>

ቅዱስ ሲኖዶስ ምዕመናን ከእንቅስቃሴ እንዲታቀቡ አስጠነቀቀ! (ታምሩ ጽጌ)

ቅዱስ ሲኖዶስ ምዕመናን ከእንቅስቃሴ እንዲታቀቡ አስጠነቀቀ!)

ታምሩ ጽጌ
ከግንቦት 5 ቀን 2012 ዓ.ም. ወዲህ ባሉት ሳምንታት የኮሮና ወረርሽኝ ሥርጭት እየጨመረ በመሆኑ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ምዕመናን ከእንቅስቃሴ እንዲታቀቡ አስጠነቀቀ፡፡
በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የቅዱስ ሲኖዶስ ጸሐፊ አቡነ ዮሴፍ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ቤተ ክርስቲያን የሚከተላትን ምዕመን ቀርቶ በመላው ዓለም ያለ ሕዝብ አንዱም ቢሆን በዚህ ወረርሽኝ ሕይወቱ እንዲያልፍ አትፈልግም፡፡
የአባቶች የጠዋት ማታ ፀሎት ይኸው ነው ያሉት አቡነ ዮሴፍ፣ ‹‹እግዚአብሔር የሰጠንን አዕምሮ በመጠቀም ሕግ ማክበር፣ የባለሙያዎችን ምክር መስማትና የሃይማኖት አባቶችን ምክር በመስማት ይህንን የወረርሽኝ ጎርፍ መሻገር ተገቢ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ከጥንቃቄ ውጪ ይህንን አደጋ መሻገር ስለማይቻል ያለው አማራጭ ራስን ከእንቅስቃሴ በማቀብ መጠንቀቅ ብቻ መሆኑንም አክለዋል፡፡
ለአንድ ወር በተደረገው የፆምና የፀሎት ቆይታ የተሻለ ውጤት መገኘቱንና እግዚአብሔርም ፊቱን እንደመለሰ የጠቆሙት ዋና ጸሐፊው፣ ምዕመናን ‹ቤተ እምነት እንዴት ይዘጋል? እግዚአብሔር ቤት ገብተን እንሙት› በማለታቸው ሙሉ በሙሉም ባይሆን በተወሰነ ለቀቅ እንዲል መደረጉን ተናግረዋል፡፡ ሕዝብ ለማዳን የተሠራውን በጎ ሥራ አንዳንዶች ከፖለቲካ ጋር፣ ከጎሳና ጤና ከማይሰጥ ነገር ጋር በማገናኘት፣ ምዕመናን ከአብያተ ክርስቲያን መራቅ እንደሌለባቸው በመስበክ የተወሰደውን ዕርምጃ ትክክል እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡
ነገር ግን አሁን ያለው የቫይረሱ ሥርጭት እጅግ በጣም እያስፈራ በመምጣቱ፣ ቅዱስ ሲኖዶስ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመምከር የራሱን ዕርምጃ እንደሚወስድ ጠቁመዋል፡፡
ፀሎት የግድ አብያተ ክርስቲያን ተሂዶ መሆን እንደሌለበትና ሁሉም ምዕመናን በቤታቸው ሆነው በመፀለይና አምላካቸውን በመለመን፣ ከዚህ መቅሰፍት መዳን እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡ ‹‹እግዚአብሔር አሳልፎ አይሰጠንም፤›› ያሉት አቡነ ዮሴፍ፣ መንግሥት አሁን እያደረገ ባለው መልካም ሥራ ላይ ይበልጥ በመሥራትና አስፈላጊውን ቁጥጥር በማድረግ፣ ይህንን ጊዜ ማሳለፍ ተገቢ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ቅዱስ ሲኖዶስ አብያተ ክርስቲያናትን እንደ ዘጋና እንደ ከፈተ በማስመሰልና ሰበብ በማቅረብ አባቶች እርስ በርሳቸው እንዳይስማሙና ግጭት እንዲፈጠር የሚያደርጉ ልቦና እንዲሰጣቸው አሳስበው፣ ምንም ይሁን ምንም በጎ ነገር በማድረግ ይህንን ጊዜ ማለፍ ካልተቻለ ውጤቱ የከፋ እንደሚሆን አስጠንቅቀዋል፡፡
Filed in: Amharic