>

እስልምናን በሰላም የተቀበለ፣ ለፍትሕ እና ለእውነት የቆመ ኢትዮጵያዊ/አክሱማዊ ማንነት ዛሬ ወዴት አለ…?! (በተረፈ ወርቁ)

እስልምናን በሰላም የተቀበለ፣ ለፍትሕ እና ለእውነት የቆመ ኢትዮጵያዊ/አክሱማዊ ማንነት ዛሬ ወዴት አለ…?!

 

በተረፈ ወርቁ


‘‘… በዛች ምድር ለእውነት፣ ለፍትሕ የቆመ ሐቀኛ፣ ደግ የሆነ የሐበሻ ንጉሥንና እንግዳ ተቀባይ ሕዝብን ታገኛላችሁ… ወዳጆቼ እባካችሁ ነፍሳችሁን አድኑ… ነፍሳችሁን ከክፉዎች፣ ከዓመፀኞች ቁጣና ሰይፍ አድኑ፣ የሰላም ጌታ፣ የአላህ እዝነት ከእናንተ ጋር ይሁን…!’’

(ነቢዩ መሐመድ- ሰ.ዐ.ወ.)


በአንድ ወቅት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ እያለሁ በኢትዮጵያ ታሪክና ቅርስ ላይ ጥናት እና ምርምር የሚያደርግ አንድ አሜሪካዊ ወዳጅ ነበረኝ፡፡ ይህ ጎልማሳ የሚቺጋን ስቴት ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ሲሆን ወደሀገራችን የመጣበት ምክንያትም፤ ለድኅረ ምረቃ ትምህርቱ ምረቃ ማሟያ የሚሆነውን የጥናት ድርሳኑን፤ ‘‘the Little Hìjìra to Aksum’’ በሚል አርእስት ዙሪያ ለመሥራት ነበር፡፡ ታዲያ አንድ ወርኻ ክረምት ከዚህ ወዳጄ ጋር ለጥናት ሥራው ወደ ትግራይ ክልል አብረን ተጉዘን ነበር፡፡ የዚህ የመስክ ጉዞ ሥራ ዓላማም የመጀመሪያዎቹ የነቢዩ መሐመድ ተከታዮች/ሱሃባዎች ከሳውዲ ዐረቢያ ወደኢትዮጵያ፣ ወደአክሱም ግዛት ያደረጉትን ስደት/ሂጅራ በተመለከተ መረጃዎችን ለመስብሰብ ነበር፡፡

ታዲያ የዚህ ጥናት የመስክ ጉዞ አንዱና ዋንኛ መዳረሻችን የነበረው ደግሞ በኢስላም ኡለማዎች፣ ምሁራን ዘንድ- ‘‘የእስልምና ሃይማኖትን በሰላም ተቀብሏል፤’’ ተብሎ በሚታመነው በኢትዮጵያዊው ንጉሥ አርማሕ (አልነጃሺ) ስም የታነፀው መስጊድ ነበር፡፡ በአልነጃሺ መስጊድ ጉብኝት ቆይታችንም ያገኛናቸው የሃይማኖቱ ታላላቅ አባቶችና ሼኽዎች ወደዚህ ቅዱስ ስፍራ የመጣንበትን ጉዳይ በትሕትና አስረዳናቸው፡፡

እነርሱም በኢትዮጵያዊ መልካም መስተንግዶ በሰላም ተቀብለውን በክብር አስተናገዱን፡፡ ከመስተንግዶው በኋላም እነዚህ የሃይማኖቱ መምህራን ኢስላም በተወለደበት በሳውዲ ዐረቢያ ምድር (መካ እና መዲና) ገና በሁለት እግሩ ከመቆሙ በፊት በኢትዮጵያ ምድር በሰላም ተዘርቶ ያበበትን የኢስላምን ወርቃማ የታሪክ ዘመንን፤ በታሪክ ሰነዶችና በትውፊት/በቃል ከሃይማኖቱ ታላላቅ አባቶች፣ ኡለማዎች ዘንድ የተላለፈላቸውን መሳጭ ታሪክ ተረኩልን፡፡

 

እንደ ኢስላም ሃይማኖት አስተምህሮ- ነቢዩ መሐመድ በዘመናቸው በሕዝባቸው መካከል የነገሠውን የሞራል ውድቀት፣ የሥነ ምግባር ዝቅጠትና የባዕድ አምልኮ መንሰራፋት ለማጥፋት በአላህ የተመረጡ ታላቅ ሰው ነበሩ፡፡ ታዲያ ነቢዩ መሐመድ ሕዝባቸውን፤ ‘‘ከባዕድ አምልኮ ራቁ፣ አላህን ብቻ እመኑ፣ እርሱን ብቻ ተከተሉ፣ ፍሩ፣ ክፋትንና ጥላቻን ተጸየፉ፣ ከእኩይ ሥራ ራቁ፣ ለፍትሕና ለእውነት ቁሙ!’’ የሚለው የኢስላም ሃይማኖት አስተምህሮአቸው በዘመኑ ከነበሩ የቋረሽ ጎሳ ሹማምንትና ባለሟሎች ዘንድ ከባድና አስጨናቂ የኾነ ተቃውሞን አስነስቶባቸው ነበር፡፡

ነቢዩ መሐመድ ግን በዚህ ከጠላቶቻቸው በተነሳባቸው ተቃውሞ፣ ስደትና መከራ በፍፁም አልተበገሩም፡፡ እናም ለተከታዮቻቸውም እንዲህ አሏቸው፤

እኔ እዚሁ ሆኜ ከአላህ ከጌታዬ ለተሰጠኝ ሃይማኖት በትዕግሥት፣ በጽናት የመጣውን ሁሉ እቀበላለሁ፤ ለኢስላም ሞትንም ቢሆን ለመቀበል እንኳን ሳይቀር ቆርጫለሁ፤ እናንተ የአላህ ፍሬዎቼ፣ እውነተኛ ወዳጆቼ የሆናችሁ ተከታዮቼ- የክፉዎች መከራ፣ የወደረኞቻችን፣ የጭካኔ ሰይፍ በእናንተ ነፍስ ላይ ያልፍ ዘንድ አልፈቅድም… የእናንተ መከራ ለእኔ ይሁን! እናም ወገኖቼ ለነፍሳችሁ እረፍትን፣ ሰላምን፣ ፍትሕን ወደምታገኙበት ወደ ኢትዮጵያ ግዛት፣ ወደ ሐበሻ ምድር በፍጥነት ሂዱ፣ ሽሹ…

በዛች ምድር ለእውነት፣ ለፍትሕ የቆመ ሐቀኛ፣ ደግ የሆነ የሐበሻ ንጉሥን ታገኛላችሁ… ወዳጆቼ እባካችሁ ነፍሳችሁን ከክፉዎች፣ ከዓመፀኞች ቁጣና ሰይፍ አድኑ፣ የሰላም ጌታ፣ የአላህ እዝነት ከእናንተ ጋር ይሁን! ብለው ነቢዩ ተከታዮቻቸውን ዱኣ አድርገው በሰላም ሸኟቸው፡፡

እንግዲህ የኢስላም ሃይማኖት ሊቃውንት እንደሚያስተምሩት፤ ይህ የነቢዩ መሐመድ ተከታዮች ወደ ኢትዮጵያ ምድር ያደረጉት ሂጅራ/የስደት ጉዞ፤ ነቢዩ መሐመድ ከመካ ወደ መዲና ካደረጉት ሂጂራ በፊት የተደረገ ‘‘the Little Hìjìrà/ትንሹ ሂጂራ’’ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ በነቢዩ መሐመድ መልካም የምክር ቃል ባሕር አቋርጠው ነፍሳቸውን ለማዳን ወደ ኢትዮጵያ ግዛት የመጡትን የነቢዩ ተከታዮችን/ሱሃባዎችን ጠላቶቻቸው ግን እስኪያጠፏቸው ዘንድ እረፍትን አልፈለጉም፡፡ እናም የቋረሽ ሹማምንት ወደ አክሱም ነጉሥ አርማህ ወርቅና የከበረ ስጦታን የያዙ መልእክተኞችን በፍጥነት እንዲህ ሲሉ ላኩ፤

‘‘የተከበረክ ንጉሥ ሆይ! ወደግዛትህ የመጡ እነዚህ ሰዎች ሕዝብን ያወኩ፣ እምነታችንን ያረከሱ፣ ክፉዎችና ዓመፀኞች ናቸውና እጃቸውን ይዘህ ትልክልን ዘንድ እንለምንሃለን፣ እናማጽንሃለን፡፡’’

የቋረሽ ገዥ መልእክተኞችን በቤተ መንግሥቱ የተቀበላቸው የአክሱም ገዥ፣ ንጉሥ አርማህ ወደ ግዛቱ የገቡ የነቢዩ መሐመድ ተከታዮችን ወደ እርሱ አስጠርቶ በጠላቶቻቸው ዘንድ የተከሰሱበትን ክስና ስለሃይማኖታቸው አንዳንድ መሠረታዊ ጥያቄዎችን አቀረበላቸው፡፡ በአክሱም ንጉሥና የሃይማኖት ሊቃውንት ፊት ዘንድ የቀረቡት የነቢዩ መሐመድ ተከታዮችም የቀርበባቸው ክስ ሐሰት መሆኑንና ወደ ኢትዮጵያ ግዛት፣ ወደተከበረው የሐበሻ ንጉሥ የመጡትም፣ ፍትሕንና ሰላምን ተጠምተው፣ ከአሳዳጆቻቸው ዘንድ መጠጊያና መሸሸጊያ ፈልገው እንደሆነ የታላቁን ጌታ፣ የአላህን ስም ጠርተው አስረዱ፡፡

በ፰ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነቢዩ መሐመድን የሕይወት ታሪክን የጻፈው- ኢብን ኢሻቅ የተባለ ምሁር እንደሚነግረን፤ የነቢዩ መሐመድ ተከታዮች ከነበሩት መካከል ከጃፋር አቡ ጣሊብ ጋር በክርስትና ሃይማኖት አስተምህሮ ዘንድ በነበራቸው ውይይት ወቅት- በኢስላም አስተምህሮ ያለውን እውነት ሲገልጽለት- የሐበሻው ንጉሥና ሊቀ ጳጳሱ ልባቸው ተነክቶ ማልቀሳቸውን ይተርክልናል፡፡

የአክሱም ንጉሥ ከሳውዲ ዐረቢያ ለመጡት መልእክቶኞች እንዲህ አላቸው፤

‘‘ወደ ግዛቴ የገቡ እነዚህ ሰዎች በአስተምህሮአቸው ዘንድ አንዳችም ክፉ ነገርን አላገኘሁም፡፡ መጠለያና መሸሸጊያ ፈልገው የተማጸኑኝን እነዚህን ሰዎች አሳልፌ አልሰጣችሁም፡፡ የሃይማኖቴ መምህር የኾነው ጌታዬና መድኃኒቴ ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን አላስተማረኝም… እነዚህ ሰዎች ፍትሕን፣ ሰላም ሽተው ወደ እኔ መጥተዋል፣ በግዛቴ ተጠልለዋልና በእውነት እጠብቃቸው ዘንድ ይገባኛል፡፡ እናንተም ጠላትነትን፣ ክፋትን ትታችሁ በግዛቴ በሰላም ለመኖር ከፈለጋችሁ ሀገሬ በአክብሮት ሕዝቤም በፍቅር ይቀበልሏችኋል፤ በዚህ ለመኖር ፈቃዳችሁ ካልሆነም በሰላም ወደ ሀገራችሁ መመለስ ትችላላችሁ፤’’ ብሎ አሰናበታቸው፡፡

በሳውዲ ዐረቢያና መካከለኛው ምሥራቅ ስደትና መከራ የገጠመው የእስልምና ሃይማኖት በኢትዮጵያ ምድር- በአክሱም ግዛት እንደ ክርስትና ሃይማኖት ሁሉ በሰላም፣ በነጻነት ተዘርቶ ለመብቀል ቻለ፡፡ ይህን አስደናቂ የሆነውንና ለሁለቱ ታላላቅ የመካከለኛው ምሥራቅ ሃይማኖቶች የሰላም ሀገር ስለሆነችው ኢትዮጵያ/አክሱም፤ በአዲስ አባባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ትምህርት ክፍል የመካከለኛው ምሥራቅ ፖለቲካ ታሪክ ተመራማሪና የእስልምና ሃይማኖት ምሁር የነበሩት ፕ/ር ሁሴን አህመድ፤ Aksum in Muslim Historical Tradition በሚለው ጥናታዊ ጽሑፋቸው እንዲህ ይላሉ፤

Aksum possesses the unique distinction of being at once the cradle of both Christianity and Islam in Ethiopia, and perhaps represents the earliest example of a geographical setting favorable for a peaceful encounter and harmonious coexistence between two great monotheistic religions: Christianity and Islam.

ጥንታውያን ኢትዮጵውያን የእስልምና ሃይማኖት ታላላቅ አባቶች እንደሚሉት- የነቢዩ መሐመድን ተከታዮች በግዛቱ በሰላም ተቀብሎ ያስተናገደው የአክሱም ንጉሥ የነበረው ንጉሥ አርማህ ነቢዩ መሐመድን ለመጎብኘት ወደ መካ ለመሔድ ሲዘጋጅ ሳለ ሞት እንደቀደመው በሚከተለው ትውፊታዊ የመንዙማ ግጥም ያስታውሳሉ፤

ወዳንቱ ሲመጣ ወዳንቱ ሲሸሽ፣

ትግሬ ላይ የቀረው ወዳጅዎ አል-ነጃሽ፡፡

 ታሪክ እንደሚመሰክርልን ኢትዮጵያ ለሙስሊሙ ዓለም ታላቅ ባለውለታ የሆነች ሀገር ናት፡፡ ይህችን በዛ ክፉ ዘመን ለነቢዩ መሐመድና ለተከታዮቻቸው ጥላ ከለላ የሆነች ሀገረ ኢትዮጵያ በእስልምናው ዓለም ልዩ ስፍራ አሰጥቷታል፡፡ ከላይ በጠቀስኩት ጥናታዊ ሥራቸው ፕሮፌሰር ሁሴን አህመድ፤ al-Tiraz al-Manqush fi Mahasin al-Habush (The Colored Brocade on the Good Qualities of the Ethiopian) በሚል ርእስ- መሀመድ አብዱል ባኪ አል ማቅዚ እ.አ.አ. በ1583 የጻፉትን ታሪካዊ ሰነድ ዋቢ አድርገው፤ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን በነቢዩ መሀመድና በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ ያላቸውን ተወዳጅነት እና ክብር እንዲህ ገልጸውታል፤ ‘‘who brings an Ethiopian man or woman into his house brings the blessings of God there’’

ይህ ልቦለድ ታሪክ ወይም የፈጠራ ድርሰት አይደለም፡፡ ይህ በኢትዮጵያ ምድር፣ በአክሱም ግዛት ከ1400 ዓመታት ገደማ በፊት የኾነ የኢስላም ሃይማኖት ወርቃማ ታሪክ አንድ/ዐቢይ አካል ነው፡፡ ይህ ዓለም ሁሉ በአድናቆት፣ በአግራሞት እጁን አፉን ላይ እንዲጭን የተገደደበት፣ ፍቅር ያሸነፈበት፣ ፍትሕ ድል የነሳበት፣ ከፈጣሪ ዘንድ ለሰው ልጆች ሁሉ የተሰጠ የሕሊና ነጻነት፣ ነጻ ፈቃድ ከፍ ያለበት አኩሪ የታሪካችን አካል ነው፡፡

በእውነት ነው የምላችሁ ለጸሎትም ሆነ ለጉብኝት በጥንታዊውና በታሪካዊው የአልነጃሽ መስጊድ፣ በነቢዩ መሐመድ የመጀመሪያዎቹ ተከታዮች/ሱሃባዎች ቅዱስ መካነ መቃብር መካከል በርጋታ ስታልፉ የሚሰማችሁ ስሜት የከበረና ታላቅ ነው፡፡ ይኸውም ሰው የመሆን ክብር፣ ታላቅ የመንፈስ ልእልና… ለሕሊና ነጻነት፣ ለሰው ልጆች ሁሉ ከፈጣሪ ዘንድ ለተቸረ ነጻ ፈቃድ- ለፍትሕና ለእውነት ዘብ የቆመ፣ የኢትዮጵያዊነት/የአክሱማዊነት ሕያውና ክቡር መንፈስ፣ ታላቅ ማንነት! የሰው ልጅነት! 

‘‘እውነት ወደነገሠባት ወደኢትዮጵያ ምድር፣ ወደ አክሱም ግዛት ሂዱ- በዛ ለእውነት የቆመ፣ ለፍትሕ የሚሟገት የሐበሻ ንጉሥ፣ ደግና እንግዳ ተቀባይ የሆነ ሕዝብ አለና…’’ ዛሬ እንዲህ እንድንጠይቅ ግድ ይለናል… በደምና በአጥንት ቆጠራ ሰይፍ በምንማዛዝበት፣ በዘርና በጎሳ ልዩነት፣ በሃይማኖት ጥላቻ በምንገፈፋፋበት፣ በምንጋደልባት ኢትዮጵያችን፣ ምድራችን- የሕሊና ሚዛን፣ ሰው የመሆን ክብር መገለጫ፣ የፍትሕ ተምሳሌት አድርጎ ነቢዩ መሐመድ፣ ዓለም ሁሉ የመሰከሩለት- የኢትዮጵዊነት/የአክሱማዊነት ታላቅና ሕያው የነጻት መንፈስ፣ ሰው የመሆን ክብር ዛሬ ወዴት አለ…?!

ሰላም!

ለእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ዒድ ሙባረክ! እንኳን ለኢድ አልፈጥር አደረሳችሁ!

Filed in: Amharic