>

«የፖለቲከኞች የመጨረሻ ግባቸው ሥልጣን መያዝ ሳይሆን ኢትዮጵያን ማስቀጠል ሊሆን ይገባል»  (አቶ ኢብራሂም ሙሉሸዋ የታሪክ ምሁርና የሚዲያ ባለሙያ)

«የፖለቲከኞች የመጨረሻ ግባቸው ሥልጣን መያዝ ሳይሆን ኢትዮጵያን ማስቀጠል ሊሆን ይገባል» 

አቶ ኢብራሂም ሙሉሸዋ የታሪክ ምሁርና የሚዲያ ባለሙያ

ቱርኮች በታሪካቸው ልክ እንደእኛ ሁሉ እርስበርስ አለመስማማታቸው ከእኛ ጋር ይበልጥ ያቀራርባቸዋል። ለምሳሌ እኛ በአፄ ምኒልክ ጉዳይ ላይ አንግባባም። አፄ ምኒልክ የታሪክ አንድ አካል ቢሆኑም እሳቸውን በሚመለከት ጫፍና ጫፍ የረገጡ አመለካከቶች አሉን። ለአንዳንዶች አፄ ምኒልክ እናት ናቸው። አፄ ምኒልክ ባይኖሩ ኖር እኛ አንኖርም ብለው የሚያስቡም አሉ። በሁለተኛው ጫፍ ደግሞ አፄ ምኒልክን እንደወንጀለኛ፤ ምንም ነገር እንዳልሰሩ፤ እንደጨቋኝ አድርገው የሚቆጥሩ ነበሩ።
 እንደእኛ ሁሉ ቱርኮችም አዲሲቷን ቱርክ የመሰረተው አታቱርክ ላይ ተመሳሳይ ሁለት ፅንፎች የያዙ አመለካከቶች አላቸው። ለአንዳንዶች በተለይ እስላማዊ አስተሳሰብ ላላቸው ሰዎች አታቱርክ ጠላት ነው። አታቱርክ የቱርክ መስራች ሳይሆን ቱርክ በኦቶማቾ ዘመን የነበራት ክብርና ገናናነት ያፈረሰና ለነጮች አሳልፎ የሰጠ ነው። ለሌሎች ደግሞ አታቱርክ ባይኖር ኖሮ ቱርክ የምትባል አገር አትኖርም ብለው እስከማምለክ የሚደርሱ አሉ። ቱርኮች አዲሱ መንግሥት እስከሚመጣ ድረስ ለ80 ዓመታት የአታቱርክ ደጋፊዎች ስልጣን ላይ የነበሩባት አገር ነች። በዚያን ወቅት አታቱርክን መንካት እንደወንጀል ነበር የሚያስቆጥረው።
ከ20 ዓመታት ወዲህ ግን እነኤርዶዋን የሚመሩት ፀረ አታቱርክ ኃይል መጣ። ይህ ኃይል የአታቱርክ ደጋፊዎች በተለይ በእምነት ላይ ያደርጉት የነበረውን ተፅእኖ በይፋ ይቃወም ነበር። ይሁንና ሥ ልጣን ሲይዙ ግን ግራ ገባቸው። ምክንያቱም አታቱርክ የሰራው መጥፎ ነገሮች እንዳሉ ሁሉ በርካታ መልካም ነገሮች መኖራቸውና ይህንንም የሚደግፉ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጥቂት አለመሆናቸው ነው። እነሱ የሚከተሉት አመለካከት ከነባራዊው ሁኔታ ጋር የሚጣላ ሆነባቸው።
ይሁንና ይህን ችግራቸውን ቱርኮች የፈቱበት መንገድ ለኢትዮጵያ ጥሩ ምሳሌ የሚሆን ነው። እነ ኤርዱዋን በመጀመሪያ ያደረጉት አታቱርክ ሰው ነው እንደሰው መልካምም መጥፎ ነገር ሊሰራ እንደሚችል ማመናቸው ነው። አታቱርክ ቱርክን እንደአገር የመሰረተ እሱ ሆኖ ሳለ ከታሪክ መዝገብ ላይ መሰረዝ እንደማይችሉ ተቀበሉ። በተጨማሪም አታቱርክን እንደአንድ መሪ ማጥፋት ታሪካቸውን ማጥፋት እንደሆነም ተረዱ። ስለሆነም አታቱርክ ላይ ያላቸው ጥላቻ ከመግለፅ ተቆጠቡ። ጎን ለጎንም በሃይማኖት ላይ ይደረግ የነበረውን ተፅእኖ በተግባር አስወገዱ።
በመሆኑ አታ ቱርክን በማምለክና በመጥላት ያለውን ፅንፍ የወጣ አመለካከት ማስቀረት ቻሉ። እናም ይህ የቱርክ ተሞክሮ ለእኛም አገር የሚሰራ ይመስለኛል። ለአብነት ከጠቀስኩልሽ ከአፄ ምኒልክ ብንነሳ እኚህ ንጉስ ሰው ናቸው እንደሰው የሰሩትን መጥፎ ነገር ማውገዝ ብቻ ሳይሆን መልካም ሥራቸውንም ተቀብለን መሄዱ ጠቃሚ ነው የሚመስለኝ።
እኛ ትውልዱ አገሩንና ታሪኩን እንዲያውቅና እንዲወድ ተደርጓል ብዬ አላምንም። ታሪክን ከፖለቲካ ነጥሎ ማውራት ይከብዳል። ታሪካችን በራሱ አያጣላም ብዬ አምናለሁ። ታሪክን አሁን ላለው ሁኔታ እንዲጠቅመን አድርገን ስለማንቀርፀው ነው ችግራችን። ታሪካችንን የሁላችንም አላደረግነውም።
አሁንም አንድ ዓይነት ታሪክ፥ አንድ ዓይነት ብሔርና ቋንቋ ብሎም ሃይማኖት እንዲኖር የሚፈልጉ አካላት አሉ። አገር ወዳድና አገር ወዳድ ያልሆኑ የሚል ስያሜ የተሰጣቸው አካላትም አሉ። በሌላ በኩል ደግሞ አብረን ልክ እንዳልኖርን፤ ኦሮሞና አማራ እንዳልተጋባ አድርገው የሚቆጥሩ ጥቂት አይደሉም። አንድ ወንድ አንዲት ሴትን መንገድ ላይ አይቶ የሚወዳት ዘሯን አይቶ እንደሆነ አድርገው የሚቆጥሩም አሉ።
እንደሙስሊም እኔ እዚህች አገር ውስጥ ሙስሊሞች ተበድለዋል ብል እዚህ አገር ውስጥ ሙስሊሞችን የበደሉት ክርስቲያኖች ናቸው ማለት አይደለም። የፖለቲካና ማህበራዊ ግንኙነት ይለያያል።
ፖለቲከኞች ፖለቲከኛ ሲሆኑ ስልጣን መያዝ ብቻ ሳይሆን ኃላፊነትም እንዳለባቸው መገንዘብ አለባቸው። እርግጥ ሁሉም ወደ ፖለቲካ ሲመጣ ስልጣን ለመያዝ ነው፤ ግን የመጨረሻ ግብ አይደለም። ፖለቲከኞች የመጨረሻ ግባቸው ስልጣን መያዝ ሳይሆን የኢትዮጵያን ማስቀጠል ሊሆን ይገባል። መንግሥት ከተቃዋሚዎች ጋር ያለውን ልዩነት የጠላት ሊያደርገው አይገባም። ተቃዋሚዎች ሊሰሙ ይገባል። ምክንያቱም ዴሞክራሲ መገለጫው ይህ በመሆኑ ነው። መንግሥትን የምንከስበትና የምንቆጣጠርበት ዘዴ ሊኖር ይገባል።
ሌላው ተቃዋሚዎች የዚህች አገር ችግር በአንድ ጊዜ የሚፈታ ነው ብለው መጠበቅ የለባቸውም። ይህች አገር በብዙ ትርምስ ውስጥ እያለፈች ያለች አገር ነች። ተቃዋሚዎች ራሳቸው እንኳን አብረው ቁጭ ብለው የማይፈቷቸውና የበለጠ ችግር የሚፈጥሩባቸው ሁኔታዎች አሉ። ከሁሉ በፊት አገርን ማስቀደም ይቀድማል። ይህች አገር ስላለች እኮ ነው እኔና አንቺ ዛሬ ቁጭ ብለን የምናወራው።
ትልቁ የኢትዮጵያ መንግሥታት ችግር ስልጣን የተረጋጋ ሲመስላቸው ሁሉንም ነገር መጫን እንደሚችሉ ማመናቸው ነው። ይህ ስህተት ነው። መንግሥታት ትልቅ ደረጃ የደረሱ ጊዜ ነው የሚወድቁት። በነገራችን ላይ የቀድሞው ኢህአዴግ የወደቀው በ2002ዓ.ም ምርጫ መቶ በመቶ አሸነፍኩ ያለ ጊዜ ነው። ልክ ሁሉም ሰው ኢህአዴግ መሆን የጀመረ ቀን ነው ያከተመለት። ላይኛው ጫፍ የደረሰ ወደታች መዘቅዘቁ አይቀርም። ይህ የፖለቲካ ባህል መቀየር አለበት። መንግሥት በዚህ ጉዳይ ላይ ቁርጠኛ መሆን አለበት።
ኢትዮጵያ ትልቅ አገር ነች፤ የምር ትግራይ ከኢትዮጵያ ተገንጥዬ እጠቀማለሁ ማለት የምትችል አይመስለኝም። ግን ደግሞ ትግራይን እንደክልል መቀበል መቻል አለብን። ህወሓት ተሸንፏልና ምን አገባው የሚል አካሄድ ካለ ልክ አይመስለኝም። አሁንም ቢሆን ለድርድርና ለውይይት ልባችንንም ሆነ በራችንን ክፍት ማድረግ ይገባናል። እነዚህ ሰዎች ስልጣን ላይ የነበሩ ሰዎች እንደመሆናቸው ህሊናቸው ሽንፈትን ቶሎ ለመቀበል እንደሚቸገር ማመን ይገባናል።
ደግሞም ማንኛውም አካል እየወደቀ ሲመጣ የሚፈራቸው ስጋቶች አሉ። እነሱን ተረድተናቸዋል የሚል እምነት የለኝም። ለምሳሌ «በሰራነው ነገር እንጠየቃለን» የሚልም ስጋት ሊኖራቸው ይችላል። የእውነትም ደግሞ የፌዴራል ሥርዓቱ ሊፈርስ ነው ብለው ሊፈሩ ይችላሉ። እነዚህ ላይ ግልፅ ውይይት አድርገናል ወይ? የሚለው ጉዳይም አሁንም ጥያቄ ነው።
በሌላ በኩል ብልፅግና ከተለያዩ ኃይሎች ጋር እያደረገ ያለው ውይይት በግልፅ ተረድተነዋል ወይ? የሚለው ነገር በደንብ መገምገም አለብን። እኔ አሁንም ቢሆን በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ተጽእኖ ያለው አይደለም ህወሓት ማንኛውም ጥያቄ ያለው አካል መግፋት ጉዳት ሊያስከትል ይችላል።
ለሙሉ ቃለምልልሱ https://www.press.et/Ama/?p=32432
Filed in: Amharic