ፍጻሜያቸውን ዘለግ አድርጌ ለማቅረብ የፈለግሁት በጃንሆን ዘመንና ከሳቸው በኋላ የመጡት ደርግና ወያኔ አርበኞቻችንን እንዴት እንደያዟቸው አንባቢ ይገነዘብ ዘንድ ነው።  አርበኞችን አርቀዋል እየተባሉ የሚወቀሱት ግርማዊ ጃንሆይ ለአገራቸው የደሙ አርበኞቻችንን  ቀደም ሲል እንደቀረበው ይሾሙ ይሸልሙ፣ በኑሮም እንዳይቸገሩ ማደሪያ ይሰጡና  የሕይወታቸው ፍጻሜ ሲሆንም የቻሉትን ተገኝተው በማስቀበር፣ ያልቻሉትን ደግሞ ሽኝታቸውም ያማረ ይሆን ዘንድ  ለቢትወደድ አያሌው እንደተደረገው ያደርጉ ነበር። አዲስ አበባ የሞቱት አርበኛው ደጃዝማች ነጋሽ በዛብህ ከዚህ አለም ሲያልፉ ንጉሡ ቆመው አስቀብረዋል።
እነ ቢትወደድ አያሌው ካለፉ ከሶስት ዓመታት በኋላ  ወደ ሥልጣን የመጣው ደርግ ግን አይደለም አርበኞችን ሊያከብር እንደ ቢትወደድ አያሌው ላገራቸው የደሙ ጀግና አርበኞችን ሁሉ  <<ፊውዳል>> በማለት ያፈሩትን ሀብት በመውረስ ያለፍርድ  የገደላቸው በአውሮፕላን ጭምር አሳዶ  በመደብደብ ነው። እንደ ቢትወደድ አያሌው ያገራቸው የደሙቱ የጎጃሙ ስመ ጥር አርበኛ ደጃዝማች ስሜነህ ደስታ የተገደሉት በደርግ የአውሮፕላን ድብደባ ነው፤ የሸዋው አርበኛ ደጃዝማች ፀሐዩ እንቁ ሥላሴ ከሶስት ወንድሞቻቸው ጋር በግፍ  ያለፍርድ የተገደሉት በደርግ ነው። አርበኞችን እንደዚህ አድርገው የገደሉት ደርጎች ዛሬም ንጉሡን  በአርበኞች አያያዝ እየወቀሱ መጽሐድ ይጽፋሉ።
ፋሽስት ወያኔና ናዚ ኦነግ ደግሞ  በዘመናቸው ደርግ ሳያጠፋው ያገኙትን ንጉሡ ላርበኞች ያቆሙትን መታሰቢያ አጥፍተው ጀግኖቻቸን ማስታወሻ እንዳይኖራቸው አድርገዋል።  በፋሽስት ወያኔና በናዚ ኦነግ ዘመን  አዳማ ሆስፒታልና ትምህርት ቤት ተደርገው የተሰየሙት ንጉሡ፤
ኃይለ ማርያም ማሞ የጦሩ ገበሬ፤
ፈረሱን እንደሰው አስታጠወው ሱሬ፤
ለተባለላቸው  ለጀግናው አርብርኛ ለደጃዝማች ኃይለ ማርያም ማሞ ያቆሙትን መታሰቢያ ነው። በአገር ገንጣዩ በሓዬሎም አርአያ ስም  የተሰየመው  የወያኔ የጦር ማሰልጠኛም ለአርበኛውና የኢትዮጵያ የልማት አባት የሚል መጠሪያ ለነበራቸው ለጀኒራል ሙሉጌታ ቡሊ መታሰቢያ እንዲሆን ንጉሡ የሰየሙትን ማስታወሻ ነው።
እነ ቢትወደድ አያሌው መኮንን ነጻ ባወጡት ባሕር ዳር የሚገኘው የአውሮፕላን ጣቢያ ፋሽስት ወያኔ ኢትዮጵያን በወረረበትና ኢትዮጵያን የአማራው መታረጃ ቄራ ባደረገበት እለት በግንቦት ፳ ስም እየተጠራ ይገኛል። ይህንን በሕዝባችን ላይ የተፈጽመ ንቀትና በግንቦት ፳ ስም ተሰይሞ ባሕር ዳር የሚገኘውን ውርደት የአባቶቹ ታሪክ ወራሽ የሆነው የኔ ዘመን ወጣት ቀይሮ ስያመውን  ክብሩ ለሚገባቸውና ከተማውን ነጻ ባወጡት በነቢትወደድ አያሌው  መኮንን ስም እንዲጠራ በማድረግ ታሪክ እንደሚሰራ አልጠራጠርም።
ታሪኩን ለመጻፍ የተጠቀምኳቸው ምንጮ፤
1. ደጃዝማች ከበደ ተሰማ  “የታሪክ ማስታወሻ”  በሚል በ፲፱፻፷፪ ዓ.ም. ካሳተሙት  የታሪክ መጽሐፍ ከገጽ 233-276;
2. Shireff, D. (2009). Bare feet and bandoliers: Wingate, Sandford, the Patriots and the part they played in the liberation of Ethiopia. Pen & Sword: ከገጽ 35 – 45;
3. Pearce, J. (2014). Prevail: The Inspiring Story of Ethiopia’s Victory over Mussolini’s Invasion, 1935-? 1941. Simon and Schuster: ከገጽ 520- 530;
4. Sandford, C. L. (1946). Ethiopia under Haile Selassie. JM Dent & Sons, Limited፡ ከገጽ 106 – 115 ;  እና
5.  የክቡር ቢትወደድ አያሌው መኰንን <<አጭር የሕይወት ታሪክ>>  በሚል በቤተሰብ ከተዘጋጀ ሰነድ ከገጽ1- 4 ከተጻፈው ከነ ፎቶግራፉ።
Filed in: Amharic