>

እናሸንፋለንና እናቸንፋለን! (ያሬድ ጥበቡ)

እናሸንፋለንና እናቸንፋለን!

ያሬድ ጥበቡ
* …መኢሶን ለደርጉ ሂሳዊ ድጋፍ በመስጠት በሚገኘው የፖለቲካ ምህዳር ህዝቡን አንቅተን ፣ አደራጅተንና አስታጥቀን ወደነፃነቱ እንመራዋለን ብሎ ሲያስብ፣ ኢህአፓ በበኩሉ ደርግ የተሰኘው የምርጥ መኮንኖች ቡድን ወደጦር ካምፑ እንዲመለስ በማስገደድ በምትኩ ከተደራጀው ህዝብ የተውጣጣ ጊዜያዊ ህዝባዊ መንግስት በመመስረት ወደ ህዝባዊ መንግስት ምስረታ መሄድ የተሻለው መንገድ ነው ብሎ ያምን ነበር..
*   *    *
 ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢያንስ ሁለት ጊዜ በ”እናሸንፋለንና እናቸንፋለን የትጫረሰትውልድ ” ሲሉ አዳምጫለሁ። በእውን ግን ባልረባ የእናሸንፋለንና እናቸንፋለን ልዩነት እርስ በርስ የተጫረሰ ትውልድ ነበርን? በፍፁም አልነበረም፣ ታዲያ የክሱ መንስኤ ምን ይሆን?
ነገሩ እንዲህ ነው ። መነሻም አለው። እናሸንፋለንና እናቸንፋለን በራሳቸው የልዩነት ምክንያቶች አልነበሩም። የጎራ ወይም የፖለቲካ ዘር መለያ እንጂ። ከሁለቱም ቃላት በተጨማሪ ሌሎችም ዘር መለያዎች ነበሩ። ለምሳሌ ወዛደርና ላብአደር፣ ወይም ተራማጅና አብዮተኛ ወዘተ ወዘተ። እናሸንፋለን፣ ወዛደርና ተራማጅ የመኢሶን ተከታዮችን መለያ ቃላት ሲሆኑ፣ እናቸንፋለን፣ ላብአደርና አብዮተኛ የኢህአፓውያን የይለፍ ቃላት ነበሩ ። ትግሬዎች ቅንድባቸው ላይ 11 ቁጥር እንደሚበጡት ወይም እንደሚተረተሩት ማለት ነው።
ከነዚህ መለያ ቃላት በስተጀርባ ግን መኢሶንና ኢህአፓ ትልቅ የስትራተጂ ባይሆንም የታክቲክ ወይም ስልት ልዩነቶች ነበራቸው። ብዙውን ጊዜ ደግሞ የፖለቲካ ልዩነት በረጅም ጊዜ ግብ ሳይሆን በአካሄድ ስልት ላይ የሚያተኩር መሆኑ በኢትዮጵያ አልተጀመረም። መኢሶን ለደርጉ ሂሳዊ ድጋፍ በመስጠት በሚገኘው የፖለቲካ ምህዳር ህዝቡን አንቅተን ፣ አደራጅተንና አስታጥቀን ወደነፃነቱ እንመራዋለን ብሎ ሲያስብ፣ ኢህአፓ በበኩሉ ደርግ የተሰኘው የምርጥ መኮንኖች ቡድን ወደጦር ካምፑ እንዲመለስ በማስገደድ በምትኩ ከተደራጀው ህዝብ የተውጣጣ ጊዜያዊ ህዝባዊ መንግስት በመመስረት ወደ ህዝባዊ መንግስት ምስረታ መሄድ የተሻለው መንገድ ነው ብሎ ያምን ነበር ። ይህ ልዩነት ቤቲና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሊያሳምኑን እንደሞከሩት ትርጉም የለሽና እርባናቢስ አልነበረም። በተለይ ከዘውድ አገዛዝ ጨለማ በመውጣት ላይ በነበረና የፖለቲካ ድርጅትም ሆነ ልምድ ባልነበረበት ሃገር ውስጥ፣ እነዚህ ልዩነቶች ገንነው መውጣታቸው ሊያስገርም አይገባም።
ስህተቱም የስልት ልዩነት መነሳቱ ሳይሆን፣ ልዩነቱ የተያዘበት መንገድ ነው። የኢህአፓ መሪዎች ይህን አቋም የያዙት አስበው ተጨንቀውበት የተሻለ መንገድ ነው ብለው ስላመኑ ነው ብለው የመኢሶን መሪዎች ለማሰብ አልወደዱም። የኢህአፓ መሪዎችም መኢሶኖች የሚሉት ስልት ውስጥ አርቆ ማስተዋልና ብልጠት አለ ብለው ከማሰላሰል ይልቅ “ባንዳ” ብለው የሂሳዊ ድጋፍ መስመሩን መኮነናቸው ለውይይትና ክርክር ቁጭ ማለት እንዳይቻል አግዷል።
ከዚህ ታሪካዊ ፍፃሜ ተገቢውን ትምህርት ለመውሰድ ባለመቻላችንም፣ ችግሩን የእናሸንፋለንና እናቸንፋለን ቃላት አልባሌ ልዩነት አድርገነው ቁጭ አልን፣ ስለሆነም ሳንማርበት አለፈ። ሆኖም ዛሬም ላለንበት ሁኔታ እጅግ አስፈላጊው ትምህርት ነው ስላቅ ውስጥ የወደቀው። ዛሬም የፖለቲካ ስልት ጥያቄ ጥርሱን አግጦ መጥቷል። የዜግነት ፖለቲካ እናራምዳለን ወይም ኢትዮጵያዊነት መድህናችን ነው ብለው የሚያምኑት መሃል “አቢይን ይዘን እናልቅስ” የሚለው የመኢሶኑ አይነት ግን የተለየ የመንግስታዊ ድጋፍ መስመር ሲቀነቀን፣ በአንፃሩ “ህገመንግስታዊ መሻሻልና ይህንንም ማስፈፀም የሚችል የሽግግር መንግስት አስፈላጊነት” እሳቤ ይቀነቀናል። የፊተኛው የአቢይን ይዘን መስመር በቀደምት ምሁራን በእነ ፕሮፌሰር መስፍን፣ ዶክተር ዳኛቸውና ኢሳት አዲስአበባ ወዘተ ሲቀነቀን፣ የኋለኛው መስመር ደግሞ በወጣት የሚዲያ ሰዎችና የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች እንደ ርእዮት ሚዲያ፣ ኢትዮጲስ ጋዜጣ ወዘተ በመሳሰሉ ይቀነቀናል።
የሚያሳዝነው አንዱ ሌላውን በማክበር፣ ሌላው የሚለውም ውስጥ ለሃገር የሚጠቅም እሳቤ ሊኖር እንደሚችል ከመፈተሽ ይልቅ፣ እልህና የማጠልሸት አካሄድ ይስተዋላል ። እነሲሳይ አጌና የጀመሩት ቴዎድሮስ ፀጋዬን በትግሬነቱ የማጥቃትና ከወያኔ ጋር የማዳበል ክስ ከሌላውም ወገን ተመጣጣኝ ምላሽ የሚጠይቅ መስሎ ስለታየ፣ ከመወያየት ይልቅ ወደመካረር መሄዱ የማይቀር እዳ ሆኗል።
እዚህ ላይ ቴዎድሮስ ፀጋዬን ከቢሮው እስከማጀቱ ለማወቅ እድል ያገኘሁ ሰው በመሆኔ፣ ውሎውንና ትዳሩን ስላየሁ፣ ቴዲ በኢትዮጵያ ፍቅር ያረረ አርበኛ እንጂ ማንነቱን መነሻ አድርገው ሊያጠቁት እንዳሰቡት ሃይሎች አባባል የወያኔ ደጋፊና ቅምጥ አይደለም። የህገመንግስቱ ድክመት ዛሬ የተንሰራፋውን አበሳ ያመጣ መሆኑን የሚያቀርበውን ሙግት መግጠም ያቃታቸው ሰነፎች ክስ መሆኑን ህዝቡ ሊረዳ ይገባል እላለሁ።
ከየካቲቱ ትውልድ ግን የዛሬው ትውልድ መማር የነበረበት ሆደሰፊነትን፣ በሃሳብ መለያየት ሃጢያት አለመሆኑን፣ የተለየ ሃሳብ ያለውን ሰውም በክብርና ወንድማማችነት ማየት ተገቢ መሆኑን ነው። አሁንም ይህን ትምህርት ለመቅሰም የረፈደ አይመስለኝም። ይቻላል። ትምህርቱም ሊቀሰም የሚችለው፣ ያን ትውልድ ለማሳነስ በሚደረጉ አጉል ብልጠቶች ሳይሆን ለትውልዱም የሚገባውን ክብር ሰጥቶ፣ ከድክመቱ ለመማር በሚደረግ ቅን ጥረት እንጂ ነው። የነገ ሰው ይበለን አያ!
Filed in: Amharic