>
5:13 pm - Friday April 19, 5957

የኤርትራውያንን "የባርነትና የጨለማ ኑሮ" እያየን እንዳላየን የሆንበት ዘጠኝ ምክንያቶች? (ከኤርሚያስ ለገሰ)

የኤርትራውያንን “የባርነትና የጨለማ ኑሮ” እያየን እንዳላየን የሆንበት ዘጠኝ ምክንያቶች?

  ከኤርሚያስ ለገሰ

     መግቢያ
የዛሬ ሁለት አመት ገደማ ራሳቸውን የለውጥ አመራር በመሆን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ከፕሬዝዳንት ኢሳያስ ጋር ሲገናኙ ልባችን በተስፋ ተሞልቶ ነበር። ምናልባትም የሁለቱ መሪዎች ግንኙነት ወደ ሁለቱ አገር ህዝቦች ወርዶ የአፍሪካ ቀንድ ከድቅድቅ ጨለማ የመውጣት ጅማሮ ይኖራል ብለን ፈንድቀን ነበር። ጮቤ ረግጠን ነበር።
በተለይ ከበረዶ በባሰ ቅዝቃዜ ተዘፍቆ የነበረው የኤርትራ መንግስትና ሕዝብ ወደ አለም ይቀላቀላል ብለን ተስፋ አድርገን ነበር። ህወሓት ፓለቲካዊ ሞቱን ተከናንቦ የኢትዮጵያን ፓለቲካ ከተሰናበተ እና ከመቶ ሚሊዬን በላይ ያላት ኢትዮጵያን ዲሞክራታይዝ ማድረግ ከተቻለ ከ7ሚሊዮን በታች ያላትን ኤርትራ ዲሞክራታይዝ ማድረግ የጉም ያህል ቀላል ይሆናል እንል ነበር። በዚህም ምክንያት ከተለመደው የሁለት አገሮች “ሰጥቶ መቀበል” መርሆ አልፈን በመሄድ በመሰጣጣት ላይ እናተኩር ብለን በተደጋጋሚ ጨቅጭቀናል። በጫጉላ ሽርሽር ውስጥም ሆነን በርካታ ፕሮግራሞችና ፕሮዳክሽኖች ሰርተንም ነበር። ነበር ባይሰበር!!
ይሁን እንጂ ተስፋ ያደረግነው ብዙም ርቀት ሳይሄድ የበረሃ ውሃ በላው። ግንኙነቱ የአገራት መሆኑ ቀርቶ የሁለቱ ተናጠል መሪዎች የሚሆንበት ሁኔታ ተፈጠረ። ሳይውል ሳያድር አቅጣጫውን ሳተ። በጓዳ ምን እንደሚሰራ ሳናውቅ በአደባባይ “ኢሱ!ኢሱ!” ብቻ ሆነ። ጭራሽ የአዲስአባ የልማት ፕሮጀክቶች “ኢሱ ጭሱ ያስረዳችኃል!” እሰከ መባል ተደረሰ። በኢትዮ-ኤርትራ ጉዳይ ላይ ውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ተረስቶ እነ “ኢትዮጵያ ሱሴ” የፊት መስመር ያዙ። ሳውዲን ጨምሮ አረብ አገራት አስር ጣታቸውን ነከሩ። የሜዳሊያ ሽላሚ ከመሆን አልፈው የመከላከያ ደህነት ቢሮን የሚገነቡና የሚቆጣጠሩ ሆኑ።
ይህንን ሁኔታ በአጭር ጊዜ ብንገነዘብም አንዳንድ ጊዜ በይሉንታ፤ ሌላ ጊዜ “ትላንት የተናገርነውን እንዴት አድርገን ሂሳችንን እናወራርድ?” በሚል ምንተሀፍረት ችግሩን ሸፋፍነን ቆይተናል። ኖረናል!
ከላይ የጠቀስኩት ግላዊ ወቀሳዎች የሚጀምሩት ከለውጥ በኃላ የሆነበት ምክንያት ከዛ በፊት ያለው ራሱን የቻለ መድብል ስለሚወጣው ነው። በርግጥ በዛን ዘመን የነበረው መረጃን ደብቆ የመጓዝ ሂደት አሳማኝ የምንላቸው የራስ መከራከሪያዎች ነበሩት። ከዚህ አንፃር ቢያንስ ዘጠኝ ምክንያቶችን ማንሳት ይቻላል።
                      ***
#የመጀመሪያው ምክንያት በክፋትና ተንኮል የተሞላችው ህውሓት የኤርትራን ህዝብ ከምድረ-ገጽ ለማጥፋት የሄደችበት ርቀትን ለመግታት በማሰብ ነው። የህውሓትን ምቀኝነት፣ ክፋትና ስግብግብነት ለተመለከተ ማንም የሰው ፍጡር ከኤርትራውያን ጐን መቆም የሚገባው ወቅት ነበር። ህውሓት የቀረፀችውን ፀረ-ኤርትራዊ የውጪ ጉዳይ ፓሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ማጋለጥ ፍትሐዊም ተገቢም ነበር። ይሄን ያለመታከት ስናደርግ ኖረናል። ሁለት ጥገኛ መንግስታት በተናከሱበት ህዝብን ለመቅጣትና ትስስሩን ለመበጠስ መሄድ ከሃጢያትም አልፎ ምድራዊ ወንጀል ነው ብለን ተሟግተናል። በወቅቱ በዙሪያችን የነበሩት ጥቂቶች እንደሆኑ አስታውሳለሁ።
                     ***
#ሁለተኛው ምክንያት ሻዕቢያ ለምንም አላማና ግብ  ይፈልገው በመንግስታዊ አሸባሪዋ ህውሓት ኢትዮጵያውያን የሚደርስባቸውን ግድያና አፈና በመሸሽ ወደ ኤርትራ ለገቡት መጠለያ መሆኗ ሌላኛው የድጋፋችን ምንጭ ነበር። በርካታ በዙሪያችን ያሉ አገሮች ከትግራይ ነፃ አውጪ ጋር በመስማማት የተሰደዱ ዜጐችን አሳልፈው በሚሰጡ ስአት ብቸኛ መጠለያ የነበረችው ኤርትራ ብቻ ነበረች። ለምሳሌ ወዳጆቻችን የሆኑትን እነ ካፒቴን ተሾመ ተንኮሎን ልብ ይሏል!
                   ***
#በሶስተኛ ደረጃ ህውሓትን በትጥቅ ትግል ለማንበርከክ የቆረጡ ለመሰሉ ኢትዮጲያውያን ነፃ መሬት በመስጠትና ስንቅ እና ትጥቅ ድጋፍ በማድረግ ሻዕቢያ የተጫወተው ሚና በማንም ኢትዮጵያዊ የሚረሳ አይደለም። እርግጥ ሻዕቢያ ለኢትዮጵያዊ አማጽያን መሬት እንደሰጠ ሁሉ ኢትዮጲያን በቀኝ ግዛት በማየት ለመበታተን ቆርጠው ለተነሱትም ነፃ መሬት መስጠቷ ግራ አጋብቶን እድሜያችንን በውስጥ ማጉረምረም አሳልፈናል።
                       ***
#አራተኛው ምክንያት ህውሓት በደንታቢስነትና አላዋቂነት አለም-አቀፍ ፍርድ ቤት በመሄድ የተከናነበውን ህጋዊ ሽንፈት መቀበል ግዴታ ነበር። ለምሳሌ የባድመ ጉዳይ በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ የሚታይ ነው። ሲጀመር የአለም አቀፍ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ይግባኝ የለውም። ሲቀጥል ህውሓት እንድንሸነፍ ያደረገው በአለም አቀፍ አደባባይ ነው። ስለዚህ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ቅር ቅር ቢለንም መቀበል ግዴታችን ነው።
                        ***
#አምስተኛው ምክንያት ቀደም ብሎ እንደተጠቀሰው ህውሓት ተወግዶ ኢትዮጲያን ዲሞክራታይዝ ማድረግ ከተቻለ በቀላሉ ኤርትራንም ዲሞክራታይዝ ማድረግ አያስቸግርም የሚል መከራከሪያ ነበረን። በዚህም ምክንያት በጊዜያዊነት ለኤርትራ የሚያስፈልጋት መንግስት ለህውሓት የመረረ ጥላቻ ያለው፣ የህውሓትን ሰርጐ ገቦችና የስለላ መዋቅር የሚቋቋምና የሚበጣጥስ፤ ለኤርትራ አማጺያን ክፍተት የማይሰጥ ሊሆን ይገባል የሚል ግንዛቤ ተይዞ ነበር።
                         ***
#ስድስተኛው ምክንያት በኤርትራ የነፃነት ትግል ሂደትም ሆነ የደርግ ወታደራዊ መንግስት ከተገረሰሰ በኃላ ኢሳያስ አፈወርቂም ሆነ ሻዕቢያ በአግባቡ ያልገለጧቸው አስገራሚ መረጃና ማስረጃዎች መውጣት መጀመራቸው ነበር። ለአብነት ያህል” የኤርትራ ትግል ከየት ወዴት?” የሚለውን መጽሀፍ ማየት ይቻላል። ህውሓት በፃፈችው በዚህ መጽሀፍ ገጽ 170 ላይ ፣
       ” ሻዕቢያ በኢትዮጵያ ባለው ተጨባጭ ሁኔታ የዲሞክራቲክ አንድነት መብት እንጂ በመገንጠል የገዛ ራስን መንግስት መመስረት መጨመር የለበትም። ስለዚህ ህውሓት በፕሮግራሙ ማስፈር የሚገባው ዲሞክራቲክ አንድነት ምርጫን ብቻ እንጂ ዲሞክራሲያዊ አንድነት ወይም መገንጠል የሚሉትን ሁለት አማራጮች ማስቀመጥ የለበትም በማለት ህዝባዊ ግንባር ሓርነት ኤርትራ ብሎ አቋሙን ግልጽ አድርጐ አስቀምጧል” ይላል።
ከዚህ የህውሓት ዶክመንት መረዳት እንደሚቻለው ሻዕቢያ ህውሓት የሰነቀረውን “መገንጠል” የሚል የኢትዮጵያ የጥፋት መንገድ እንዳልደገፈ ነው። ህውሓትን እስኪያበሳጫት ድረስ ተቃውሞም አሰምቷል። የሻዕቢያ ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን ኢትዮጵያ እንዳትገነጣጠል መፈለጉና ህውሓት የተከተለው የአውዳሚነት መንገድ መቃወሙን ማወቅ አስተሳሰባችንን እንድንመረምር የሚያደርግ ነው። ከዚህ በተጨማሪም አንጋፋ ኢትዮጵያውያን በተለያዩ ወቅቶች የሰጧቸው ምስክርነቶች ለድጋፋችን ተጨማሪ ግብአት ነበር።
                           ***
#ሰባተኛው ምክንያት ከድህረ ትግራይ ነፃ አውጪ (ህውሓት) ዘመን በኃላ የሚመጣው መንግስት ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም አጥብቆ ይሰራል የሚል እምነት ተይዞ ነበር። በተለይም የትግራይ ነፃ አውጪ በታቀደ መንገድ ያጠፋቸውን ታሪካዊ ሰነዶች በመሰነድና ከኤርትራ መሪዎች ጋር በጠረጴዛ ዙሪያ በድርድር አሊያም በአለም አቀፍ ሕግና ስምምነቶች በመመራት ብሔራዊ ጥቅማችን ይከበራል ብለን እናልም ነበር። በህልማችን መሰረት ከህውሓት ነቀላ በኃላ መንግስት የሚሆኑት ከኤርትራ በረሃ የሚመጡት ስለሚሆኑ በጫካ የትግሉ ወቅት ከኤርትራ መንግስት ጋር የሚፈጥሩት የጠበቀ ቁርኝት በጠረጴዛ ዙሪያ የሚደረገውን ድርድር አልጋ በአልጋ ያደርገዋልም እንል ነበር። በተለይም የአሰብ ራስ ገዝን በተመለከተ መፍትሄ የሚያገኘው በድህረ-ህውሓት የአሰብ ጉዳይ የእግር እሳት ሆኖ ያንገበግባቸዋል ብለን በምናስባቸው ተጓዥ በረኸኞች፣ የቀጣዩ የብሩህ ተስፋ ዘመን መሪዎች እንደሚሆን እምነቱ ነበረን። እነዚህ የአሰብ ልጆች የኢትዮጵያን መንግስት በዴሞክራሲያዊ ምርጫ ሲይዙ የአባት አያቶቻቸውን አካባቢውን የማቅናት ስራ በመረጃና ማስረጃ አስደግፈው እየተደራደሩ ብሔራዊ ጥቅማችንን ያስጠብቃሉ ብለን በምኞት ተሞልተን ነበር።
                       ***
#ስምንተኛው ምክንያት ከድህረ-ሻዕቢያ እና ህውሓት በኃላ ሁለቱ ህዝቦች ተመልሰው ወደ አንድ ይመጣሉ የሚል ህልም ነበረን። አሁንም አለን። ለዚህም የተለያዩ ገፊ ምክንያቶችን አስቀምጠን ነበር። የመጀመርያው የኤርትራ ህዝብ ከኢትዮጵያ ህዝብ በመገንጠሉ አንዳችም ያተረፈው ነገር የለም። ይሄንንም ከነፃነት የጫጉላ ሽርሽር ሳይወጣ የደረሰበት ነው። የኢትዮጵያ ህዝብም በግልጽ ከሚታይ መጐዳት ውጪ ያተረፈው ነገር የለም። የመገንጠል የፓለቲካ ጨዋታው የጋራ ድል የሚያመጣ ሳይሆን የጋራ መሸነፍን ያከናነበ ነበር። የበርሊን ግንብ ፈራርሶ እየተመለከትን፤ ግሎባላይዜሽን አለምን ወደ አንድ መንደር እየወሰዳት መሆኑን እያየን፣ አውሮፓውያን የተለያዩ ዋልታዎች ከጨዋታ ሊያስወጧቸው ሲተጉ ወደ ህብረት ሲመጡ እየተገረምን፤  አንድ ህዝብ ነን የምንለው ኢትዮ-ኤርትራውያን መለያየታችን እጅግ አሳፋሪና አንገት የሚያስደፋ ነበር።
                       ***
#ዘጠነኛውና ዋናው ቁልፉ ምክንያት ፕሬዝዳንት ኢሳያስን ጨምሮ የሻዕቢያ ባለስልጣናት እኛ ለምንደግፋቸው እና ሁሉን አቀፍ ትግል ለማድረግ በረሃ የገቡትን ግንቦት ሰባትና ኢሳትን በልዩ ሁኔታ ስለሚንከባከቡ እኛም ልዩ ድጋፍ ማድረግ እንዳለብን ያልተፃፈ ውስጣዊ ስምምነት ነበረ። የሰጥቶ መቀበል አቅጣጫው የሚመነጨው ከዚህ እሳቤ ነው። ምንም እንኳን ይህ ውሳኔ “የፀረ-ህውሓት” የትግል ጐራውን ለሁለት የሰነጠቀ እና እስካሁንም መጠገን እንዳልቻለ በቀላሉ ማየት የሚቻል ቢሆንም።
እርግጥም ግንቦት ሰባትም ሆነ ኢሳት የፕሬዝዳንት የኢሳያስ አፈወርቂ ውለታ አለበት። ቀደም ብዬ በመነሻዬ እንደ ጠቆምኩት እንደ አንድ የሚዲያው አካል እንደነበረና የትግሉ ደጋፊ እንደሆነ ሰው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ለእኔም ባለውለታዬ ነበሩ። በዚህም ምክንያት መደበቅ የማይችሉና የሰማይ ስባሪ የሚያካክሉ የሻዕቢያና የፕሬዝዳንቱ ወንጀሎች ስንሸፋፍን ኖረናል። ውስን ያነሳ ውብ ይሁን በማለት የኤርትራን ህዝብ ለዴሞክራሲና ነፃነት ሊያነሳሳ የሚችለውን ቁስሉን፣ እባጩንና የሕሊና ህመሙን ስንሸፋፍን ከርመናል። ሻዕቢያ በዜጐቹ ላይ የሚፈጽማቸውን ግፎች አይተን እንዳላየን አልፈናል። የኤርትራ ዜጐች ሰቆቃ፣ ስደትና የጨለማ ኑሮ ዋነኛ መንስኤ የሚቀዳው ከሌላ አካል እንደሆነ አድርገን በማመን ሰብከናል። በዚህ አቋማችን በርካታ ኤርትራውያን እና የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች አዝነውብናል። ጽፈውብናል።
ዛሬ ግን ህውሓት ዳግም ላትመለስ ፓለቲካዊ ሞትን ስለሞተች ራሳችንን እንዲህ በማለት መጠየቅ ይኖርብናል! እንዲህ በማለት ግለ-ወቀሳ ማቅረብ ይኖርብናል፣
“እኛ ኢትዮጲያዊ ልሂቃን፣ ፓለቲከኞች፣ ጋዜጠኞች መቼ ነው በኤርትራውያን ጉዳይ ላይ ለህሊናችሁ መኖር የምንጀምረው?…መቼ ነው ከራሳችን ጥቅምና ራስ ወዳድነት አልፈን የኤርትራ እናቶችን የደም እምባ መመልከት የምንፈልገው?…ኧረ ለመሆኑ የኤርትራ ወጣቶችን እንደ ወንድምና እህታችን አድርገን በማሰብ እስከመቼ በመሃይምነት አረንቋ ውስጥ ተዘፍቀው ብቸኛ ምርጫቸው በሆነው ስደት የባህርና የበረሃ ሲሳይ ሲሆኑ በዝምታ እንመለከታለን?… እስከመቼ በሚዲያችን ሽፋን ለመስጠትና ለመወያየት እንፈራለን?…
” እስከ መቼ በኤርትራ ስንት የፓለቲካ ፓርቲ ፣ ስንት የሚዲያ ተቋም፣ስንት የፋይናንስ ተቋም እንዳለ እያወቅን አፋችንን እንለጉማለን?..ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ለቤቱ ቀጋ መሆኑን ልቦናችን እያወቀ ለእኛ አልጋ ነው ብለን ምስክርነት እየሰጠን እስከመቼ ከህሊናችን እየተጣላን እንኖራለን?…ከኤርትራ ደርሶ መልስ ላይ በአልኮል ብርጭቆ ማጋጨት ሰአት “ኤርትራን አይደለም ለልጆቼ ለጠላትም አልመኛትም” እያልን በተቃራኒው በህዝብ ፊት አገር ቤት የሚገኝ ሚዲያ ላይ ወጥተን የኢሳያስን ስትራቴጂክ አጋርነት እንናገራለን? የዴሞክራሲ ሽታ የሌለው፣ የነፃ አውጪነት ካባውን ጥሎ እርቃኑን የቆመ ግለሰብ ስትራቴጂ አጋራችን ነው ስንል ትንሽ ምንተሃፍረት አይሰማንም? ዛሬ እኮ የአንዳንዶቻን አጥብቆ ጠያቂና ሞጋች ልጆች ኮሌጅ ገብተዋል? “ዳዲ ምን እያልክ ነው?” ብለው ይጠይቁናል። ለምን በሰው ቁስል ላይ እንጨት ትሰዳለህ ብለው ይሞግቱናል። …እውነት እነጋገር ከተባለ እንዲህ አይነት ምስክርነቶች የኤርትራን ህዝብ የአበሳ ዘመን እንደሚያራዝም አጥተነው ነው?…በአስመራ ቆይታችን የመከራ ብዛት አቅላቸውን ያሳታቸው እናቶች አይተን ስቅስቅ ብለን አለቀስን ያልን አርበኞች እንዴት የቴሌቪዥን መስኮት ላይ አክሮባት እንሰራለን? ያውም ፈርሃ-እየሱስ ያደረብን ሃይማኖተኛ ነን እያልን?…ለእራቱ የሚሮጥ ውሻ ሆነን እስከመቼ እንኖራለን?
” በኤርትራ የህውሓትን ማዕከላዊ የሚስተካከሉ በርካታ የሰቆቃ እስር ቤቶች መኖራቸውን እያወቅን ለምን ዝም አልን?…ለኤርትራውያን ሰው ከመሆን የሚመነጭ አዘኔታ ሳይኖረን እንዴት ራሳችንን “የሰብአዊ መብት ተሟጋች” እያልን በአደባባይ እንገልጣለን?…ተሟጋችነቱ ይቅርብንና አንድ ሰብአዊነት የተላበሰ ሰው አይኑ እያየ፣ ጆሮው እየሰማ፣ ልቦናው እያስተዋለ፣ መቅኖውን አፍሶ በወገኖቹ ላይ የሚደርሰውን ጭቆናና የባርነት ኑሮ እያየ ዝምታን ይመርጣል?”
          —ይቀጥላል
( የግርጌ ማስታወሻ:- በሻዕቢያና ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ላይ መድብል እያዘጋጀሁ እንደሆነ የሚያውቅ አንድ ከመንግስት ቁልፍ አመራሮች ጋር ቁርኝት ያለው የቀድሞ ወዳጄ በጥብቅ ፈልጐ አገኘኝ። በደስታና ብስራት ስሜት ውስጥ ሆኖ ፕሬዝዳንት ኢሳያስና ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ በሚስጥር እየሰሩት ያለ ተአምረኛ ፕሮጀክት በማለት ዝርዝሩን መሰጠረኝ። በፍጹም ማመን አልቻልኩም። በዚህም ምክንያት ለወዳጄም ቅዠት ነው በማለት ተከራከርኩ። መቼም ለተናጋሪው ተስፋ ለእንደ እኔ ቢጤው ደግሞ ቅዠት የሆነን ነገር አካፍለን እንደማትሉኝ ተስፋ አደርጋለሁ። ይሁን እንጂ ወዳጄ እንደመሰጠረኝ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ የአቡነ አረጋይ መንፈስ አርፎባቸው የኢትዮጵያን ቅርጽና ይዘት የሚቀይር ተግባር ለመፈፀሙ አሲረዋል። በርግጥም የተባለውን ካደረጉ የኢትዮጵያ የዘለአለም ባለውለታ ይሆናሉ። እኔም የፌስቡክ የህይወት ዘመኔ የፊት ገጽ በማድረግ ዘወትር ሳመሰግናቸው እኖራለሁ። መዲናዬ አዲስ አበባ ላይ የምስጋና ሐውልት እንዲቆምላቸው እቀሰቅሳለሁ። የኤርትራ ህዝብ ይቅር እንዲላቸው በትጋት እሰራለሁ።… እስቲ ይታያችሁ የኢትዮጵያ የብስ ወደ ውሃ ተቀይሮ ባህር ሰርጓጅ የጦር መርከቦች በኢትዮጵያ ምድር ሲያጓሩ!ሲንቧቸሩ!…እስቲ ይታያችሁ አድሚራል እከሌ፣ ኮማንደር እንቶኔ እያልን ስንጣራ!…እስቲ ይታያችሁ በጀግናው ባህር ሃይላችን ስንኩራራ! …ያኔ! አዎ ያኔ! ሙዚቃውና ሪትሙ ስለሚቀየር እኛም እስክሳችንን እንቀይራለን። የዛ ሰው ይበለን። እስከዛው ግን ስራችንን እንቀጥላለን። )
Filed in: Amharic