>

አያቶቹን ገርባ ካደረገው ኦሮሞ በላይ ኦሮሞ ለመሆን ያዙኝ ልቀቁኝ  ባዩ ከማል ገልቹ . . .!!!  (አቻምየለህ ታምሩ)

አያቶቹን ገርባ ካደረገው ኦሮሞ በላይ ኦሮሞ ለመሆን ያዙኝ ልቀቁኝ  ባዩ ከማል ገልቹ . . .!!! 

አቻምየለህ ታምሩ
 
* የኦነጋውያን የድንቁርና ትምህርት ቤት ከሰራባቸው ትላልቅ ሕጻናት መካከል የአርሲው ከማል ገልቹ ቀዳሚው ነው። ይህ ትምህርቱን እንኳ ያልጨረሰ የማትሪክ ተፈናቃይና የ11ኛ ክፍል ቁስለኛ ከሰሞኑ በጃዋር ቴሌቭዥን ላይ ቀርቦ  ነፍጠኛ የሰራት ኢትዮጵያ እንደገና ፈርሳ ካልተሰራች ለኦሮሞ አትሆንም ሲል  ድንቁርና በሚሰጠው ድፍረት እየተመራ ተናግሯል።
—-
ሲጀመር ከማል ገልቹ ኦሮሞ አይደለም። ከማል ገልቹ ልክ እንደ ኦቦ ጂኔይዲ ሳዶ [Loodee የሚባል የሐድያ ጎሳ ተወላጅ]፣ የምዕራብ ሶማሊያው ጀኔራል እንደነበረው እንደ ዋቆ ጉቱ [ Rayayitu የሚባል የሐድያ ጎሳ ተወላጅ]፣ እንደ ፕሮፌሰር አባስ ገነሞ [Assala/Akkiya የሚባል የሐድያ ጎሳ ተወላጅ]፣ እንደ ዶክተር ኑሮ ደደፎ [Assala የሚባል የሐድያ ጎሳ ተወላጅ]፣ እንደ ጠይባ ሐሰን [ኦሮምያ ክልል የሚባለው ምክትል ፕሬዝደንት የነበረች ስትሆን Saymannaa የሚባል የሐድያ ጎሳ ተወላጅ ናት]፣ እንደ አሚን ጁንዲ [ካናዳ ሲኖር የኦነግ ለአንድነት ዋና ፀሐፊ የነበረና በአሁኑ ወቅት የ«ኦሮሚያ» ክልላዊ መንግሥት ፕሬዚዳንት አማካሪ ሆኖ በመስራት ላይ የሚገኝ ሲሆን Shafila የሚባል የሐድያ ጎሳ ተወላጅ ነው] ወዘተ ሁሉ ሐድያ ነው። እነዚህን የዘረዘርኋቸውን ኦሮሞ ያልሆኑ ዛሬም ድረስ አርሲ ውስጥ የሚገኙ ጎሳዎች መሆናቸውንና የኦሮሞ አባ ገዳ አካባቢውን ወርሮ በነባሩ ሕዝብ ላይ በኃይል ኦሮሞነትን ሲጭን ማንነታቸው የሆነውን ሐድያነትን እንዲተው የተደረጉ ጎሳዎች መሆናቸውን ማረጋገጥ የሚሻ ቢኖር ጀርመናዊው ፕሮፌሰር በርካምበር «A History of the Hadiyya in Southern Ethiopia» በሚል በ1966 ዓ.ም. ባሳተሙት መጽሐፍ ውስጥ ከገጽ 459-462 የጻፈውን ማንበብ ይችላል።
ባጭሩ ከማል ገልቹ ዛሬ ኦሮምኛ ተናጋሪ የሆነው የኦሮሞ የገዢ መደብ የሐድያን ምድር [ዛሬ አርሲ የሆነውን]  ወርሮ ማንነታቸውን ተገደው እንዲተው፣ ቋንቋቸውን እንዳይጠቀሙና ባሕላቸውን በኃይል እንዲለውጡ ተደርገው የኦሮሞ ማንነት ተጭኖባቸው ኦሮምኛ እንዲናገሩ ከተገደዱ የሐድያ ቤተሰቦች በመወለዱ ነው። ከማል እንደገና ፈርሳ ካልተሰራች ለኦሮሞ አትሆንም ሲል  ያዙኝ ልቀቁኝ የሚለው በኃይል የተጫነበትንና አያት ቅድመ አያቶቹን እንደከብት እየነዳ የሸጠውንና ራሱን ረስቶ ሌላ ሰው እንዲሆን ስላገደደው የባዕድ ማንነት ነው። ከማል ማንነት እንዲከበር የምሩን የሚታገል ቢሆን ኖሮ ከሁሉ በፊት በኃይል የተጫነበትን የኦሮሞ ማንነት አሽቀንጥሮ ጥሎ የአያት ቅድመ አያቱ የሆነውን የራሱን ማንነት ሐድያነትን ይላበስ ነበር። ግና ሰውዬው  ድንቁርና በሚሰጠው ድፍረት እየተመራ ያልሆነው የለምና በሰው ወርቅ ሊደምቅ አያት ቅድመ የአያቶቹን ማንነት ክዶ አያት ቅድመ አያቶቹን ገርባ ካደረገው ኦሮሞ በላይ ኦሮሞ ለመሆን ያዙኝ ልቀቁኝ ያላል።
ከማል ገልቹ እ.አ.ኤ. በ2016 ዓ.ም. በአትላንታ ጆርጂያ  በጃዋር መሐመድ አጋፋሪነት በተካሄደው «የኦሮሞ ትግል መሪዎች ኮንቬንሽን» ያስቀመጠው ግብ እንዲያሳካ ስብስቡ በወያኔ ቋንቋ አንድ «ኮማንድ ፖስት» ሰጥቶት ነበር።  በነገራችን ላይ «የኦሮሞ ምሑራንና ብሔርተኞች ስብሰባ» በተባለው የጆርጂያው «የኦሮሞ ትግል መሪዎች ኮንቬንሽን» ባወጣው መግለጫ «የኦሮሞ ሕዝብ ትግል ለነጻነት የሚበቃው እንደ ኤርትራ፣ ትግሬ እና ደቡብ ሱዳን ሲኾን ነው!» ይል ነበር።ያገራችን ሰው «ቸር ተመኝ ቸር እንድታገኝ» ይላል። ፈረንጅም “Aim to the stars! If you miss, you will hit the top of the tree” ይላል። «የኦሮሞ ምሑራንና ብሔርተኞች ስብሰባ» የተመኛት የኢሳይያስ አፈወርቂ ኤርትራ መላው ዓለም ማዕቀብ ያደረገባት፣ የአፍሪካ ሰሜን ኮርያ፣ ዜጎቿ በዓለም ላይ በየዓመቱ በገፍ የሚሰደዱባትና ያልተሰደዱትም የምድር ሲኦል ኑሮን የሚገፉባት፣ መሪዋ ከዛሬ ነገ የዓለም ጦር ፍርድ ቤት ይቀርባል እየተባለ የሚባንን ጉድ ያለባት ሀገር ናት።
ሌላው  የአትላንታው «የኦሮሞ ምሑራንና ብሔርተኞች ስብሰባ» የተመኛት የወያኔዋ ትግራይም ገዢዋ ወያኔ ጭንቅ ላይ ነው፡፡ ደቡብ ሱዳንም ሀገር ሳይኾን የከሸፈ ሀገር (failed State) ነው። የተሻለ አድማስ ባይኖር ወይ መግዛት አልያም መዋስ ሲገባ «የኦሮሞ ትግል መሪዎች» ነን ያሉን ኦነጋውያን በቃላት እንኳን ቢኾን «ታላቅና ገራገር» ለሚሉት የኦሮሞ ሕዝብ የቀረጹለት አድማስ ግን የመከራ ዘመን እየገፉ ከሚገኙበት ከታሰሩበት የኑሮ ሰንሰለት፣ ከገቡበት ምድራዊ ሲኦል ነበልባላዊ እቶን የሚታደጋቸው መድኅን የሚፈልጉ ዜጎች ምድር እንዲኾኑ የተደረጉ ሀገሮችን ነው።
ከማል ገልቹ አስመራ ተከፍቶ የነበረው የኦ.ነ.ግ ቅርንጫፍ መሪ ነበር። ከማል የአስመራው ኦ.ነ.ግ መሪ ሆኖ የተመረጠው በኦ.ነ.ግ ጠቅላላ ጉባኤ ነበር። ኾኖም ግን ዳውድ ኢብሳ አሻፈረኝ ብሎ መፈንቅለ መሪ በማካሄድ ከሥልጣኑ አባረረው። በዚህም ከማል የዐባይ ፀሐዬ እድል ገጠመው። ዐባይ ፀሐዬ ከስብሓት ነጋ በኋላ በሕ.ወ.ሓ.ት ጠቅላላ ጉባኤ የሕ.ወ.ሓ.ት መሪ ሆኖ ተመርጦ ነበር። ኾኖም ግን በ1977 ዓ.ም. «ሕንፍሽፍሽ» ባሉት አውራጃዊ ክፍፍል ወያኔዎች ሲራኮቱ መለስ ዜናዊ በጠቅላላ ጉባዔ የተመረጠውን ዐባይ ፀሐዬን አውርዶ በመፈንቅለ መሪ በጉልበቱ የሕ.ወ.ሓ.ት መሪ ለመኾን በቃ። ዳውድ ኢብሳም ከማልን ያደረገው እንደዚያ ነው።
ዳውድ ኢብሳ በኦ.ነ.ግ ጠቅላላ ጉባኤ መሪ ተደርጎ በተመረጠው በከማል ገልቹ ላይ መፈንቅለ መሪ ያካሄደው ኢሳይያስን ተማምኖ ነበር። ዳውድ ኢብሳ እንደ አንዳርጋቸው ጽጌ ኢሳይያስ የማይጠረጥረው የኢሳይያስ ታማኝ ነበር። ዳውድ አስመራ የተከፈተው የኦ.ነ.ግ ቅርንጫፍ መሪ ኾኖ በንግድ ሥራ ተሠማርቶ መካከለኛው ምሥራቅ ይመላለስ ነበር። አንድ አስመራ አብሯቸው የኖረ ወዳጄ እንደነገረኝ አሥመራ ከተማ ውስጥ ቄንጠኛ መኪና ከሚነዱት ሰዎች መካከል አንዱ የሻዕብያ ሰላይና የቡርቃ ዝምታ ደራሲው ተስፋዬ ገብረአብ ነው። ቄንጠኛዋን መኪና ለተስፋዬ የሸጠለት ደግሞ ዛሬ የኦነግ መሪ የሆነው ዳውድ ነበር።
ከማል ገልቹ ዐቢይ አሕመድ ከወያኔ እንዲያመልጥ ምሥጢር አሾልኮ ሰጥቶት ወደ ኤርትራ ሳይኮበልል በፊት ታማኝ የወያኔ አገልጋይ ነበር። ከማል በደርግ  ዘመን ውትድርና የጀመረው ዛሬ  እንደገና ፈርሳ ካልተሰራች ለኦሮሞ አትሆንም የሚላትን  ኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ አንግቦ ወደ ሰሜን  በዘመተበት ወቅት ነበር። ከዚያም ትንሽ እንደዋጋ ሻዕብያ ማርኮት ለወያኔ በምርኮ ከተሰጡና ኦ.ሕ.ዴ.ድን እንዲመሰርቱ ከተደረጉት የሻዕብያ ምርኮኞች አንዱ ሆነ።
ወያኔን ፈርቶ ወደ አስመራ ከፈረጠጠበት ሀገር የአማራ ልጆች ከወያኔ ጋር ተፋልመው በከፈሉት መስዕዋትነት ወያኔ መቀሌ ሲመሽግ፣ በግብዣ በኡጋንዳ አድርጎ በቦሌ በኩል ገብቶ ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ ቡራ ከረዩ የሚለው ከማል ከዚህ በፊት ሁለት ጊዜ በሻዕብያ በምርኮኝነት የተያዘ ሲኾን ሦስት ጊዜ ደግሞ ከድቷል። የአትላንታው ስብሰባ የደቡብ ኮማንድ ፖስት የተባለውን ቦረናን፣ ባሌንና አርሲን የሚያጠቃልለው ኮማንድ ፖስት አዛዥ ያደረገው ከማል ገልቹን ነበር ብያለሁ።  ከማል ጀኔራል የሆነው ከተራ የገበሬ ወታደርነት ተነስቶ ነው። ከማል መጽሐፉ «ብርሃን ይኹን አለ ብርሃንም ኾነ!» እንዳለው መለስ ዜናዊ ጀነራልነት ሲያድል ከምንም አስንቶ ‹ጀነራል› ያደረገው ‹ጀኔራል ኹን ተባለ፣ ጀነራልም ኾነ!› የሚባል ዓይነት ሰው ነው።
ከማል አስመራ በዳውድ ኢብሳ መፈንቅለ መሪ ከተካሄደበት በኋላ አምባሳደር ኾኖ ነበር። ከማል አምባሳደር የኾነው ለሀገር እንዳይመስላችሁ። ከማል አምባሳደር የኾነው ለኢሳይያስ አፈወርቂ ነበር። ከማል የኢሳይያስ አፈወርቂ አምባሳደር ኾኖ ምሥራቅ አፍሪቃ ተልኮ ነበር። ኢሳይያስ ከማልን በዚህ አካባቢ አምባሳደር አድርጎ የላከው በአርሲ አካባቢ እንቅስቃሴ እንዲያደርግ ነበር። ይህ የከማል ሹመት ኋላ ላይ የአትላንታው ጉባዔ የሰጠውን «ኮማንድ ፖስት» ስለማጠቃለሉ እርግጠኛ አይደለሁም። ስለ ማጠቃለሉ ማጣራት ቢያስፈልግም የአትላንታው ጉባዔ ለኦሮሞ ሕዝብ ከቀረጸለት አድማስ መካከል ኤርትራ መኾኗን ስናስታውስ ግን የከማል የአምባሳደርነት ሹመት በአትላንታው ጉባኤ የተሰጠውን የኮማንድ ፖስት አዛዥነት የሚጠቀልል ቢኾን አያስደንቅም።
ኢሳይያስ አፈወርቂ ከማል ገልቹን ወደ ዩጋንዳ ከመላኩ በፊት ታማኝነቱን ለማረጋገጥ አንድ የበላይ አካል ተቆጣጣሪ ሰጥቶት ነበር። ኢሳይያስ ለከማል ያስቀመጠለት የበላይ ተቆጣጣሪ ከማል እንዲያገባት የተደረገች የአንድ የሻዕቢያ ጀነራል ልጅ ነበረች። በሌላ አነጋገር ኢሳይያስ ከማልን በአምባሳደርነት የላከው የአንዱን የሻዕብያ ጀነራል ልጅ ድሮለት፣ ሚስቱን አብራው እንድትሄድ በማድረግ ነበር። ኢሳያስ ከማል ገልቹን «የጴጥሮስ ታናሽ ወንድም» እያለ እንደሚጠራው አንድ ኮብላይ ጋዜጠኛ የጻፈውን ማንበቤን አስታውሳለሁ። እንደሚታወቀው የመጽሐፍ ቅዱሱ ጴጥሮስ ሦስቴ ከድቷል። ኢሳይያስም «የጴጥሮስ ታናሽ ወንድም» የሚለውን አምባሳደሩን  ከማል ገልቹን ለማመን ተጨማሪ ጥንቃቄ አድርጎ ነበር። ኢሳያስ ለተጨማሪ ጥንቃቄ ሲል ከማል ገልቹ ሳያውቅ የከማል ገልቹን አንድ ልጅ ከኢትዮጵያ አስመጥቶ በመያዣነት ኤርትራ ውስጥ አስቀምጦ ነበር። ከማል የኢሳይያስ አምባሳደር ኾኖ ዩጋንዳ በነበረበት ወቅት ልጁ መያዣ መኾኑን ያወቀ አይመስለኝም። አሁን ማወቅ አለማወቁን እርግጠኛ አይደለሁምና አጣራለሁ።
ይታያችሁ! የሻዕብያው ምርኮኛ፣ የወያኔ ሎሌው እና ኢሳይያስ የዳረለት ሚስት የበላይ አለቃ፣ ልጁን ደግሞ በመያዟነት አሳግቶ የኢሳይያስ አምባሳደር የነበረው ከማል ገልቹ ነው እንግዲህ ታግሎ ነጻ እንደወጣ ሁሉ እስካፍንጫው ከታጠቀው ወያኔ ጋር ፊት ለፊት በመጋፈጥ በኢሳይያስ ምርኮ ከተያዘበት ሀገር አስፈትተው፣ ወያኔን ሸሽቶ እግሬ አውጭኝ ብሎ ከፈረጠጠበት የሰው ሀገር እንዲመለስ ባደረጉት የአማራ ልጆች ሲኩራራና ለስድብ ሲጋበዝ የምታዩት።
ያገራችን ገበሬ ክረምት ይዞት ይመጣል ብሎ የሚያስበውን በሽታ፣ ችግርና ተንከሲስ ሁሉ መስከረም ሲጠባ በችቦ የተስፋ ብርሃን እንጉሮጎባሽ እያለ በመተርኮስ ያባርራል። ሰኔ፣ ሐምሌና ነሐሴን በጎመን የባጀው ገበሬ፣ መስከረም ላይ ገብስ ሲደርስ ለነፍሱ ገብስ እንደደረሰለት ያስገነዝብና ተመልሶ ገብስ በዚህ እንዳይኮራ፣ የጎመን ውለታ እንዳይረሳ ሲል «ገብስ ስማ ስማ ነፍሴን አትርፎ ለአዲስ ዘመን ያደረሰኝ ጎመን ነውና አትንቀባረር» ለማለት «አትኩራ ገብስ፣ ጎመን ባወጣው ነፍስ» ብሎ ሸንቆጥ ያደርገዋል። እስካፍንጫቸው ከታጠቁ የወያኔ ነፍሰ በላዎች ጋር ተፋልመው ወያኔ መቀሌ እንዲመሽግ ከተገደደ በኋላ ወያኔን ፈርቶ ከፈረጠጠበትና ልጁን በማስያዝ የኢሳይያስ ጀኔራል ልጅ የበላይ ተቆጣጣሪ ተመድቦለት ከሚኖርበት የግዞት ሀገር በቦሌ በኩል እንዲገባ ያደረጉትን የአማራ ልጆች ሊሰድብ የሚጋበዘውንና በሰው ማንነት የሚኮፈሰውን ከማልን ገልቹን «አትኩራ ገብስ፣ ጎመን ባወጣው ነፍስ» ልንለው ይገባል! «ማንነታችን ካልተከበረ. . . » እያለ በተጫነበት የሰው ማንነት ከሚፎክር መጀመሪያ የተጫነበትን ማንነት አውልቆ ለመጣል  የራሱን ማንነት ሐድያነትን ለማጥለቅ  «የሐድያ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ» የሚል ያቋቁምና ለራሱ ማንነት ክብር እንዳለው ያሳይ!
በእውነቱ ግን ኢትዮጵያ የሆነችው ለኦሮሞ ነው። ኦሮሞ በወረራ በያዘው ምድር ላይ ባለርስት ያደረገችው ኢትዮጵያ ናት። ከዚህ በተጨማሪ ከማል በድንቁርና አረንቋ ስለሰጠመ አይገባውም እንጂ ቤተሰቦቹን ወርሮና መሬታቸውን ቀምቶ ጭሰኛ ካደረጋቸው የኦሮሞ  የገዢ መደብ ጭቆና ነጻ እንዲወጣና አያቶችና ቅድመ አያቶቹን ባርያ ሆነው ከመሸጥ ያዳነቻቸው  እንደገና ፈርሳ ካልተሰራች ለኦሮሞ አትሆንም  የሚላት ኢትዮጵያ ናት። ከማል እንደገና ፈርሳ ካልተሰራች ለኦሮሞ አትሆንም  የሚላት ኢትዮጵያ ዘሮቹ በኦሮሞ የገዢ መደብ ከተሸጡበት  እስከ ደቡብ አፍሪካ ድረስ እየተላላካች የሚከፈለውን በመክፈል ከባርነት ነጻ እንዲወጡና ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ያደረገቻቸውን ኢትዮጵያ ነው።
ከፍ ብዬ ስላነሳሁት ታሪክ ማወቅ የሚሻ ቢኖር  ሳንድራ ሼል የሚባሉ ተመራማሪ «From slavery to freedom : the Oromo slave children of Lovedale, prosopography and profiles» በሚል ርዕስ እ.ኤ.አ. በ2013 ዓ.ም. ባሳተሙት መጽሐፍ የኦሮሞ ባላባቶች ባሪያ አድርገው የሸጧቸውን የኢትዮጵያ ነገዶች አባላት ዝርዝርና ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ ደቡብ አፍሪካ ድረስ በመላላክ ገንዘብ ጭምር እየከፈሉ ነጻ እንዲወጡና ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ስላደረጓቸው ገርባዎች፣ ጰለታዎችና ባሮች የጻፉትን ያንብብ። ጥናቱ የኦሮሞ ባላባቶች  የጥንቱን ነገድ ባሪያ አድርገው ወደ ደቡብ አፍሪካ የሸጧቸውን ሰዎችና ዳግማዊ ምኒልክ ገንዘብ እየከፈሉ ያስለቀቋቸውን ባሮች ትውልዶች ጭምር አካቷል። በኦሮሞ ባላባቶች ከተሸጠበት ከደቡብ አፍሪካ ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ ገንዘብ ከፍለው ነጻ ያወጡት ያንዱን ማንነቱ ተቀይሮ ኦሮምኛ እንዲናገር የተደረገ  ሰው ዘሮች  በደርግ ዘመን ከኢትዮጵያ ወደ ካናዳ ተሰደው አሁንም ድረስ ካናዳ ውስጥ እንደሚኖሩ  ሳንድራ ሼል  ጥናት ያሳያል።
ኢትዮጵያ በባርነት ከመሸጥ ያተረፈቻቸው ውለታ ቢሶቹ እነ  ከማል ገልቹ  ግን ይህን እውነት ማወቅም መናገርም አይፈልጉም። ከማል  ኦነጋውያን የነገሩትን በመድገም  ስለቋንቋ መጨፍለቅ አብዝቶ ያወራል። ሆኖም ግን ኦሮሞ ወርሮ ገርባ ያደረጋቸውን የሱ ዘሮች ቋንቋ ጨፍልቆ እንዳጠፋውና ማንነታቸውን እንደቀየረው መናገር አይፈልግም።  ከማል  ራሱን ሳያውቅ እስከመቼ ነው ነጻነትን የማያውቅ ነጻ አውጭ ሆኖ የሰው ማንነት ተጭኖበት የሚዘልቀው? በእውነቱ የከማል  ዘሮች ኦሮሞ በባርነት ሰንሰለት ካሰረበት ጨለማ ወደ ብርሀን እንዲወጡ ያደረገችው ኢትዮጵያ ካልፈረሰች የሚል ቢኖር ራሱን የረሳና ነጻ በመውጣቱ የሚቆጭ፤ የባርነቱንና የገርባነት ዘመኑን የሚናፍቅ  የስቶኮልም ሴንድሮም ተጠቂ የሆነ ፍጡር ብቻ ነው።
Filed in: Amharic