>

መሆዶ❗️... አንዳንድ ሰዎች አሉ፤ ክፉ ተናግረው ክፉ የሚያናግሩ፦ መሆዶዎች! (ወሰን ሰገድ ገብረኪዳን)

መሆዶ❗️

አንዳንድ ሰዎች አሉ፤ ክፉ ተናግረው ክፉ የሚያናግሩ፦ መሆዶዎች!

ወሰን ሰገድ ገብረኪዳን
 
ሰውየው ምን ማለት እንደፈለገ ለማወቅ ነቢይነት አይጠይቅም፤ እናውቀዋለን። በ27  በሕወሐት መራሹ ኢህአዴግ ዘመን ሲባል የነበረ ነው። “እንበለው”፣ “ስም እንለጥፍበት”፣ “በጠላትነት እንፈርጀው”፤ “እንቅጨው” ወዘተ ማለት መሆኑን ጠንቅቀን እናውቃለን። አልፈንበታል….. ኖረንበታል…..
—–
፩] ትናንትና የወጣው ሪፖርተር ጋዜጣ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማስፈጸም ከተቋቋመው የሚኒስትሮች ኮሚቴ መሀከል አለመግባባት መፈጠሩን የሚያትት ዜና ይዞ ወጥቷል። የሚኒስትሮቹ ኮሚቴ አለመግባባት ደግሞ በዳንኤል በቀለ የሚመራው ሰብአዊ መብትኮሚሽን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጂ፣ እንዲሁም በአዋጁ ማስፈጸሚያ ደንብ የተወሰኑ አንቀጾች ላይ ማሻሻያ እንዲደረግ ጥያቄ ማቅረቡ ነው።
.
፪] ይኼ ሰውዬ ተስፋዬ ዳባ ይባላል።  አዋጁን ለማስፈጸም ከተቋቋመው የሚኒስትሮች ኮሚቴ ቦርድ አባልና  ምክትል ሰብሳቢ ነው። ኧረ እንደውም ረዥም ሥልጣን አለው፦ “የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰላምና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ” የሚል።
እናም ይህንን ዘልዛላ ሥልጣን የተሸከመው አቶ ተስፋዬ ‹‹ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን እየገጠመን ያለው መፈታተን በቀላሉ መታለፍ የለበትም። የሚኒስትሮች ምክር ቤት ያወጣውን ደንብ ኮሚሽኑ መተቸቱ በቀላል የሚታለፍ አይደለም፡፡ የሚኒስትሮች ኮሚቴ ይኼንን ጉዳይ በጥንቃቄ ማስተዋል አለበት፤›› ማለቱን ሪፖርተር ዘግቧል።
ሰውየው ይህንን ብሎ አላበቃም፦
 “ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በኩል የመጡ መፈታተኖችን ቆም ብሎ ከጀርባው ምን እንደተፈለገ ማየት አስፈላጊ ነው” ይላል።
.
፫] ይህ ማለት ምን ማለት ነው? ኮሚሽኑ ተፈታተነን ማለት ምን ማለት ነው? በቀላሉ መታለፍ የለበትም ማለትስ? ከጀርባው ምን እንደተፈለገ ማየት አለብን ማለት ምን ማለት ነው?
.
ሰውየው ምን ማለት እንደፈለገ ለማወቅ ነቢይነት አይጠይቅም፤ እናውቀዋለን። በ27  በሕወሐት መራሹ ኢህአዴግ ዘመን ሲባል የነበረ ነው። “እንበለው”፣ “ስም እንለጥፍበት”፣ “በጠላትነት እንፈርጀው”፤ “እንቅጨው” ወዘተ ማለት መሆኑን ጠንቅቀን እናውቃለን። አልፈንበታል። ኖረንበታል።
.
፬] መሆዶዎች እንዲህ ናቸው። ወደፊት አያዩም፦ ወደኋላ እንጂ። ነገረ ሥራቸው ሁሉ ከጀርባ ነው። የዓለም የፖለቲካ ልሂቃኖችንም የሚነግሩን ይኼንን ነው።
 “በየትኛውም ሃገር ለውጥ ሂደት ውስጥ፤ ለውጥ  እጅግ ፈታኝ ነገር የሚገጥመው ከተቃዋሚዎች አይደለም። ለውጥን እንደግፋለን ከሚሉ፣  የለውጥ ባቡር ውስጥ ከተንጠለጠሉ፣ በስልጣን በተጠቀለሉ፣ በለውጥ ስም ከሚፏልሉ ወገኖች ነው” ይላሉ።
.
 ፭] ይህ ሰው እንደዚያ ነው። ፓርላማ ውስጥ ስለ ለውጥ ይተረተራል፤ በየስብሰባው ይተረተራል። በዚያው አጋጣሚ የለውጡን “ቁጭት” ይተረትራል።
ገና አንድ ሁለት ገለልተኛ ነፃ ተቋማት ፈጠርን ብለን ሳናባቃ፣ የፈጠርናቸው አንድ ሁለት ተቋማት ፍፁማዊ ነፃነት ማግኘታቸውን እርግጠኛ ባልሆንንበት ሁኔታ፣ “ከጀርባ ምን እንዳለ መታየት አለበት” እያለ ጣቱን ይቀስራል።
.
፮] መሆዶዎች እንዲህ ናቸው። ማፍረስ እንጂ መገንባት አይሆንላቸውም። የጀርባቸው (የኖሩበት) እንጂ የፊታቸው አይታያቸውም። መጠየቅ እንጂ መጠየ’ቅ አያውቁም። ሲጠየቁ ዳቦውን እንደተነጠቀ ሕፃን ማለቃቀስ ነው የሚቀናቸው። ደግሞም እንደሕፃን ስለዳቦ ብቻ ነው የሚያስቡት፦ ስለ መብላት። የቀን ከሌት ሃሳባቸው ዳቦ ብቻ ነው። ስለ ነፃነት፣ ስለ ነፃ ተቋማት አያገባቸውም፤ አይገባቸውምም። የጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ መንግስት እንደዚህ ዓይነት መሆዶዎችን ይዞ የት እንደሚደርስ እንጃ።
.
፯  እንደዚህ ዓይነት መሆዶዎች ያስጠሉኛል። ያንገፈግፉኛል። ፊት ለፊታቸው ቆሜ መሃል ጣቴን ባሳያቸው  እና ….ብላቸው ደስ ይለኝ ነበር። ነበር ፦ በነበር ቀረ እንጂ!…
(ግን ግን …..መሀል ጣት መቀሰር በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ውስጥ ተካቷል እንዴ!? ቢያስጠይቅም፣ ባያስጠይቅም “ባፋንኩሎ!” ከማለት ወደ ኋላ አልልም።)
Filed in: Amharic