>

አቶ በረከት ስምኦን በአብይ መርከብ ላይ በጊዜ ተሳፍረው ቢሆን ኖሮ ብዮ አሰብኩና...!!! (ያሬድ ሀይለማርያም)

አቶ በረከት ስምኦን በአብይ መርከብ ላይ በጊዜ ተሳፍረው ቢሆን ኖሮ ብዮ አሰብኩና…!!!

ያሬድ ሀይለማርያም
በእነ አቶ በረከት ስሞን ላይ የእስር ፍርድ መሰጠቱን ስሰማ ግለሰቡ ከመታሰራቸው በፊት በአንድ ቃለ ምልልስ ላይ የተናገሩት ነገር ውል አለብኝ። አቶ በረከት እንደተናገሩት ዶ/ር አብይ ጠቅላይነቱን እንደያዙ ሰሞን ለስልጣን አጭተዋቸው እንደነበር እና እሳቸውም ስላልፈለጉ ሹመቱን ሳይቀበሉ መቅረታቸውን ሲገልጹ ሰምቻለሁ። አርፈው እንደ እነ ወርቅነህ ገበየው እና ሌሎቹ ሹሞች ተደምረው እና ሹመታቸውን ተቀብለው ቢሆን ኖሮ ዛሬ የአንዱ አገር አምባሳደር ሆነ ሲያስለቅሱት የኖሩትን ሕዝብ እና ያጎሳቆሏትን አገር ወክለው በዲፕሎማሲው ፍልሚያ ከተሰለፉት ሹማምንት ተርታ አንዱ ይሆኑ ነበር። በረከት በሙስናው ብቻ ሳይሆን በፈጸሙትም የመብት ጥሰት ሊጠየቁ ከሚገባቸው የመንግስት ተሿሚዎች አንዱ ስለሆኑ የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ከፈጸሙት ጥፋት አንጻር አይበዛባቸው ይሆናል። ይሁንና የእዚህች አገር የፍትህ ሥርዓት ዛሬም የፖለቲካው ምርኮኛ ስለሆነ መደመር ያለመከሰስ ዋስትናን ወይም ከለላን የሚያሰጥ መሆኑን ግን ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። ይህን ለማየት ከበረከት እኩል ወይም የበለጠ ወንጀል ፈጽመው የመደመሩ ፍልስፍና ዋና አቀንቃኝ በመሆናቸው እና በአብይ መርከብ ቀድመው በመሳፈራቸው ብቻ በሹመት ላይ ሹመት እየተጨመረላቸው እና ማንም ሳይነካቸው የሚንጎማለሉ ባለስልጣናትን በገፍ መጥራት ይቻላል።
እንግዲህ ኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካ እስረኛ የሆነችው ‘ፍትሕ’ ከታሰረችበት ነጻ እስክትወጣ ድረስ ነገራችን ሁሉ የእምቧይ፤ የእምቧይ ካብ ሆኖ መቀጠሉ አይቀሬ ነው። ፍትህ ነጻ ትውጣ!
Filed in: Amharic