>
5:13 pm - Monday April 19, 9317

" ግብፆች የፖለቲካ  ቼዝ  ጨዋታ ላይ ናቸው!!!   (አለባቸው ደሳለኝ አበሻ )

” ግብፆች የፖለቲካ  ቼዝ  ጨዋታ ላይ ናቸው!!!”

   አለባቸው ደሳለኝ አበሻ (ለንደን)
በሰሜን ምስራቅ ኣፍሪካ የምትገኜው ግብፅ  ዘጠና ሰባት .ነጥብ ሀምሳ አምስት ሚሊዮን (97.55 million ) ከሚሆነው ህዝቧ አብዛኛው ከናይል ወንዝ ዳርቻ በአንድ ኪሎሜትር ክልል ውስጥ ይገኛል። የታሪክ ድርሳናት ስንፈትሽ እንደሚሉት ከሆነ ግብፅ በሰሜን  ከሜዴቴራኒያን ባሕር በምሥራቅ ከቀይ ባሕር፤ በደቡብ ከኖብያ፤ በምዕራብ ከምድረ በዳው አገር ትዋሰናለች ።
 አብዛኛው መሬቷ  በሰሃራ በረሃ ክልል ውስጥ ሲሆን ዋና ከተማዋ ካይሮ ከአፍሪካ ትልቁ ከተማ ነው።
የግብፅ ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ ታሪኳ ፤ ከፈሮዖኖች ጀምሮ ፣ 4500 አመታት ግዛት በኋላ በግሪኮች፣ ሶስት መቶ   አመታት ገደማ  ፤ ቀጥሎም በሮማውያን ሶስት መቶ ፣ አመታት ፤ ከዚያም በቢዛንቲያ ለሶስት መቶ አመታት ፤ በመቀጠልም ለአንድ ሽህ አንድ መቶ አመታት አረቦችና ማምሉኮች በየተራ እየተፈራረቁ ሲገዟት ፤  የትውልደ አልባኒያዊው የሞሀምድ አሊ ስርወ-መንግስት በቀጥታ ወደ ሰማኒያ አመታት  አንቀጥቅጦ አስተዳድሯታል  ::
ቀሪዎቹም  የመሃመድ አሊ ልጆች የእንግሊዝን ቅኝ ገዢነት ተቀብለው  ከ1922 -1952   በንጉስነት ገዝተዋታል ::
በዚህ አይነት ግብፅ ከፈሮዖኖች በኋላ ፤ 2500 አመታት ገደማ ግብፃዊ ባልሆኑ ባዕዳን  በቅኝ ግዛት ተቀጥቅጣ ተገዝታለች ።
ከነዚህ የባእዳን ቅኝ ግዛት በኋላ የመጀመሪያውን ግብፃዊ መሪ በወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት ስልጣን ያዘ  ::  በነገራችን ላይ ሶስቱም ግብፃውያን  መሪዎቿ   ወታደሮች ነበሩ ::
 ጀማል አብደል ናስር ፤ አንዋር ሳዳትና  ሆስኒ ሙባረክን ጨምሮ ሶስቱም ለ60 አመታት እስከ 2012ድረስ በይስሙላ ምርጫ  እንደ እሳት አንገብግበው ግብፅን ገዝተዋታል ።
 ወዳጆቼ የዚህ ፅሁፍ  አላማ የግብፅን ታሪክ ለመተረክ ሳይሆን  ለዘመናት የባዕዳን ሎሌ ሁና በቅኝ ግዛት ፍዳዋን ስትቆጥር የነበረችው ግብፅ የአባይን ውሀ በጦርነት ለማስገበር ማሰቧ እራሱ
ከቅኝ ግዛት ታሪኳ ስንነሳ ከኢትዮጵያ ጋር የያዘችው እስጥ አገባ በእሳት እንደመጫዎት ይመስለኛል ::
በእርግጥ ደምስ በለጠ የተባሉ ፀሀፊ እንደሚሉት ከሆነ ” ግብፅ (ምስር)እንደሃገር ከምትታውቅበት ማለትም ከፈሮኦኖች ዘመን ጀምሮ ፤ የታሪኳም ሆነ የህልውናዋ መሰረት አባይ ነው። አባይ ባይኖር የግብፅ የቆየና ጥንታዊ ታሪኳ የለም ፤ የፈርኦኖች ታሪክ የለም፤ አባይ ባይኖር የክሊዮፓትራ ታሪክ የለም ። ባጠቃላይ አባይ ባይኖር ግብፅም ታሪኳም፤ ጥንታዊ ስልጣኔዋም፤ የአለማችንን እውቅ የታሪክ ምርምር መፃህፍት ገፆች ባላጣበቡ ነበር ። ታላቁ የግሪክ የታሪክ ሰው ሄሮዶቱስ ግብፅ የአባይ ስጦታ ነች”  ያለውም ለዚህ ነበር በማለት ሀሳባቸው ያጠቃልላሉ  ::
እኔም በግሌ ባደረኩት የታሪክ ዳሰሳ ሁሉም የታሪክ ተመራማሪዎች እንደሚስማሙበት አባይ  ከጎጃም ምድር መንጭቶ፣ ጎጃምን አካቦ ወርዶ ሱዳንንም አቋርጦ አራት ሺህ ማይል ዐልፎ፣ ከሜዲትራኒያን ባሕር   የሚቀላቀለው አባይ
 የናይል ወንዝ ታላቁ ገባር ወንዝ ሲሆን መነሻው ኢትዮጵያ ነው።
አባይ 70 በመቶ የሚሆነው የሀገሪቱን ወንዞች የውሃ ድርሽ ሲይዝ አጠቃላይ የውሃድርሻውም ቢሆን 50 በምቶ የሚጠጋ ነው። በኢትዮጵያ ከአባይ ውጭ ያሉት ወንዞች ድምር ድርሻ 30 በምቶ ሲሆን ለግብጽና ለሱዳን ዋና የወሃ ምንጭ እንደሆነው ሁሉ ለኢትዮጵያም አባይ ወሳኝ ወንዟ በመሆኑ ኢትዮጵያ በብሔራዊ ሐብቷ ለሰከንድም የማንም ምርኮኛ ልትሆን እንደማትችል እርግጠኛ ነኝ  ::
ሌላው ቢቀር ግብፅ አስዋን ግድብን ግርጌዋ ላይ አስቀምጣ በህዳሴው ግድብ ላይ የምትዝት ከሆነ እዚያም ቤት እሳት አለ ፣ እንዲሉ  ግብፅ ልትረሣው ባልተገባት ነበረ ::
በአፍሪካ በሀብት ብዛት ሁለተኛ የሆነችውን እና እንዲሁም የመከላከያ ሰራዊቷ የተደራጀ እና በጠንካራ አቋም ላይ ያለችን ኢትዮጵያን ለመውረር  ቀርቶ ማሰቧ ምን ያህል ዋጋ ሊያስከፉላት እንደሚችል  አረቦቹም ሆነ አሜሪካኖቹ ጠንቅቀው የሚያውቁት ይመስለኛል ::
እውነታውን ስንፈትሽ ግን  ” ግብፆች የፖለቲካ  ቼዝ ”   ጨዋታ ላይ ናቸው  ::
ግብፅ  የቀድሞውን መሪ ሞሀመድ ሆስኒ ሙባርክን ከስልጣን ካስወገደች በኋላ እንደ ሐገር የመቀጠሉ ሁኔታ አልሳካላት ብሎ  የአረብ ሐገራትንና አሜሪካንን ተደግፋ ገና ወፌ ቆመች እያለች ነው  ::
 እውነቱን ለመናገር ከተፈለገ በአሁን ስአት ግብፅ ያለባትን ውስብስብ  የውስጥ ችግሯን ለመፍታት ከእቅሟ በላይ ሆኖባት እየተንገዳገደች በሁለት እግሯ መቆም አቅቷት በምትዳክርበት ወቅት ለፖለቲካ ፍጆታ ብላ አባይን ከግድቡም ሆነ ከምንጩ ለመቆጣጠር ማሰቧ እብደት እንጅ የጤነኝነት ምልክት እንዳልሆነ አለም አይኑ ከፍቶ ጉዳዩን እየተካተተለ፣ ይገኛል ::
 የፕሬዝዳቱ ከፍትህ ሚኒስቴር ጋር እስጥ አገባ ንትርክ ፣ ከሊበራሎች ጋር ባለ ጭቅጭቅ  እንዲሁም እጅግ በጣም ከሚያከሩት ከሳላፊስቶች ጋር በተያያዘ ፓለቲካዊ ትንቅንቅ ፣ የሐይማኖትን ጉዳይ ተከትሎ በክርስቲያች ላይ እየደረሰ ያለው መጠነሰፊ  ችግር እንዲሁም  ካለህዝቡ ፍቃድ በግርግርና በሁከት በፀደቀው ህገ-መንግስት ተከትሎ  በግብፅ ውስጥ ያለው መከፋፈል በጥቅሉ የሞርሲን ስልጣን ጥርሱን እያነቃነቀው ባለበት ወቅት በርህኛውን የአባይ ወንዝ በጠመንጃ አፈሙዝ ለማስገበር መመኜት  ግብፅን እንደገና አፍሪካ ካርታ ላይ መታየቷ አጠራጣሪ ሊያደርገው ይችላል ::
የአባይ ወንዝ ግድብ ታላቅ ሀገራዊ ሕልምና ተስፋ  ሰጭ በመሆኑ የዛሬው ብቻ ሳይሆን የመጪውም ትውልድ ታላቅ ሀገራዊ የልማትና የእድገት ራእይ በተግባር የሚገለጥበት ግዙፍ ግድብ  በመሆኑ ሁሉም ኢትዮጵያዊ እጅ ለእጅ ተያይዞ ለግድቡ ፍፃሜ መነሳት ይኖርበታል ፡፡
Filed in: Amharic