>

ጠቅላይ ሚንስትሩን  በመረጃ  እንሞግት !! (ተስፋዬ መንበሩ)

ጠቅላይ ሚንስትሩን  በመረጃ  እንሞግት !!


በተስፋዬ መንበሩ

ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ ሰባተኛው ንጉስነታቸውን አውጀው ወደ ዙፋኑ እንደወጡ እንደ መና ካዘነቧቸው ቃላቶቻቸው በመነሳት ከፈጣሪ እንደተላከ መሲህ ተቆጥረው የተጣለባቸው  አገራዊ  ተስፋ የትየለሌ ነበር።
ሰባተኛው ንጉስ  ዙፋናቸውን አፅንተው ተቀናቃኞቻቸውን መቀመቅ እስኪያወርዱ ህዝቡን ከጎናቸው ለማሰላፍ ከምድር ሳይሆን ከመላዕክት መካከል ናቸው እስኪባል ድርስ ያልሰጡት ተስፋ ያልገቡት ቃል አልነበረም።
ይሁን እንጂ  ንጉሱ ቃላቸውን በግርድፍ እየሰባበሩ በልተው  “ያሉት ከሚጠፋ የወለዱት ይጥፋ” የሚባለውን አገረኛ ብሂል  መና ለማድረግ አመታት ማስቆጠር አላስፈለጋቸውም … የገዛ ቃላቸውን እየጎመዱ ጣሉት።  ለቃላቸው ያልታመኑት ንጉስ  ከገደፏቸው ቃል ኪዳኖቻቸው መካከል እንዳንዱን እየጠቀስን እንሞግታቸው  !!

1ኛ) ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ …

ዶ/ር አቢይ ይህንን መሠረታዊ ጥያቄ ባግባቡ ላለማስተናገድ እንደ ዋና ምክንያት ያስቀመጡት የመንግሥትን ቅቡልነት ነበር። “ይኸ መንግሥት በህዝብ የተመረጠ መንግሥት ስላልሆነ እሱ ያሻሻለው ሕገ መንግሥት ቅቡልነት አይኖረውም”  ነበር ያሉት።
በወቅቱ ጠቅላይ ሚንስትሩ መንግሥት ቅቡልነት (legitimate) የሌለው መሆኑን መጥቀስ አልበቃቸው ብሎ 27 ዓመታት በፖለቲካ ድህው ያደጉበትን መንግስታቸውን አሸባሪ ነው እስከማለት ደርሰው እንደነበር እናስታውሳለን። በእርግጥ ሕገ መንግስታዊ ማሻሻያ ለማድረግ  በህዝብ የተመረጠና ቅቡልነት ያለው መንግሥት መኖር የግድ ባይሆንም ያነሷቸው ነጥቦች ግን በአመዛኙ ተቀባይነት ያላቸው ነጥቦች ነበሩ ብሎ መከራከር ያስችላሉ።
አሁን ግን ያ መሞገቻ ቃላቸው ማፈሪያና መሸማቀቂያ ሆኖ የዛሬው አቋማቸውን እየሞገተ አላወላዳ ሲላቸው እያስተዋልን ነው። ጠቅላይ ሚንስትሩ ትላንት ከልባቸው ሳይሆን ካንደበታቸው እያነቁ ያግተለተሏቸው የተስፋ ቃላት  ከሰሞኑ ዛቻና ዘለፋቸው ጋር በተቃርኖ እርስ በእርስ እየተጋጩ የአገራችንን ፖለቲካ በጩህት ሞልተውታል።
“ያኔ በህዝብ የተመረጠ አይደለም ተቀባይነትም የለውም”  ያሉትን መንግሥት ዛሬ ግን በተቃራኒው “በህዝብ የተመረጠና ቅቡልነት ያለው ነው ሲሉ አይናቸውን በጨው አጥበው ሾርት ሚሞሪ ሲሉ ለተቹት ህዝብ  ያለምንም መሸማቀቅ ተናግረዋል። ጠቅላዩ በህዝብ የተመረጠ መንግሥት እያለ “የሽግግር መንግሥት” የሚባል የብጥብጥ መንግሥት አይታሰብም ሲሉ ለአማራጭ ሃሳብ ያላቸውን ጥላቻና ፍራቻም በግልፅ አሳይተዋል። በህዝብ ያልተመረጠውና ቅቡልነት የሌለው መንግሥታቸውም በእርሳቸው ቡራኬ ቅቡል ሆኖ ቀርቧል።  “ለአንድ ክልል ብለን ህገ መንግስት አናሻሽልም” ያሉት ጠቅላይ ሚንስትር ስልጣናቸውን የሚፈታተን ጉዳይ ሲመጣ ማደስ ብቻ ሳይሆን አራግፈዋለሁ ብለው ብቅ አሉ።

2ኛ ምርጫው ይራዘም አይራዘም ክርክር…

ጠቅላይ ሚንስትሩ ለዚህ ያቀርቡት የነበረው ምክንያት
 “ምርጫው ለአንድም ቀን ከተራዘመ ሕገ መንግሥታዊ ጥሰት ነው ከዚያ በኋላ ሕጋዊ መንግሥት አይኖርም።”
የሚል ነበር። ይኸኛው መከራከሪያም ከቅንነትና እንደ ሀገር ያለንበትን ነባራዊ ሁኔታ ከመረዳት አንፃር ጉድለት ቢኖርበትም ከሕግ አንፃር ትክክል ነው ሊባል ይችላል።
ጠቅላዩ ሰሞኑን በወሰዱት አቋምና እሱን ተከትሎ ባደረጉት ንግግር ይኸንን የቀደመ መከራከሪያቸውንም በካልቾ ብለው በተቃራኒው መቆማቸው ግን አጃይብ የሚያሰኝ ነው። በዓለም አቀፉ ወረርሽኝ ምክንያት ምርጫው ከተራዘመ (መራዘሙን የተቃወመ የለም) ከመሥከረም 25/2013 ዓ.ም በኋላ ሊፈጠር የሚችለውን የመንግሥት ሥልጣን ክፍተት(power vacuum) እንዴት እንሙላው የሚለውን ጥያቄ በሥልጣን ጥመኝነት መንፈስ የቀረበ አስመስለው በማጣጣል መንግሥታቸው ብቻውን በሥልጣን ላይ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
“ምርጫው ከተራዘመ መንግሥት የለም ማለት ነው”  ሲሉ የነበሩት ዶ/ር አብይ የሌለ ቀዳዳ ከሕገ መንግሥቱ ውስጥ በመፈለግ በበድኑ ላይ ነፍስ ከመዝራት ውጭ አማራጭ የለም ብለዋል። ስልጣን ወይም ሞት መፈክራቸውን በይፋ አውጀዋል !!

3ኛ የተለየ ሃሳብን ማክበር…

ጠቅላዩ ወደ ሥልጣን እንደመጡ  “ከተቃዋሚ ፓርቲዎች የሚነሱ ሃሳቦችን ከወንድም የተሰጠ ሃሳብ አድርገን በመቁጠር የሃሳብ ብዝሃነትን እናስተናግዳለን”  ሲሉ ተደምጠው ነበር።
በወቅቱ እነዚህ ወንድሞች የተባሉ ተቃዋሚዎችን “ተፎካካሪ” የሚል ስም አውጥተውላቸው እንደነበርም የሚታወስ ነው። በሂደት ግን ይኸ ተለውጦ በተለይም በሰሞኑ ንግግራቸው የተለዬ አማራጭ ሃሳብ ያቀረቡ ፓርቲዎችና ግለሰቦችን በሀገር አፍራሽነትና ፀረ ሰላምነት ፈርጀው ሲያስፈራሩና ሲዝቱ ሰንብተዋል። ይህ ያለፈው ሥርዓትና የአብዮታዊ ዴሞክራሲ መንፈስ ያልተለየው አቋማቸው ካሳለፍነው ጊዜ አንፃር የሚጠበቅና ብዙ የሚገርም ባይሆንም ከዚህ በፊት ሲናገሩት ከነበረው አንፃር ግን ተቃራኒ ነው። ተስፋ ተደርጎበት የነበረው የለውጥ ሂደቱም በዚህ ፍጥነት መክሸፉ አሳዛኝ ነው…
ይቀጥላል
Filed in: Amharic