>
5:13 pm - Monday April 19, 8990

የብልጽግናው የመሰናክል ችካሎች!  (ዳንኤል ሺበሺ)

የብልጽግናው የመሰናክል ችካሎች! 

ዳንኤል ሺበሺ
… እባብ ቆዳውን ቢቀይር እንሽላሊት አይሆንም!! እንዲያው ጠንክሮ፣ ታድሶና ብዙ መርዝ በዕጢዎቹ አከማችቶ፣ በልምድ፣ በታክቲክና በስልት ተክህኖ፣ በልምድ ፣ በአካላዊ እንቅስቃሴና በጡንቻ ፈርጥሞ የሚመለሰ ወጣትና አደገኛ እባብ እንጂ!!!
 
ማግለያ ወይስ ፖሊስ ጣቢያ?

<><><><><><><><><><><>

< PS
ፎቶው በ2006 ዓ/ም ከዛሬ 6 ዓመታት በፊት ሀብትሽ ጋር ወላይታ እና  አርባ ምንጭ ሰላማዊ ሰልፍ በመራንበት ወቅት የተነሳ ነው።  ያን ጊዜ የገጠመን ፈተና ዛሬም በጥሬው መኖሩን ለገለፀበት ፅሁፍ ማስታወሻ እንዲሆን ተጠቀምኩት።
ሐሙስ ግንቦት 6ቀን፡ 2012 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ወደ 400 ኪሜ ያህል ርቄ ደቡብ ክልል ቁጫ ወረዳ  ሰላምበር ከተማ ስደርስ የተሰናዳልኝ ነገር <ሽልማት ሳይሆን እስር> ነበር። ድብደባ አለመፈጸሙ፣ በቀዝቃዛ ክፍል አለመታሰሬ፣ ከተሳቢ ነፍሳት ጋር መታሰር እንጂ በኳራንታይን ስም ወደ ሌላይኛው ማዕከላዊ ገባሁ ። ነገር ግን ኮሽ ባለ ቁጥር ከመጮኸ እስቲ የነገሮቹን አዝማሚያ ማጤንና ጊዜ መስጠቱን ምርጫዬ አድርጌ ለሁለት ቀናት ያህል ዝምታን፤ በርጋታ ማስረዳትን/መነጋገርን መረጥሁ ። ሆኖም ግን ከብልጽግና ካድሬዎች በኩል የሚፈጸሙ ነገሮች ትዕግሥትን የሚፈታተኑ እየሆኑ መጡ። በቅድሚያ ኮሮናን እንደ ሰበብ ወስደው ለ14 ቀናት፤ በመቀጠልም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሰበብ በመፈበረክ ወደ ፍ/ቤት በመውሰድ በጊዜ ቀጠሮ ለተወሰነ ሳምንታትን ለማንከራተት መወጠናቸው ገባኝ። የተካኑበትም ነውና። ውሸት የህይወታቸው አካል፣ የእንጀራቸው ገመድ ነውና።
ከአዲስ አበባ ቀጥታ ወደ ጎፋ ሳውላ የሚወስደው ዋና መንገድ ሰላምበርን እንደ ደሴ ከተማ በርዝሜቷ ለሁለት ከፍሎ ያቋርጣል ። የጉዞዬ ምክንያት የነበረው የማልቀርበት ዘመድ ከዚህ ዓለም በሞት በመለየቱ ነበር ። ከኮሮና ወረርሽኝ በፊት 62 ሰው የሚጭን አገር አቋራጭ አውቶብስ በኮቪድ_19 ምክንያት 31 ሰዎችን ብቻ ነበር ይዘ የዘለቀው። ከእነዚህ ውስጥ #24 ተሳፋሪዎች ሰላምበር ከተማ የወረዱ ሲሆኑ ቀሪዎቹ ሰባት ሰዎችንና በወራጅ ምትክ ከሰላምበር የተሳፈሩ መንገደኞች ይዞ ቀሪውን #70 ኪ.ሜትሩን ተጉዘው ወደ #ጎፋ_ሳውላ የሚዘለቁ ናቸው ። በጉዞው ወቅት 5_ጊዜ በሙቀት መለኪያ (Thermosenser) የሙቀት ናሙና  የተወሰደ ሲሆን #(36.4, 36.1, 35.8, 36.2, 34.4)°c የእኔ የቀኑ አማካይ የሙቀት መጠን #35.8 ነበር። ዕሁድ ግንቦት 9ቀን፡2012 ዓም ወደ ለይቶ ማቆያ ከገባሁበት እስከ ወጣሁበት (ማክሰኞ ግንቦት 11ቀን፡2012 ዓም) በየቀኑ በተወሰደው ናሙና መሠረት ከፍተኛው 36.0°c ዝቅተኛ 34°c ነበር። ውጤቱ ተመሳሳይ ነው ማለት ይቻላል። ለነገሩ በአዲሳባም ቢሆን በተለካሁባቸው ሁሉ ከዚህ የተለየ አልነበረም ። የተጓዝንበት የአውቶቡስ ውስጣዊ ክፍሎች በሙሉ በሳኒታይዘር በደንብ የታሹና ንጽህናው የተጠበቀ ሲሆን አንድ ወንበር ለአንድ ሰው ነበር ተቀምጠን የተጓዝነው ። በዚህ አጋጣሚ በትራንስፖርት ዘርፉ እየተደረገ ያለው ጥንቃቄ ተስፋ ሰጭ እንደሆነ መመስከር ይቻላል ።
ከእኔ ጋር ተጉዘው በሰላምበር ከተማ ከወረዱት ውስጥ አራታችን(4) የአንድ ቤተሰብ አባላት ስንሆን የጉዞው ዓላማችንም መራር ሐዘን ምክንያት እንደነበረ ከላይ ጠቅሽያለሁ ። ከተጓዦቹ ውስጥ ሃያዎቹ #20 በራሳቸው ጉዳይ ሲሆኑ፤ አንዳንዶቹን በስም ባይሆንም በመልክ የማውቃቸው ናቸው።
ከሐሙስ እስከ ዕሁድ (ከ6-9/9/2012) በከተማይቱ ሰላምበር በከፍተኛ ጥንቃቀ ቆይታ አድርግያለሁ። ርቀትን ፣ ንጽሕናን፣ የሰላምታ ግንኙነትን ጨምሮ ሌሎች የእጅ ንክክዎች፣ ማስክ፣ ሳኒታይዘር ወዘተ የሚባሉ የጤና መመሪያን ተግባራዊ አድርግያለሁ/ናል ። ይህም ያደረኩት ህግ ከማክበርም ባሻገር ለራሴና በዕድሜ የገፉ ወላጆቼን ጨምሮ ለመላው ቤተሰቦቼ በማሰብና፣ ለከተማው ሕዝብም እንደ ፖለቲካ ሰው አርአያነቴን ለማሳየት ነበር ። ደግነቱ ማኅበረሰቡም ቢሆን እኔ ከጠበኩት በላይ ንቁና ጠንቃቃ ነበረና በጣም ደስተኛ ነበርኩ።
…   …
ከዚህ ኋላ ነበር ፈጽሞ ያልጠበኩት ነገር ገጠመኝና ነገሮቹ የፖለቲካ መልክ መያዝ የጀመሩት !
… “በሬ ከአራጁ ጋር ይውላል” እንዲሉ ሆነና የሰላምበር ዙሪያ ወረዳ እና የቁጫ ወረዳ ካድሬዎች በየመንገዱ ሳገኛቸው በቅርብ ርቀት በጥሩ ፈገግታ ሰላምታ እንለዋወጣለን። በጎን ደግሞ እኔን በቁጥጥር ሥር ለማዋል መዶለት የጀመሩት ወደከተማዋ ከገባሁበት ዕለት ጀምሮ፤  በዞን፣ በክልልና በፌዴራል ካለው ስውሩ መዋቅሮቻቸው (chain) ጋር መነጋገር እንደተጀመረ፤ እንዲሁም ቀደም ስል አንድ ወረዳ የነበረው አሁን ሶስት ወረዳ በመሆኑ፤ የሁለቱ ወረዳዎች የጋራ ዋና ከተማቸው ሰላምበር በመሆኗ የትኛው ወረዳ ፖሊስ መያዝ እንዳለበት የሥልጣን ክርክር እንደተደረገ ከተፈታሁ በኋላ ለማወቅ ችያለሁ።
በዚህ ጉዳይ ዋና ተዋንያን የነበሩት እነ፦
1ኛ. አቶ አላተ ሽብሩ (የቁጫ ወረዳ ም/አስተዳዳሪ)፣
2ኛ. አቶ ትቆ ትላንተ (የቁጫ ዋ/አስተዳዳሪ)፣
3ኛ. አቶ ብርዙ ባዴ (የብልጽግና ፓርቲ ገጠር ፖለቲካ አደረጃጀት ኃላፊ)፣
4ኛ. አቶ ሶፎንያስ ሶርሳ (የሰላምበር ከተማ ጤ/ጥ/ጽ/ቤት ኃላፊ)፣
5ኛ. አቶ ተመስገን ታዴዎስ (የቁጫ ወረዳ ጤ/ጥ/ጽ/ቤት ኃላፊ)፣
6ኛ. ኢንስፔክተር አብርሃም ቡሄ (የሰላምበር ከተማ ፖሊስ አዛዥ) እና
7ኛ. አቶ መኮንን ጋቲሶ (የቁጫ ወረዳ ብልጽግና ጽ/ቤት ኃላፊ) ናቸው።
ከእነዚህ ውስጥ በተ.ቁ. 7 ላይ የተጠቀሰውና ስሙ አቶ መኮንን ጋቲሶ የተባለው አመራር “አቶ ዳንኤል’ን የምንፈለገው በወንጀል ጉዳይ ከሆነ በየትኛው ፖሊስ ይያዝ? በከተማው ፖሊስ ወይስ በወረዳው? በሚለው ነው መነጋገር ያለብን፤ ይህንንስ ለማድረግ ምን ተጨባጭ ወንጀል ፈጽሟል? አይ! ከኮሮና ጋር በተያያዘ ከሆነ ደግሞ ይህ የጤና ባለሙያዎች ጉዳይ ነው፤ እኛ ለምንድነው ከሙያችን ውጭ በጤና ባለሙያ ጉዳይ ጣልቃ የምንገባው” በማለት በስብሰባቸው ወቅት እንደተቃወማቸው ከአስተማማኝ ምንጭ ማረጋገጥ ችያለሁ ። ይሁን እንጂ ከመታሰር አላዳነኝም።
…   …
ዕሁድ (09/9/12) አመሻሽ በግምት ከምሽቱ 12፡15 ገደማ ከአንዱ ቅርብ ዘመዴ ጋር ለሁለት ሆነን እንደ ማንም ከተማዋ ነዋሪ ነፋስ እንውሰድ ብለን ወደ አንዱ ወንዝ (በአካባቢው መጠሪያ <ጎርማ> ተብሎ ወደሚጠራው) አከባቢ ቀስ ብለን ወክ (walk) እያደረግን ሳለ ቀደም ስል ማለትም በቀዳማዊ ኢህአዴግ ዘመን ለረጅም ጊዜያት የወረዳዋ አስተዳዳሪ ሆኖ (በተለይም በምርጫ 97 ወቅት እና እስከ ዛሬ ድረስ) እኔን ጨምሮ የተቀረውን ሕዝብንና የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አባላት ላይ ብዙ መከራ ሲያዘንብ የነበረውና የምርጫ ውጤት እንዲቃጠል በማድረጉ የተመሰከረለት፤ በኋላም ዴኢህዴን_ኢህአዴግ ለውለታው የትም/ት ዕድል ሰጥቶት ከሲቪል ሰርቭስ ዪኒቨርስቲ ከተመለሰ በኋላ በአሁኑ ሰዓት ቦታ እስክለቀቅ በሚል በም/አስተዳዳሪነት እንዲሰራ ተሹሞ እየሰራ ያለና ከእኔ ጋርም በደንብ የምንተዋወቅ፤ ስሙም አቶ አላቴ ሽብሩ የተባለ ካድሬ በመንገድ ላይ አግኝቶኝ በቅርብ ርቀት በጥሩ ስሜት ሰላም ከተባባልን በኋላ ወደየ አቅጣጫችን ተጓዘን።
ከዚያም #10-ደቂቃ እንኳን ባልሞላ ጊዜ ከኋላችን ሶስት ሞተር ቫይክል፣ ሁለት እግረኛ ወታደሮች እና አንድ አንቡላንስ ተከትሎን መጣና ከፊት ያለው ሞተረኛ ጠራን። ሲቭል ልብስ ለብሷል። ከፊል ግንባሩ፣ ዓይኑ፣ አፍንጫውና ከአፉ ውጭ ሌላው ከአንገት በላይ ያሉ አካላት በራስ መከናነቢያ ሹራብ ተሸፍኗል፤ የእጅ ጓንትም አጥልቋል ። ከዛ በፊት ግን ከፈጣን ፓትሮል መኪና ወርደው ከመንገዱ ግራና ቀኝ ቦታ ቦታቸውን የያዙ በቁጥር ስድስት የሚሆኑ ወታደሮችን በቅርብ ርቀት አይቼያቸው ነበር፤ ነገር ግን ለመደበኛው የፖሊስ ሥራ የተሰማሩ መስሎኛል እንጂ ለእኛ ስለመሆናቸው ልብ አላልኩም ነበር ። ለነገሩ እንዴትስ ልብ ልበል? ጊዜው ያ! ጊዜ አይደለምና፤ ያነማ ቢሆን ኖሮ ለጥርጣሬና ለስለላ ማን ደርሶኝ?
…   …
ከፊት ያለው ሞተረኛ ጠራንና “ኢንስፔክተር አብርሃም እባላለሁ! የሰላምበር ከተማ ፖሊስ አዛዥ ነኝ” ሲል ሌላይኛውም ተጠግቶ አቶ ብርዙ እባላለሁ! የሰላምበር ከተማ የሆነ? ዘርፍ ኃላፊ ነኝ (በደንብ ሳልሰማ አለፈኝና ወደ እስር ቤቱ ለክትትል ስመላለስ የገጠር ፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ መሆኑን አወቅሁ) እያሉ ሁለቱም በአንድ ላይ ወደ እኔ ተጠጉ ። እኔም እየተለመደ በመጣው ኮሮና’ዊ ሰላምታ ልውውጥ ቀኝ እጄን በደረቴ ላይ እየለጠፍኩ ሰላም! ኢንስፔክተር!
 እኔም ዲንኤል ሺበሺ እባላለሁ ምን ሊታዘዝ ጌታዬ? አልኩተኝ። “አንተ ፀጉር ልውጥ ትመስለኛለህ እንፈልጋችኋለን”  አለኝ። አይ! ተሳስተሃል <<እኔኮ የከተማዋ ልጅ ብቻም ሳይሆን በምርጫ 2002 መድረክ-አንድነትን ወክዬ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተወዳድሬ ኢህአዴግን በዝረራ ያሸነፍኩ ሰው መሆነን እያስታወስኩለት፤ እንደ አሁኑ ጊዜ  አበል፣ ደመወዝ ፣ ጥቅማጥቅም፣ እንዲሁም ተሽከርካሪና ማዕረግ … ባልነበረበት ወቅት እግሬ እስኪቀጥን ድረስ ወረዳዋንም ሆነ ከተማዋን ፈግቼ ያቃናሁ ንጹህ የከተማዋ ልጅም ነዋሪም ነኝ! ባይሆን አንተ ነህ ፀጉር ልውጥ!>> እያልኩ ትንሽ ወደ እነሱ ተጠጋሁና ግን በሰላም ነው የፈለጋችሁኝ? ስለው አይ! በሰላም ነው፤ ከየትና መች ነው የመጣሄው? የኮሮና ሙቀት ተመርምረሃል? ብሎ ሲጠይቀኝ፤ አዎን!  <ከመጣሁ ዛሬ 4ኛ ቀኔ ነው (ማለትም ሐሙስ ግንቦት 6ቀን፡2012 ዓም)፤ ወደ ከተማዋ ከገባሁ በኋላ ግን የመረመረኝ የለም፤ ሌላውም ሕዝብ እየተመረመረ አይደለም።
በጉዞው ወቅት በየመንገዱ ወደ አምስት ጊዜ ተመርምሪያለሁ፤ የሙቀት መጠኔም በአማካይ ከ34-36°C ውስጥ ይገኛል ብዬ መለስኩለት። የመጨረሻውና ወደ ከተማዋ መግቢያ ላይ ባለው ምርመራ ጣቢያ ስመረመር (የጣቢያው ስም ‘ማንቻ’ ወይም አልፎ አልፎ ‘ዳና’ ይባላል) የተነበበው #36.1°C እንደሆነ ነገርኩለት። እሺ አሁን በተጨማሪ እንመረምርሃለን ወደ አምቡላንሱ ግባልን” ተባልኩ። እኔን ለመያዝ ከመጡ ፖሊስ አባላት ውስጥ ሁለቱ እና ከእኔ ጋር ከነበረው ዘመዴ ጋር ለአራት ሆነን ወደ አምቡላንሱ ውስጥ ገባን ። ከዚያም ወደ ሰላምበር ፩ኛ/ደ/ት/ቤት ቅጥር ግቢ አደረሱን።
…   …
የሙቀት መለኪያ (Thermosenser) የያዘ ባለሙያ ተጠርቶ በግምት 1:00 ስዓት ያህል ከቆየ በኋላ መጣና ሲያነብ የእኔ #34.9°c እንደሆነ እየነገረኝ እኔንም አዙሮ አሳየኝ። ከዚያም አንደኛው ወታደር በፖሊስ ጣቢያ እንዳለ እስረኛ “እዚያጋ ቁጭ በል!” አለኝ አንድ በውጭ ተጥሎ የበሰበሰ የተማሪዎችን ወንበር እያሳየኝ። ከዚያም እስከ ምሽቱ 5፡15 ድረስ ቁጭ ብለን ቀረን። በመጠናቸው የወንዝ ዳርቻ ቢምቢዎች  የሚያካክሉ እንደ ጉድ ይለብልባሉ ። አንዴ ደም መቅዳት ከጀመሩ ለነፍሳቸው እንኳ የማይሳሱ ቢምቢዎች ናቸው፤ ይመጣሉ፣ በጆሮ ግንዳችን በቋንቋቸው ይዘፍናሉ ። ከክፍል ውጭም ውስጥም ለቢምቢዎች ልዩነት የለም። ስወጉ እንጂ ስቀመጡ አይታወቁም። በብልጽግና ካድሬዎች የታዘዙ እስኪመስል ድረስ ነፍስን ያሰቃያሉ። መብራት ጨርሶ የለም፤ እንዲኖርም አልተፈለገም። በግቢውም ቢሆን መብራት የለም። ድቅድቅ ጨለማ። ውሃ የለም፣ የወባ ትንኝ መከላከያ አጎበር፣ የተባይና የነፍሳት መግደያ ፕሊቲ፣ የእጅ መታጠቢያም ሆነ የሻውር ውሃና ሳሙና የለም። ባጠቃላይ ለኮሮና ሲባል ምንም ዝግጅት አልተደረገም። ምንም ጥንቃቄ ባልተደረገ ወይም ባልታከመ ክፍል በር ላይ ቁጭ አልን። እንደ እስር ቤት ሲመሽ በሩ ከውጭ በኩል በፖሊስ ይከረቸማል፤ ስነጋ በፖሊስ ይከፈታል። ከጥበቃ ውጭ ሌላ ሰው ዝር የማይልበት። ማታ ማታ ቢምቢዎች፣ ጉንዳኖችና ሌሎች በራሪ ነፍሳትን ጨምሮ በእግራቸው የሚራመዱና የሚሳቡ ትላትሎች፣ እባብ ወዘተ ነፍስህን ያውካሉ፤ በምድርና በጣሪያ ይርመሰምሳሉ ። ከተቆለለው ኩይሳ ውስጥ እንደ ምንጭ ይፈልቃሉ ። ነገሩ ምሪር ስለኝ ለአንዱ ከተማዋ ባለሥልጣን  (ይህን ጽሁፍ እያዘጋጀሁ ሳለ በሆነው ነገር ሁሉ ተጸጽተው ይቅርታ ስለጠየቀኝ ስሙን መጥቀስ አልፈለኩም) ስልክ መታሁና አጥብቀ እየወቀስኩ ፦
የሶማሌው ዐብዲ ኤሌ ነው ሰውን ልጅ ከዱር አራዊት ጋር የሚያስረውና እናንተ እንደት እኛን ከእባብ ጋር ታስራላችሁ? ብዬ ጠየኩ ። በምላሹም “እኛም ከእባብ ጋር ነን ያለነው፤ ምንም አዲስ ነገር የለም!” ብሎ መለሰልኝ፤ ቀጠልኩና በአሁኑ ሰዓት አንተ በቤትህ ከእባብ ጋር ነው ወይ የሚትተኛው? ብዬ ስጠይቀው “አዎን! ከእባብ ጋር ነው የምኖረው” በማለት መለሰልኝ። ከዚያም ምን ብዬ መመለስና መነጋገር እንዳለብኝ ግራ ገብቶኝ እሺ ቻው! አመሰግናለሁ ብዬ ስልኬን ዘጋሁ። [… ውድ አንባቢያን ይህ! ለህልናዬና ለሃይማኖቴ ስል ቃል በቃል የጻፍኩት የስልክ ንግግር ነው]
…   …
ባጠቃላይ በእኔ ላይ የተፈጸመው ነገር በወረዳ አመራሮቹ ዕውቀት፣ ኃላፊነትና ፍላጎት ብቻ የተፈጸመ አይደለም ። ከወረዳ እስከ ፌዴራል ድረስ በተዘረጋው በስውሩ መዋቅር እንጂ። የአዲስ አበባዎቹን እነ ተስፋዬ ቤልጅጌ’ን ፣ የደቡቡ’ን እነ ጥላሁን ከበደ’ን መጥቀስ ይቻላል። አይ! የለንበትም ካሉ ወደፊት በሚወሰደው እርምጃ የምናረጋግጥ ይሆናል ። ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ በወረዳ ደረጃ ግን ዋና ተዋንያንና የአፈናው መረብ አባል የሆኑትን ዝርዝር ከላይ ጠቅሽያለሁ። ከዚህም ባለፈ በተለይ ሁለቱ  የፖሊስ አባላት በግላዊ ባሕርያቸው እና በሥነ ምግባራቸው በሕዝቡ ዘንድ ከፍተኛ ቅሬታ ውስጥ የገቡ ናቸው። ጾታዊ ትንኮሳን ጨምሮ በምሽትና በአሳቻ ቦታዎች ከአንድ ፖሊስ ባልደረባ ፈጽሞ የማይጠበቅ ነገሮችን እንደሚፈጽሙ በመረጃ ደረጃ ተነግሮኛል። የሚመለከተው አካል ልከታተል ካለ ብዙ ዓይኖቹ አለውና በማስረጃ ይጠይቃቸው ይሆናል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ ።
…   …
ፈጽሞ በኮሮና ኮቪድ-19 የተጠረጠሩ ሰዎችን ማግለያ/ማቆያ ልባል በማይችል ክፍል ውስጥ ከእኛ የቀደሙ ሁለት ሰዎች ነበሩ። አባትና ልጅ ናቸው። ልጁ ሙሴ፤ አባት ሙቁሴ። ከ10 ቀናት በላይ ሆኗቸዋል። አብዘኛውን ጊዜ እንደ ባሕርይ ሆኖባቸው ከወረዳዋ ካድሬዎች ጋር ተስማምተው የማያውቁ ነዋሪዎች ሲሆኑ ፍትህ ስጓደል፣ መብት ስነካ ወዲያው ስሜታቸውን በማንፀባረቅ ይታወቃሉ ። ይንን የሚያደርጉት ግን የፓርቲ አባል ሆነው አይደለም። በዚህም ምክንያት በካድሬዎቹ ጥርስ ገብተው ብዙ ዋጋ ከመክፈላቸው የተነሳ በተመልካቹ፣ ቤተሰቦቹ፣ በወዳጆቹ እና በዘመድ አዝማዱ ዘንድ በተገላቢጦሹ እነሱ ይኮነናሉ፤ እኔን ግን ከእነሱ የምለየው የፓርቲ አባል መሆኔ ይመስለኛል።  ዛሬ ከእነሱ ጋር እዛው ክፉ ቦታ ተገናኘን። አብረው ይበላሉ፣ አብረው ይስተናግዳሉ፤ ልጅ አባቱን በለመደው ኢትዮጵያዊያን ባሕል መሠረት ይንከባከባል፤ የተለመደው ማህበራዊ ህይወታቸውም  እንዳለ ቀጥሏል ። ሁለቱም በጥሩ ሁኔታ አስተናግደውኛል። ምስጋናዬ ይድረሳቸው ። በቆይታችን ወቅት የደረሰባቸውን መከራ በስፋት ያጋሩኝ ሲሆን ስንቱን ጽፌ ስንቱን እተዋለሁ? ነካክቼ ከመተው መዝለልን መረጥሁ ።
…   …
አንዱን ክላሽንኮቭ ጦርነት መሣሪያ በደረቱ በኩል ወደ ታች ያንጠለጠለውን ወታደር “ሣጅን” ብዬ ጠራሁና ምንድነው እየሆነ ያለው? አልኩኝ። ሰዓቱኮ ከምሽቱ 5:ስዓት ሆኖ አልፏል። ለምን የምንገባበትን ክፍል አታሳየንም? ብርዱ፣ ቢምቢው አስጨንቆናልኮ አልኩት። እሱም “አይ! እኔ የማውቀው ነገር የለም፤ የእኔ ሥራ መጠበቅ ነው” ብሎ በአጭሩ መለሰልኝ። ግን ወዲያው ዞር አለና ለአለቃው ደውሎ ትዕዛዝ ከተቀበለ በኋላ ክፍሉን አሳየን። ነገር ግን ለማሳደር እንደፈለጉ ስለገባኝ አስቀድሞ ወደ ቤተሰቦቼ ደውየላቸው ነበረና ፍራሽ፣ አንሶላ፣ ውሃ፣ ራት፣ ነጠላ ጫማ፣ ሻማ፣ ሳሙና፣ ሳኒታይዘር፣ ፕጃማ፣ አጎበር የመሳሰሉ ቁሳቁሶችን አምጥተውልኝ ነበር ። እነሱም ወደ ዕኩል ሌሊት ገደማ ፍራሽና ሻማ ይዘውልን መጡ። አልፈልግም ብዬ ስነግራቸው፤ እዛው በረንዳ ላይ ጥለውት ሄዱ ።
…   …
ከላይ እንደጠቀስኩት እኔ ወደ ክፍሉ ስገባ ከእኔ በፊት ማግለያ ክፍል (Quarantin) በሚል ሰበብ ለ10-ቀናት ያህል የቆዩ ሁለት ነዋሪዎች ነበሩ። አባትና ልጅ። አባት ከኮንሶ መምጣቱን ቢነግራቸውም እነሱ ግን ከሞያሌ መጥተሃል በሚል ነበር እንዲገለል የተደረጉት። የልጁ ዕድሜ በትክክል 21ኛውን ዓመት እያገባደደ የሚገኝ ሲሆን  ከሰላምበር ከተማ ወጥቶ አያውቅም ። በጊዜው ሲያዝ ንክክ ሊኖር ይችላል በሚል ጥርጣሬ ሳይሆን አባቱን ሲይዙ ስላመናጨቁትና ስለሰደቡት ልጅ ተበሳጭቶና መቆጣጠር አቅቶት ከኮሚቴዎች ጋር ስለተጋጨ ነበር  ከአባቱ ጋር የተደረበው ። ስለደረሰባቸው በደል በእምባ እየታጠቡ ይተርካሉ ። ሳሙና፣ ውሃ፣ አከባቢው ወባማ እንደመሆኑ መጠን የትንኝ መከላከያ ወዘተ በለሌበት አምጥተው፤ ከእባብና ከትላትል ጋር ስንታገል ነው እዚህ የደረስነው፤ እስካሁን ማንም ጠይቀውን አያውቅም … እያሉ ያሳለፉትን የመከራ ጊዜያቸውን ለፈጣሪ ይናገራሉ፤ ለእኔም ያጫውታሉ ። በወሬ መካከል “እርግጠኛ ነኝ! እግዚአብሔር እኛን ልረዳ ነው አንተን ያስመጣው አለ፤ አባት።” እንዳለውም እኔ ስወጣ አብሮ ነው ከእኔ ጋር የተለቀቁት ።   ከዚህም ሌላ በወረዳዋ ሰበብ እየተፈለገ ወጣቱ አዛውንቱ ይደበደባል፤ ይረገጣል። ጉዳይን በገንዘብ ማስፈፀም እንደተቀደሰ ሽቀላ ይቆጠራል። የተለመደና የተፈቀደ ሥራ ሆኗል። ለዚህ ሁሉ ጥሩ አጋጣሚ የሆነው ኮሮናና አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ነው። ቀስ እያልኩ ነገሮቹን በጥልቀት መከታተልና መረጃ ማሰባሰብ ጀመርኩ። የበፊቱ ቀርቶ እኔ ወደ ከተማዋ ከገባሁበት በኋላ እንኳን በሕዝብ ማመላለሻ አውቶብሶች እና በሌሎች  ትራንስፓርት አማራጮች  ወደ ከተማዋ የገቡ በርካታ ዜጎች እንዳሉ ለማወቅ ችያለሁ ። ግን ዞር ብሎ ያያቸው አልነበረም ። የነገሮቹ ማቀጣጠያ ቤንዚንና ማብረጃ ውሃ ሳንቲም የመኖርና አለመኖር፤ በእጅና በእግር መምጣትና አለመምጣት ነውና። በርግጥ ከመንግሥት (ከፌዴራል እና ክልል መንግሥት) በኩል ኮሮናን በተመለከተ ከቴክኒክ፣  ከተለመደው ደመወዝ፣ ከአበል እና ባጠቃላይ ከመደበኛ በጀት ወጭ ለወረዳው የተደረገ ድጋፍ ባይኖርም ግን ከአከባቢው ሕዝብ የተዋጣ  ገንዘብ በግምት ከ400,000 ብር በላይ  እና ለጊዜው ግምቱ ያልታወቀ ቁሳቁስ ከሕዝቡ የተሰበሰበ ሀብት መኖሩን እየተነገረ ነው ። እኔ ግን በብሩ መጠን ላይ ርግጠኛ አይደለሁም፤ ማለትም ሊበዛም ሊያንስም  ይችላል።
ይሁን እንጂ ራሳቸው ያመኑት ገንዘብና ቁሳቁስ እንኳን ለኮሮና ማዕከል አገልግሎት እየዋለ አይደለም። በጥበቃ ላይ የተሰማሩ ፖሊስ አባላት እና ለጤና ባለሙያዎች ተገቢው ክብካቤ እየተደረገላቸው አይደለም ። ለሁለቱ ወረዳዎች በሰላምበር ከተማ ውስጥ አንድ ኮቪድ-19 ማግለያ ማዕከል ያለ ሲሆን አሁን ለጊዜው ሰው ያለባቸው ክፍሎች ግን ሁለት ብቻ ናቸው። በአንደኛው ክፍል አንዲት ወጣት ሴት እና በአንደኛው ክፍል እኛ ያለንበት ነው። ነገር ግን ለሁለቱ ክፍሎች፤ ሁለት ሻማ፤ በሁለት ቀን አንድ፤አንድ መግዛት እንኳን አልተቻለም። የዚህ ምክንያት ግልጽ ነው። ሙስና፣ ሽቀላ፣ ቅፈላ፣ ለሕዝብ ጉዳይ ቅድሚያም ያለመስጠት ወዘተ ነው። ባጠቃላይ የወረዳዋ ነዋሪዎች፣ የፀጥታ ሰራተኞች፣ የጤና ባለሙያዎች … የመንግስት ሠራተኞች ከእኔ ጋር በማግለያ ያሉ ሁሉም በአከባቢው አገዛዝ ላይ ሲያማሪሩና ምሬታቸውን ሲገልጹ በጆሮዬ ሰምችያለሁ፤ በዓይኔም ተመልክችያለሁ ።
…   …
ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ማግለያ? የገባሁት ዕሁድ አመሻሽ መሆኑን ከላይ አንስችያለሁ። በማዕከላዊ እንኳን እንቅልፍ አጥቼ የማላውቅ ሰውየ እንቅልፍ የሚባል በዓይኔ ዝር ሳይል ማደር እየተለመደ መጥቷል። የማይነጋ የለምና ነጋ፤ ሰኞ ሆነ። ግንቦት 10ቀን: 2012 ዓም። ከሰዓት በኋላ ጀምሮ ስንቅ ከያዘ ሰው ውጭ ሌላ ጠያቂ እንዳይገባ መከልከል ተጀመረ ። በዚህም ምክንያት ከእኔ ጋር እስጥአገባ ውስጥ ገብተናል። ከውስጥ ወደ ውጭ ተንጠራርቼ ሳይ በሁለት መስመር የተሰለፈው ሕዝብ ብዛት የምርጫ-97 ሰልፍን አስታወሰኝ። ከሰዓት ወደ ሰዓት የታሸገ ውሃና ሳህን ያንለጠሉ ሰልፈኞች ቁጥር እየጨመረ መጣ። እንዲሁም በደቂቃዎች መካከል የጠያቂው ሰልፍ እንደ ጄት ጢስ እየረዘመ መጣ። በዚህም ካድሬዎቹ ደስተኛ አይመስሉም። በጠያቂዎቼ ላይ ጫና ለማሳደራቸው አንዱ ምክንያት ይህ ይመስለኛል ።
 …   …
ማክሰኞ ጧት ወደ 3፡30 ገደማ አንዱ ወጣት የሙቀት ማንበቢያ ሽጉጥ መሳይዋን ሸጉጦ መጣ ። ከኋላ ሳጣራው የሰላምበር ከተማ ጤና ጥበቃ ጽ/ቤት የጤና ባለሙያ እንደሆነ አረጋገጥኩ ((በዚህ ግለሰብ አማካኝነት የተፈፀመው ጉድ ቀጥሎ የሚዘረዘር ሲሆን፤ ከተፈታሁ በኋላ ግን በተፈጠረው ነገር እጅግ ማዘኑን ገልጾ ይቅርታ! ከጠየቀኝ በኋላ፣ ከሀለቆቹ በኩል “ሁላችም አንድ ወጥ የሆነ ዳታ መያዝ አለብን” የሚል ትዕዛዝ ደርሶት እንደነበረና እሱም  “እኔ ያነበብኩት የሙቀት መጠን በቀጥታ ለእናንተ ሪፖርት አደርጋለሁ፤ እናንተ ግን የመሰላችሁትን ማድረግ ትችላላችሁ” እንዳላቸው በራሴ መንገድ ያጣራሁት ስለሆነ ስሙን ከመጥቀስ ተቆጥብያለሁ)) ። ይህ ግለሰብ እንደመጣ በግንባሬ ላይ በቀጥታ ደቅኖ ያነብና ደታውን (Data) በማስተወሻው ላይ አስፍሮ ቀና ሲል ስንት ነው? ብዬ ጠየኩት። አይነገርህም! አለኝ።
እንዴ! ለምን? እንዲህማ አይደረግም!! የራሴን የጤና ሁኔታ እኔ የማወቅ መብት አለኝ፤ አንተም የማሳወቅ ግዴታ አለብህ፤ አልኩኝ። ከእኔ በላይ ስለጤናዬ መጨነቅ አትችልም ስለው “እኔ ልነግርህ አልችልም ምናልባት አለቃዬ ይነግርህ እንደሆን እነሱን ጠይቀው” ብሎኝ እየፈጠነ ተመልሶ ሲሄድ እኔም በጥበቃ ላይ የነበረ አንድ ፖሊስ አባልንና ከእኔ ጋር የነበሩ ሁለት ሰዎችን (እስረኞች) “ልብ በሉ!” በማለት ምስክር ቆጥሬ ወደ መቀመጫዬን ተመለስኩ። በርግጥ እሱ ያለው ትክክል ነበር። ከተፈታሁ በኋላ ሐቁን ለማጣራት ባደረኩት ጥረት ባለሙያው አጣብቂኝ ውስጥ እንደገባና ከላይ በተ.ቁ.1-7 የተጠቀሱ አመራር አባላት ባደረጉት ስብሰባቸው በወሰኑት መሠረት በ4ኛ ተ.ቁጥር የተጠቀሰው ማለትም በአቶ ሶፎንያስ (የሰላምበር ከተማ ጤ/ጥ/ጽ/ቤት ኃላፊ) በተባለ በቅርብ አለቃው እንደታዘዘ ለማወቅ ችያለሁ ። አቶ ሶፎንያስ’ን በአካል አግኝቼው ለምን የሙቀት መጠኔን እያዛባች ትናገራላችሁ? ብዬ ስጠይቀው አንተን የለካው ባለሙያ የነገረኝ ነው የሚቀበለው በማለት የመለሰልኝ ሲሆን፤ አያይዤም ለምን የራሴ ሙቀት መጠን ለእኔ እንዳይነገረኝ ይከለከላል? ስለው እኔ አልከለከልኩም ብሎ ሽምጥጥ አድርጎ ዋሽቷል ። የለካኝ ባለሙያ ግን በፍርድ ቤትም ጭምር ባደባባይ እመሰክራለሁ እያለ ነው። የኋላ ኋላ እንዳይነገረኝ ስለተከለከለው ውጤት በ3ኛው ቀን ከእስር ቤት ወጥቼ በከተማዋ በቆየሁባቸው ጊዜያት ሳጣራው 38.9°c ሳይሆን 34.3°c እንደነበረ ለማረጋገጥ ችያለሁ። ይህንን ያደረጉበት ዋናው ምክንያት <ለምን? እንደታሰርኩ ለሚጠይቋቸው የሙቀት መጠኑ ጨምሮ  38.9°c ስለደረሰ ነው ለማለት አስበው እንደሆነ ለማወቅ ችያለሁ ።
በተመሳሳይ ሁኔታ እንዲህ ከሙያ ሥነ ምግባር ያፈነገጠ ነገር ለምን ይደረጋል? ምን ይጠቀማሉ? ብዬ ሳጣራው  “… ለማጉላላትና ለመጉዳት የሚፈልጉትን ሰው የሙቀት መጠኑ በመጨመሩ ነው እያሉ በማግለያ ለማቆየት ስለሚፈልጉ ነው” የሚል ትክክለኛ መረጃ የራሳቸው አመራር አባል አስረድቶልኛል ። በኋላም የሶስቱም ወረዳ የኮሮና ወረርሽኝ ጤና ዘርፍ ቡድን መሪ (ዶ/ር አለፈ) ለተባለ ሀኪም አመልክቼው እንዲህ ያደረገውን ጤና ባለሙያውን ክፉኛ ገስጾና ትክክል አለመሆኑን ከገለጸልኝ በኋላ ከዚህ በኋላ ራሱ እንደሚከታተል ቃል በገባው መሠረት እስከሚወጣ ድረስ ራሱ እየተከታተለና ውጤቱን በግልጽ ሲያሳየኝ ቆይቷል።
…   …
መንግሥት የሕዝብ ትራንስፖርት ዘርፉንና መንገዶችን ሙሉ በሙሉ እስካልዘጋ ድረስ የሕዝብ እንቅስቃሴ መቀጠሉ አይቀርም ። እንዲህ ከሆነ ወደ ከተማዋ የሚገባውን ሁሉ  እንደ እኔ ይዘው ለ14 ቀናትና ከዚያ በላይ ማቆየት መቻል አለባቸው። ይህ ደሞ የሚቻል አይመስለኝም ። እኔም ለመጓዝ የተገደድኩት እጅግ አስጨናቂና መንፈስን የሚረብሽ ጉዳይ ከማጋጠሙም በላይ የትራንስፖር አገልግሎት ስለነበረ ነው።  የትራንስፖርትንና የጤና መመሪያን አክብሮ ከመቀሳቀስም በላይ በኃላፊነት መንፈስ የሚቀሳቀስን ሰው ለእንግሊት ማድረግ ፈጽሞ ተቀባይነት የለሌው ጉዳይ ነው። ከዚህ በፊትም ተናግሪያለሁ፤ <ኢህአዴግ ጋንግሪን በሽተኛ ነው> በማለት። የዛሬውም ገጠመኝ የሚነግረን ይህንኑን ነው። የማይጠራ፣ ሊጠራም የማይችል፣ አሊያም እስኪጠራ ድረስ ሀገሪቷን ብዙ ዋጋ በሚያስከፍሉ አባላት የታጨቀ ፓርቲ ነው። የጠቅላዩ የብልጽግናና የመደመር መሻታቸው በሀሳብ ደረጃ አንጀት የሚያርስ ቢመስልም ግን የሚደምረን/የደመረንም አይመስልም ። ምክንያቱ ከዘሪውና ከዘሩ ምርጥነት ሳይሆን <የተዘራው ዘር> የወደቀበት መሬቱ ጭንጫ ስለሆነ። ጩሄታቸው ፣ ምልጃቸውና ልምምጣቸው ወይም ቆፍጠን ማለታቸው ፈቅ አላደረገውም፤ ፈዋሽ መድኃኒትም አልሆነም። በፓርቲያቸው ውስጥ የተሰገሰጉ ፀረ_ዴሞክራሲያዊያን የተገመዱበት ሚስጢራዊው ገመዳቸው አልተደረሰበትም፤ አልተበጣጠሰም፤ ከዚህ የተነሳ ዛሬም ህያው ናቸው። እንዳሻቸው እየዘወሩት ይገኛሉ ።  እርሳቸውም ምንም እንኳ የሀገር መሪ ቢሆኑም ግን አንድ ሰው መሆናቸውን ልብ ማለቱ አይከፋም ። በሽታው ውስብስብ ነውና ብዙና የተለያዩ ባለሙያዎችን ያስፈልጉታል ። አዋጅን ሰበብ አድርገው ዜጎችንና የሚቃወሟቸውን ለማጥቃት በብዙ ዋጋ የተሻገርነውን ጨለማ ወመን ለመመለስ መሞከር #በእውነት የሥርዓቱ ካድሬዎች ክፉ ደዌ ነው። ይህንኑ የቆሸሸና የረከሰ አስተሳሰባቸውን የተለማመዱትም  የለመድነውም ቢሆንም ግን ላለፉት ለ28 ዓመታት የተቀጠቀጠውን ሕዝብ ፈጽሞ  የማይመጥኑ ስብስብ ናቸው። ለዚህ ነው እኔ ብዙውን ጊዜ <<ቀዳማዊ ኢህአዴግ ከወደ አናቱ፤ ዳግማዊ ኢህአዴግ ከወደ እግሩ ነው መበስበስ የጀመረው>> የምለው።
…   …
ወደተነሳሁበት ጉዳዬ ስመለስ እኔ ለማንሳት የፈለኩት ለምን እኔን ኳራንታይን አስገቡኝ አይደለም። ራሴን ከተጠራጠርኩ አመልክቼም ቢሆን የሚገባ ሰው ነኝ ። ጥያቄው ፦
1ኛ/ እኔን ከሌላው ተሳፋሪ፤
2ኛ/ ከእኔ ጋር ከተጓዙ ቤተሰቦቼ፤
3ኛ/ ከተቀባዩ ቤተሰብ እና
4ኛ/ እኔ ወደ ከተማዋ (ሰላምበር) ከገባሁ ወዲህ (ላለፉት ከ10 ቀናት በላይ) በየዕለቱ ወደ ከተማዋ ከሚተምመው ሕዝብ ለይተው እኔን ብቻ ለምን ለማስገደድ ፈለጉ? የሚል ነው።
በዚህ ቆይታዬ የታዘብኩት ነገር ቢኖር አንድም ሰው ወደ ለይቶ ማቆያ/ማግለያ ሲወሰድ አለማየቴ ነው ። ምክንያቱ ደሞ ግልጽ ነው ። የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አባላትን በሚመለከት ዛሬም ከውስጣቸው ወጥቶ ያላለቀላቸው ክፉና ገዳይ ስሜት አላቸው ማለት ነው።
 እኔና የ28 ዓመታት የትግል ጓዶቼ ይቅር ብለን ብንተዋቸውም እነሱ ግን መተው አልፈለጉም። ፓርቲዬንም (ኢዜማ) እንደ ሥጋት ማየታቸው አልቀረም። ለዚህ ነው በቀጥታም በተዘዋዋሪም  እየተነኮሱ ያሉት ። እነሱ ምን ያደርጉ? እኛ በመራራ ትግል፣ እንደ እባብ ተቀጥቅጠን፣ ከሞቀ ቤታችንና ከቀያችን ተፈናቅለን፣ ተሰደንና ሞተን … ባመጣነው ለውጥ ዛሬም እነርሱ ተንፈላስሰው እየኖሩ፤ እንደት ስለ ድካምና ትግል ምንነት ይግባቸው? እንዴተ የዓላማና የግብ ፋይዳ ባይገባቸው እንገረማለን? አዎን! ልንደነቅ አይገባም ።
 ለሀገርና ለሰው ልጅ ያደረግነውን እልህ አስጨራሽ ትንቅንቅን ቁጭ አድርገን፣ በዓላማ ልዩነት ምክንያት መፈራረጅን ትተን፣ የተለመደውን መራራ ትግልን አለዝበን፣ በሁለንተናዊ መልኩ ወደ ሀገር ግንባታ እና ወደ ዴሞክራሲ ሽግግር ፊታችንን ማዞራችን ለምን እንደሆነ የሚያገናዝብ አንጎል በጮማ ከተደፈነ ጥፋቱ የእነሱ አይመስለኝም ። ሽልማት የሚገባውን ሰው ደግመው ደጋግመው በእስር ካጎሳቆሉ ጥፋቱ የእነሱ አይመስለኝም። አብረን እንሻገር ማለታችን በብዙ መልኩ ካልጣማቸው ጥፋቱ የእነሱ አይመስለኝም ።
…   …
ባጠቃላይ ይህ ክስተት የምነግረኝ/ን ብዙ ቁምነገር አለ። ለብዙዎቻችን ስለ <Reform, Transform, Revolution> ልዩነት፣ አንድነት፣ አስፈላጊነት እና ባሕርያት በጥልቀት በመረዳታች፤ በየጊዜው በካድሬዎች የሚፈጽሙ ነገሮችን በዛው ልክ በመውሰድ በአዝጋሚ ለውጥ ሂደት ሰው! ይሆናሉ ብለን ነበር ። ከዚህ የተነሳ በጣም አፍጥነን ወይም ወደ ኋላ ጎትተን፣ ለግመን ወይም ዋሽተን ለውጡን ከምጎዱ ነገሮች ርቀን ፍጹም የቅንነት መንገድን መርጠናል። ይሁን እንጂ ከትላንት የቀጠሉና የዛሬዎቹ በየአካባቢው የተሰገሰጉ ራዕይ_ቢስ ካድሬዎች ይህንን የመረዳት አቅም አጥተዋል ። ከዚህ የተነሳ ባገኙት አጋጣሚ የለመዱትን ዱላ ከማሳረፍ፣ በሌብነታቸውና በፀረ-ዴሞክራሲያዊ አገባብ ቀጥለውበታል። ለሀገር ጉዳይ ደንታቢስ ከመሆን ወደኋላ አለማለታቸው እየተለመደ መጥቷል ። ስለ ራሴን ብዙውን ጊዜ ማውራት አልፈልግም፤ አውርቼም አላውቅም፣ አሁንም ማውራት አልፈልግም ። ነገር ግን በጥቅሉ ልንገራቸው ፦ … አነሰ በዛ እዚህ ሀገር ለውጥ እንዲመጣ ላለፉት ሩብ መ.ክ.ዘ በላይ ሰቅጣጭ ዋጋ ከከፈሉት ውስጥ አንዱ ነኝ። ዛሬም በትግል ላይ ነኝ። ቢያንስ ለትግል የቆረብኩ ባህታዊ መሆኔን፤ የእውነት ፀኃይ በኢትዮጵያ ምድር እስኪትበቅል ድረስ ወደኋላ የማንመለስ መሆናችንን መረዳት ነበረባቸው። ይህን የማደርገው እንደ እነሱ ከሚመጣው ጋር እየተለጠፍኩ መኖር አቅቶኝ ሳይሆን የደረስኩበት የግንዛቤ ጣሪያ ስለማይፈቅድ ነው። ሌላው ደግሞ ትግል ሱስ ወይም በዕድል ያገኘሁት ዕጣ ፋንታዬ ስለሆነ ሳይሆን በምርጫዬ ለሀገሬ ራሴን ስላሰረከብኩት ነው።  በሌላ አነጋገር ከፍተኛ ኃላፊነት የሚሰማው ዜጋ ነኝ። እኔ ያለሁበት ፓርቲም ቢሆን ትልቅ ኃላፊነት የሚሰማው መሆኑን የእኔ ምስክርነት የሚያስፈልገው አይመስለኝም ። እኔም በግሌ ካለኝ ኃላፊነት በተጨማሪ ፓርቲው ባስቀመጠው አጠቀላይ ዲስፒሊን መሠረት የምቀሳቀስ አመራር ከመሆኔም ባሻገር ስለኮሮና ወረርሽኝም ቢሆን ከአሳሪዎቼና ከተራው ዜጋ የተሻለ ግንዛቤ አለኝ ብዬ አምናለሁ። በዚህ ደረጃ ያለውን ሰው  ይህንን ያህል ከመመሪያ ውጭ የሚያሰቃዩ ከሆነ፤ በሌላው ዜጋ ላይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁንና የኮሮና ወረርሽኝን እንደ ጥሩ አጋጣሚ በመቁጠር ምን ያህል በደል እንደሚፈጸሙ መገመት ለማንም አይከብድም። ስንቱ በገንዘብና በወንዘኝነት ኃይል ይለቀቃል? ስንቱ በድህነቱ ምክንያት ይማቅቃል? እንደነዚህ አይነት ነገሮችን በደንብ አጮልቀን ስናይ ወደ ሀገር ግንባታ ውስጥ እንገባለን የምንለው ከእነዚህ ጋር ሆነን ነው ወይ? የሚል ጥያቄ ብናነሳ እንደት ስህተት ይሆናል ??
…   …
እንደ ቀድመው ሁሉ ዛሬም ከትናንሽ እስከ ትላልቅ ጉዳዮች በጨበጣና በጉልበት ይሰራል ። በፖለቲካ አመለካከት፣ በቡድናዊ  ትስስር እና እንደ ጉንዳን የየጎሳቸውን ሽታ እየተከተለ ይከናወናል ። ሹመት፣ ዕድገት፣ እምነት ተጥሎበት ኃላፊነት የሚሰጠው በዕውቀት፣ በችሎታ፣ በሕዝብ ፍላጎት ወዘተ መመዘኛ (Merit) ሳይሆን ከታች እስከ ላይ በተዘረጋው ኔትወርክ ነው ። ለዚህም ዋናው ምክንያት ደሞ በዚህም በዚያም የቀድሞ ኢህአዴግ ባለሥልጣናት እንዳለ የብልጽግና ባለሥልጣን ሆነው መቀጠላቸው ነው። ቀደም ስል ባደረግነው ትግል ሲያሳስሩ፣ የሀሰት ምስክር ሲያደራጁ፣ ሲያሳድዱ፣ ከቀያችንና ከሥራ ገበታችን ሲያፈናቅሉ ወ.ዘ.ተ ግፍ ሲፈጸሙ የነበሩ ዛሬም እዛው መሆናቸው አሊያም ወደተሻለ ሥልጣን እርከን መሸጋገራቸውና የሥራ አከባቢ እየቀየሩ መቀጠላቸው ነው። አከባቢን ቀየሩ እንጂ አስተሳሰብ ስላልተቀየረ ሰበብ ፈጥረው፣ ምክንያት ፈበርከው የለመዱትን ሥራቸውን ቀጥለውበታል። ብልጽግናን ያቀነቅኑ እንጂ የበፊት ወንጀል የሚያስከትለው ውጤት/መዘዝ (Serious consequence) የለም። ኑሮውና ተግባሩ የቀድሞው ንግግሩና ማነብነቡ አድሱን የብልጽግና ቋንቋ እየተዋሰ በየመድረኩ መለፍለፍ ይሁን እንጂ ኃጢዓቱ ተሰርይለታል። አዝናለሁ! በታዘብኳቸው ነገሮች ሁሉ ውስጤ ቆስሏል።  ነገር ሁሉ  “አንድ ጣት አያጸዳም፤ አንድ እንጨት አይነድም” እንዲሉ ሆኗል ።
…   …
የዜጎች እሮሮ የሚደመጥ መስሎኝ በእኔ ላይ ስለተፈፀመውን ጨምሮ ባጠቃላይ በሕዝቡ ላይ እየደረሰ ሲላሌው ጉዳይ መረጃ ለመስጠት ለጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ (0468810085) ስልክ መታሁ ። ያነሳችልኝ ሴት አማካሪውን እንጂ እርሳቸውን በቀጥታ ማግኘት አትችልም አለችኝ ። እሺ ስልኩን ስጭኝ አልኳትና 0468810081 አለችኝ። እኔም ወዲያው ደወልኩለትና አገኘሁት ። ሁሉንም በዝርዝር ነገርኩለት። “አይ ዋሽተሃል! የእኛ አመራር እንዲህ አይነት አይነት ነገር አይፈጽምም፤ በአንተም ላይ ቢሆንም ምንም የተፈጸመ ነገር የለም” ብሎ ለበዳይ ጥብቅና ቆሞ ስከራከር በጣም እየተገረምኩ ቻው! ብዬ ስልኬን ዘጋሁና ተለያየን ።
… …
በእስር ቤቱ (ማግለያ) ቆይታዬ ባደረኩት ትግል የተገኘው ውጤት ፦
በእስር ቤቱ ባደረኩት ትግል ቀጥሎ ለሚመጣው ሰው ጥሩ ሁኔታ ተፈጥሯል። ከብዙ ንትርክና ትግል በኋላ ቢሆንም ማለቴም ወደ መፍቻዬ አከባቢ ባለሥልጣናት አንዳንድ ቁሳቁሶችን ለማሟላት ሲጥሩ አይቸዋለሁ። በዛች ሰቀቀን ክፍል ውስጥ የእኔ መገኘት ወደፊት የሚገቡ ካሉ ጥሩ መሠረት ተጥሏል ማለት ይቻላል ። ሻማ፣ ፍራሽ፣ አንሶላ፣ የወሌል ጅባ አቅርበዋል። የታሸገው ሻውር መውሰጃ እና የመጸዳጃ ክፍሎች ተከፍቷል ። አንዲት የጽዳት ሰራተኛም ተቀጥራለች። ይሄ ጥሩ ጅምር ቢሆንም፤ ተደናግጠው ግማሽ ቀን ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በቀላሉ ማሟላት የቻሉትን ባለማድረግ እኔን ለመበቀል መነሳሳት ተገቢ ነው ብዬ አላምንም ። ባጠቃላይ የእስሩ ምክንያት፣ ሁኔታ እና ሐቁ ይህንን ይመስላል ። ከዚህ የተለየ ነገር ካለ ንጹህ ውሸት፤ የተለመደ ውዥንብር እና የእነሱ ሴራ ነው ።
…   …
በመጨረሻም ሶስት ነጥቦችን ላጋራችሁና እንሰነባበት ፦
 
፩. <ምክር!>
<><><><>
ለብልፅግና አጭርና ግልጽ ምክር አለኝ። … ብልጽግና እግሮቹን ያክም!!!
በአሁኑ ሰዓት እንኳ ለውጥ የሚባል ሽታ ያልደረሰበትን ሕዝብ መታደግ የሁላችንም ትግል የሚጠይቅ፤ የሁላችንም ኃላፊነት ቢሆንም ከመንግሥት (ከብልጽግና ፓርቲ) በኩል እጅግ ብዙ ይጠበቃል። ብሔራዊ የብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት እንደ ሀገር የራሳቸውን ክትትል በማድረግ የቁጫንም፣ የሰላምበር’ንም … የብልጽግና ካድሬዎቻቸውን አፋጣኝ እርምጃ በመውሰድ ከሕዝቡ ጫንቃ ያራግፋቸዋል የምል እምነት አለኝ።
<ብልጽግና እግሮቹን ያክም!!!>
…   …
፪. ሁለት ማስተወሻ ስለ ሰላምበር!
<><><><><><><><><><><><>
የመጀመሪያው፦ … <ሰላምበር> የሚለው ስያሜ የተቀዳው ከራሱ ከሕዝቡ ነው። ሕዝቡ እንደ ስሙ ሰላማዊ ነው። መግቢያውም መውጪያውም በሮች አማን ናቸው። ሰላሙ እንደ ወንዝ የሚፈሰው ከራሱ ከሕዝቡ ልብ ነው፤ ከሕዝቡ አዕምሮ ነው ። በዚያው ልክ ፍትህን ተነፍገው በመንግሥት አጭበርባሪዎች ተከቦ ሰላሙን የተነጠቀ፣ አማኑን የተገፈፈ ሕዝብ ነው ። ስለሆነም <ከብልጽግና ፓርቲ> በቅርብ ቀን ምላሽ የምጠብቀው፤ የምንጠብቀውም ይሆናል።
ሁለተኛው፦ … ሰላምበርን ሳስብ ሁሌ ትዝ የምትለኝ የደሴ ከተማ ነው። እንደ ሀገሬ ሰው የሀገሬ ከተሞችም አቀማመጥ መመሳሰላቸው ይገርመኛል። እንደ ደማችንና አጥንታችን፤ ተራሮቻችና መልክዓ ምድራችን በውስጣዊ ህዋስ (Cell) የተያያዙ፤ በውጫዊ ገፅታ የተዋቡ ስለመሆናቸው የበቀልንባት ምድራችን ሕያው ምስክር ነው ።
አዎን! ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት ሁሌም ድንቅ ነው ።
ከአዱ ገነት ወደ ደሴ ስንደርስ የመግቢዋ ቀኝና ግራ በሰንሰለታማ ተራራዎቿና በልዩ ልዩ ተፈጥሮ ተሸፍና፣ ተውባና  ታጥራ እናገኛታለን። በግራ በኩል በርቀት የሚታየው #ጦሳ ተራራ በዓይን_ህልናዬ ይታየኛል።
ወደ ሰላምበርም ስንገባ ደግሞ በቀኝ በኩል እንደ ደሴው ሰንሰላታማ ጦሳ ተራራ፤ ሰላምበርም በደሌ እና በውዛቴ ሰንሰላታማ ተራራዎች የታጠረች ስትሆን፤ በግራ በኩል ደሞ ማቀዝቀዣ ለምኔ? ከሚያሰኝ  ደጋ እና ተራራማው መልክአ ምድር በመፍለቅ፤ ግራ ቀኙን አረስርሶ እያለመለመ፤ ከየመንገዱ የሚያገኛቸውን ሰፈርኛ ወንዞችን ጠቅልለውና በአንጀቱ ውስጥ ደብቆ፣ ሰፍቶና ደልቦ፣ እንደ ዓባይ ወንዛችን ምርጥ ምርጡንም ፣ ግሳግሱንም ተሸክሞ እንደ አንበሳ እያጓራ አጭር ርቄትን ተጉዞ መዳረሻውን ኦሞ ወንዝ ያደርጋል።
እንግዲህ ሰላምበር ፊታችንን ወደ ስሜን ዞሬን ስንቆም በቀኝ በኩል በዚህ <በዴሜ ወንዝ> ፣ በቦሮዳ አባያ እና በዲታ ተራራዎች፤ በግራ በኩል በደሌ፣ በውዛቴ እና ሳአ-ቱሳ (የምድር ምሶሶ) ተራራዎች የተከበበች ከተማ ናት ።
…   …
፫. <ምስጋና!>
<><><><>
ለሰላምበር ከተማ ሕዝብ፣ ለአንዳንድ ፖሊስ አባላት እና ለጤና ባለሙያዎች ከልብ የመነጨ ምስጋናዬ ይድረሳቸው ። ከእግሩ ኮቴው እስከ አጠቃላይ እንቅስቃሴው፤ ብሎም እስከ ንግግሩ ድረስ የተረጋጋ፣ በሙያዊ ሥነ ምግባሩ፣  ሰከን ባለ መንፈሱ፣ እና በሙያው ላይ ብቻ ቆሞ  እየመከረ መንፈስን ለሚያድስ የሰላምበር ሆስፒታል ሜዲካል ዳይረክተር ለሆነውና ለወጣቱ ሀኪም ዶ/ር አለፈ (ከይቅርታ ጋር ለጊዜው የአባቱን ስም ያላወኩት) ትልቅ አክብሮት አለኝ።
ሰላም!
Filed in: Amharic