>
5:14 pm - Monday April 20, 2364

ትናንትና ዛሬ ፣ የውጭ ጉዳይ እና የዜጋ ክብሩ  !  (ነቢዩ ሲራክ)

የማለዳ ወግ…

ትናንትና ዛሬ ፣ የውጭ ጉዳይ እና የዜጋ ክብሩ  ! 

ነቢዩ ሲራክ
* ከቶ የቱ ይቅደም ?
* የአሳት አጥፊ የኃልዮሽ ጉዞ …
* የዜጋ ክብሩ ? ወይስ ገንዘብ ? 
* የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሲያስከፋን …
* የዲፕሎማሲያዊ ዝቅጠቱ እስከ መቸ ? 
 
የዜግነት ፖለቲካ ስኬት ጅማሮው
    ፊስ ቡክ ከሁለት አመት በፊት እኔ በመላው አለም የምንገኝ የብላቴናው ያሳካነው የፍትህ ጥያቄ አስታወሰኝ። ውስጤ በእርካታ ደስታው ተሟሟቀ ። እናም በትዝታ ነጉጄ ዶር አቢይ አህመድ የዜግነት ክብሩን ከፍ ያደረጉባትን ይህችን ቀን እያመሰገንኩ ከሳምንታት በፊት በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የጎበኘሁትን ብላቴናው መሐመድን አስታወስኩት። በብላቴው መሐመድ ጤና ዙሪያ ለውጥ ባላይም ግፍ ተፈጽሞበት ፍትህ እንደዘገየበት ፣ ፍትህ ተነፍጎ ከባጄባት ሆስፒታል አልጋ ወድቆ አልቀረምና ደስተኛ ነኝ ።
የአሳት አጥፊ የኋልዮሽ ጉዞው …   
     ትናንት የሆነውን አስታውሸ ዛሬስ የዜግነት ክብሩን የት ድራስ ነው ?  አጠየቅኩ።  እርግጥ ነው የዜግነት ክብራችን ተመለሰ ብለን በተስፋ ብዙ ተመኝተናል ፣ ብዙ ብለናል ። ከአመታት በኋላ ነገሮች ተቀያይረዋል ። የክብር ኩራታችን ፣ ተስፋችን ሙሉ በሙሉ በማይባል ደረጃ ባትከሸረፍም የምናየው ሰንካላ ዲፕሎማሲ ግን ተስፋ እያስቆረጠን ተቸግረናል።  እናም የቱ ይቅደም የዜጋ የዜጋ ክብሩ ? ወይስ ገንዘብ ? እል ዘንድ ተገድጃለሁ  !
    የውጭ ጉዳይ መ/ቤት በዚህ የጨነቀ የኮሮና ወረርሽኝ ወቅት ዜጎችን ከመደገፍ ይልቅ ካረፈብን የመከራ ቀንበር ላይ ሌላ ቀንበር እየጫነብን ተቸግረናል። ከአረብ ሀገራት ወደ ሀገር ቤት ለመመለስ በሚፈልጉ ዜጎች ዙሪያ እየሰራ ያለው የውጭ ጉዳይ መ/ቤት ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በመቀናጀት በዜጎች ላይ እያደረጉ ያሉትን ጫና ያርሙ ዘንድም እናሄሰው ዘንድም ግድ ሆኗል …
የስደተኛው እንግልት በወረርሽኙ መባቻ  …
  በኮሮና ኮቪድ 19 ወረርሽኝ መባቻ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲያችን ጋር የሚጣረስ ስራ እየተመለከትን ነው። በድብቅ የሚታየው ስህተት በጉልህ ግላጭ ክስረት ክሽፈት ሆኖብናል። በዜጋ ተኮር የውጭ ፖሊሲ ተመራን እያልን እየደሰኮርን በተጨባጭ ግን የምንሰራው ከምንናገረው ይለያይል። ስደተኛውን እንዲረዱ አቅጣጫ የተቀመጠላቸው የውጭ ጉዳይና ሚሲዮኖች ስደተኛውን ከመደገፍ  ይልቅ ወደ ባሰ ችግር ገፊ መሆናቸው ደግሞ ኤሎሄ ያስብለን ይዟል ።
   ተወካዮቻችን በእርምጃ መንገዳችው  ችግራችን ተረድተውና መርምረው ወደ ተሻለ አቅጣጫ ሊወስዱን በሚገባበት ክፉ ጊዜ ድጋፋቸው ርቆናል።  ዛሬም እንደ ትናንት ባለንበት የመርገጥ አባዜ ተጠናውቶናል ። ይህ የመሰንበቻ ክራሞታችን አካሄድ ዜጋን ለመርዳት ከተቀመጠው የውጭ ጉዳይ ቀዳሚ መርህ አኳያ ትክክል አለመሆኑ እውነት በስደት አለም ገፈት ቀማሽ ለሆነው ስደተኛ የእለት ተለት ሀዘኑ ሆኗል ።
የእሳት አጥፊ የኃልዮሽ ጉዞው …
  እናም የዜጋ ክብሩ ወይስ ገንዘብ ? ከቶ የቱ ይቅደም ? በማለት ቅሬታ ፣  ወቀሳዬን በመጠይቅ አስቀድሜ አቀርባለሁ። ቅሬታ ፣  ወቀሳዬን የማቀርብባቸው በአረብ ሀገራት የሚገኙ የቆንስላና የኢንባሲ ተወካዮች ብቻ አይደሉም። እንደ አገር በዚህ ጭንቅ ወቅት የስደተኛውን ደህንነት የመጠበቅ ቀዳሚ ስራቸውን በማዕከላዊ እዝ ደረጃ ማስተባበር የነበረባቸው የውጭጉዳይ መ/ቤትና የዳያስፖራ ጉዳይ ኤጀንሲ መ/ቤት ኃላፊዎች የሚያጎድሉት አስከፍቶናልና ተውን ይበቃል እላቸዋለሁ። ከምንም በላይ ስደተኛውን በሚመለከት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴት በኩል የሚሰሩ ስራዎች በተቋማዊ ትብብር በመናበብ ፣ በተሳለጠ የመረጃ ልውውጥ አደረጃጄትና ቅንጅት መስራት አለምቻሉ ሁሌም ስራ ጉዟችን የኃሊዮሽና የእሳት አጥፊ ሚና ብቻ እንዲኖረን አድርጎታልና በእርጥቡ ካለረተስተካለ ውሎ ሲያድር የሚየስከትለው አደጋ ከፍ ያለ ነውና እንደ ዜጋ ያሳስበኛል ።
 
በስደተኞች ቁስል እሾህ …
   አዎ ፣ በሳውዲ ፣ በሊባኖስ ፣ በኢምሬት ለሚሰማው የስደተኛ ወገን ሮሮ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መ/ቤት ያልተቀናጄና ያልተደራጄ ምላሽ ዜጎች ለከፋ እንግልት እየተዳረጉ ነው። ለዜጎች ደህንነት ቅድሚያ ሰጥተው መስራት ያለባቸው የውጭ ጉዳይ መ/ቤት ኃላፊዎችና የሚመለከታቸው ስራቸውን በአግባቡ እያከናዎኑ አይደለም። ገና የዜጎች ማስመለስ ጉዳይ ምክክር ሲደረግና ውሳኔው ከመተላለፉ በፊት አካሄዱን ተቃውመው ይሁንታ ያልሰጡትን ኃላፊዎች መስማት አልተቻለምና ለከፋ ክሽፈት ተዳርገዋል።
    በቁስል ላይ እሾህ እንዲሉ ስደተኛው ” እንዴት የተቸገረው ዜጋ ለከፍተኛ ኪሳራ የሚዳርግ ስራ ትሰራላችሁ ? ” ብሎ በመጠየቅ ከፍ ያለ ተቃውሞና ወቀሳ እያሰማ ነው ። ከዜጋ ይልቅ የኢትዮጵያን አየር መንገድ ጥቅም ለማስከበር የቲኬት ዋጋና ለኳራንቲን የተጋነነ ዋጋ እንዲከፈል አስገዳጅ ማድረግ የዜጋ ተኮር አካል ሊሆን አይችልም። ዜጋን ማንገላታትና አየር መንገዱን መደገፍ የዲፕሎማሲው ክሽፈት ከማሳየት ባለፈ የተወካዮቻችን የጭካኔ ልክ ያመላከት ይመስለኛል ። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ፍትሃዊ ባልሆነ ዋጋ ዜጎች የአየር መንገዱን ግልጋሎት እንዲጠቀሙ አስገዳጅ መምሪያ አውጥቶ ማስፈጸም ተገቢ ነው  አልልም።
የቱ ይቅደም የዜጋ ክብሩ ? ወይስ ገንዘብ?
  ከውጭ ጉዳይ ዋና መስሪያ ቤት እስከ ሚሲዮኖች በተዋረድ በዚህ የኮሮና ወተትሽኝ በጭንቁ ጊዜ በጭንቅ ላይ ያለውን ወገን ሊደግፉ እንጅ ሊገፉት ባልተገባ ነበር። ስደተኛው በአረብ ሀገራት መሪዎች ወደ ሀገር መግባት እንደሚችል ሲፈቀድለት ንብረቱን ሽጦ ፣ የቀረውን እቃ ሸካክፎ  ወደ ሀገሩ ለመሄድ ሲዘገጃጅ ውጭ ጉዳይ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር ወግኖ ዜጎችን ከመደገፍ ይልቅ የአየር ቲኬትና የ14 ቀናት የኳራንቲን መቆያ ዋጋን ቆልሎ ለመበዝበዝ የተኬደው መንገድ በስደተኛው መካከል መረር ያለን ቁጣ ፈጥሯል ።
    ሳውዲ ላይ ከሰሞኑ የሆነውን እንደ ምሳሌ አስረጅነት ላንሳው። በሽዎች የሚቆጠሩ ታራሚዎችን በሳውዲ መንግስት ወጭ በነጻ ፣ ከማረሚያ ቤት ውጭ ያሉትን  ተመላሾችን ደግሞ ተመጣጣኝ በሆነ ዋጋ ወደ ሀገራቸው ለመመለስ የሳውዲ አየር መንገድ ፍላጎት ቢያሳይም አገልግሎት እንዳይሰጠ በመታገዱ አልተሳካለትም። በእርግጥም የሳውዲ አየር መንገድ በተመጣጣኝ ዋጋ ሊያገለግል ሲል አገዳ ጥሎ የማመላለሱን ስራ ተገቢ ባልሆነ ዜጎችን በሚጎዳ ዋጋ ለኢትዮጵያ አየር መንገድ መስጠቱ  ፍትሃዊነት የሚያስረዳኝ አላገኘሁም። የሳውዲ አየር መንገድ በረራ እየከለከሉ ለገንዘብ “ለቢዝነስ ” ማግኛ ብቻ ሲባል ዜጋን እያንገላቱ የኢትዮጵያን አየር መንገድ በግዳጅ ተጠቀሙ ብሎ ማለቱ ዲፕሎማሲያዊ ቀውስ ሊያመጣ ይችላልና ሊታሰብበት ይገባል ስል እመክራለሁ ። ቀውስም ባያመጣ ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ ማለት ድርጅትን ጠቅሞ ዜጋን መጉዳት አይደለምና እርማት ሊወሰድበት ይገባል ።
  በቀጣይ ወጌ ከቀናት በፊት በተቆለለው የቲኬትና የኳራንቲን ዋጋ በማስከፈል በሽዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ወደ ሀገር ለመመለስ አስቦ ግንቦት 8 ቀን 2012 ዓም በጀመረው ከጅዳ አዲስ አበባ በረራ ከ40 ያልበለጡ ተመላሾችን ይዞ የመመለሱን ሂደትና ክሽፈት አንስተን ከቶ የቱ ይቅደም  ? የዜጋ ክብሩ ? ወይስ ገንዘብ? በማለት አናዎጋዋለን
እስኪ ቸር ያሰማን   ! 
Filed in: Amharic