>
5:13 pm - Friday April 19, 8858

ፖለቲካዊ ፊስቱላ በነጃዋር ቱልቱላ! (ዳግማዊ ጉዱ ካሣ)

ፖለቲካዊ ፊስቱላ በነጃዋር ቱልቱላ!

 

ዳግማዊ ጉዱ ካሣ

 

ይሄ የሥልጣን አምሮት እንዴት አድርጎ ከሰውነት ተራ እንደሚያስወጣ ሰሞኑን በነጃዋርና ልደቱ ንግግር ታዘብኩ፡፡ ኢትዮጵያውያን በርግጥም ከልሂቅ እስከ ደቂቅ በጭንቅላታቸው ላይ ትንንሽ ዘውድ ደፍተው በቅዠት ዓለም ንግሥና ውስጥ እንደሚኖሩ በቀልድ መልክ የሚነገረው ትዝ አለኝ፡፡ ሌላው ቀርቶ ማንም ጋለሞታና የትምህርትና የዕውቀት በሮች የተከረቸሙበት ማይም እረኛ ሁላ እየተነሣ “ስምንተኛው ንጉሠ ነገሥት ሆኜ ተቀብቻለሁ”፣ “ማርያም ተገልጣ የቆሎ ጓደኛዋ ያደረገችኝ ንግሥተ ነገሥት እህተ ማርያም ነኝ” ሲሉን በማያፍሩባትና ሃይ ባይም ባጡባት ምድራችን የማንሰማው ተዓምር ላይኖረን በፈጣሪ ተፈርዶብናል፡፡ መጨረሻውን ዝም ብሎ ማየት ነው፡፡ 

ወደጥራዝ-ነጠቅ ዕውቀቴ ገባ ልበልና ጥቂት ነገር ልበል፡፡ በሥነ ልቦና የትምህርት ዘርፍ Id ego እና superego የሚባሉ የአእምሮ ትንተና ሥልቶች አሉ፡፡ የአንድ ሰው አእምሮ በተፈጥሮ፣ በአስተዳደግና በባህል፣ በትምህርትና በሃይማኖት … ለዓመታት ታሽቶ ሰውዬው ለአቅመ ኃላፊነትና ለጉልምስና ሲደርስ ሆኖ የምናየውን፣ ሲያደርግ የምናስተውለውንና ኖሮት የምንታዘበውን ሁሉ እንደሚሆን ይታመናል፡፡ እነዚህ ሦስት የሥነ ልቦናዊ ጤንነትን መለኪያ መንገዶች ከእውነትና ከስሜት ጋር አለመጣረሳቸውን የምናስተውለው እንግዲህ ሰውዬው በሚኖረው ማኅበረሰብኣዊና እያንዳንዱ ምናምናዊ ግንኙነቱ ላይ ተመሥርተን ነው (ቤተሰባዊ፣ ጓደኛዊ፣ ኢኮኖሚያዊ… ማለቴ ነው)፡፡ ይሉኝታ፣ ሀፍረት፣ ፍትሃዊነት፣ ሃቀኝነት፣ ራስ ወዳድነት፣ ጭፍን ፍርድ፣ ስግብግብነት፣ ሥልጣን ወዳድነት፣ ሴሰኝነት፣ ዘሟችነት፣ አንደበተ ርቱዕነት፣ ሃይማኖትን አክባሪነት፣ ትዳር አክባሪነት፣ እንደልቡነት፣ ሌብነት፣ ዋሾነት፣ ጉረኝነት፣ ነውረኝነት፣ ቃል አክባሪነት፣ ቸርነት፣ ንፉግነት፣ ገንዘብ ወዳድነት፣ ከሃዲነት፣ እምነት ጠባቂነት፣ አስመሳይነት፣ ስሜታዊነት፣ ስክነት፣ ጡዘት፣ ግልብነት፣ አስተዋይነት፣ ወዘተ. በአብዛኛው ከነዚህ ሦስት ነገሮች አያያዝና የርስ በርስ ስንስል (ማኔጅመንት) ጋር ይገናኛሉ፡፡  

“ኢድ”ን ያልተቆጣጠረ “ኢጎ” የሰውዬውን “ሱፐርኢጎ” ድራሹን ያጠፋውና ሰውዬው የፊስቱላ ችግር ይገጥመዋል፡፡ የፊስቱላ ችግር ደግሞ በህክምናው ዘርፍ የሚስተዋል የመዋለጃና የመጸዳጃ አካላት መቀላቀል ነው፡፡ አንዲት ሴት ይህን መሰል ችግር ሲደርስባት ሁሉም ነገር ከቁጥጥሯ ይወጣና ምኑን ከምን፣ የትኛውን ከየትኛው እንደምታስቀድም አታውቅም፡፡ ይህ ክስተት ወደ ፖለቲካው ሲገባ አሁን አሁን በግልጥ እንደምናየው ሀገርን ይንጣል፤ የሕዝብን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብር በማወክ ላልተጠበቀ ሰብኣዊ ዕልቂትና ቁሣዊ ውድመት ይዳርጋል፡፡ በዚህ በሽታ የሚመቱ ሰዎች ሥነ ልቦናቸው የተበላሸ እንደመሆኑ እነሱ ለነሱ ሁልጊዜ ትክክል ናቸው፡፡ በተቃራኒው እነሱን የሚቃወም ነው በህመምተኛነት የሚፈረጀው፡፡ እነዚህ ሰዎች በሌላ አገላለጽ የ Illusion ተጠቂዎች ናቸው፡፡ ኢሉዥን ደግሞ በራስ ዓለም የመኖር ምናባዊ (ሚራዣዊ) የአእምሮ መታወክ ውጤት ነው – ለአብነት ጭው ባለ በረሃ ስታቋርጥ ከፊት ለፊትህ ውቅያኖስ ያለ ይመስልህና ስትደርስበት ግን የለም – የነጃዋር ዓይነት የብዥታ ዓለምም እንደዚሁ ነው … ፡፡ እንደነዚህ ያሉ ሰዎች የፖለቲካውንና የኢኮኖሚውን ልጓሞች ሲይዙ በሀገር ደረጃ ምን ዓይነት ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚችል በተለይ ካለፉት 40 እና 50 ዓመታት ወዲህ በተግባር እያየን ነው፡፡ የነዚህን ዓይነት ሰዎች ለማከም ሂደቱ Disillusion ይባላል፡፡ ግን ቀላል አይደለም፡፡ ምናልባት የሚያዋጣው ልጆችን ስናሳድግ በአግባቡ ቢሆን ቀስ በቀስ ልንስተካከል እንችላለን፡፡ እንደማስበው ደርግ የጀመረው ሁሉንም ነገር የማጥፋትና ከዜሮ የመጀመር አባዜ ሞራላችንንም፣ ሃይማኖታችንንም፣ ግብረ ገብነታችንንም … አጥፍቶ ባዶ ሳያደርገን አልቀረም፡፡ በሰው አምሳል የምንገኝ አሻንጉሊቶች ሆነናል፡፡

በዚህ በጠቀስኩት የሥነ ልቦና ደዌ ያልተመታ ሰው ለማግኘት በመሠረቱ ቢቸግርም ሰሞነኞቹ ጃዋርና ልደቱ ግን ለዚህ ጽሑፌ መነሻ የሆኑኝ ቀዳሚና ተከታይ የሌላቸው ቀንዳም ማነው ቀንደኛ የሥነ ልቦና ህመም ሰለባዎች ናቸው እላለሁ፡፡ አሳሳቢው ደግሞ ተከታይ አለማጣታቸው ነው፡፡

የዓለምን ፖለቲካ በእጁ ቁጥጥር ሥር እንዳደረገና ከሰማይ በታች የማያማክረው አካል እንደሌለ በአንድምታውም የገቢው መጠን በዚያው ልክ መሆኑን ለማጠየቅ በትዕቢት ስለራሱ የሚደሰኩረው ጃዋር እንዳለው “ከሰኔ 30/2013 በኋላ መከላከያውም አይታዘዝም፤ ፖሊስም አይታዘዝም፤ ሕዝብም አይታዘዝም፡፡…”  ይልና  “ስለዚህ መንግሥት ቅቡልነቱን ለማረጋገጥ አንድ ነገር ያድርግ…” በማለት ምርጫው እንዲካሄድ ወይም እርሱ ከጠቀሰው ቀነ ገደብ በኋላ የኢትዮጵያ ጠ/ሚኒስትር ራሱ ጃዋር መሀመድ እንዲሆን አኳኋኑ በሚያሳብቅ ሁኔታ አሁን ከምናየውና ከምንሰማው ዓለማቀፋዊም ሆነ ሀገራዊ  ነባራዊ እውነት አንዱም አጥር ሳያግደው ይወተውታል፡፡ የዘረመል ወይም የወንዴና ሴቴ ዕንቁላሎች ጥምረት ችግር ያለበት ሌላው ጭንጋፍ ልደቱ ሆዬም ያን ሁሉ የክህደት ሥራውን ረስቶ “እንዲያውም ከመስከረም በፊት ችግር ሊፈጠር ይችላል፤ ስለዚህ የሽግግር መንግሥት መፈጠር አለበት ወይም ምርጫው መደረግ አለበት” ይላል – በትክክል ካልጠቀስኩ ይቅርታ – በነገራችን ላይ እንደነዚህ ዓይነት ጽንሶች በጠማማ ቀን የሚፈጠሩ ናቸው – በሃይማኖታዊ አባባል ‹የሰንበት ጽንስ!› ይባላሉ፤ ኮከባቸው እጅግ ጽልመታዊና ለአጋንንቱ ዓለም የቀረበ ነው፤ በሣይንስም የኤክስና ዋይ ክሮሞዞማዊ የተመጣጥኖ ችግር (disproportion) እንዳለባቸው ይታመናል፡፡ እነዚህ የአእምሮ-ሥውራን ልጆች ናቸው እንግዲህ ወጉ ደርሷቸው ስለኛ ዕጣ ፋንታ እንዲህ የሚደነፉት፡፡ ጥፋቱ የነሱ አይደለም፤ “ዐዋቂና ደጋግ ሰዎች ሲደበቁና ሲፈሩ ዐውሬዎች ከተደበቁበት ዋሻ ወጥተው የመንግሥትን ሥልጣን ይይዙና ሕዝብን ያሰቃያሉ” ይል ነበር ‹ሌኒን›፡፡

ማን ሊስምሽ ታሞጠሙጭ ይባላል፡፡ ሲጀመር ከመስከረም በፊትም ሆነ በኋላ መከላከያው መንግሥት ለሚባለው ሌላው ጉልበተኛ አልታዘዝም ሊል የሚችልበትን ፖለቲካዊ ልማድ ሳስበው “ልጆቹ ለይቶላው አበዱ እንዴ?” አስብሎኛል፡፡ እነዚህ ዕብዶች ስለሌትጅሜሲ የሚያውቁት ነገርም እንደሌለ ተረድቻለሁ፡፡ እነሱ ራሳቸውንስ እንደምን ቆጥረው ይሆን? እነሱ ራሳቸው ቅቡልነት (ሌጂትሜሲ) አላቸው ለመሆኑ? ማን ሰጥቷቸው? በዚህች አገር የፖለቲካ ሕይወትስ እንዲህ ያለ ሰዓትና ቀን ተቆርጦለት “ከዚህ ደቂቃ በኋላ ሌጂትሜሲው ያበቃልና…”ተብሎ የተደነገገለት መንግሥትና ተቋም ኖሮን ያውቅ ይሆን ወይንስ እነልደቱ አሁን ሊፈጥሩልን ነው? ያባቴ አምላክ ይሌጂትምሳቸውና በዚህች አገር የትኛው መንግሥት ሌጅትሜሲ (ቅቡልነት) ኖሮት ያውቃል?  “ ህገ መንግሥት እኛ ሰጠናችሁ” ይለን የነበረው የአፄው መንግሥት? “አሳደህ በለው ያንን ዐመፀኛ፤… ራስ እንትና፣ ፊታውራሪ እንቶኔ፣ ዤኔራል እገሌ፣ ቢትወደድ እንትና እና ሌሎችም እርምጃ ተወስዶባቸዋል፡፡ የቀብር ሥነ ሥርዓቱም በመንግሥት ተፈጽሟልና ቤተሰብ ሬሣ መጠየቅ አይችልም…” ይለን የነበረው የደርግ መንግሥት? “አማራንና ኦርቶዶክስን ማጥፋት ቀዳሚው አጀንዳችን ነው” ይለን የነበረው የወያኔ መንግሥት? … ኧረ የትኛው መንግሥታችን ነው ቅቡልነት የነበረው? “ራሷ ሄዳ ጅብ-አይበላሽ የከለከሏት ‹ምላስ ሰምበር በሰው ላኩልኝ›” አለች አሉ እመት  ውሮ፡፡ የምን መቀናጣት ነው – የትኛው ወገን እንደሚታጠን ጠፋኝ እንጂ “ለማያቁሽ ታጠኝ” ልል ዳድቶኝ ነበር፡፡ የወያኔን ሌጋሲ አስቀጣይ መሆኑ በግልጽ የሚስተዋለው የአቢይ አጭቤው መንግሥትም ከሌሎቹ የሚለይበት ጎልቶ የሚታይ በጎ ነገር የለውም፤ ያው ነው፡፡ ሕዝብ ያለቀበትንና ብዙ ነገዶች በተለይም አማራው ያልተሳተፈበትን እንደሚባለውም ከተጻፈበት ወረቀትና ብዕር የማይበልጥ ዋጋ ያለውን ህገ መንግሥት ተብዬ እንደሚያስቀጥል አቢይ አዘውትሮ በኩራት መናገሩ ለዚህ አባባል ምስክር ነው፡፡ “ለዚህ ለዚህማ ወያኔስ ምን አለን?” የምንለውም ለዚህ ነው፡፡ ለነገሩ ህገ መንግሥቱም ወያኔና የወያኔ ድጋፍ ያለው ምትኩ ኦነግም ድራሻቸው ሊጠፋና ወደታሪክ መዝገብ ሊወረወሩ ቀኑ ቀርቧል፡፡ ትዕግሥቲ ግበሩ! እንደ ሙሤ የአሠርቱ ትዕዛዛት ህግ ከሰማይ የወረደ ይመስል ማንም ቢሆን ይህን አገር በታኝ የወያኔ ሰነድ “ህገ መንግሥታችን አይነካም!” ቢል በፈጣሪ ቀጭን ትዛዝ አንደበቱ የሚለጎምበትና ኢትዮጵያ የምትነሳበት ጊዜ በፍጥነት እየመጣ ነው፡፡

ነገር ለማሳመር አይደለም፡፡ ጃዋርና ራሷን “እህተ ማርያም” የምትለዋ ተቀጣጣይ ፈንጅ አንድ  ናቸው፡፡ እርሷ ሰሞኑን ታስራለች – በጣም ዘግይቷል እስሯ፡፡ ጃዋር ደግሞ ልክ እንደዚህች እስፊንክስ ሴትዮ ወንጀል እንዲሠራ በአቢይ መንግሥት ዋስትና ተሰጥቶት እንደልቡ የሚንቀሳቀስ ሌላው የወንድ እስፊንክስ ነው፡፡ እንጂ ይህ የሰሞኑ ንግግር ብቻ ጦር ፍርድ ቤት ይገትረው ነበር፡፡ ሰው አልገባውም እንጂ እያለ ያለው እኮ “ቄሮ ሆይ! ወታደር ሆይ! ፖሊስ ሆይ! የምን ኮሮና የምን የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ፣ የምን የምርጫ ጊዜ መራዘም፣ … ምርጫው በታቀደለት ወቅት ካልተደረገ ወጥተህ መንግሥትን ገልብጥና እኔን ሹመኝ” እንደማለት ነው – በእግረ መንገድም ያን አሜሪካ ሆኖ የማትሪክ ፈተና እያሰረቀ በሀገር ሀብትና በትውልድ ዕድሜ (ጊዜ) ይጫወት የነበረውን ዘመን፣ ከዚያም በመቀጠል ቄሮዎችን እየቀሰቀሰ በርካታ የሰው ሕይወትና እጅግ ብዙ ሀብትና ንብረት ያወደመበትን ዘመንም በማስታወስ ሊያስፈራራቸው ፈልጎም ነው – ቀላል የሒሣብ ሥሌት ናት፡፡ ፖለቲከኛ ብዙውን ጊዜ ዕውር ነው – ለነገሩ ጃዋርና ልደቱ ፖለቲከኞች አይደሉም እንጂ፡፡ ተራ የቁጭ-በሉ ቁማርተኞች ናቸው፡፡ ግን ግን ምን ያህል ብንረገም ይሆን ፈጣሪ እነዚህን ደደብ ልጆች የሰጠን? 

የልጆቹ መርዘኛነትና የሥልጣን ፍቅር ገርሞኝ እንዲህ ተብከነከንኩ እንጂ ለአራት ኪሎ ወንበር የሚራኮቱ ሁሉ ዓላማቸውም ሆነ ፍላጎታቸው አንድ መሆኑን አጥቼው አይደለም፡፡ ነገር ግን ህዝብን የሚያጨራርስ እንደዚህ ያለ የለዬለት ዕብደት በሚዲያ ሲተላለፍ ማንም ይሁን ማን ሃይ ሊ(ባ)ል ይገባል፡፡ ልደቱ ደግሞ እባክህን ንግድህን ብቻ አጧጡፍ፡፡ ፖለቲካ ይቅርብህ፤ አያዋጣህም፡፡ የኢትዮጵያን ሕዝብ ከምወድለት ባሕርያቱ አንደኛው የበደሉትን አይረሳም፡፡ ሌላው ይቅር ባይ ነው፡፡ ስለሆነም ልደቱ ተጸጽቶ ይቅርታ ሳይጠይቅና ጥፋቱን ሳያምን ወደፖለቲካው ቢገባ አያተርፍም፡፡ 

በተረፈ አሁን ወቅቱ የጭንቀት ነው፡፡ ከቤት ለመውጣት ጣራና ግድግዳውን ማመን አቅቶን እንዲህ በሃሳብ ስንዋትት፣ ሥራ ቆሞ ማኅበራዊ እንቅስቃሴ ተገድቦ፣ ርሀብና ቸነፈር ከፊታችን ተጋርጦ እያለ ለዚህ ከትያትር ለማያልፍ የውሻሸት ምርጫ ይህን ያህል ቡራከረዩ ማለት ወሸባ የሚያስገባ ሌላ ፖለቲካዊ ኮሮና ነው፤ በፍጹም የጤና አይደለም፡፡ እንዲያውም ከናካቴው ምርጫ አይኑር፤ ይቅርብን፡፡ ለምርጫ የሚመደበውም በጀት ለምንጭ ውኃ ማጎልበቻና ለሀኪም ቤት መገንቢያ ይሁን፡፡ ትያትር ሰልችቶናልና ይህን ነገር የሚመለከታቸው ወገኖች ያስቡበት፤ ኤርትራ ምን ሆነች? ነገር አትጠምዝዙብኝ! “ዴሞክራሲ አያስፈልገንም” እያልኩ አይደለም፡፡ ነገር ግን ዴሞክራሲ እንኳንስ እኛ ድሆቹ አደጉ፣ በለጸጉ የሚባሉት አሜሪካኖቹም አላገኙትም፡፡ ዴሞክራሲ ሳይሆን ጉልበቶ-ክራሲና አዱኛ-ክራሲ ናቸው ዓለማችንን እያንቀጠቀጡ ያሉት፡፡ ዘገምተኛው ትራምፕ በዴሞክራሲ መጣ እንዳትሉና እንዳታስቁኝ ደግሞ፡፡ … የተፈቀደልህን ያህል ብቻ ነው የምትኖረው ወንድሜ፡፡ እዬዬም ሲደላ ነው እህታለም፡፡ ወንዶቹ እንዳሳደሩን የፖለቲካን ቤተስኪያን እንሳለማን እንጂ የኛ መብት በብዙ መንገድ የተገደበ መሆኑን መርሳት የዋህነት ነው፡፡

ግን ግን ከመጪው መስከረም 30 በኋላ ጃዋር አቶሚክ ቦምብ ያፈነዳ ይሆን እንዴ? አነጋገሩ እንደዚያ ነው የሚመስል፡፡ እናንተዬ ፈራሁ… ለነገሩ ዕድሜ ለኮሮና … እግዜር አይበለውና አሁን 140 የደረሰው ኮሮና ያኔ 140000 ይደርስና ጃዋርን መኝታ ቤቱ ውስጥ በፍርሀት ሰንሰለት ይጠፈንግልን ይሆናል፡፡ ወይ ጃዋር! “ካላበዱ ወይ ካልነገዱ የልብ አይገኝም” መባሉ ለካንስ ለዜህ ኖሯል፡፡ ዱሮ በደርግ ዘመን “የአጋርፋ ገበሬ ማኅበር የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምን አስጠነቀቀ!” የሚል ዜና ሰምተን ስቀን ነበር – መቼ መሰላችሁ – አሜሪካ ሊቢያን ሁለት ከተሞች ላይ በአየር ደብድባ አንዷ የጋዳፊ ሴት ልጅ በሞተችበት ወቅት ነው፡፡ “ጃዋርና ልደቱ የፌዴራል መንግሥቱን  አስጠነቀቁ!” ይበል ነው! — ወይ የታሪክ ምፀት! ልጅ እናቷን ምጥ የምታስተምርበት ዘመነ ግርምቢጥ፡፡ 

በሌላም በኩል ነገሩ “ወደሽ ከተደፋሽ ነው …”፡፡ አቢይና ቡድኑ ከየትም በራስ ስሞሽ ልመና ጠርተው ያሰባሰቧቸው ውሾች ራሱ አቢይ ላይ ይጮኹበት ይዘዋል፤ የልቡን ክፋት ቢያውቁ ይሆናል – መጠርጠር መጥፎ አይደለም፡፡ የላይ ትዛዝም ሊሆን ይችላል፡፡ የመጨረሻው መጀመሪያም ቢባል ያስኬዳል፡፡ ምንም ነገር እንደተመልካቹ ነው፡፡ … “ሁሉም ነገር ለበጎ ነው” መባሉንም አንዘንጋ፡፡

Filed in: Amharic