>
5:13 pm - Wednesday April 19, 9471

ታሪክን የኋሊት!!!  በግርድፍ አተራረክ ዘዬ የቀረበ (አሰፋ ሀይሉ)

ታሪክን የኋሊት!!!

በግርድፍ አተራረክ ዘዬ የቀረበ

አሰፋ ሀይሉ
ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ህገመንግሥት ተብዬ ሲረቀቅ – በጉባዔው ላይ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ወክለው የተጋበዙ ሁለት ሰዎች ነበሩ፡፡ አንዱ ፕ/ር አስራት ወልደየስ፡፡ ሁለተኛው ፕ/ር መስፍን ወልደማርያም፡፡ ያ አጋጣሚ ለሁለቱም ምሁራን የወያኔ-ኦነግ-ኢህአዴግን ፋሺስታዊ አስተሳሰብ ግልጽ አውጥቶ አሳያቸው፡፡ ያ የህገመንግሥት ተብዬ ጉባዔ የመለስ ዜናዊን ሂትለራዊ አካሄድ አጠገቡ ሆነው ለመታዘብ አስቻላቸው፡፡ በህገመንግሥት ስም የተቀመጠው የብሄሮች እኩልነት የተረጋገጠባት ኢትዮጵያ… የብሔር እኩልነት… የዘመናት ጭቆና.. የሕዝቦች የተዛባ ግንኙነት… ወዘተ እየተባለ የተደነጎረው ሁሉ – አማራ ላይ የተደረተ ጥላቻ መሆኑን ሁለቱም ምሁራን እዚያው ዓይኑ ሥር ሆነው ከፈረሱ አፍ አደመጡ፡፡
የተጨቆኑ ብሔሮች የሚባሉት – ሁሉም ብሔሮች ናቸው፡፡ ጨቋኙ ብሔር አማራ ነው፡፡ የብሔር እኩልነት ማለት – ሁሉም ብሔር ከአማራ እኩል ይሆናል – የሚል መፈክርና ራዕይ ነበር፡፡ የሰው ልጅ እኩልነት – ከአማራ ልጅ ጋር የሁሉም ልጅ እኩል ነው – እንደማለት ሆኖ ነበር ግንዛቤ የሚወሰድበት፡፡ አማራ – በእነ መለስና ፋሺስት አጋሮቹ አመለካከት – ኢትዮጵያ ውስጥ የተወለደ አውሮፓዊ ቅኝ ገዢ ነው፡፡ እና ሁለቱም ምሁራን መለስ ዜናዊን አምርረው ለመቃወም ተነሱ፡፡
ፕሮፌሰር አስራት መለስን – አንተ አማራ የምትለው በደሙ ይህችን ሀገር ያቆየ ከሌላው ብሔር ጋር ተዋዶ የኖረ ጨዋ ሐይማኖተኛ ህዝብ እንጂ አንተ የምትለውን ዓይነት ፋሺስት ህዝብ አይደለም – በአማራ ጥላቻ የተለከፋችሁት የለየላችሁ ፋሺስቶቹ አንተና ጭፍሮችህ ናቸው – ብለው ፊትለፊት ተናግረው – አንጨረጨሩት፡፡
ፕሮፌሰር መስፍን ደግሞ – አንተ የምትለውን ዓይነት አማራነት – አማራ የምትላቸው ህዝቦች ራሱ አያውቁትም – አማራ ራሱን ጎጃሜ፣ ጎንደሬ፣ ወሎዬ፣ ይፋቴ፣ መንዜ – እያለ ነው እንጂ የሚቆጥረው – አንተ እንደምትለው ሁሉም በአንድ ላይ ተጠራርቶና ተሰብስቦ አማራ ነኝ ብሎ ሌላውን ሕዝብ ለመጨቆን ተነስቶ አያውቅም – አማራ ብሔር ነኝ ብሎም በአንድላይ ተነስቶ አያውቅም – ይልቁንስ አንተ በጥላቻህ ብዛት አማራ እያልክ ሁሉንም ሰንገህ ስትቆርጠው – አሁን ገና አማራን አንተ ፈጠርከው – ብለው ቁርጡን ነገሩት፡፡
ፕሮፌሰር መስፍን የኢትዮጵያን ሰብዓዊ መብት ጉባዔ መስርተው የመለስ ናዚያዊ አስተሳሰብ የወለደውን ግፍ መፋለም ጀመሩ፡፡ ያሉት ጠብ አላለም፡፡ እርስ በእርሱ ሲጋደልና ሲዋጋ የኖረው ብሔረ አማራ – እና አማራ ነህ ተብሎ በእነ መለስ ናዚያዊ አገዛዝ በያለበት እንዲታረድና እንዲሳደድ የተደረገው አማራ – ጥቃቱን ሊመክት ከያለበት ተጠራርቶ – አዎ አማራ ነኝ ብሎ ተነሳ – በፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ ፊት መሪነት፡፡
መለስ ዜናዊ ይሄን ከማይ ሞቴን እመርጣለሁ አለ፡፡ እና አዛውንቱን ዕውቁን ፕሮፌሰር በዝንጀሮ ዳኞቹ ሁለት ዓመት አስፈርዶ እስርቤት ወረወራቸው፡፡ ደሞ እሱን ጨርሰው ሊወጡ ሲሉ – ሌሎች ዝንጀሮዎች ፈልጎ የሶስት ዓመት እስር ፍርድ ጨመረላቸው፡፡ በህመም ተቀስፈው ህክምና ከልክሎ አሰቃያቸው፡፡ አማራ አማራ የሚል ቅስማቸውን ሊሰብር ምሎ ተዘባበተባቸው፡፡ እርሳቸው ግን ቅስማቸው የሚሰበር አልነበሩምና የናዚውን ፀረ-አማራ ሥርዓት ለመፋለም በገቡት በአቋማቸው ፀንተው ቆዩ፡፡ በመጨረሻም በዓለማቀፉ ማህበረሰብ ግፊት – በሞት አፋፍ ላይ ሆነው ወደ አሜሪካ ተሸኙ፡፡ በአምስተኛ ወራቸው ህይወታቸው አለፈች፡፡
“አንደበት ላጣ ህዝብ ካልተናገሩለት
ወንጀል አይሆንም ወይ ወገኑ ነኝ ማለት?”
  – ኃይሉ ገብረዮሐንስ (ገሞራው)
የመለስ ናዚ አገዛዝ በአነሳሱ ከአንድ ብሔር በተውጣጡ በጥላቻ የታወሩ ዘረኞች ቢነሳም – መንበረ ሥልጣን ላይ ሲወጣ ግን – ከብዙ ብሔር የተውጣጡ በአማራ ላይ ጥላቻ እንዳላቸው ታማኝነታቸውን ያስመሰከሩና “ከአማራ ጋር እኩል መሆን እንፈልጋለን” በማለት የበታችነታቸውን ያረጋገጡ ከብዙ ብሔር የተውጣጡ ጭፍሮችን በዙሪያው ለመሰብሰብ ችሎ ነበር፡፡
ከእነዚህ በናዚው መለስ ዜናዊ ዙሪያ ከተሰባሰቡ ፀረ-አማራ ብሔሮች አንዱ – ኦሮሞን ወከልኩ የሚለው ኦነግ አንዱ ነው፡፡ ኦነግ ከመለስም ብሶ አማርኛ ቋንቋን – ቆሻሻ ቋንቋ፣ ተናጋሪውንም ቆሻሾች በማለት – የአማራ ሴቶችን ጡት እየቆረጠ፣ እርጉዝ እናቶችን ሆዳቸውን በሳንጃ እየተለተለ እስከ መዝናናት የደረሰ የጥላቻ ከፍታውን በማሳየቱ በመለስ ዜናዊ ዘንድ ከፍተኛ አድናቆትና ግርማ ተችሮት ነበር፡፡ ሲቀብጥ ግን ከወያኔ እኩል ልሁን አለ፡፡ የኦነግ ሚና አማራን መጥላትና ማሳደድ ብቻ መሆኑን ኦነግ እንዳልተረዳ የገባው መለስ ዜናዊም ኦነግን አጥብቆ ወዶታልና መከረው፣ አስመከረው፡፡ ኦነግ እምቢኝ አለ፡፡ እና መለስ በመጨረሻ ኦነግን ከነጭፍሮቹ የገባበት ገብቶ እንደ እባብ ጭንቅል ጭንቅላቱን ቀጥቅጦ ቆሻሻ ቅርጫት ውስጥ ጣለው፡፡ እና በምትኩ ኦህዴድን ርዕሰ ኩራቱ ላይ አስቀምጦ በኦሮሞ ስም ይጋልበው ጀመር፡፡
ሌላው ናዚ መለስ በፀረ አማራነት በዙሪያው ካሰባሰባቸው ብሔሮች አንዱ ደግሞ – የአማራ ብሔር ወኪል አድርጎ ራሱን ያቀረበ ነበረ፡፡ መለስ ዜናዊ ፕሮፌሰር አስራት “የመላው አማራ ሕዝብ ድርጅት ” የሚል እውነተኛ የአማራውን ህዝብ ወኪል ሲያቋቁሙበት በድንጋጤ ደንብሮ – ቀድሞ “ኢህዲን” በሚል ራሱን ይጠራ የነበረውን ከኢህአፓ የከዳውን በእነ ታምራት ላይኔ እና በእነ ገብረህይወት (በረከት ስምዖን) የሚመራውን የመለስ ተላላኪ ጋሻጃግሬ ቡድን – “ብአዴን” የሚል ማህተም አስቀርፆ በአማራ ስም ተደራጅቶ አማራውን ልክ እንዲያስገባለት ፀረ-አማራ አጋር ቡድን አድርጎ አቋቋመው፡፡
ብአዴን በበኩሉ – የፀረ አማራ ዓላማውን እያስፈፀመ መሆኑን በተግባር እያስመሰከረ – ነገር ግን ውስጥ ውስጡን ብአዴንም እንደ ኦነግ ከወያኔ እኩል መሆን ቢከጅልም – ኦነግን ያየ ከመለስ ጋር አይጫወትምና – ፍላጎቱን በውስጡ ቀብሮ ለማስቀረት ቻለ፡፡ ኋላ ግን ናዚው ዳግማዊ ሒትለር – መለስ ዜናዊ መሞቱን ሲሰማ የብአዴን የሥልጣን ጥም ዳግም ነፍስ ዘራ! እና መለስ ዜናዊ ኦነግን ቆሻሻ ቅርጫት ውስጥ ጨምሮ በእርሱ ፋንታ ካደራጀው ከኦህዴድ ጋር የሴራ አንጃ ፈጥሮ – አንጃዎቹ ፈጣሪያቸውን ወያኔን ከኢህአዴግ እንዴት እንደሚፈነግሉት ሴራቸውን በጋራ መጠንሰስ ጀመሩ፡፡
አሁን ከአማራ ጋር እኩልነትን የሚሰብከው ህገመንግሥት ተብዬው ተረስቷል፡፡ ህገመንግሥቱ አካል ነው እንጂ ነፍስ እንዳልነበረው ሁሉም ተረድቶታል፡፡ መለስ ዜናዊ እና ወያኔ ህገመንግሥቱን በነፍሰ ስጋው ሲጫወቱበት ተመልክተዋል፡፡ እና ያ የወያኔ የብሄሮች ጭፍሮች ተሰብስበው “ከፍ ካለው ወደ ሰማያት ከተጠጋው ከአማራ ብሔር ጋር እኩል ነን” ብለው የፈረሙበትን ህገመንግሥት ተብዬ ሊቀዳድዱት አጥብቀው ሻቱ፡፡ ነገር ግን ከምትቀዳድዱት ትርጉሙን መቀየር እኮ ትችላላችሁ የሚል መካሪ ገባባቸው፡፡ እና “ከአማራ ጋር እኩል ነን” – የሚለውን የቀድሞውን የህገመንግስቱን የእኩልነት ትርጉም – “ከወያኔ ጋር እኩል ነን” – ወደሚል አዲስ ትርጉም  ቀየሩት፡፡ እና ጭቆናን ለመታገል ተነስተናል አሉ፡፡ የወያኔን ጭቆና፡፡ ለእኩልነት ተነስተናል አሉ – ከወያኔ ጋር እኩል ለመሆን፡፡ እና በብሄር ብሄረሰቦች እኩልነት ላይ የተመሰረተ ዲሞክራሲ ይስፈን አሉ፡፡
ምን ማለታቸው ነው? – ማለትም ወያኔ ከምትወክለው የትግራይ ብሄር የበለጠ ቁጥር ስላለን ዕድሜ ልክህን ከኛ ስር ጉድ ጉድ ስትል ትኖራለህ አሉት – ወያኔን፡፡ እና በእርግጫ ብለው ፈነገሉት፡፡ ለአማራ የወጣው ህገመንግሥት ተብዬና በህገመንግስት ተብዬው ስም የቆመ ነው የተባለለት “በአማራ ሲጨቆኑ የኖሩ ጭቁን ብሔሮች” በወያኔ ጥላ ሥር ተሰባስበው የመሰረቱት ነው የተባለለት የብሄሮች ሥርዓት ተብዬው ግን አሁንም አለ፡፡ የተቀየረው ትርጉምና አጋፋሪ ብቻ ነው፡፡ እና ፊት መሪውም ጭምር፡፡
አሁን የወያኔው ናዚ መሪ መለስ ሰማይ ቤት ገብቷል፡፡ አሁን – ወያኔ ባለ በሌለ ኃይሏ በቀድሞዎቹ የመለስ ጭፍሮች ላይ ክተት የምታውጅበት ሰዓት – አሊያም አደቧን ገዝታ – ወያኔ በፊት ሌሎቹን እንዳደረገችው – አሁን ደግሞ በተራዋ ለሌሎቹ እንደ ጩሎ እየተላላከች ለመኖር የምትወስንበት ሰዓት ላይ ትገኛለች፡፡ አሁን ኦነግ በመለስ ዜናዊ ከተጣለችበት የቆሻሻ ቅርጫት ውስጥ ወጥታ – በሻዕቢያው የቀድሞ ፋሺስት በኢሳያስ አፈወርቂ ታዝላ – በአራት ኪሎ ቤተመንግሥት በአብዮት አህመድ አሊ ፊት ተጥላለች፡፡ ስትጣል ደግሞ የኦነጓ እባብ – የኦህዴዶቹን እባቦች እየበላቻቸው ነው፡፡ አሁን በዚህ ሁኔታ ላይ ነን፡፡ ቀጥሎ ምን እንደሚሆን አብረን የምናየው ይሆናል፡፡
እንደ ቀደሙት ናዚዎች ሁሉ – የእኛም ናዚዎች ከፊሎቹ አልፈዋል – ከፊሎቹ ከታሪክ ፊት ሊጠፉ በሂደትና በመበላላት ላይ ናቸው፡፡ በእልቂት ወይ በድርድር ዳግም ነፍስ ዘርተው የዘረኝነት መረባቸውን በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ለመጣል አሰላለፋቸውን እያሳመሩ፣ ወጪና ኪሳራቸውን እያሰሉ ነው፡፡ ናዚያዊ ጥላቻና ግፍ ተከምሮ በቁጭት ለብሔራቸው እንዲቆሙ ያስገደዳቸው – እና የናዚው መለስ ዜናዊ ቀዳሚ ገፈት ቀማሽና ሰለባ የሆኑት እውነተኛው የአማራ ሕዝብ ወኪልና ፈጣሪ – ፕ/ር አስራት ወልደየስም በአሳዛኝ ሁኔታ አልፈዋል፡፡ ፕ/ር መስፍን አዲሱ የአማራ ብሄርተኛ እንቅስቃሴ እውቅና ነስቷቸው (እና ተፃርሯቸው) ሁሉን ነገር እርግፍ አድርገው በኦነጓ እባብ በተበላው በአብይ አህመድ ላይ የቀረቻቸውን እምነት ጥለው ከታሪክ እና ከእድሜ ጋር በመኖርያ ቤታቸው እየታገሉ ይገኛሉ፡፡
ሁሉንም ታሪክ በየሥራው ይመዝነዋል፡፡ እንደየሥራው ያወሳዋል፡፡ ታሪክ ሠሪዎች ታሪካቸውን ይፅፋሉ፡፡ ታሪክ ፈሪዎች ታሪካቸውን ይሸሻሉ፡፡ ታሪክ አውሪዎች ታሪካቸውን ያወራሉ፡፡ ሁሉም ግን ሁልጊዜም በታሪክ ፊት ሲዘከሩ፣ በቋሚ ሰዎች ልብ ውስጥ ሲታሰቡ ይኖራሉ፡፡ ሰዎች ያልፋሉ፡፡ ስምና ሥራቸው ብቻ ከመቃብራቸው በላይ ይውላል፡፡ የታሪክ ተዋንያንም፣ ታዳምያንም ሁሉም አንድ ቦታ ላይ ሲደርሱ ይቆማሉ፡፡ ታሪካቸው ያበቃል፡፡ ትውልድ ሁሉ ከታሪክ ጋር አብሮ እየተጓዘ፣ በታሪክ ሂደት ያሸልባል፡፡ ታሪክ ግን ሁልጊዜ ይጓዛል፡፡ ታሪክ ግን መፍሰሱን አያቆምም፡፡ ለሚያልፍ ሕይወት፣ እና ለሚቀጥል ታሪክ ስንል – ምናለ እንደ ፕ/ር አሥራት ወልደየስ -ሰብዓዊነትን ያነገበ፣ ግፍን የታገለ፣ ለፋሺስቶች ያልተበገረን ታሪክ አስፅፈን ብናልፍ?
አበቃሁ፡፡
Filed in: Amharic