>
5:13 pm - Sunday April 19, 1103

ኢሳያስ አፈወርቂ: አጥፊያችን  ወይስ  የኢትዮጵያና የኢትዮጵያውያን  ባለውለታ  ብርቅዬ  ወንድማችን? (ታጠቅ  መ  ዙርጋ)

ኢሳያስ አፈወርቂ  አጥፊያችን  ወይስ  የኢትዮጵያና የኢትዮጵያውያን  ባለውለታ  ብርቅዬ   ወንድማችን ?

ታጠቅ  መ  ዙርጋ 


 

  የሀገራዊና የሕዝባዊ ሉዓላዊነታችን ጸሮች፣አጥፊዮቻችንና ገዳዮቻችን  እንደ ብርቅዬ መሪዮቻችን፣ልጆቻችን ወይም ወንድሞቻችን አድርገን ፥ ስናነግሥ፣ ስናሞካሽ፣ስናዳንቅ ወዘተ..ኖረናል። በዚህ አርእስት አጭር መልዕክት ማስተላለፍ እፈልጋለሁ።በቅድሜያ ከመልዕክቴ ጋር ተዛማጅ የሆኑ ያለፉትን ሃምሳ ዓመታት የአገራችን ፖለቲካዊ ታሪካችን ወይም ኩነቶች በጣም አጠር አጠር ባለመልኩ አስጨብጣለሁ።

 መንግሥቱ /ሃይለማርያም 

የኢትዮጵያ ሕዝብ ለረዥም ዓመታት ታግሎ ያገኘውን ድል፤ መስከረም ሁለት 1967 ዓ.ም በመፈንቅለ መንግሥት  የቀማበትን  ቀን  የአብዮት ቀን ብሎ ሰየመው።ከዚያ በመቀጠል ዙፋኑን  ይቀናቀኑኛል ፣ እንደልቡ እንዳይልጋልብ  እንቅፋት ይሆኑብኛል ያላቸውን ሁሉ በጥይት መመንጠር ጀመረ።

ለነጻነት፣ለፍትኅ፣ለዲሞክራሲያዊ  የአስተዳደር ሥርዓት ወዘተርፈ  አርበኞች የነበሩ፤ ከግለኝነት የፀዱ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያ ሕዝብ የኖሩ፤ ከ300,000 -500,000 የሚደርሱ ዕንቁ ዜጎች  ጨፈጨፈ (carnaged)። የገደለበትን ጥይት ዋጋ ክፈሉኝ ብሎ አንድ አስክሬን በ250 ብር ሸጠ። ሟቾቹ 250 ብር የመክፈል አቅም ከሌላቸው  ቤተሰብ  ከሆኑ  አስክሬናቸው ቆሻሻ በሚሰበስብ መኪና  ወደ አንድ ጫካ ወይም ዋሻ እየተወሰዱ ለጅቦችና ለአሞሮች ተሰጡ ፤  በአንድ የጅምላ መቃበር ተቀበሩ ።

ወላጅና ዘመድ አዝማድ እንዳያለቅስና  የሃዛን ልብስ እንዳይለበስ ተከለከለ። የሚያለቅስና የሃዘን ልብስ የሚለብሱትን ለመሰለልና ለማሰር የቀበሌ ካድሬዎች አሰማሩ። ወንድም ተጠርጥሮ ሊዙት እቤት ስሄዱ ካልተገኘ፣ ምንም ማታውቀው  እህት ወስዶ መግደል። ታላቅ ወንድም ተጠርጥሮ ሊዙት ካልቻሉ ታናሽ ወንድም ወስደው መግደል። ባል ተጠርጥሮ እሱ ካጡት ሚስት ወስዶ መገደል። ልጆች ተጠርጥረው  እነሱ መያዝ ካልቻሉ አባትና እናት ወስዶ  መግደል ። አንድም ፣ ሁለትም፣ ሶስትም፣ አራትም፣ አምስት   ም ፣ ስድስትም  ልጅች የነበሯቸው ወላጆች፣  ከሁለት እስከ ሶስት ዓመት ባልሞላ ግዜ ሁሉንም ልጅ አልባ አደረጓቸው ። እናቶች መውለዳቸውን የረገሙበት፣ እንደ ሃጥያት የቆጠሩበት፣ መካን መሆን እንደ ጸጋ የተቆጠረበት ግዜ ሆነ ።  

በደርግ ዘመን ከ12 -40 ዓመት ዕድሜ  ከነበረው  ትውልድ አብዛኛው  ዘር ሳያስቀጥል ፤ልጅ አልባ ሆኖ አለፈ። በሰው ልጅ ታሪክ ሬሳ/አስክሬን  ስለሽጠ ገዢ ሰምቼም አንብቤም አላውቅም።

ለነዚያ ዓይነት የመንግሥቱ  ፍጹም  ፋሽስታዊ ድርጊቶች አፀፋ ማመጽ ፣መሸፈት፣እምቢይ ማለት ሲገባ፦ 

1) መስከረም ሁለት 1967 ለኢትዮጵያ ሕዝብ የቁጣ ቀን መሆኑን እየታወቀ ፣የአብዮት በዓል በመባል  በየዓመቱ  በውድም ሆነ በግድ ፤ከታላቁና ከቆራጡ መሪያችን ጋር ወደፊት ! እያልን ለ17 ዓመታት በመፈክር  እያዳነቅን፣ እያጋነን ፣እያሳበጥን  ወዘተርፈ አከበርን ።

2) ለመጨፍጨፍ ሲያቅድ ወይም ካስጨፈጨፈ በኋላ ሕዝብ  እሰይ ፣ ጥሩ ሥራ እየሰራህ  ነው  ወይም ደግ አድርገሃል እንዲልለት ፣ በቀበሌ ካድሬዎች ጠመንጃ  አፈሙዝ ተከቦና ተገፍቶ መስቀል አደባባይ ከጠዋት እስከማታ በፀሃይ ሲያንቋቁት፣ ዝናብ ሲያስደበድቡት፣ፀረ-አብዮተኞች ይመንጠሩ! በፀረ አብዮተኞች ላይ እንዘምታልን! በአናርኪስቶች ላይ እንዘምታለን! ወዘተርፈ እያለ  ይውል ነበር። 

ወያኔ/ህወሃት

ወያኔዎች ሶስት ፀረ አገራዊ  ሉዓላዊነት እና  ፀረ  ሕዝባዊ አንድነት) መርሆችን ይዘው  ነው ወደ ደደቢት በረሃ መጭ ብለው ነው፤  ከኢትዮጵያ ሠራዊት እና ከኢትዮጵያ  ሕዝብ አብዮታዊ ሠራዊት (ከኢ ሕ አ ሠ)  ጋር ለ17 ዓመታት  የተዋጉት ። ( 1) ትግሬ እነሱ ከሚሉት የአማራ  ቅኝ  አገዛዝ  ነጻ ለማውጣት  (2) በኢትዮጵያ የብሄር ብሄረሰቦች ፦ የፖለቲካ፣የኢኮኖሚ፣ የባህል፣የቋንቋ ወዘተርፈ የኢ-እኩልነት  መብቶች የሚፈቱት ብሄር ብሄረሰቦች ተለያይተው በመኖር ብቻ ነው በማለት  (3) ኤርትራን  ከኢትዮጵያ ቅኝ ግዛት ነጻ አደርጋለሁ  ብሎ  ለተነሳው  ኢሳያስ አጋር ለመሆን።            

 በመሆኑም ከላይ የጦቆምኩትን 3ኛውን ዓላማቸውን ያሳኩት ገና ጫካ እያሉ ነው።  ኤርትራን  ካስገንጠ  ሉና የባህር በሮቻችን ካስወስዱ  በኋላ ነው ወደ አዲስ አበባ የገሰገሱት።  

ወያኔዎች  ግንቦት 20  1983ዓ.ም የፋሽስቱ መንግሥቱ ሃ/ማ ዙፋን ለመረከብ አ/አ ሲገቡ  የወያኔዎች ደባ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ፤ ሁሉንም የአ/አ ሕዝብ ባይሆንም  ከመንግሥቱ የከፉ አይሆኑም በማለት እህልና ውሃ በማቅረብ  እንኳን ደኅና መጣችሁ ብሎ የተቀበላቸው ማኅበረስብ እንደነበረ በወቅቱ ተስተውሏል ።

ግንቦት 20/1983 ዓ. ም ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያንን  በሞኖፖል እየገዙ – ለማጥፋት፣ለመከፋፈል፣ ለመግደል ፣ ለመበዝበዝ ወዘተርፈ የሚያስችል ሥልጣን የተቆናጠጡበት ቀን ነው ።ከዚያ ዕለትና ዓ/ም ጀምሮ ፦ ከወል (ታሪክችን፣ባህላችን፣ሕባዊ አንድነታችን ፣ማኅበራዊ  ትሥሥራችን፣አውደ በአሎቻችንና ሥነ-ልቦናችን) ለማፋታት፣ ለማለያየትና ለማድፍረስ ፦ 

  • አገር በቀል የዘር መድሎ/አፓርታይድ ፣ የብሄር ቋንቋን ተኮር የአገዛዝ  ክልል እና  የብሄር ብሄረሰቦች  ክብረ በዓል ቀን ሥርዓት(system) ዘረጉ። የብሄር ብሄረሰቦች ቀን ማለት እያንዳንዱ ብሄር ብሄረሰቦች ስለተናጥል  ማንነት እንጂ ስለጋራ ማንነት ወይም እሴቶች  እንዳያስቡ ለማድረግ የታቀደ አስተምሮት (discourse) ነው ። 
  •   አበይት የንግድና የኢኮኖሚ ዘርፎች <በገዢዮችና በገዢ ጎሳዎች ቁጥጥር ሥር እንዲውሉ መመርያ ነድፏል። 
  • ታሪካችንና ባንድራችንን አንቋሽው  ተረኩ፣  ሰንደቅ ዓላማችን የሰይጣናዊ እምነት ተከታዮችን (the satanic cult) ምልክት ባለበት ሰንደቅ ዓላማ ተኩት። 
  • ማሰብና መጠየቅ የማይችል፣ የወያኔዎች ታዛዥና አገልጋይ ሆኖ መኖር የሚያስችል የትምህርት ሥርዓት አዋቀሩ።
  • እንደ መንግሥቱ ሃ/ማ እዩልኝ ስሙልኝ ሳይሉ እሱ የገደለውን ያህል  በሥውር  ገደሉ ፤ በጅምላ መቃብር ቀበሩ 
  • የሂትለርን (the Aryan race ) ሞዴል/ናሙና  በመጠቀም ፣ ትግሬአውያት ያልሆኑ ሚስቶች  ትግሬአያውያን ከሆኑ ባሎቻቸውና በእነሱ መካከል ከተወለዱ ለጅ/ጆቻቸው  ተነጥለው  እንዲባረሩ ፖሊሲ/መመርያ አወጡ።  በመሆኑም  የቤተሰብ ሕይወት አናጉ፣ አቃወሱ ፣አካል ሰነጠቁ ።ይህንን በተመለከተ በዲስፖራውም ዓለም ብዙ ጉድ ታይቷል። 

ለእነዚህ ድርጌቶች አጸፋ አመጽና እምቢተኝነት መሆን ሲገባው፦  

  •  ለእኛ የመከራና የውርደት ቀን ለእነሱ የድል ቀን የሆነው  ግንቦት 20 ሲያከብሩ፤  አንድም በውድ፣ ሁለትም በፀረ-ሕዝብ  ካድሬዎቻቸውን ቅስቀሳና አስገዳጅነት  ሕዝብ አደባባይ  እየወጥ  አከበርላቸው  
  • ዢያችን የነበረው  ወደል ውሻው (top dog) መለስ ዜናዊ አገዛዝ በመደገፍ አደባባይ  ተወጣ ።
  • የምዕራባውያን ጋዜጠኞች፣የመንግሥታት  መሪዮች (በተለይም  በምዕራባውያንና በአረቦች)  ባለራኢ መሪ! ባለልማት መሪ!  ወጣት መሪ!  ሙሉ አፍሪካ መግዛት የሚችል መሪ!  የተማረ፣ የተመራመረ መሪ! በህክምና ሞያ የሁለተኛ ዓመት የዩኒቨርሲቲ ተማሪ የነበረ መሪ
  •  ኢትዮጵያ በታሪኳ በተማረ ሰው ስትመራ የመጀመርያ ግዜ  በተሰኙ መፈክሮችና ዲስኩሮች ተካበ፣ተቆነነ ፣ጀገነነ  ወዘተ..። እነዚያን መፈክሮችና ዲስኩሮች በአገር ቤትም በዳያስፖራውም  ዓለም  በበርካታ ትግራዊ ባልሆኑ ኢትዮጵያውያን ሲደጋገሙና ሲለጠጥ አስተውለናል። 

ያንኑ አጥፊያችን ሲሞት  ሁሉኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ አለቀሰለት ለማሰኘት ፦አካለ ስንኩላልንና ዱኩማንን ሳይቀሩ የሁሉንም  የኢትዮትዮጵያ ክፍላተ ሃገራት ሕዝብ  በነቂስ አደባባይ እንዲወጣ አስገድደው  ለብርቅዬ መሪያቸውን ሲያለቅሱ ፤ እንባቸውን  በተለቪን  መስኮት እንዲታይ አደረጉ ።

ከዚህ በተጻራሪ – የብሪቲሽ ጠቅላይ ሚኒስተር ማርጋሬት ታቸር እ.ኤ.አ በ8 ኤፕሪል ሙታ እስከ ተቀበረችብት 17 ኤፕሪል 2013 ዕለት ፣ በመሞቷ ያዘኑ ሲያለቅሱ ፤ በመሞቷ የተደስቱ አደባባይ ወጥተው ሲጨፍሩና ሲደንሱ ታይቷል። እ.ኤ.አ ከሜ 1979 -1990 በነበሩ የሥልጣኗ ዓመታት ፥  የሠራተኛ ማህበራት አዳከመች ፣ፋብሪካዎችና ኢዱስትሪዮች ወደግል በማዞር በጣም ብዙ ቁጥር ያላቸው ሠራተኞች ከሥራቸው ተወገዱ፣ ኮምኒቲ የሚባል ነገር የለም ሁሉ የግሉ ይሩጥ/ይኑር በማለት የ(social Darwinism Theory) ተግባራዊ በማድረግ ብዙ ድሆችና ችግረኞችን ጎዳች። ስልሆነም ያንን ጥቃት የደረሰባቸውና ያንን ይቃወሙ የነበሩ የማኅበረሰቡ አካሎች ( ‘we are happy you are gone, ,, ,, ,,’ !) በማለት በቤቷ ደጃፍ አበባ አኖሩ፣ በመሞቷ ድስታቸውን የሚገልጹ መፈክሮች እያሰሙ እና የውሸት የአስክሬን  ሳጥን ተሽክመው የተቀብረችበት ቦታ ወስደው አስቀመጡ። 

ያ ሁሉ ሲሆን ከፖሊስም ሆነ ከፀጥታ አካል ምንም አልደረሰባቸውም። አይ ነጻነት! ነጻነት ማለት ይህ ነው ! በማለት በውቅቱ ከላይ በንጽጽር የገለጽኳቸውን ኩነቶች በእንግሊዘኛ ጽፌ ለድረ ገጾች ማሰራጨቴ አስታውሳለሁ ።    

   ኢሳያስ አፈወርቂ  (ለእኔ  ኢሳያስ አፈ ጨርቂ) 

በቀን አንድ ግዜ መብላት ከማይችሉ የኢትዮጵያ – አርሶ አደሮች ፣አርብቶ አደሮች፣ ሰርቶ አደሮች ፣ንግዶ አደሮች ወዘተርፈ  በተሰበሰበ ቀረጥ/ታክስ እስከ  ዩኒብርስቲ የመማር ዕድል አግኝቷል። አሁን የደረሰብትን ቦታ ለመድረስ ማለት የኤርትራ ፕሬዝዴንት ለመባል ፣ በፈጠራ ታሪክ ኤርትራ የኢትዮጵያ ቅኝ ግዛት ነው ብሎ ፈረጅ። 

ስለሆነም ፀረ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን አቋም አንግቦና  ጠመንጃ አንስቶ እ.አ.አ ከ1961 – 1991  እንዲሁም  ከ1998- 2000 ዓ.ም ከኢትዮጵያ ሠራዊት ጋር ባደረገው  ጦርነት የግማሽ ሚሊየን (500,000) ኢትዮጵያውያንና ኤርትራ ውያንን  ሕይወት መጥፋት  እንዲሁም  የ700,000 ኤርትራውያን መሰደድ  ምክንያት የሆነ መሰሪ ሰው ነው።

 ወያኔዎች ትግራይን ገንጥሎ ራሱን የቻለ አገር ለማድረግ ሲነሱ – ትጥቅ፣ እስትራተጂና ስልት በመንደፍ  አደራጅቷቸዋል  ። በተመሳሳይ  ያለወያኔዎች  እገዛ በምንም ታዓምር የኤርትራ ክ/ሀገራችንና ሁለቱ የባህር በሮቻችን በኢሳያስ ቁጥጥር ሥር አይውሉም ነበር።  

ወያኔዎች የኢትዮጵያን በትረመንግሥት  ለመጨበጥ ያስቻላቸው በዋናነት መንግሥቱ ሃ/ማርያም እና ግብረ አበሮቹ  ቢሆኑም ወይም ወያኔዎች መንግሥቱ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያበረታቸው ስጦታ ቢሆኑም  ኢሳያስ ለዚያ ምርኩዛቸው ነው ። ኢሳያስ የወያኔዎችን  ጭንቅላት ኮትኳች (mentor or the brainchild) ስለነበረ ፣ መንግግሥቱን ከዙፏኑ አባረው  የአ/አበባን ቤተመንግሥት  (ለኔ ቤተ ጥፋት) ከተረከቡ በኋላ  ወያኔዎች ኢትዮጵያን ለመቶ ዓመታት  እንደሚገዙና  እየገዙ በሚዘርፉት ሃብት  ትግራይና ኤርትራን እንዲገነቡ  ፤ ካልሆነም  ኢትዮጵያን   እንዲያዳክሙና  እንዲበታትኑ  ምክር የሰጠ ፤ ‘ለኢትዮጵያ የመቶ  ዓመት  የቤት ሥራ ሰጥቼአለሁ’ በማለት በአደባባይ   የፎከረ ሰው  ነው ።

የሂትለርን  (The Aryan race ) ሞዴል/ናሙና በመከተል   የሌሎች ብሄር ብሄሰብ ተወላጅ ሚስቶች የነበርዋቸው   ኤርትራውያን  ባሎች-  ሚስቶቻቸው  ኤርትራዊያት   ባለመሆናቸው  ብቻ  ከልጆቻቸ  ተነጥሎ  እንዲባረሩ  መመርያ  ያወጣ  ሌላው ሂትለር ፤ሌላ አካል ሰንጣቂ  ፋሽስት  ነው። 

እ.ኤ.አ በ 1991 ኤርትራና ሁለቱ የቀይ ባህር በሮቻችን ሙሉ በሙሉ  በኤሳያስ እጅ ከወደቁ  በኋላ    በብዙ  ሺ የሚቆጠሩ የኢትዮጵያ ወታደሮች ፤ ትጥቃቸውን  ፈትተው  ለሻቢያ  ሠራዊት እጅ መስጠታቸ ውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ያውቃል። 

እ.ኤ.አ ከሜያዚያ 21 እስከ ነሃሴ 12/ 1949 እና በየካቲት 12/1950 ዓ.ም የተባበሩት መንግሥታት የጦር ምርኮኛ እስረኞችን በተመለከተ ከደነገጋቸው ሕጎች  አንዱ ፦, (prisoners of war must at all times be protected, particularly against acts of violence or intimidation and against insults and public curiosity. Measures of reprisal against prisoners of war are prohibited, Article 13). የጦር ምርኮኞች  ደህንነት ሁሌ መጠበቅ አለበት።በተለይም  ከአመጽ፣ ከማስፈራራት፣ ከስድብ  እንዲሁም  ከአካባቢዩ ሕዝብ የተለየ ትኩረት  መጠበቅ/መከላከል። የጦር ምርኮኛ እስረኞችን መበቀል ክልክል ነው ማለቱ ይመሰለኛል ።  

በተባበሩት መንግሥታት (U N) እ.ኤ.አ በዴሴምበር  10/1948 ዓ.ም ካወጣቸው የሰብአዊ  መብቶች  ውል/ድንጋጌ አንዱ አንቀጽ 5 (No one shall be subjected to torture or to cruel, inhuman or degrading treatment or punishment Article 5).  በማንም  ሰው ላይ ሶቆቃ  ወይም  ጭካኔ  ወይም ኢ-ሰብአዊ  ወይም ስብዕናን ዝቅ  የሚያደርግ  ድርጊት ወይም ቅጣት መፈጸም የለበትም/አይፈቀድም/ክልክል ነው  እንደማለት ይመስለኛል። 

ከላይ የጠቀስኳቸውን ዓለም አቀፋዊ ሕጎችን  በመጻረር ወይም በመናቅ፦

 ከፊሎቹ  ባስረከቡትን  መሳርያና ጥይት ወዲያውኑም ሲረሸኗቸው  ከፊሎቹ  ወደ በርሃ ወስደው የጉልበት ሥራ ሲያሰርዋቸው ፦ ምግብ፣ውሃና ህክምና በማጣት ማቅውና ተሰቃይተው መሞታቸውን ተነግሯል/ታውቋል። 

ከድኽረ  ኢትዮጵያን  ቅርመታም  በኋላ ኢሳያስና ወያኔዎች የተጣሉ ቢመስሉም ፣ የአንድ ሳንቲም ፊትና ኋላ እንደነበሩ ሳይገባቸው፣ በእዋህነት በኢሳያስ አጋዥነት ታግለውና ተዋግተው  የኢትዮጵያ  ሕዝብ  ከወያኔ ቀንበር ለማላቀቅ  አልሞ  ወደ አስመራ የተጓዙትን በርካታ  ሃቀኛ ፀረ ወያኔ ተቃዋሚዮች ፤ ከፊሎችን   በመግደል ግማሾቹን  እንደ  ናዚዮች  አስሮ ከባድ የጉልበት ሥራ በማሰራት  አማቅቆና አመንምኖ በመግደል፤ በቤርሙዳ ትሪያንግል ሰምጠው እንደቀሩ  መርከቦችና አይሮፕላኖች ሆነው ቀሩ ።

አብይ አህመድ  የኢትዮጵያ የስልጣን ማማ ከጨበጡ በኋላ  ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱት፦ 

» በፀረ ኢትዮጵያና  በፀ-የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድነት  መርህ ተሰልፈው ለረዥም  ዓመታት ላይና ታች ሲኳትኑ የነበሩ

»  ስለኢትዮጵያና  ሕዝባዊ  አንድነት ሲነሳ፣ ምን አንድ ያደርገናል ? በማለት የአሉታ ጥያቄ ሲያነሱና  ፀረ-አንድነቶቹን  ሲኮተኩቱ  የነበሩ

» ኢሳያስን ሲያሽሞነሙኑ የነበሩ ፣ባጠቃላይ  በልፍስፍስ ኢትዮጵያዊነት አቋም  እና  በፀረ- ኢትዮ ጵያ ኢትዮጵያዊነት  መርህና ድርጊት ፤ ኢሳያስ የሚፈልገውን ሲፈጽሙና ለኢሳያስ ሲላላኩ የነበሩ ናቸው።   
በመሆኑም  ላለፉት  ሰልሳ ዓመታት የአገራችን  ነቀርሳ ከነበሩትና ከሆኑት  እንዲሁም ላለፉት ስላሳ ዓመታት  ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን  ለገጠማቸው  ዘርፈ ብዙ ቀውሶች ምክንያቶች አንዱ ኢሳያስ ነው ።

ከላይ ለማሳየት  የሞከርኳቸውን  ኩነቶች /ድርጊቶች  ባለፉት ሃምሳ ዓመታት ከኢትዮጵያ ፖለቲካ ጋር  ተቆራኝተው  የኖሩና  በዚያ ውስጥ ያለፉትን  ኢትዮጵያውያን ጠንቅቀው የሚያውቋቸውና በተለያዩ ፀሃፊዮች የተነግሩ ሃቆች  መሆናቸው  ባውቅም ፤ በዚህ  አርእስት  ማስተላለፍ  ከምፈልገው  መልዕክት  ጋር ስለሚዛመዱ ለንጽጽ ር  ፈልጌቸው ነው ። 

ስለሆነም  የዚህ ጽሁፍ አርእስት  ዋና  መልዕክት ከዚህ ይቀጥላል ።

ኢሳያስ  አዲስ አበባ፣ባህር ዳርና ጎንደር ሲጎበኝ የተደረገለትን አቀባበል ሳስበው ያመኛል።በኢትዮጵያና በኢትዮጵያውያን ላይ ከላይ የጠቀስኳቸውና ያልጠቀስኳቸው ዓይነት የከፋ ግፎች ሲፈጸመ ለኖረ ሰው  የዚያን ዓይነት የእልልታና የፈንጠዝያ አቀባበል ይገባው ነበርን? (does he really deserved such thrilled reception or welcome) ። 

የተደረገለት አቀባበልና መስተንግዶ  እንደ አንድ አጥፊያችን ሳይሆን፤ እንደ አንድ ታላቅ ውለታ የዋለልን ብርቅዬ ወንድማችን  የመጣ ወይም እየሱስ ክርስቶስ እነዚህን ከተማዎች የረገጠ ይመስል ነበር። 

ኢሳያስ ወደ ኢትዮጵያ ለመሄድ መደረግ የነበረባቸው ሁለት በጣም አነስተኛ ቅድመ ሁኔታዎች ፦

 (1)  በኢትዮጵያና በኢትዮጵያውያን ላይ  ላደረሰው ክህደትና ግፍ  ተማጽኖ  ይቅርታ መጠየቅ ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብም  ተጠይቆ የኢትዮጵያውን  አውንታ ማግኘት 

 (2) የአሰብና የምጽዋ የባህር በሮቻችን  የተወሰዱት በወያኔዎች እገዛ  በፋሽስቱ መንግሥቱ አገዛዝ  ወቅት ሲሆን፤የሁለቱ ወደቦቻችንን ባለቤትነት  በይፋ ለኢሳያስ የተሰጡት  በወያኔዎች ሥርወ-መንግሥት  መሆኑን ለኢትዮጵያውያን ሁሉ ግልጽ ነው ። እነዚህ  ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን የቆመ መንግሥት ባልነበረበት ወቅት  ከተወሰዱት  የባህር በሮቻችን  አንዱ የአሰብ የባህር በራችን መመለስ  ። 

ያ ባልሆነበት  ያንን ዓይነት ምንቀረሽ የአክብሮት አቀባበል እነዚያን  ግዙፍ  ግፎቹና  ደባዎች ፤ እስይ እንኳን አደረካቸው ማለት አይሆንምን?  እንደ አንድ ሕዝብ የማሰብ ብቃታችን የሚፈታተን አይሆንምን ? የእነዚያ  ግፍች  ጠባሳ ያለበት ትውልድ ሙተው አልቆ ይሆን? ወይስ ፋሽስቱ  መንግሥቱና ባንዳው መለስ እንዳደረጉት  ሕዝቡ ተገዶ ነው የወጣው?

ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ፣ የፍልስጤሞች ፕሬዝዳንት ማህሙድ አባስ  የእስራኤል ፕሬዝደንት የነበረው ናታ ኛሁ ፤ የፍልስጤሞችን ዋና ከተማ ‘ራማላህ’ እንዲጎብኝ ቢጋብዝ   ኢትዮጵያውያንን ለኢሳያስ ያደረጉትን  ዓይነት አቀባበል ያደርጉ ይሆን ? ከይጎዝላቪያ የመገንጠል ታሪካዊ መብት ቢኖራቸው እንኳን ባልመረጧቸው ገዢዮቻችውን ፈቃድ ብቻ –  የኮሶቮን፣ የኩሬሺያን፣ የቦሲኒያን ወዘተርፈ መሪዮች ወደ ቤልግሬድ ቢሄዱ  የኢትዮጵያ ሕዝብ ለኢሳያስ ያደረገውን  ዓይነት አቀባበል ያገኙ ይሆን?

ኢሳያስ ያለቅድመ ሁኔታና ያለሕዝባዊ አውንታ  ባልመረጥናቸው ገዢዮቻችን ተጋብዞ ስለመጣ ተቀባዮችና አስተናጋጆቹ ፦ የኢሕ አድግ  ባልሥልጣናት ፣ውለታ የዋለላቸው የፖለቲካ ድርጅቶች ለምሳሌ (ኦነግና ግንቦት 7)፣  በእነዚህ ከተማዎች  የሚኖሩ ኢሳያስን አፍቃሪ  ኤርትራውያን ብቻ ዝቅባለ ደረጃ (low profile መሆን በተገባው ነበር ። 

በነዚህ  በአገራችን  ዋና  ዋና ከተማዎች የተደረገለትን ጀግናዊነት የተላበሰ ወይም ሄረዊክ አቀባበል፤ በዓለም መንግሥታት፣  መሪዮችና ዲፕሎማቶች  ከተረሳበት ወደ መኖሩን እንዲታወስ አሸጋግ ሮታል ። ኢሳያስ ወደ  አ/አ ሲመጣ እና  ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ ወደ አስመራ ሲሄዱ ፤ግንኙነቱ ሕዝብ ለሕብ ለማቀራረብ  የሚል ሽፋን ነው የተሰጠው ። 

የኢሳያስ ዓይነት አምባገነን ገዢዮች ሕዝብ ለሕዝብ ያናክሳሉ እንጂ ሕዝብ ለሕዝብ የማገናኘት ስብዕና የላቸውም ። እውነተኛ/ኦርጋኒክ ሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት የሚገኝው  በዲሞክራሲያዊ መርህና አስራር  ተመርጠው ሕዝብ በወከላቸው መሪዮች መሪነት ብቻ ነው። ያንን ሁኔታ በኢትዮጵያም ሆነ በኤርትራ ስለሌለ ፣ የኤርትራ ሕዝብ  ከኢትዮጵያ ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸውን ተቀላቅሎ መኖር ከፈለጉ  በመጀመርያ ሰው በላው ኢሳያስ ማስወገድ፤ በመቀጠል ምሥራቅ ጀርመኖች እንዳደረጉት ማለት በእነሱና በምዕራቡ ጀርመን የተጋረደውን ግንብ እንዳፈራረሱ  በታንክ የታጠረው የኢትዮ-ኤርትራ  ድንበር  በአመጽ ማስከፈት ይኖርባቸዋል።  

?በእኔ ግምት ኢሳያስ ወደ ኢትዮጵያ ለመቅረብ የፈለገበትና አብይ አህመድ ወደ ኢሳያስ የሄዱበት   ምክንያቶች (5) ናቸው ፥ ይኽውም  (1) አሜሪካኖች  ወደ ምጽዋና አስብ ወደቦች ለመጠጋት የነበራቸውና ያላቸውን  ምኞት  በዚህ አጋጣሚ ለማሳካት ከመፈለግ፤ ከኢትዮጵያ ጋር  ብትጠጋ የተሻለ ተጠቃሚ ትኆናለህ  እኛም አለንልህ  ስላሉት (2) ፕ/ብርሃኑ ነጋን፣ አቶ አንዳርጋቸው  ጽጌን እና  የኦነግ ሃይሎች ባለውለታቸ ኢሳያስን ወደ ኢትዮጵያ ቢጠጋ ተጠቃሚ እንድሚሆን በሰጡት  ምክር  (3) እሱም  ወያኔዎችን ከመፍራትና አጋር ከመፈለግ  (4) አብይ አህመድም  ኢሳያስ  መልሶ ከወያኔዎች ጋር  እንዳያብር (alliance) እንዳይፈጥር ከመፍራት (5) በወያኔዎች እገዛ በጠመንጃ አፈሙዝ የወሰደውን ፤ የወጪና የገቢይ ሸቀጦቻችን ማራገፌያ ወደብ እንዲሰጠን ሳይሆን እንዲያከራየን ከማሰብ  ሊሆን ይችላል ባይነኝ ።

ኢሳያስ ከወያኔዎች ጋር መልሶ ይወዳጅ ይሆን?  ምን ለማግኘት ወይም ምን ጥቅም በማሰብ? በትግራይ ከሚመረተው  የህል ክምችት ለኤርትራ  ሕዝብ ዳቦ ለማቅረብ? ከኢትዮጵያ ከተዘረፉትና በኢትዮጵያ ሕዝብ ስም ከተበደሯቸው ብዙ ብሊየን ዶላር፣ ይሮና ዩዋን (yuan)  ክምችት ያካፍሉኛል ብሎ ከማሰብ? ወደ ትግራይ ተወስዶ ከተከማቸው  የጦር መሳርያና ወታደራዊ ቁሳቁስ ያካፍሉኛል ብሎ ከማሰብ? በትግራይ ከተመረቱ የኤሌትሮኒክስ፣ የኮምኒኬሸን፣ የኢንዱስትሪ ፣የግብርና ወዘተርፈ ቴክኖሎጂዮች እጠቀማለሁ ብሎ  ከማሰብ ? በጋራ ኢትዮጵያን ዳግም ውግተውና ወረው ሃብቷን ለመቀራመት በማሰብ?          ለእኔ የማይታሰቡ  የሩቅ ጭሆቶች ናቸው ። ለመላምንቶቼ  አንባቢ የመሰለውን ሊል ይችላል። 

አቶ ኢሳያስ የኢትዮጵያን ሕዝብ ተማጽኖ ይቅርታ ሳይጠይቅና ሳይክስ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣቱ ያለኝ ተቃውሞ እንዳለ ሆኖ፤ የኢሳያስን  ከኢትዮጵያ ጋር  መወዳጀት  ላይ ሥጋትም ተስፋም አለኝ ።

ለግዜው የሚታዩኝ ሥጋቶች፦

«  የአቶ ኢሳያስ አቻ አምባገነን ገዢ በኢትዮጵያ እንዲሰፍን ይመክር ይሆናል

   « በስለላ አውታሮቹ የኢትዮጵያ የውስጥ አገራዊ ሚስጥር ወስዶ ለወዳጆቹ  አረቦች ይሸጥ ይሆናል

« ከወያኔ ጋር ጦርነት ቢገጥም ጦሱ ለኢትዮጵያም ይተርፋል 

ለግዜው የሚታዩኝ ተስፋዎች ፦

»  ረከስ ባለ ክራይ ወደቦቹ ያከራየን ይሆናል

»  በሂደት  ከኢትዮጵያ የሚያገኘው ሁለገብ ጥቅም ካስደሰተው  አስብ ያለክራይ እንድንጠቀምበት ይስጥ ይሆናል

» የኤርትራ ሕዝብ ከኢትዮጵያ ወንድሞቹ አብሮ መኖር  የበለጠ ተጠቃሚና  ሙሉዕ እንደሚያደርጋቸው ስለሚያውቅ  በሩቅ ሂደት በድሮ ዓይነት ፌደራላዊ ሥርዓት መተዳደር ይፈልግ ይሆናል

»  ያም ካልሆነ ኮንፈደሬሽን ይጠይቅ ይሆናል    

የዚህ ጽሁፍ  ማጠቃላያ  

ለግማሽ ምዕተ ዓመት ፥ 

ሀ)  ሕዝባዊ አንድነታችን የሸረሸሩና ያናጉ፣ሃገራዊ ሉዓላዊነታችን  የቆራረሱ፣  ዳርድንበራችንን የደፈሩና  ያስደፈሩ ፣የባህር በሮቻችንን የነጠቁና ያስነጠቁ 

ለ) የተለያዩ የአፍ መፍቻ ቋንቋቸውና የተለያዩ ንዑስ ባህል ስላላቸው ብቻ የተለያየ ዘረመር/ጂንስ እንዳላቸው  አድርጎ በመኮትኮት አገር በቀል የአፓርታይድ ሥርዓት የዘርጉ፣በጎሳዎችና ብሄር ብሄረሰቦች መካከል የቁጥጥር ኬላ የፈጠሩና አካል የሰነጠቁ 

ሐ)  የአገር ሃብት በተለያየ መንገድ  የዘረፉና ያዘረፉ፣ እየገዙ የእነሱን የዘር ምንጭ ከሚልዋቸውና  የሥልጣን ዕድሜያቸውን  ለማራዘም ከተጠቀሙባቸው  የጀርባ አጥንታችወን ከጎበጠ  ኢትዮጵያውያንና ባዕዳን ጋር በመሆን የሃገራችንን የሃብት ምንጭና  የንግድ  ዘርፍ  በቁጥጥራቸው  ሥር ያዋሉ

መ) ሥልጣን በመነፓል ይዞ ለመቆየት-  በዋናነት ወጣቱና የተማረውን ዜጋ በመመንጠር ኢትዮጵያን ሲያፈርሱና ሲያዳክሙ የነበሩ

ሠ)  መከራ፣ ሰቆቃ፣ የገፍና የግፍ እስር፣ የገፍና የግፍ  መፈናቀል፣ መጠነ  ሰፊ የጅምላና የተናጥል ግድያ ፣ የጦር ሜዳ  የሰው እልቂት ፣ቀውስ፣ ሽብር – ባጠቃላይ መሪር  ሃዘንና ቁጣ  በአገራችንና  በሕዝባችን ላይ ስላሰፈኑ  ስለሶስስቱ  ነቀርሳዎች -ስለ (መንግሥቱ ሃ/ማ ፣መለስ ዜናዊ እና ኢሳያስ አፈጨርቂ )በየቀኑ ተጽፎ ባይ ደስይለኛል።

ምክንያቱም  (1) በነዚያ ጨለማና የመከራ  ሥርዓቶች  ውስጥ ያለፈን ትውልድ በሙሉ ሙቶ አፈር እስኪለብስ ፤ እነዚያ በቃላት ለመግለጽ የሚያስቸግሩ ግፎች እንድናስታውሳቸው  (2) ያኔ በጨቅላ ዕድሜ ከነበረው ትውልድ አሁን  እስካለው  ትውልድ ስለሶስቱ የኢትዮጵያና የኢትዮጵያ ሕዝብ  ነቀርሳዎችን  ዘርፈ ብዙ ጥፋትችና ጭፍጨፋዎች  ጠንቅቆ አውቆ ለነገው ትውልድ እንዲያስተላልፍ  (3)  መንግሥቱ ሃ/ማ ጀግናና አገር ወዳድ እንደሆነ አሁንም በካድሬዎቹ የሚነዙ ፕሮፓጋንዳዎች ፍጹም ውሸትና  ከእውነት የራቀ፤ ተረት ተረት እንደሆነ ይህ ትውልድ እንዲያውቅ። 

በዘመናዊ ትምህርት ዓይኑን የከፈተውና የነቃውን ፦ ወጣት፣ ጎልማና አዛውንቱን  ዜጌ የጨፈጨፈና የመተረ ገዢ  አገር ወዳድ መሪ ነበር ማለት ፦

ብቻውን ተመችቶት እንዲኖር – ልጆቹን ጨፍጭፎ ካጠገቡ ያስወገደ  አባት ጥሩ አባት ነበር እንደማለት አይሆንምን? ወይም  ምዕምናንን ጨፍጭፎ የገደለ/ያስገደለ ቄስ ጥሩ ቄስ ነበር እንድ ማለት አይሆንምን?  ወይም  ሁሌ  በጎችን  በቀበሮ/በተኩላ  ያስበላ እረኛ ጥሩ እረኛ ነበር እንደ ማለት አይሆንምን?  ወዘተ..     

Filed in: Amharic