>

ትዝታ ዘ ጎንደር:- የሱዳን ህገወጥ ወረራና የጎንደር ፖሊስ ...(ብርሀኑ ተክለያሬድ)

ትዝታ ዘ ጎንደር:

የሱዳን ህገወጥ ወረራና የጎንደር ፖሊስ …!!!

ብርሀኑ ተክለያሬድ
ይህ ታሪክ የተፈፀመው መጋቢት 2006 ዓ/ም በጎንደር ከተማ ነው ከሰሞኑ ሱዳን የኢትዮጵያን ድንበር ጥሳ መግባቷን ተከትሎ ብልጭ ያለች ትዝታ ናት በታሪኩ ውስጥ የነበራችሁ ወጣቶች በትዝታዋ ፈገግ ትሉ ዘንድ ሌሎችም የተመቻችሁ ታነቧት ዘንድ ተፃፈች።
ወቅቱ ከኢትዮጵያ መሬት ተቆርሶ ለሱዳን የተሸጠው መሬት በኢትዮጵያ “መንግስት” መልካም ፈቃድ የድንበር ማካለል ሊደረግ መሆኑ በተለያዩ ሚዲያዎች የሚነገርበት ወቅት ነበር። የወቅቱ ጉልበተኞች ራስ ምታት በሆነው ሰማያዊ ፓርቲ ውስጥም በዚህ ጉዳይ በንቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ተጀመረ ንቅናቄው 2 ክፍሎች ነበሩት የመጀመሪያው በአዲስ አበባ የሚደረግ ህዝባዊ ውይይት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በጎንደር ከተማ የሚደረግ ሰላማዊ ሰልፍ ነበር። የጂኦግራፊ ሊቁን ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያምን በመጋበዝ የመጀመሪያው ክፍል የሆነው ህዝባዊ ውይይት በፓርቲው ፅ/ቤት ግቢ ውስጥ ተካሄደ ሊቁ ውይይቱን ሲጀምሩ “ስለምንድነው የተሰበሰብነው?” ብለው ጠየቁ
“ለሱዳን ስለተሰጠ መሬት” ተሰብሳቢው መለሰ
“የት?” አሉ የኔታ ተሳታፊው ዝምምም አለ።
ይሄኔ የኔታ “ስለማታውቁት ነገር ነው በየሚዲያው የምትናገሩት? መጀመሪያ ስለምትናገሩት ነገር በደንብ እወቁ ጥናቶችንም አዘጋጁ ከዚያ መከራከር ትችላላችሁ”የሚል ግሳፄ ካሰሙ በኋላ ይዘውት የመጡትን ካርታ ግድግዳው ላይ ለጠፉ።
ይኼኔ መካሪው መስፍን ጠፍቶ ጂኦግራፈሩ መስፍን ተተካ እያንዳንዷን የኢትዮጵያ መሬት ስንዝር በስንዝር የሚያውቋት የኔታ ካርታውን እየጠቆሙ በከሀዲው መንግስታችን የተሰራውን ሸፍጥ ለተሳታፊው መግለጥ ጀመሩ።
ሲጨርሱም ከተሳታፊዎች ጥያቄ መቀበልና ማብራራት ቀጠሉ በእለቱ ተጋባዥ የነበረው የሰአሊ አምሳሉ ገብረ ኪዳን Amsalu Gebrekidan Argaw  ወኔ ነቅናቂ ግጥም ተጨምሮበት የእለቱ ውይይት በተሳካ ሁኔታ ተጠናቀቀ። ከጥቂት ቀናት በኋላም ሰላማዊ ሰልፉን በጎንደር ከተማ ለማካሄድ የፓርቲው አመራርና አባላት ወደጎንደር አቀኑ።
ቡድኑ ጎንደር ከመድረሱ በፊት የፓርቲው የጎንደር ከተማ ሰብሳቢ የሆነው አግባው ሰጠኝና ጓዶቹ ከሰልፉ ጋር በተያያዘ በእስር ላይ ነበሩ ይሁንና የቡድኑ አባላት ጎንደር ሲደርሱ እነ አግባው ከእስር ተፈተው ቡድኑን ተቀብለው የሰልፉ ዝግጅት ቀጠለ።ቡድኑ ስራ ተከፋፈለ ይልቃል  እኔና ዮናታን ለሚዲያዎች የሚሰጡ ቃለመጠይቆች ላይ ተጠመድን።
ስለሺ ፈይሳ፣አግባው፣ ጌታነህ ባልቻና ይድነቃቸው ከበደ የቅስቀሳ ቡድኑን ማስተባበር ያዙ። የወቅቱ የነገረ ኢትዮጵያ ጋዜጣ አዘጋጅ ጌታቸው ሽፈራው የዝግጅቱን ሁኔታ በማህበራዊ ሚዲያ ማሰራጨትና ለጋዜጣው የሚሆኑ ዜናዎችን ያለድካም ማዘጋጀት ያዘ። ብርቱዎቹ እንስቶች ወይንሸት ሞላ ኢየሩሳሌም ተስፋውና ንግስት ወንድይፍራው ElduAbissu የቅስቀሳ ቡድኑን ተቀላቅለው ጎንደርን ከእግር እስከራሷ በቅስቀሳ አደመቋት ወዳጄ ፍቅረ ማርያም አስማማውም ካሜራውን ደቅኖ የዝግጅቱን ድባብ የማስቀረቱን ስራ ወሰደ።
የወቅቱ የጎንደር ከተማ/ብአዴን አመራሮች ሰልፉ እንዳይካሄድ የተቻላቸውን ሁሉ ሞከሩ ቡድኑ አልበገር ሲልም የከተማዋ ከንቲባ “ለሰማያዊ ፓርቲ በጎንደር ከተማ የተሰጠ የሰልፍ ፈቃድ የለም የሰልፍ ፈቃድ የተሰጠው የማንነት ጥያቄ አለኝ ለሚለው የቅማንት ኮሚቴ ነው” በማለት ወደሚዲያ ወጥተው ተናገሩ። ሰልፍ አዘጋጅ ኮሚቴው ወይ ፍንክች አለ  የቡድኑ አባላትም ሌሎች ስራዎችን ትተው ሁሉም ወደ ቅስቀሳ ተሰማሩ። ቅስቀሳው ራሱ ሰላማዊ ሰልፍ መሰለደ በመኪኖች ላይ የተጫኑ ሞንታርቦዎች
ተከብረሽ የኖርሽው በአባቶቻችን ደም
እናት ኢትዮጵያ የደፈረሽ ይውደም
  የሚል መዝሙር እስከ አፍንጫው ተከፍቷል፤በየመሀሉ ማይክሮፎን የያዙ ወጣቶች ሰልፉን ያስተዋውቃሉ፤የፋሲል ደመወዝ ዘፈን ይቀጥላል፤ወጣቶች ከመኪናው ጎን ለጎን በእግር እየሄዱ ወረቀቶችን ያድላሉ፤ጎንደር በቅስቀሳ ቀለጠች።
ከከንቲባው ንግግር በኋላ ትእዛዝ የተሰጣቸው የፖሊስ አዛዦች ለቅስቀሳ የወጡ አባላትን መኪኖች እያሳደዱ ማሰር ጀመሩ።የኛ ቡድን በከተማው እየተዘዋወረ ቅስቀሳ ሲያደርግ ቆይቶ መስቀል አደባባይ ቆሞ ወረቀት በመበተን ላይ ሳለ በፖሊስ ተከበበ። ወደፖሊስ ጣቢያ ሂዱ አንሄድም የሚል ውዝግብ ተካረረ ውዝግቡን ለማየትም ህዝብ ተሰበሰበ የሰማያዊ ወጣቶችም የሰዉን መሰብሰብ እንደ መልካም አጋጣሚ በመውሰድ መፈክር ማሰማት ጀመሩ።
የወያኔና የአልበሽርን ህገ ወጥ ስምምነት አንቀበልም!!”
“አንቀበልም!!”
“ታሪካዊ መሬታችን ለባእዳን አይሸጥም!!”
“አይሸጥም”
ህዝቡ እየተቀበለ ሰልፉ የተጀመረ መሰለ።
ጌታቸው ሽፈራው መሀላችን ቆሞ መፈክሩን በመቅረፀ ድምፅ በመቅረጽ ላይ ነው። ወዳጃችን ፍቅረ ማርያምም ህንፃ ላይ ሆኖ ይህን ታሪክ በካሜራው ያስቀራል፤ፖሊሶች ቀና ሲሉ ተመለከቱት። ጥቂት ፖሊሶች “ካሜራ ማኑን ያዘው አስወርደው” የሚል ትእዛዝ ከአለቃቸው ተቀብለው ወደህንፃው ዘለቁ።ፍቅረማርያምን አጅበው ከህንፃው ወጡ።
ከህንፃው እንደወረደ አዛዡ ወደሱ ሄዶ “ካሜራውን አምጣ” አለ “አልሰጥም” ነበር መልሱ “ቀሙት” ለፖሊሶቹ ትእዛዝ ተሰጠ። ይኼኔ ካሜራውን አናስቀማም ባሉ የፓርቲው ወጣቶችና በፖሊሶች መሀል ግብግብ ተጀመረ ፍቅረ የካሜራውን ቀበቶ አንገቱ ላይ አድርጎ ይጎትታል ፖሊሶች ካሜራውን ይጎትታሉ ወጣቶቹ ደሞ “ልቀቁት!” እያሉ ፍቅረን ይጎትታሉ፤ ፖሊሶቹን ይገፈትራሉ፤ በመሀል ቤት ፍቅረ ማርያም አንገቱ ታነቀ።በዚህ ግብግብ መሀል “ኧረ ልቀቀኝ አስለቅቁኝ” የሚል ጩኸት ተሰማ የአንድ ፖሊስ ጩኸት ነበር፤ ፍቅረ ለካ መታነቁ ሲበዛበት የአንዱን ፖሊስ እጅ በጥርሱ ለቀም አርጎታል።
ግማሹ በሳቅ ግማሹ በድንጋጤ አፈገፈገ፤ፖሊሶች በንዴት ያገኙትን መደብደብ ጀመሩ የአዛዡ ጥፊ የደረሰው ለኔ ነበር ኮሌታዬን ይዞ በጥፊ አላጋኝ  ጥፊው ንዴትም ድፍረትም ጨምሮልኛል መሰል አንገቱን ያዝኩት እሱም ያዘኝ ተናነቅን ከወገቡ ሽጉጡን ሊያወጣ ሲል አየሁት ወደ ቀልቤ ተመለስኩ ጉድ ፈላ አልኩ፤ እጄ አንገቱን እንደያዘ በአይኔ ገላጋይ ማማተር ጀመርኩ አግባው ሰጠኝ ወደኔ ሲመጣ አየሁት በውስጤ ‘እፎይ ገላጋይ መጣ’ እያልኩ አንገቱን አጠበቅኩ አግባው አጠገቤ ሲደርስ በመገላገል ፈንታ ፖሊሱ ላይ አፍጥጦ “ትገለው ነው? አስኪ ተኩስማ!ግደለውማ! የት ልትገባ?” አለው የፖሊሱ  ደምስር ሲገታተር አየሁት በአግባው የጎንደሬ ወኔ ተያይዘን ስንሞት ታየኝ አንገቱን አልለቀቅኩም የሽዋስ አሰፋ ከየት መጣ ሳይባል በፖሊሱ ወገብ ላይ ተጠመጠመ።
ይቀጥላል
Filed in: Amharic