>

ሰሚ ያጡ 11 ሺህ የወሎ ተፈናቃዮች ሰቆቃ!!! "  (ዉብሸት ሙላት) 

ሰሚ ያጡ 11 ሺህ የወሎ ተፈናቃዮች ሰቆቃ!!! ” 

ዉብሸት ሙላት 
ለዜጎች ሥቃይ ደንታቢስ በሆነ ስርአት ከቀያቸው ተፈናቅለው ላሉ ወገኖች  የሚደርስላቸው መቼ ነው??
ጥቅምት 2010 ዓ.ም ጀምረው ከኦሮሚያ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ በወቅቱ የነበረውን ግድያ፣ ሃብት ንብረት ዘረፋና ቃጠሎ እንዲሁም ማፈናቀል ተከትሎ በስፍራው የነበሩ   ከጥቃት ሸሽተው በወሎ ይገኛሉ።
እነኚህ ተፈናቃዮች  ከሁለት አመት በላይ ቢሆናቸው የፌደራሉም ሆነ የአማራ ክልል መንግስት ዘላቂ መፍትሄ አላበጀላቸውም። አሁንም በከባድ ችግር ውስጥ ሆነው የሲሚ ያለ እያሉ ነው ። ተፈናቃዮቹ ለከፋ ችግር ተጋልጠው የቆዩ ሲሆን በአካባቢው ነዋሪዎችና በውጭ ሀገር በሚኖሩ በጎ ፈቃደኞች ጥረት እስካሁን ቆይተዋል።
አሁን ላይ በሰሜንና ደቡብ ወሎ የሚገኙት ከ11 ሺህ በላይ ተፈናቃይ ወገኖች፤ በኮሮና ወረርሽኝ መስፋፋት ምክንያት አቅም ያላቸው እንደልብ በመንቀሳቀስ ሰርተውም ሆነ ለምነው ማግኘት ባለመቻላቸው ይበልጥ የችግሩ ተጋላጭ ሆነዋል። ወቅቱ የረመዳን ጾም በመሆኑም ብዙውን ቁጥር የሚይዙት ሙስሊም ተፈናቃዮች ለተደራራቢ ቀውስ ተጋልጠዋል።
ለዜጎች ሥቃይ ደንታቢስ በሆነ ስርአት ከቀያቸው ተፈናቅለው  ላሉ ወገኖች የሚደርስላቸው መቼ ነው??
ሀ. ከተለያዩ ክልሎች፣በተለይም ከኦሮሚያ፣ ተፈናቅለው በአማራ ክልል በተለያዩ ቦታዎች የሚገኙ ወገኖቻችን ሁኔታ ያሳዝናል፡፡ በተለይ በሰሜን ወሎ  ያሉት ከተፈናቀሉ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ወደተፈናቀሉበት ክልል የተመሱ ቢኖሩም ያልተመለሱ አሉ፡፡ በዚያ ላይ ለዓመታት የማስፈርና የማቋቃም ሥራ ሳይሠራ በተረጂነት ብቻ እንዲኖሩና እንዲተዳደሩ ተደርገዋል፡፡ ወደ ተፈናቀሉበት ክልል ተመልሰው መሔድ ካልቻሉ፣ ማስፈርና ማቋቋም ያስፈልጋል፡፡
ለ. ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ተፈናቃዮችን ወደመጡበት ክልል እንዲመለሱ ማድረግን በተመለከተ ኃላፊነቱ የፌደራል፣የተናቀሉበት ክልል የአማራ ክልል መንግሥት ነው፡፡ እንደ ፓርቲ ደግሞ ብልጽግና፡፡ የፌደራል፣ኦሮሚያና የአማራ ክልል መንግሥታት ይህንን ችገር መፍታት እንዴት እንዳቃታቸው አልገባኝም፡፡ ምናልባትም ትኩረት አልጠሰጡትም ሊሆን ይችላል፡፡ ይሄ ኃላፊነት ከሚሰማው መንግሥት የማይጠበቅ ነው፡፡ በአጭሩ ኃላፊነት የጎደለው፣ለዜጎች ሥቃይ ደንታቢስ መሆን ነው፡፡
ሐ. ተፋናቃዮች ቀድመው በነበሩበት አካባቢ (ክልል) በደረሰባቸው በደልና የማፈናቀል ተግባርና ሌላም ሌላም ችግር ምክንያት መመለስ ካልፈለጉ፣ኅልውናቸውን አደጋ ላይ የሚጥል ስጋት ኖሮ፣ መፍትሔ ማፈላለግና በቋሚነትም ማቋቋም ግድ ይላል፡፡
መ. ተፈናቃዮቹ እስኪመለሱ አልያም እስኪቋቋሙ ድረስ ምግብ መጠለያና አልባሳት ማቅረብ የፌደራልና የክልሉ የአደጋ መካላከልና ዝግጂነት መሥሪያ ቤቶች ግዴታ ነው፡፡  በዚህ ረገድ የምግብ፣የመጠለያና የአልባሳት ችግሮችን የክልሉ የአደጋ መከላከልና ዝግጂነት መሥሪያ ቤት (በቀጥታ የሚያቀርበው የክልሉ ስለሆነ) መቅረፍ አለበት፡፡ ኃላፊነቱ የዚህ መሥሪያ ቤት ነው፡፡ ከክልሉ መንግሥት ቢሮዎች ደግሞ በቀጥታ የሚመለከተው የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮን ነው፡፡ የክልሉ አንዱ ማኅበራዊ ችግር ስለሆነ፡፡
ሠ. ወደተፈናቀሉበት ክልል ካልተመለሱ በክልሉ ውስጥ እንዲቋቋሙ የመሥራት ኃላፊነት በጥቅሉ የክልሉ መንግሥት ኃላፊነት ቢሆንም በቀጥታ የሚመለከተው ግን የአማራ መልሶ ማቋቋም ድርጅትን  (አመልድ) ነው፡፡ አመልድ መልሶ በማቋቋም ረገድ ምን እየሠራ እንደሆነ መረጃ የለኝም፡፡ ይሁን እንጂ፣ መልሶ ለማቋቋም አንድም በክልሉ ውስጥ በመንግሥት ይዞታ ሥር ያሉ ቦታዎችን ፈልጎ ማስፈር ይጠይቃል፡፡ ካልሆነም፣ የመሬት ድልድል ማድረግ ያስፈልጋል ማለት ነው፡፡ በመሆኑም የክልሉ መንግሥት ከሁለት አንዱ መርጦ  መሬት እንዲያገኙ ካደረገ በኋላ ለአመልድ ማስረክብና የማቋቋም ሥራውን እንዲያከናውን ማድረግ ነው፡፡ የመሬት ድልድል ማድረግ አስቸጋሪ ስለሚሆን የተሻለው አማራጭ በመንግሥት ይዞታ ሥር የሚገኙ ጠፍ መሬቶችን ከየወረዳው አፈላልጎ ማስፈር ነው፡፡ በአጭሩ መልሶ ማቋቋሙ የሚፈጸመው በግብርና እንዲተዳደሩ በማድረግ ከሆነ በፍጥነት መፈጻም ሊዳግት ቢችልም ይህን ያህል ጊዜ መዘግየትም የተናቃዮቹን ሥቃይ ከቁብ አለመቁጠር ነው፡፡
ረ. ከአመልድ በተጨማሪ ተፈናቃዮቹን  ለማቋቋም አልማ ገንዘብ ማሰባሰቡ ይታወቃል፡፡ በወቅቱ ወደ 110 ሺ ገደማ ተፈናቃዮችን ለማቋቋም ወደ 1.5 ቢሊዮን ብር ገደማ እንደሚያስፈልግ ይፋ አድርጎ በቴሌቶን ከ700 ሚሊዮን ብር በላይ ቃል መገባቱን እናውቃለን፡፡ ባለኝ መረጃ ቃላቸውን ጠብቀው ገቢ ያደረጉና የተሰበሰበው ጠቅላላ ብር 400 ሚሊዮን አይሞላም፡፡ አልማ ተፈናቃዮችን ለማቋቋም ከሚያስፈልገው 1.5 ቢሊዮን ገደማ ይህን ያህል ገንዘብ አሰባስቧል ማለት ነው፡፡ በዚያን ወቅት የተፈናቀሉትን ለማቋቋም ማለት ምን ማለት ነው? እንዴት ነው የሚቋቋሙት? ምን ምን ድጋፍ እንዲደረግላቸው ነው አልማ ገንዘብ የሰበሰበው? በየወሩ ቀለብ መሥፈር፣አልባሳት ማሟላትን ይጨምራል ወይ? አልማ ገንዝብ ሲያሰባስብ ከሌላ ክልል የተፈናቀሉትን በምን መልኩ ለማቋቋም ነበር ፕሮጀክቱ?
 ከሌላ ክልል ተፈናቅለት  ቤት፣ ትምህርት ቤት፣ ጤና ጣቢያ ወዘተ ለመሥራትም በቅድሚያ የሚሠፍሩበት ቦታ ያስፈልጋቸዋል፡፡
ሰ. የተፈናቃዮቹ አኗኗር ያሳዝናል፡፡ አስቸኳይ መፍትሔ ያስፈልገዋል፡፡ ይህ እንዲሆን አክቲቪዝም ሥራ ማከናወን የተቀደሰ ተግባር ነው፡፡ በአክቲቪዝም ሰበብ ሌላ አጀንዳ መፍጠር ደግሞ ለዚህ ቅዱስ ተግባር ተቃራኒ ነው፡፡ ለአክቲቪዝሙ የሚሆኑ መረጃዎችን ማሰባሰብ መመዘንና ማጣራት፤  የሚመለከተውን አካል መለየት የሁላችን ጥንቃቄ መሆን አለበት፡፡ እንደዚያም ሆኖ ተቋማትን እየገደልን ግለሰቦችን እየሰደብን ፣ ተሳስተንም ወደ ጎጥ ወስደንም፣ ሌሎቻችንም የሰፈሬ ሰው ምን ሲደረግ አንድም ሰው ስሙን ጠራው በማለት ቡራ ከረዩ የማለት አባዜ….  በአማራነት ላይ የተጋረጠ ሾተላይ ነው!
በጥቅሉ የክልለ መንግሥት በተለይ ከሌላ ክልል ተፈናቅለው  በምግብ፣በመጠለያና በአልባሰት ችግር ለሚሰቃዩ ተፈናቃዮች መፍትሔ እንዲያበጅ ድምጽ እንሁን!
ተጨማሪ መረጃዎች :-  ከመረጃ ቲቪ የተወሰዱ
Filed in: Amharic