>

የሰኔ ሟርት የሐኪም ጥናት....!!!  ( ከማዕበል ፈጠነ )

የሰኔ ሟርት የሐኪም ጥናት….!!!

 ከማዕበል ፈጠነ
ፖለቲከኛች ለወንበር: ወንዘኞች ለመንደር ወገባቸውን ታጥቀው በሚፋለሙባት ሀገር ወረርሽኙ ከ እስከ የሚል ቀመር የለውም። በተለይ  አሁን በዓለም ዐቀፍ ደረጃ የፍሥሓ  ዘመን አልፎ የመከራው ዘመን ተበግሯል። ይህ እኩይ ዘመን የወለዳቸው  አፈ ጮሌዎች ደግሞ በዐይናማ ጠቢባን ዐይን ላይ የጨለማ መጋረጃ ጋርደውባቸዋል። 
* በኢትዮጵያም ያለው ተመሳሳይ ነው። ትውልዱ መድኃኒት የሚጠብቀው ከነጮች ነው። የወረርሽኙን ወርም  የሚያውቀው በነጮች አእምሮ ነው።  የኢትዮጵያ ሕዝብ በነጮች ፍልስፍና እስከ ተመራ ድረስ  በዚች ዓለም ተስፋ ቢስ ሆኖ ይቀጥላል።
አንድ ዶክተር ጥናት ቢጤ አቀረቡ መሰልኝ?። መሰለኝ ያልሁት ወድጄ አይደለም። የምር ራድዮ መስማት: ተሌቪዥን ማየት ደመኛዬ ስለሆነ ነው። ይኸውም ሊታወቅ የትናንቱን የቄስ መዝገቡንና የሊቀ ሊቃውንት ስሙርን የሚዲያ ውዝግብ አላየሁም። ከfb አይቼ ለምወደው የቀለም ጓደኛዬ ደውዬ ጭብጡን  ተረዳሁ። ከጓደኛዬ ጋር ቅኔ ቤት አብረን ተምረናል። ዛሬ እሱ በዚህ በEoTc ውስጥ ያገለግላል። እኔ ሥራ የለኝም። በእርግጥ ምሽት ምሽት የተፈጥሮ ፀሐይን ወደ አድማስ እሸኛለሁ። ጨረቃን በአበቅቴ ክፍለ ብርሃን ከመስዕ  እቀበላለሁ። የፍሥሓዬ ቁንጮ የፀሐይ ሙቀት የጨረቃ ድምቀት ነው።  ለመሆኑ በዚች ዓለም  በእኒህ ፍጥረታት ከመደሰት የበለጠ  ደስታ ይኖር ይሆን? እኔ እንጃ!:: ባለ ብዕሩ ደራሲ  ባለ ድግሩ ሐራሲ ባለ ቅኔው ሐያሲ ውስጣዊ  ፍሥሓን ከእኒህ እንደሚቀዳ አልጠራጠርም። ለእኔም  ከዚህ ያለፈ ፍሥሓ የለኝም። ባይኖረኝም መምህር  ስሙርን  ቀርቤ አውቀዋለሁ። ጥርሱን ነቅሎ ሙጀሌውን መንግሎ  ባደገበት  መንፈሳዊ ቀለም ቀርቶ በዓለማዊ መርሐ ግብር የመሞገት ክሕሎት አለው። በግሉ ተደብቆ ያነባል። ካነበበው  ተነሥቶ ሐሳብ ያፈልቃል።  በባሕርዩ ግን ከሁላችንም ወጣ ይላል። በክርክር ጊዜ  ሐሳቡን  ከናቀው ይስቃል።  ከአመነበት በእውቀት ተመርኩዞ ይሞግታል። እባብ መሰል: መርፌ ቀመስ ዐይኑን ወደ ጎን እያጨለቀ ይሞግታል። ሙግቱ መቼትና ጭብጥ አለው።  በዐጽመ ታሪክ ክልስ ፕ/ር ባሕሩ ዘውዴ ሲሆን በትክክል ትችቱ  የሊቅ መዶሻ ነው።  ባንድ ዘመን  ደግሞ እንደ  ሰደፍ ወፍ ተናዳፊ ሆኖ ነበር። ካነበበውም ሆነ ከመረመረው ተነሥቶ ላብ በላብ  እስኪሆን መከራከርን እንደአመል አድርጎ ይዞት ነበር።
በሌላም ከኩል በግሌ የማንደንቅለት ሰብእና አለኝ። ልናዘዘውና ወደ ርእሴ ልምጣ!!
…ስሙር  መጽሐፈ ሊቃውንት በዳግማዊ ምኒልክ መታሰቢያ በታዕካ ነገሥት በአታ ለማርያም ገዳም የአብነት ትምህርት ቤት በሥነ ሥርዐት የተማረ የሊቅ መምህር ነው። ነገር ግን “ሊቀ ሊቃውንት” ሲሉት ይቃወማል።   ትልቁ ስም ለእኔ አይገባም  ከማለቱ ተነሥቼ ሳየው የትናንትናው ሚዛን ለስሙር አይሆንም ። በግሌ የቤተ መቅደሱ ሚዛን በሌለበት ሚዲያ ለምዘና የሚቀርቡ ምሁራንን ሳይ አዝናለሁ። እርግጥ ነው ዝና ፈላጊዎች በቴሌቪዥን መታየትን የትልቅነት ቁንጮ አርገው እንደሚወስዱት አውቃለሁ። በግሌ ግን  ከሚዲያ  እይታ ርቆ ሥራዬውን ብቻ  ለሚሠራ ሊቅ አክብሮት አለኝ። እኔም አንዳንድ ሊቆች ሚዲያዎችን እንደ ቡዳ ዐይን ሲፈሩ አይቼ  ከሕይወታቸው ተምሬአለሁ።
..የሆነ ሆኖ  መምህር ስሙር  ትናንት ከርእሰ ጉዳዩ በወጣ ሚዛን መርሐ ግብር ላይ   “እምተናግሮ ይኄይስ አርምሞ” እንዳለ ለመስማት ተሌቪዥን አላየሁም።
“ወደ ርእሴ እየመጣሁ ወጣሁ ነው!!።
..የጤና ባለሙያዎች
 “በሰኔ መጨረሻ በሐምሌ መጀመሪያ ወረርሽኙ እንደ ገብስ ምርቅ በሀገር ይነሰነሳል። ይህም  በጥናት ተረጋግጧል።
የሰኔ መጨረሻ የወረርሽ ወር ነው  ያሉት የጤና ዶክተር ሰኔን  ከምን አንጻር መረመሩት። ከጉሙ ጋር ከሆነ ወረርሽኑ በንክኪ እንጂ በጉም ጢስ አይተላለፍም።  ሐምሌም የዝናም ወቅት ነው። ወረርሽኙ ደግሞ በዝናም አይዛመትም።  ነጮች የተወረሩት ኮሮና በተከሠተ በስድስተኛው  ወር ነው። እኛም በስድስተኛው ወር በሰኔ እንወሩራለን  ከሚል  የነጮች ወር  ተነሥቶ  ከሆነ  የጥናቱ ጭብጥ የሰኔው ወር ወረርሽኝ ለሟርት  ይቀርባል። ከዚች ቅጽበት ጀምሮ መጠንቅቅ እንጂ በነጮች ቀመር ለሰኔ ወር ቸነፈርን  መቅጠር ከሕዝቡ ሥነ ልቦና አንጻር ጥሩ አይመጣም።
.. በግሌ የነጮችን ሳይንሳዊ ምርምር አምናለሁ። በኮሮና በኩል ግን  ከነጮች ጥናት ተነሥቶ ስድስተኛውን ወር ቆጥሮ ወረርሽኝን መተንተን በኢትዮጵያ አይቻልም ባይ ነኝ።
..ሰኔ በሀገራችን የዘር ወቅት ነው። ይህ በሀገራዊ ጥበብ መጠናት አለበት። ዘር ወደ አፈር እንደሚወርድ ሁሉ ሰውም አፈር ነውና ወደ አፈር ይመለሳል ባዮች ካሉ በቀመር ቀምረው የሰኔን ወር  በሀገረኛ ጥበብ ቢያጠኑት ለማመን ይዳዳኝ ይሆናል።
.. ወደ ኋላም ተመልሰው በእኛ ሀገር ኮሮና ሲገባ ወሩ መጋቢት ነበር። መጋቢት ደግሞ የሥነ ፍጥረት እንጂ የሞት ወር አልነበረም። የመጋቢት ወር በራሱ   ሐመል የሚባል  ኮከብ የሚወጣበት ወር ነው። ሐመል ደግሞ ግብሩ የአውራ በግ ሥራ ነው። አውራ በግ  ከበግ በግ እየተንጠላጠለ በጎች ዘር እንዲተኩ ግልገል እንዲያስወልዱ ያደርጋል። ስለዚህ በመጋቢት ፍጥረታት ይበዛሉ እንጂ አይሞቱም። ለዚህም ቀመር አለው ብሎ የሚመራመር ሊቅ  ሲፈጠር በሰኔ ወር መጨረሻ  ሞት በመጋቢት  ፍጥረት እያልን ወሮችን እናመልክ ይሆናል።
በቀር  በቀመር ቀምሮ  ከነጮች ላቅ ብሎ ስለ ኢትዮጵያ ወሮች የሚፈላሰፍ ሊቅ  እስከሌለ ድረስ ወረርሽኙ መቼ እንደሚያገረሽ መቼ እንደሚሸሽ መተንበይ አይቻልም።
እንደ ሀገር ካየነው ለሀገር ለወገን የሚሠሩ ሰዎች እጅግ ጥቂቶች ናቸው። ፖለቲከኛች ለወንበር: ወንዘኞች ለመንደር ወገባቸውን ታጥቀው በሚፋለሙባት ሀገር ወረርሽኙ ከ እስከ የሚል ቀመር የለውም። በተለይ  አሁን በዓለም ዐቀፍ ደረጃ የፍሥሓ  ዘመን አልፎ የመከራው ዘመን ተበግሯል። ይህ እኩይ ዘመን የወለዳቸው  አፈ ጮሌዎች ደግሞ በዐይናማ ጠቢባን ዐይን ላይ የጨለማ መጋረጃ ጋርደውባቸዋል። በኢትዮጵያም ያለው ተመሳሳይ ነው። ትውልዱ መድኃኒት የሚጠብቀው ከነጮች ነው። የወረርሽኙን ወርም  የሚያውቀው በነጮች አእምሮ ነው።  የኢትዮጵያ ሕዝብ በነጮች ፍልስፍና እስከ ተመራ ድረስ  በዚች ዓለም ተስፋ ቢስ ሆኖ ይቀጥላል። የሀገሩን  ጠቢባን ጥበብ መቋደስ አይችሉም።
.. ሰኔ የወረርሽኝ ወር ነው ሲባል ይጨነቃል። ሐምሌ ይብሳል ሲባል ምጥ ይይዘዋል። ወረርሽኙ በእግዚአብሔር  ቸርነት እስኪያልፍ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደ ማርቆስ ወልደ ቀንበር የመከራ ቀንበር ተሸክሞ እግሩ ወደ ጉድጓድ ይወርዳል።
.. ነጮች ሆይ! ስለ ኢትዮጵያ አታስቡ።  ቸር አምላክ አለን!!
ሰኔ በፍሥሓ ያልፋል። ሐምሌም ያው ነው። ከክረምቱ ክብደት በቀር ሐምሌም የእኛ ቀን ነው። ከሞትጋር ቀጠሮ የለንም።
Filed in: Amharic