>

ተፍጻሜተ ስብከት?!? (ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም)

ተፍጻሜተ ስብከት?!?

ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም
በመጀመሪያ ስለጠቅላይ ሚኒስትሩ ትንሽ ልናገር፤ በሥልጣን ወንበሩ ላይ ሲወጣ ሕግንና ሰይፍን በመጨበጥ ፋንታ ሁለቱንም ጥሎ መጽሐፍ ቅዱስን አነሣ፤ ስለፍቅርና ስለይቅርታ ሰበከ፤ ጉዳት የለውም፤ ጥቅምም የለውም፤ምክንያቱም ያንን የኢትዮጵያ ሕዝብ ቢያንስ ለአንድ ሺህ ስድስት መቶ ዓመታት ሰምቶታል፤ ከዚያም በላይ ፈረንጅ ያስተማራቸው ባይሆኑም በሺዎች የሚቆጠሩ ካህናት አሉ፤ በወንጀለኞች ላይ ሕጉንና ሰይፉን ለማንሣት ፈቃደኛ ሳይሆን ብዙ ወራትን አስቆጠረ፤ አዳዲስ ወንጀለኞችም ሲፈለፈሉ ቲያትር እንደሚያይ ሰው እየተመለከተ አለፈው፤ በዚህም ዋና ተዋናይ የሆነውን ጀዋርን አፈራ፤ ዛሬ ጀዋር ልደቱን የሚያህል አጫዋች አገኘ፤ በእንግሊዝኛ አንድ የአነጋገር ፈሊጥ ልጥቀስ፡– a tough nut to crack የማይቆረጠሙ ጥሬ ሆኑበት፤ ስለዚህም የቲያትሩን መጨረሻ አልወደደውም! ቲያትሩን ማየት ሲጀምር ይቺ ባቄላ ቢል ኖሮ ዛሬ አያዝንም ነበር፤ ዛሬ እኔም ከሱ ጋር አዝናለሁ፤ ይህ የፍቅርና የይቅርታ ሰው በንዴት ሰይፉን ሊመዝ እያስፈራራ ነው፤ በዚህን ጊዜ ሙፈሪያን በሚኒስትርነትዋ ሳይሆን በመንፈሳዊ ሰውነትዋ ታስፈልገዋለች፣ ካወቀበት!
በ2008 በታተመው አገቱኒ በሚለው መጽሐፌ ስለልደቱ አያሌው እንዲህ ብዬ ነበር፤ ‹‹ለቅንጅት መዳከምና መፍረስ በመጀመሪያ በሩን የከፈተው ልደቱ›› ነው፤ ልደቱ ከቅንጅት ‹‹የመለየቱን አቅዋም ለማጠናከር ሲል ለምርጫ ቦርድና ለወያኔ/ኢሕአዴግ ቅንጅትን የመምቻ ሀሳቦችን እየደጋገመ በይፋ በጋዜጣ ይገልጽ›› ነበር፤ ዛሬ ደግሞ ልደቱ አያሌው የዓቢይ አህመድን አገዛዝ ለመጣል በመንገድ ዳር ካገኘው ጓደኛው ጋር እየዛተ ነው፤ ምሕረቱን ይላክለት!
Filed in: Amharic