>

የመለስ አጓጉል ትሩፋቶች! (- ክፍል አምስት) አሰፋ ሃይሉ

የመለስ አጓጉል ትሩፋቶች!

አሰፋ ሃይሉ
(- ክፍል አምስት)

እንደ መግቢያ
ደጋግሜ እናገራለሁ፡፡ ዘረኛ አይደለሁም፡፡ ዘረኞችን ግን እቃወማለሁ፡፡ ዘረኝነትን ስለምጠየፍ ነው የዘረኝነት ሥርዓትን እና ዘረኝነትን አራማጆችን በፅኑ የምቃወመው፡፡ በኢትዮጵያ የ8ሺህ ዓመታት ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ዘረኝነትን የመንግሥት ሥርዓት አድርጎ የተከለው መለስ ዜናዊ ስለሆነ ባራመደው አመለካከት ልክ ተገቢ አይደሉም የምላቸውን አጓጉል ትሩፋቶቹን ሁሉ በፅኑ እተቻለሁ፡፡ ያን የማደርገው ትውልድ ከዘረኝነት ነፃ እንዲወጣ ለማገዝ ነው፡፡ የመለስ የዘረኝነት ሥርዓት ሃት-ስፓቶች የቱ ላይ እንደሆኑ ለማሳየት ነው፡፡ ዘረኝነት አውሬ ነው፡፡ የአውሬ ሃት-ስፓት ጥርሱ ነው፡፡ አውሬ ጥርሱን ከታመመ አድኖ መዘነጣጠል ስለማይችል ይሞታል፡፡
ዛሬ ላይ ያለን ትውልዶች፣ እና መጪ ትውልዶች ኢትዮጵያ ሀገራችንንና ህዝቦቿን እየገዘገዙ ያሉትን የዘረኝነት ተናካሽ መርዘኛ ጥርሶች በጋራ ማርገፍ አለብን፡፡ ዘረኝነትን ጥርስ የሌለው አንበሣ አድርገን ወደ ሙዝየም መክተት አለብን፡፡ ለዚህ ዓላማ የዘረኝነት ቁንጮ የሆነውን የመለስን ጉልህ ግድፈቶች በ48 ነጥቦች ሰድሬ ማስነበቤን እቀጥላለሁ፡፡ ለዛሬ ካቆምኩበት ከ9ኛው ነጥብ እጀምራለሁ፡፡ ደግሜ ደጋግሜ የማሰምረው ነገር – የምፅፈው ነገር – ከመለስ – ወይም አሁን የእርሱን የዘረኝነት ውርስ በአደራ ተረክበው እያስቀጠሉ ካሉት ግለሰቦችና የታሪክ ተዋናዮች ዘር፣ ብሔር፣ ጎሳ፣ ነገድ፣ አሊያም ዘውግ ጋር የሚያገናኘው ነገር አለመሆኑን ነው፡፡ ከኋላቀር የጎሳ አስተሳሰብ ነፃ ሆኖ የሚያነብ ሰው እንዲያነበው ነው ምኞቴ፡፡ ለዚህም ስል ነፃ ሆኜ እፅፋለሁ፡፡
9ኛ/ አባይን የደፈረ ጀግና?
መለስ ዜናዊ ተደጋግሞ ‹‹አባይን የደፈረ ጀግና!›› እየተባለ ሲጠራ እሰማለሁ፡፡ እንደምገምተው ‹‹የደፈረ›› የሚሉት ለመጀመሪያ ጊዜ የነካ ለማለት መሰለኝ፡፡ በእርግጥ አባይን የደፈረው እርሱ ነው ወይ? በጥንት ዘመን ንጉሥ ዳዊት ሳልሳዊ አባይን ሊገድብ አልሞከረም ወይ? ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ አባይን ሊገድቡ ብዙ ሥራ አልሰሩም ወይ? መንግሥቱ ኃይለማርያም በጣና እና በአባይ ተፋሰሶች ላይ የግድብና መስኖ ሥራዎችን አላከናወነም ወይ? የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ ለታሪክ አጥኚዎች እተወዋለሁ፡፡ በእርግጥ መለስ ዜናዊ – በአንድ ትልቅ ነገር ምስጋና ከተገባው – ምናልባት ግብፅ ባልጠረጠረችበት የአባይን ተፋሰስ ሀገሮች ከኢትዮጵያ ጋር ወግነው ስምምነት እንዲፈራረሙ ማድረግ መቻሉ መሆኑን ከዚህ ቀደም በጻፍኩት አርቲክል ያስቀመጥኩት ነጥብ ስለሆነ ደግሜ አልመለስበትም፡፡ አሁን ግን ‹‹አባይን የደፈረ ጀግና›› በሚለው የመለስ ዝና ላይ – አንድ ብዙ ጊዜ ስጠይቀው የኖርኩትን ጥያቄ ጠይቄ ብቻ አልፋለሁ፡-
መለስ ዜናዊ በብሔር በሸነሸናት ኢትዮጵያ እና እርሱ በተለከፈበት የብሔር አባዜ መነፅር አንፃር ስናይ – ሌላ ቀርቶ ወንዝና ሸለቆዎችን ሳይቀር ብሔር አበጅቶላቸው፣ የተፈጥሮ ሃብቶችን በብሔር አከፋፍሎ – ያ የእዚህ ብሔር ሀብት ነው፣ ይሄ የዚያ ብሔር እያለ እግዜሩ የሰጠንን ብሔራዊ ሀብት ሲተነትን የኖረ ሰው – ለምን ታዲያ ከአማራ ክልል ፈልቆ፣ የጣናን ውሃ ቀዝፎ፣ የአማራ ክልል ውሃ እየተገበረለት የሚጓዘውን አባይን ለመገደብ ሲነሳ፣ የአባይን ውሃ ገድቦ ታላቅ ሰው ሠራሽ ሃይቅ ለመሥራት ሲነሳ፣ የአባይን ውሃ ገድቦ ታላቅ የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ ሲነሳ፣ የአባይን ውሃ ገድቦ ታላቅ የኤሌክትሪክ ማመንጫ ለማድረግ ሲነሳ – ታዲያ ምነው – ግድቡንም፣ ሃይቁንም፣ ኃይል ማመንጫውንም፣ የቱሪስት መዳረሻውንም – ምነው ከአማራ ክልል አርቆ ቤኒሻንጉል ከተተው?
… ምነው ከአማራ ክልል የሚመነጨውንና የአማራው መመኪያና መፎከሪያ የሆነውን ወንዝ – የአማራ ክልል ብሎ ከሸነሸነው ክልል አርቆ – ወደ ሱዳን አስጠግቶ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ላይ ገነባው? የጣናን ሃይቅ የተፈጥሮ ውሃ ከአማራ የውሃ ሃብት ላይ ወስዶ – ሌላ ከጣና የበለጠ የተፈጥሮ ሃብትን በሌላ ሩቅ ክልል ላይ ለመፍጠር ማሰብ ከምን የመነጨ ነው? የመለስ ዜናዊ በወያኔ ማኒፌስቶ የተገለጠ ፀረ-አማራ ጥላቻው – የአባይን ወንዝ በማድረቅና የጣናን ሃይቅ ከአማራ በመንጠቅ መቋጨቱ ይሆን? ወይስ መለስ ይህን የአባይ ግድብ ዲዛይን አልሰራውም? ወይስ አባይን የደፈረው ሌላ መሪ ነው? ለዚህ ምን ዓይነት ምክንያት ነው ማቅረብ የምንችለው?
ዘረኛ አይደለሁም ብዬአለሁ፡፡ ዘረኛ አይደለሁም ማለት – ዘረኞች በሚያስቡበት ሎጂክ ነገሮችን ለመረዳት አልሞክርም ማለት ግን አይደለም፡፡ በመለስ ዘረኛ ጭንቅላት – የአማራን መመኪያ አንጡረ ሃብት አባይን ከአማራ ላይ ነጥቆ – የአባይን ግድብ ልማት በሌላ ሥፍራ ላይ መገንባት – ዘረኛ አስተሳሰብ የወለደው ነው – ወይስ ምን? የመለስ ዜናዊ ጭንቅላት – የትም ተሠራ የት – ሁሉም ኢትዮጵያ ነው – ብሎ የሚያስብ ጭንቅላት ቢሆን ኖሮ – ይሄን የወረደ ዘረኝነት የሞላበት ጥያቄ አልጠይቅም ነበረ፡፡
ይሄን እንድጠይቅ ያስገደደኝ ሃቅ ግን የመለስ ዜናዊ በዘረኝነት የታወረ አዕምሮ የሚያፈልቀውን ነገር ለመረዳት በራሱ አስተሳሰብ አንፃር ማየት ስላለብኝ ነው፡፡ የቆመን ቅርስ የአክሱም ሃውልት ለወላይታው ምኑ ነው? ያለ ዘረኛ ጀግና – የአባይስ ወንዝ ለሱዳን እና ለቤኒሻንጉል ጉሙዝ ምኑ ሆኖ አግኝቶት ነው – የጣናን ውሃ ስቦ፣ የአባይን ወንዝ ጠልፎ፣ ጢስ አባይን አድርቆ – ፓዌ በረሃ ላይ ሌላ ሃይቅ የሚሞላው፣ ኃይል የሚያመነጨው፣ የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ የሚተጋው? በዘረኛ ጭንቅላት – ይሄን ለማድረግ የሚያነሳሳው ነገር ምንድን ነው? – መልሱን ‹‹ለምን?›› ብሎ ለሚጠይቅ ሰብዓዊ ጭንቅላት፣ ታሪክን ለሚመረምር አጥኚ እና ለተከታዩ ትውልድ እተወዋለሁ!
 
10ኛ/ ጠባብነትን የኢትዮጵያዊነት መታወቂያ ያደረገ ጀግና! ሀገራዊ የፖለቲካ አስተሳሰብ እንዳይሰፍን የተጋደለ ጀግና!
በመለስ ዜናዊዋ ኢትዮጵያ ሀገር አቋራጭ መንገድ እንጂ – ሀገር አቋራጭ አስተሳሰብ መገንባት በፍፁም ክልክል ሆኖ ቆይቷል፡፡ መለስ ዜናዊ ጠባብነትን በሁሉም የህይወት መስኮች ለማስፈን እጅጉን የተጋ – እና በሀገሪቱ የመሪነት መንበር ላይ ለመቀመጥ ዕድሉን ካገኙ መሪዎች ሁሉ – በጠባብነት ተስተካካይ የማይገኝለት ጠባብ አመለካከትን ለማስተናገድ ብቻ እንዲመች ሆኖ የተሰፋ ሀገራዊ ሥርዓት መሥርቶ አልፏል፡፡ መለስ ዜናዊ ፖለቲካን የጠባቦች መፈንጫ አደረገው፡፡ መለስ ዜናዊ ለኢትዮጵያ ህዝብ ሁሉ የሚበጅ ሀገርአቀፍ የፖለቲካ ፕሮግራሜ ይህ ነው – የሚሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዳይፈጠሩ በአስገዳጅ ህግ እያስደገፈ ሌት ተቀን የሠራ ከዶሮ ጭንቅላት የጠበበ ጠባብ አስተሳሰብ ባለቤት ነበር – ብል ፍጹም ማጋነን የለበትም፡፡
በመለስ ዜናዊ ጭንቅላት – የባስኬቶ ሕዝብ የፖለቲካ ፓርቲ፣ የአማራ ሕዝብ የፖለቲካ ፓርቲ፣ የስልጤ ሕዝብ የፖለቲካ ፓርቲ፣ የደንጣ ድባሞ ክችልችላ ሕዝብ የፖለቲካ ፓርቲ፣ የትግራይ ህዝብ የፖለቲካ ፓርቲ፣… ወዘተ የሚሉ በጠባብ ዘረኛ አስተሳሰብ የተቃኙ፣ ለጠባብ የጎሳ መንጋ መብት ቆሜያለሁ የሚሉ፣ እና እንደጋሪ ፈረስ ቆምኩለት የሚሉትን ጠባብ ጎሳ ብቻ እንዲመለከቱ ተደርገው የህግና የጠብመንጃ ልጓም የተበጀላቸው ጠባብ ‹‹ፖለቲከኛ ነን ባዮች›› የሚርመሰመሱባት የጠባብ መንገኞች ፖለቲካ የሰፈነባት ኢትዮጵያ ብቻ ነች ያለችው፡፡ የትግሬንና የደንጣ ድባሞን፣ የኦሮሞንና የአኙዋክን፣ የስልጤንና የወላይታን ህዝብ ሁሉ የሚመለከት – ለእነርሱም የሚቆረቆር – ትልቅ ሀገራዊ ፕሮግራም አለኝ – ያንን ለመተግበር እጥራለሁ የሚል – ሀገራዊ ፖለቲካ የሚያራምድ አካል – ለመለስ ዜናዊ ‹‹ደርግ›› ብቻ ነው፡፡ ጠባብነት ነፃነት ነው፡፡ ሀገራዊ አስተሳሰብ ደግሞ ባርነት ነው፡፡ ምን ዓይነት የተንሸዋረረ ‹‹ፐርቨርትድ›› አስተሳሰብ ነው?
ይሄን የመለስን ከእውነታው ጋር የተገለባበጠ አዕምሮ ሳስብ የጆርጅ ኦርዌል ‹‹1984›› የሚል መጽሐፍ ይመጣብኛል፡፡ እዚያ ላይ የሠላም ሚኒስቴር ዋና ሥራው ጦርነትን ማካሄድ ነው፡፡ የእውነት ሚኒስቴር ፕሮፓጋንዳን መንዛት ነው ሥራው፡፡ የፍቅር ሚኒስቴር ከሰዎች አዕምሮ ውስጥ ጥላቻን ማዝነብ ነው ሥራው፡፡ ሚኒስቴሮቹ ከስማቸው ጋር የተገለባበጠ ተግባር ነው የተሰጣቸው፡፡ የመለስ ዜናዊም አስተሳሰብ ከዚያ ምናባዊ ክስተት አይለይም፡፡ በመለስ ዜናዊ ህሊና ውስጥ – ጠባብነት ማለት ሀገራዊነት ነው፣ ጎሰኝነት ማለት ‹‹ብሔራ››ዊነት ነው፡፡ ሀገራዊ የፖለቲካ አስተሳሰብ አስተሳስሮናል የተባለለት የይስሙላ ጠባብ ብሔርተኝነትን የሀገሪቱ መታወቂያ ያደረገ ሕገመንግሥትን እንደ ታቦትና ጽዋ ተሸክሞ እየዞረ – ነገር ግን ሀገራዊ ፕሮግራምና ራዕይ ያላቸው የፖለቲካ ቡድኖች መቼውኑም እንዳይደራጁ – መለስ ዜናዊ በንቃት የዘረኝነት ታንኩን ጠምዶ ይጠባበቃል፡፡ ይሄ የጎሰኞች ሥርዓት እስካላበቃም ድረስ ደግሞ መቼም አይኖርምም፡፡
እጅግ የሚያስቀው – መለስ ዜናዊ የጠባቦች መፈንጫ ያደረገው የፖለቲካ ሥርዓቱን ብቻ አይደለም፡፡ ሌላ ቀርቶ ስፖርትን የመሰለ የሰው ልጆች ህብረትና ፍቅር ማሳያ የሆነ ነገር፣ ስፖርትን የሚያህል የየሀገራት ብሔራዊ አንድነትና የጋራ ቃልኪዳን ከፍ የሚልበት ቅዱስ ነገር – መለስ ዜናዊ በጠባብነት አዕምሮው ሰፍቶ ሊሰራው የቻለውን ሁሉ አድርጓል፡፡ ለእግርኳስ ቡድኖች የብሔር ማሊያና የብሄር ማንነት ያለበሰ፣ ለመረብ ኳስ ቡድኖች፣ ለእጅ ኳስ ቡድኖች፣ ለሳይክል ተወዳዳሪዎች.. የብሔር ታርጋ ለጥፎ ስፖርታዊ ውድድርን የጎሳ ፍጭት አውድማ ለማድረግ የተጋ፣ ሌላ ቀርቶ የምድሩን ስፖርት አልፎ – የውሃ ዋናን – የውሃ ዋናተኞችን በብሔርና በጎሳ አደራጅቶ ያስቀመጠ ጀግና እኮ ነው መለስ ዜናዊ! እንዴ!? ይሄ እኮ ህመም ነው – ነው የምለው! ዘረኝነት በትክክል ካንሠር የሆነበት እንደ እርሱ ያለ ሰው ኢትዮጵያ በታሪኳ ገጥሟት አያውቅም! የማይድን የጠባብነት ልክፍትን – ምን ታደርገዋለህ?!
መለስ ዜናዊ ሁሉንም ነገር በብሔር ለመቃኘት ካለው ፍላጎት እኮ – ዓላማቸው ትርፍ የሆነና የትም ገብተው በየትም ብለው – የገንዘብ ትርፍን ማግኘት ዓላማቸው ያደረጉ የፋይናንስ ተቋማትን በብሔር ያደራጀ ዜጋ እኮ ነው! አንዴ አንድ ወዳጄ – በአንድ ስሙን ለመጥራት በማልፈልገው ባንክ ለአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጀማሪ ነገረፈጅ ሆኖ ሊቀጠር ሔዶ – ፈተናው ላይ የትግርኛ ጥያቄዎች እንደነበሩበት እያዘነ ነበረ የነገረኝ፡፡ ልጁ የደቡብ ኢትዮጵያ ልጅ ነው! ለፈታኞቹ ይሄን ቋንቋ አላውቀውም አላቸው፡፡ ካላወቅከው ግዴታ አይደለም – መተው ትችላለህ አሉት፡፡ እና ተፈትኖ ወጣ፡፡ እንደነገረኝ – ሌሎቹ ጥያቄዎች ለእርሱ ቀላል ነበሩ፡፡ ግን መቼም ሳይጠራ ቀረ፡፡ ጥያቄውን ተወው ብለው – እርሱን ተዉት፡፡ ልጁ ዛሬም በሕይወት አለ፡፡ ሌሎችም በብሔር ተለይተው የተደራጁና – ከሙያዊ ብቃትና የሥራ ተነሳሽነት በላይ – ብሔርና ጎሳ ተጨማሪ መስፈርት የሆኑባቸው በርካታ ባንኮችና ልዩ ልዩ ተቋማት ሀገሪቱን እንደ አሸን አጥለቅልቀዋታል፡፡
 ከ100 ዓመት በፊት – ኢትዮጵያዊው ምሁር ገብረህይወት ባይከዳኝ – ገንዘብ ትርፍን ነው የሚከተለው – ብሎ ያስቀመጠውና – በዓለማቀፍ የኢኮኖሚክስ ምሁራን ጭምር ታላቅ ተቀባይነት ያገኘው ሳይንሳዊ ፅንሰ-ሃሳብ እዚህ የመለስ ዜናዊዋ ኢትዮጵያ ላይ ሲደርስ ከሽፎ ተገኘ ማለት ነው! ዘረኝነት – የማያከሽፈው ነገር የለም! ጉድ ማለት ብቻ ነው! እና ለሀገር ለሚቆረቆር ደግሞ ከልብ የመነጨ ሀዘን ያሳድራል፡፡ ያሸማቅቃል፡፡ እና ያበሳጫል፡፡
ዛሬ – ዓላማቸው ትርፍ ማግኘት ሆኖ – ነገር ግን በተመረጡ የብሔር ሰዎች የሚጠሩና ጎሰኝነትን ማዕከል አድርገው የተመሠረቱ የፋይናንስ ተቋማት የሥርዓቱ ማስቀጠያ ዓይነተኛ መገለጫ ሆነው ፋፍተዋል፡፡ ሁሉ ሲገርመኝ – ሌላው ቀርቶ – በቅርቡ የቄሮው መንግሥት ቁንጮዎች – ከሰሜኑ ኢትዮጵያ የተለየ የኩሽ ፖለቲካ እናራምዳለን ብለው በአደባባይ ባወጁ ማግስት – ‹‹የኩሽ ባንክ›› የሚባል ባንክ እየተመሰረተ ነው! ኩሽሽ ብሎ በቀረ በኮመሸሸ ሥርዓት ውስጥ ከዚህ የበለጠ የቢዝነስ ፈጠራ ከወደየት ሊመጣ ይችላል? አረም ካልሆነ በቀር – ያልዘራኸው አይበቅልም! ጠባብ ሥርዓት የሚወልደው ጠባብ አዕምሮዎችን ነው!
ጠባብነትን ለማምጣት የታተረው የመለስ ዜናዊ ጭንቅላት – ምን ያህል በጥላቻ የተመረዘ መሆኑን ለማየት – የተቆረጠ ጡትን ታላቅ ሃውልት አድርጎ ያቆመበትን – ‹‹የአኖሌ ሃውልት›› የተሰኘውን ማየት ብቻ በቂ ነው፡፡ የአኖሌ ሃውልት – የመለስ ዜናዊን እጅግ ከመጠኑ ያሻቀበ የዘረኝነትና የጠባብነት ሥርዓት በአካልም በአምሳልም የሚወክል የሥርዓቱ አምድ ነው! ብዙዎች ይፍረስ ይላሉ! እኔ ደግሞ አይፍረስ – የመለስ ዜናዊ ታላቅ ሌጋሲ ሆኖ ለትውልድ ይቆይ ባይ ነኝ! ታሪክ ለምን ይፈርሳል? ይሄ ጠባብነት፣ ይሄ ጥላቻ እኮ የመለስ ዜናዊ የእጅ አሻራ ያረፈበት አኩሪ የዘረኝነት ታሪካችን ነው!
በተለያየ አጋጣሚ ከአለፍ ገደም ወደ አዋሳ ከተማ ሄጄያለሁ፡፡ አንዴ ከብዙ ዓመት በኋላ ሀገር-አማን ብዬ ሄድኩኝ፡፡ ስሄድ – ቀድሞ ያልነበረ – በአዳዲስ ልዩ ከፍታና ግርማሞገስ ያላቸው ሚያማምሩ ባህላዊ የሣር ጎጆዎች የተንቆጠቆጠ የተዋበ ግቢ ተመለከትኩ፡፡ እና ጥቂት ሰብሰብ ያሉ የአዋሳ ወጣቶችን ጠጋ ብዬ ጠየቅኳቸው፡፡ ምንድነው? ብዬ፡፡ እኔን አይተውኝ – ከሌላ ሥፍራ ለጉብኝት የሄድኩ መሆኔን ከአኳኋኔ ስላወቁ – በፈገግታ ተሞልተው ለመናገር አመነቱ፡፡ በመጨረሻ አንዱ፡- ‹‹የሰማዕታት መናፈሻ›› ነው አለኝ፡፡ ውስጡ ምን አለ? ብዬ ጠየቅኳቸው፡፡ አንዳቸውም ገብተውበት አያውቁም፡፡ ገረመኝ በጣም፡፡
ይህ እውነት ብርቅ አልሆነብኝም፡፡ በባህርዳር ከተማም ሄጄ – ብዙ ወጣቶችን – ስለ ባህርዳሩ ‹‹የሰማዕታት ሙዝየም›› ስለሚባለው ስጠይቃቸው – ብዙዎቹ ገብተውበት አያውቁም! ፍላጎቱም የላቸውም! እዚህም ያሉት የአዋሳ ወጣቶች ተመሳሳይ ናቸው፡፡ ነገር ግን ማየት አለብኝ ብዬ ወስኜ ገባሁ፡፡ ስገባ – በትልቅ ግድግዳ ላይ በግራናይት ድንጋዮች ኮላዥ ተደርጎ የተሰራ ግሩም የግድግዳ ላይ ሥዕል ተመለከትኩ፡፡ የሲዳማ ብሔረሰብ አባቶች የሽምግልናና እርቅ ሥርዓት እንደሆነ ተነገረኝ፡፡ ፎቶ አነሳሁ፡፡ ተነሳሳሁ፡፡ በግራናይቱ ሥር፣ በየጎጆዎቹ ግርጌ፡፡
እልፍም ሳልል ዘወር ብል ግን – በዚያው የሽምግልናና እርቅ የጥበብ ሥራ ባጌጠ ግቢ ውስጥ – የሆኑ ነጫጭ ባለፈረስ ሃውልቶች (ኤክዊስትሪያን ስካልፕቸርስ) አየሁ፡፡ በግቢው – የመቃብር ሥፍራ በሚመስለው ሥፍራ ላይ ተደርደረዋል፡፡ እና ወደዚያው ብሄድ – የተለያዩ አዳዲስ ሃውልቶች (ግማሾቹ አልተጠናቀቁም ነበር!) – ከየስራቸው ላይ ‹‹እገሌ እገሌ – የነፍጠኛውን ሥርዓት የተዋጋ ጀግና!›› ይላል፡ ‹‹እገሌ እገሌ – የምኒልክን የነፍጠኛ ሥርዓት ሲዋጋ ህይወቱን የከፈለ ጀግና!››.. ‹‹እገሌ እገሌ.. ነፍጠኛውን ያንቀጠቀጠ ተዋጊ›› …. ‹‹ነፍጠኛው የሰቀለው ሰማዕት..›› …. ማለቂያ የለውም፡፡ እንዴ?! ገረመኝ! በኢትዮጵያ ብዙ ሥፍራዎች ላይ – ብዙ ታሪካዊ ኃውልቶች – ለታሪክም – በህይወት ላለው ትውልድም ቆመዋል! እንደ መለስ ዜናዊ ግን – ሆነ ብሎ – የዘር ጥላቻን ለመስበክ፣ ለማቃቃርና – ትውልዱን በጠባብ አስተሳሰብ ለመቃኘት ታልመው የተገነቡ አንድም – እደግመዋለሁ – አንድም ኃውልት አጋጥሞኝ አያውቅም!
መለስ ዜናዊ – እነዚህን የመሰሉ የጠባብነት፣ የጎሰኝነት፣ የጥላቻና የመለያየት ኃውልቶችን በኢትዮጵያ ህዝቦች መካከል የተከለ የመጀመሪያው እኩይ መሪ ሆኖ በታሪክ ሲታወስ ይኖራል፡፡ መንግሥቱ ኃይለማርያም ጥበብን ለፕሮፓጋንዳ ጠቀሜታ አውሎታል እየተባለ በጥበበኞች ሲተች ኖሯል፡፡ ወደፊትም ይተቻል፡፡ መለስ ዜናዊ ደግሞ ጥበብን ለርካሽና ለወራዳ የጠባብነትና የዘረኝነት መስበኪያ፣ ለጥላቻና የአንድን ሀገር ህዝብ ለማቃቃሪያ፣ ለማለያያ ፍጆታ ያዋለ – ጥበብን አልከስክሶ ያዋረደ እጅግ ወራዳው መሪ እየተባለ ሲዘከር እንደሚኖር ምንም ጥርጥር የለኝም!
የአክሱምን ሃውልት የገነባች፣ ገናናነቷን ለሺህ ዓመታት ለዓለም ሕዝብ የምትመሰክር ታላቅ ምድር፣ የላሊበላን ተራሮች ፈልፍላ ወደ ምድር ተምዘግዛጊ ድንቅ የሰውልጆችን ታላቅ ጥበብ ለዓለም ያነፀች ሃገር – እንዴት እንዲህ አዕምሮው በጥላቻና በጠባብነት የተመረዘ ጠባብ ጭንቅላት የያዘን እና የጥላቻንና የመለያየትን፣ የጥበትንና የመቃቃርን ሀውልት ሌት ተቀን የሚተክል ክፉ አሜከላ ልብ ያበቀለ መሪ እንዴት ወደ ዙፋኗ አመጣች?
አላውቅም! – ምናልባት – እርግማን ይሆናላ! መርገምት! መርገምት ነው ይሄስ!
ሁሉ የማይሳነው የሠማይ የምድር ፈጣሪ – ኢትዮጵያን ሀገራችንን – ከዘረኝነትና ከጠባብነት መርገምት – ጨርሶ ይማርልን!
ሌላ ምን እንላለን?
( – ይቀጥላል)
Filed in: Amharic