>
5:13 pm - Tuesday April 19, 7177

ልጆቹን የበላ ጅብ አልጮኸ አለ...!!! (ያሬድ ሀይለማርያም)

ልጆቹን የበላ ጅብ አልጮኸ አለ…!?!

ያሬድ ሀይለማርያም

I can’t keep calm. Girls are still missing! 
ከዛሬ ነገ ያሉበትን ሁኔታ አፋኞቹ አካላት እደ ቦኮሃራም ደፈር ብለው ኃላፊነቱን ወስደው እንዲህ አረግናቸው ወይም በእጃችን ላይ ናቸው ብለው ይናገራሉ ወይም ጉዳዩን ለእኔ ተውልኝ ያለው መንግሥት ቁርጣችንን ያሳውቀናል ብለን ስነጠብቅ ግማሽ መንፈቅ ሊሞላ ነው። ያህያ ባል የመሰለው መንግስታችን እና በጅብ የሚመሰሉ  ታጣቂ ቡድኖች  በተገጣጠሙበት አገር የዜጎች እጣ ፈንታ ይሄው ነው። ታፍኖ የደረሱበት ሳይታወቅ መቅረት፣ በመንጋዎች መደብደብ፣ መዘረፍ እና በሰላም የመኖር ዋስትና ማጣት። በህውሃት ዘመን ጅቡ መንግስት ነበር። አፋኙም፣ ገዳዩም መንግስት ነበር። ዛሬ ደግሞ መንግስት ያህያ ባል ሆኖ ሌሎች ጅቦች ተፈጥረዋል።
በእነዚህ ልጆች ጉዳይ ከዚህ በኋላ ሙሉ በሙሉ ተጠያቂው መንግስት ይመስለኛል። ለዜጎቹ፤ ሊያውም ኃላፊነት ወስዶ ከቤተሰብ የተረከባቸውን ተማሪዎች ከጥቃት መታደግ ባለመቻሉ ብቻ ሳይሆን ከዚህ ሁሉ ወራት ቆይታም በኋላ በቂ ምርመራ አካሂዶ የደረሰበትን ውጤት ለቤተሰቦቻቸው ማሳወቅ ባለመቻሉ መንግሥት ኃላፊነቱን እየተወጣ አይደለም። ከአቅሜ በላይ ነው ማለትም አንድ ነገር ነው። ግን ዜጎች ከመንግስት አቅም በላይ የሆነ ቡድን በአገሪቱ ውስጥ ይንቀሳቀሳል ብለው ማሰባቸውም በራሱ ሌላ መዘዝ አለው።
ብዙ ጊዜ የእነዚህን ልጆች ጉዳይ ስናነሳ ልጆቹ እራሳቸውን ደብቀው ነው እያላችሁ የምታላግጡና መንግስትን የተከላከላችሁ መስሏችሁ የምትሟገቱ እርህራሄ የራቃችው ሰዎች አንድ የሳታችሁት ነገር አለ። እንኳን አሥራ ሰባት ተማራዎች ይቅርና አንድም ግለሰብ እራሱን ከመንግስ ሰውሮ ለስድስት ወር ያህል በአገሪቱ ግዛት ውስጥ መቆየት ከቻለ የመንግስት የጸጥታና ደህንነት ዘርፋ እጅግ ደካማ ነው ማለት ነው። አገሪቱን እና ዜጎቿን ከጥቃት መታደግ አይችልም ማለት ነው። ከዚህ በኋላ ልጆቹ የት ናቸው ብዮ አልጠይቅም። በዚህ ጉዳይ መንግስትን ቀጥተኛ ተጠያቂ ማድረጊያው ወቅት ላይ የተደረሰ ይመስለኛል።
Filed in: Amharic