>
5:13 pm - Thursday April 19, 7832

ህወሓትና የሶማሌ ህዝብ.... !!! ክፍል ፩ (ሙክታሮቪች) 

ህወሓትና የሶማሌ ህዝብ…. !!! ክፍል ፩

ሙክታሮቪች

ህወሓት የሶማሌን ህዝብ በተለየ መልኩ እንደጠቀመች፣ እንደው አንዳንዶች ካድሬዎች ሰው ያደረግናችሁ እኛ ነን የሚሉት ነገር ያቅለሸልሸኛል። የሶማሌ ህዝብን አፍነው፣ ገድለው፣ አስረው፣ አሰቃይተው፣ ሞራሉን ሰብረው ያዋረዱት ህወሓቶች ናቸው።
ህወሓት የምትለው ክልል ሰጠናችሁ፣ በቋንቋችሁና በባህላችሁ መተዳደር አስጀመርናችሁ አይነት ሰራን የምትለው ነገርን ቋቅ የሚያደርገን እኛ ነን “የፈጠርናችሁ” አይነት መታበይና ትምክህት የሚመስል የድንቁርና ትዕቢት የደንቆሮ ስራ አድርገን ስለምናየው ነው።
የህወሓት ታጋዮችም ሆነ የመጡበት ህዝብ ከሶማሌ ህዝብ እና ከሶማሌ ታጋዮች አንፃር ስናያቸው እዚህ ግባ የሚያስብል የዘመናዊነት ልዩነት የለም።
ከወያኔ እንቅስቃሴ በፊት የሶማሌ ህዝብ በንጉሱ እና በስርዓቱ ላይ ነቅቶ ለለውጥ ማመፁን አያውቁም።
በ1956 የመሬት ለአራሹን የኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ ጥያቄ ለንጉሱ በፅሁፍ ያቀረቡት ሶማሌው ዶክተር አብደልመጂድ ሁሴን ነበሩ።
ያኔ እነ መለስ ዜናዊ የኢሊመንተሪ ተማሪ ነበሩ። ዋለልኝ ያንፅሁፍ ከመፃፉ በፊት በእስርቤት በኦጋዴን አመፅ የታሰሩ የሶማሌ ልጆችን አናግሮ ነበረ። (ባህሩ ዘውዴ በቅርቡ The quest for Socialist Utopia ባሉት የተማሪዎች ንቅናቄን የሚተርክ መፅሃፋቸው ላይ በግልፅ ይህን ሀቅ አስፍረውታል)
የተለየ ህዝባችን ያልታገለበት ነገር አልመጣም። የመጣው እንደውም ውርደት እና መሰቃየት፣ መደፈር እና ከአውሬ ጋር መታሰር ነው።
ልማት አመጣን ይሉሃል ልማት የታቀደለትን የሰው ልጅ ደፍጥጠው። ህልም ገድለው። ምናብ ገድለው። ከሰው በታች አድርገው። በጅምላ መቃብር ቀብረው።
ህወሓት ለሶማሌ ህዝብ የተለየ ነገር አላደረገችም፣ አሳነሰችብን እንጂ! በዘመኑ ለራሷ ስልጣን ስትል በቋንቋና ጎሳ ሀገር ስትሸነሽን የሶማሌ ክልልም በዚሁ መንገድ መጣ እንጂ ለእኛ የተለየ ተግባር ፈፅማ አይደለም። በዘመኑ በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ክፍል ህዝቦች በራሳቸው ባህልና ቋንቋ መተዳደር፣ በራሳቸው ተወካዮች መመራት የዘመኑ የፖለቲካ ቅኝት፣ አጠቃላይ በምስራቅ አፍሪካ ይተገበር የነበረ የሰው ልጆች መብት ላቅ ያለ ትኩረት ያገኘበት ዘመን ነበረ።
የሶማሌ ህዝብም ይህን የታሪክ አጋጣሚ ነው ወደ ህዝቡ የመጣው።
ከህወሓት ሌላ መንግስት ቢመጣም ይህ የዘመናት የማንነት ጥያቄያችንን ሳይመልስ አይረጋጋም ነበረ።
ይህ ሲመጣ ግን ለሶማሌ ህዝብ ልክ እንደ ትግራይ ህዝብ እኩልነትም አልመጣለትም። በመንገድ ሽፋን፣ በትምህርትቤቶች ሽፋን፣ በጤና ሽፋን ቢታይ ከትግራይ የበለጠ ህዝብ ይዘን እጅግ ያነሰ እና የመነመነ የመሰረተ ልማት ሽፋን ነው የነበረው በክልሉ።
ይህ ልዩነት በቀላሉ የሚታይ፣ ከደርግና ሀይለስላሴ እየተነፃፀረ የሚሞካሽ መሆን የለበትም። ሌላው የኢትዮጵያ ክልል በለማበት መጠን የሶማሌ ክልል ያልለማው ህወሓት ለክልሉ የሚበጀተውን በእጅ አዙር እየተቀበለች የክልሉን ህዝብ ስለበደለች ነው።
እንግዲህ የህወሓት ስራን በክልሉ ውስጥ የሰራችውን ግፍ እና ለምን አሁንም የሶማሌ ህዝብ ጉዳይ እንደሚያክለፈልፋት ደጋግመን እንፅፋለን። ለውጡ ከቂምና ከጥላቻ ይፅዳ ብለን ዝም ብንል ጭራሽ የካድሬዎቿን ድንፋታ ስናይ በጣም የሚያስገርም ነው።
ህወሓት በክልላችን በፈፀመችው ወንጀል አለማቀፍ ፍርድቤት መገተር የሚገባት የአፍሪካ ናዚ መሆን ነበረባት።
ህወሓት ለሶማሌ ህዝብ ነፃነት ሰጠሁ ትላለች። ህዝባችን የተቀበለው ግን የእጅ አዙር የቅኝ ግዛት አይነት አስተዳደርን ነው። ሿሚና ሻሪ፣ አድራጊ ፈጣሪ፣ አፋኝ እና ገዳይ፣ አሰቃይ እና ከሀገር አባራሪነቷን ነው የሶማሌ ህዝብ የሚያውቀው።
[ ] በአማካሪነት የውሸት ካባ ወደ ክልሉ የምትልካቸው የህወሃት ሰዎች በክልሉ ካቢኔ ወንበር ሳይኖራቸው የሚሳተፉ፣ ለሶማሌ ህዝብ የሚጠቅም ውሳኔ ሊያልፍ ሲል የሚያስቀይሩ፣ የተቃወማቸውን የሚያባሩ፣ በሀገሩ እንዳይኖር፣ የትም ተቀጥሮ እንዳይሰራ የሚያደርጉ ናቸው። ገብረዋህድ የተሰኘው ፣ ኋላ በፌዴራል መንግስት በአራጣ አበዳሪነት እና በግምሩክ ሙስና የተያዘው ሰው በተጨባጭ የክልሉ መሪ ነበር።
[ ] ህወሓት ሶማልኛ ስለማትችል የክልሉ ወሳኝ ስብሰባዎች በአማርኛ እንዲደረግ የምታስገድድ አይን አውጣ ነበረች። ለክልሉ የሚመከር ምክር እሷ ላይ የሚመከር አሻጥር የሚመስላት ፀረ ፌዴራሊስት እና ፀረብዛሃነት ነበረች። አሁን ለፌዴራላዊ መንግስት ጥብቅና እቆማለሁ ስትል “ጅብ በማያውቁት ሀገር ቁርበት አንጥፉልኝ ይላል” የሚለው ሳይሆን የሚገልፃት፣ በሚታወቅበት እና የሰራው ግፍ ቁስሉ ሳይደርቅ ቁርበት አንጥፉልኝ እንደሚል ጅብ ነው እኛ የምናያት። ይህች የማታፍር የማታምር ጅብ አገጭ!
[ ] ህወሓት የክልሉ በጀት እንዲሰራበት እና ወደ ልማት እንዲቀየር በፍፁም አትፈልግም ነበረ። ያልተንቀሳቀሰውን በጀት በግምገማ ሰበብ እየመጣች አንዱን አንስታ አንዱን እየሾመች በተሿሚው ፊርማ ሚሊዮኖችን እየዘረፈች መሄድ ነበረ ስራዋ። የክልሉን የተፈጥሮ ሀብት ወደ ህወሓት ካዝና ለመቀራመት ባቀደችው የረጅም ጊዜ እቅድ ወጥና ስትሰራ የነበረው በለውጥ ሀይሎች ሲከሽፍባት ጊዜ “ፌዴራሊስት” እያለች ምላ ብትገዘትም የትኛውም ተቃዋሚ የሰራችውን ግፍ ስለማይረሳ ነገሬም ያላላት ለዚህ ነው። ወያኔ ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ አይነት ተፈጥሮአዊ የእኩልነት ጥላቻ አለባት። እኩል እንሁን ስትባል ጭቆና የሚሆንባት በዚሁ የባህሪ ስንኩልናዋ ነው።
[ ] ህወሓት በመሪዋ መለስ ዜናዊ በኩል የሶማሌ ህዝብ ወደ መሀል ፖለቲካ የእንግባ ጥያቄ ስትጠየቅ በሚያሳፍር መልኩ “የአርብቶ አደርነት የኑሮ ዘይቤ ለአብዮታዊ ዲሞክራሲ ስለማይመጥን፣ የኑሮ ዘይቤው እስኪለወጥ ድረስ ወደ ኢህአዴግ መግባት አይችሉም” ነው ያለችው። እንዲህ ሲባል የታሉ የአሁኖቹ ፌዴራሊስቶች? የአንድን ህዝብ የኑሮ መሰረት ምንነቱ ለማይታወቅ ዲቃላ ርዕዮተ አለም ሲባል የፖለቲካ የተሳትፎ እኩልነትን የምትነሳ ድርጅት እንዴት ፌዴራሊስት ነኝ ትላለች?
[ ] ህወሓት የሶማሌ ህዝብን የጎሳ አወቃቀር እና ልዩነት ለፖለቲካዋ ሲል ክፍፍሉን በማስፋት አንዱን በሌላው እያባላች፣ ሁሉም የእሷን አስፈላጊነት ከጥያቄ ውስጥ እንዳይከት በከፋፍለህ ግዛ የተካነች መሰሪ ነች።
የሶማሌ ህዝብ የህወሓት ነገር ቋቅ እስኪለው በቅቶታል። ይህን ምሬት ለማያውቅለት ህዝብ የማሳወቁ ሀላፊነት የእኛ ነው ።
ወደ ሰራችው ከባባድ ወንጀሎች ቀስ እያልን እንመጣለን።
(ይቀጥላል)
Filed in: Amharic