>

የህወሓት መጫኛ ቀልቀሎ!!! (ሀብታሙ አያሌው)

የህወሓት መጫኛ ቀልቀሎ!!!

ሀብታሙ አያሌው
የህወሓት ነገር መጫኛ ቀልቀሎ –  ቀልቀሎ መጫኛ ሆኗል። “ህገ መንግስቱ ይከበር”  የሚል መግለጫ አንብባ የመጨረሻው ፊደል ከንፈሯ ላይ እያለ  ህገ መንግስቱን ለመጣስ ያደረገችውን ዝግጅት የሚገልፅ ሌላ መግለጫ ታነብባለች።
“ህገ መንግስቱን በማሻሻል የስልጣን ዘመንን ማራዘም የሚፈቅድ  አንቀፅ የለም”  የሚል የትርጉም ትንታኔ ሰጥታ ሳምንት ሳይሞላት የራሷ ህገ መንግስት በግልፅ የደነገገውን ህግ ጥሳ  ምርጫ አደርጋለሁ የሚል የቀረርቶ መግለጫ ታወጣለች።  በየትኛው ህግ ?  በየትኛው ህገ መንግስታዊ አንቀፅ ነው ክልሎች የምርጫን ጉዳይ በራሳቸው ይወስናሉ የሚለው ???   ለዚህ ጥያቄ ምላሽ የላትም።
የህወሓት እና የኦነግ የስምምነት ሰነድ የሆነው ህገ መንግስት አንቀፅ  102  እንዲህ ይላል …
 አንቀፅ  102
    1.በፌደራል እና  በክልሎች ነፃ እና ትክክለኛ ምርጫ በገለልተኛ እንዲካሄድ  እንዲካሄድ ከማንኛውም  ተፅዕኖ ነፃ የሆነ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ይቋቋማል
     2. የቦርዱ አባላት በጠቅላይ ሚንስትሩ አቅራቢነት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይሾማሉ ዝርዝሩ  በህግ ይወሰናል።
ህገ መንግስቴ ይከበር የምትለው ህወሓት ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እውቅና ውጪ ምርጫ አድርጋለሁ ስትል የራሷን ህገ መንግስት  በመጣስ ህገ ወጥ ትሆናለች።
ለገጠመን የፖለቲካና ማህበራዊ ቀውስም ሆነ ለደረስንበት የኢኮኖሚ ውድቀት  አልፋና ኦሜጋው እራሱ ህገ መንግስቱ ነው ስንል  አልሰማ ያለችው ህወሓት ጊዜ  እንደ ቂጣ ሲገለበጥባት በራሷ ህገ መንግስት ታንቃ እያጣጣረች ነው።
                              *   *   *
ሌላው የህገ መንግስት ወለፈንዲ
ገዥው ፓርቲ ብልፅግና በተመሳሳይ የቀውሱ ዋነኛ ምክንያት የሆነው ህገ መንግስት ከቀውሱ የመውጫ የመፍትሄ መንገድ ነው ብሎ የሌለ አንቀፅ ፍለጋ እየባዘነ ነው።
መንግስት እና የመንግስት ደጋፊ ተቃዋሚ ፓርቲ  ከቀውስ የምንወጣው  “በሕገ መንግስት ትርጉም ” ነው የሚል አቋም ላይ ተቸክለዋል።  በሌላ በኩል ህገ መንግስቱ የቀውሱ ምክንያት ነው፤  አገራዊ ከቀውስ የመውጫ መንገድ መፈለግ ያለብን በውይይት በድርድ እንጂ ቀውሱን ካመጣብን ህገ መንግስት መፍትሄ መፈለግ ሌላ ቀውስ መጥመቅ ነው ይላሉ።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ አቶ ማሞ ምህርቱ  Ethiopia insight ላይ ዘርዘር አድርጎ እንደጻፈው የትጉም ስራውን ከላይ የሚቆጣጠረው  በህገ መንግስቱ አንቀጵ 1እና 2 መሠረት የፌዴሬሽን ምክር ቤት ነው።
ስንታገል የኖርነው ደግሞ ይሄንን አደገኛ ቅርቃር ነበር።  ህገ መንግስት መተርጎም የሚገባው ነፃ ፍርድ ቤት ሊሆን ሲገባ በእኛ አገር የፖለቲካው አካል ፌደሬሽን ምክር ቤት ነው።
በአዋጅ ቁጥር 798/2005አንቀጽ 15/ሀ መሠረት ደግሞ የህገመንግስት አጣሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ የምትሆነው ደግሞ ይህው የህወሓት እና የኦነግ “ህገመንግስቱን “ሲፃፍ ከአርቃቂዎቹ አንዷ የነበረችው  በቅርቡ ጠቅላይ ሚንስትር አብይ  ሹመት የሰጣት  የጠቅላይ ፍርድቤት ፕሬዘዳንት ዳኛ መዓዛ እሸናፊ ናት።
ፌዴሬሽን ምክርቤቱ የበላይ ሆኖ የሚቆጣጠረው የጭልፊትና የቀብሮ ችሎት ማለት ነው።
አርቲስት ፋሲል ደሞዝን ጠቅሶ ጠበቃና የህግ አማካሪ ዶክተር ፍፁም አቻምየለህ  እንደፃፈው …  ነገሩ ሁሉ…
“ዳኛውም ዝንጀሮ መፋረጃው ገደል
 ከየት ላይ ተቁሞ ይነገራል በደል?።”
                        *    *      *
ምክረ ሃሳብ
                          *
በአገራችን ከባድ የፖለቲካ ቀውስ ተፈጥሯል።  የቀውሱ መነሻ እና መድረሻ በህገ መንግስቱ ምዕራፍ ሦስት ላይ ያሉ ዋነኛ የኦነግና የህወሓት ትብታቦች ናቸው።  27 ዓመታት ትግል የተደረገበት መስዋዕትነት የተከፈለበት ዋነኛ ምክንያት ይህ የፖለቲካ ሰነድ  በህዝብ በፀደቀ ህገ መንግስት ለመቀየር እንጂ  የስልጣን ዘመን ለማስረዘም ማሻሻያ አንቀፅ እንዲጨመር አልነበረም።
አሁን ሁሉም ነገር ለይቶለታል  ይህ ህገ መንግስት እየተባለ የሚጠራው የፖለቲካ መጫወቻ  ሰነድ ገዥውንም ህወሓትንም አልፎ ተርፎ “አንድ ፊደል ቢቀነስ እንጫረሳለን ያለው ጃዋርንም”  ቅርቃር ውስጥ ከትቷቸዋ።
ታዲያ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በእርግጥ ከስልጣናቸው በላይ ኢትዮጵያን ከወደዱ ለአንድ ክልል ብለን ህገ መንግስት አናሻሽልም ሲሉ ከርመው ስልጣናቸውን ለማስረዘም ማሻሻያ ዘዴ ፍለጋ ከሚባዝኑ ለምን ህገ መንግስቱ ለገባንበት ቀውስ መፍትሔ የለውም ህገ መንግስቱ ይታገድ ብለው በዚህ ቆራጥ አቋም ሁላችንንም ከጎናቸው አሰልፈው
የኢትዮጵያውያን የቃልኪዳን አዲስ ህገ መንግስት እንዲዘጋጅ ቁርጥ ያለ አቋም አይዙም ???
የሞት እንቅልፍ ውስጥ ያለው አዴፓ (አማራ ብልፅግና) ለህዝቤ የገባሁት ቃል ህገ መንግስት ይሻሻላል ያልኩት የምወክለውን የአማራ ክልልን ህዝብ ጥያቄ ለመመለስ እንጂ ስልጣን ለማራዘም ብቻ አይደለም ብሎ የማሻሻያ ሃሳቡን ይዞ አይቀርብም ???
ገምት ካልከኝ
ግምት ነው የቢሆናል ግምት !!
ህወሓት በአቋሟ ፀንታ ምርጫ አደርጋለሁ ብላ ድርቅ ካለች  ለምርጫ ቦርድ መፃፏ አይቀርም።  ከዚያም ብልፅግና ያልሆነ ጣጣ ውስጥ ላለመግባት ኳስ በመሬት ብሎ ምርጫ ቦርድ በልዩ ሁኔታ እንዲፈቅድ ትዕዛዝ ይሰጣል።  እናም ህወሓት፣ ባይቶና፣ ምናልባት አረናም ተሳትፎ ምናልባት ምናልባት እነ አወሉ ደፍረው መቀሌ ከሄዱ እነሱም ተሳትፈው ምርጫ ተደረገ ይባልና ህወሓት መንግስት ሆና ትቀጥላለች።  የሞተው አዴፓ (አማራ ብልፅግና)  ኦነግና ህወሓት መቃብሩ ላይ የአበባ ጉንጉን ያስቀምጡለታል።
Filed in: Amharic