>

የኢትዮጵያ ትንሣኤ መቼና እንዴት እውን እንደሚሆን ታውቃለህ? (አምባቸው ደጀኔ - ከወልዲያ) 

የኢትዮጵያ ትንሣኤ መቼና እንዴት እውን እንደሚሆን ታውቃለህ?

 

አምባቸው ደጀኔ (ከወልዲያ) 

 

“ጨዋ ሲጋባ የተፋታ ያህል ነው፡፡” ይባላልና “መጣላት” ካለብኝ ሰዎች ጋር አሁኑኑ ተጣልቼ መለያየት አለብኝ፡፡ የምጣላው ደግሞ ሀሰትንና ሙስናን መተዳደሪያቸው ካደረጉ ወይም ብሶትና በደልን ተገን አድርገው ሽንፈታቸውን ካወጁ ጋር ብቻ ነው፡፡ ሆዳም ሰው ፍቅር አያውቅምና አማራም ሆኖ ከወያኔና ኦህዲድ ጋር በመጎናበስ አማራንና ኢትዮጵያን ለሆዱ የሸጠ ሰው መሳይ በሸንጎም ጠበኛየ ነው፤ ይህን መሰሉን ፍጡር ደግሞ እንደሰው መቁጠር ይቸግራል፡፡ በቅድሚያ ግን አንዲት ማሳሰቢያ ቢጤ ልስጥ፡፡ 

ይህችነን ጸሑፍ የወያኔና ኦህዲድ/ኦነግ ሚዲያዎችም ብትሆኑ ሳታፍሩና ሳትፈሩ በልበ ሙሉነት አስተናግዷት – ግዴላችሁም ዝም ብላችሁ አውጧት፡፡ በአማራነት የምትታሙ ሚዲያዎችም ሳትሳቀቁ በነፃነት ለፍፏት፡፡ ለአማራ አላዳላም፤ ለኦሮሞም አላዳላም፤ ለትግሬም አላዳላም፡፡ ለማንም አላዳላም፡፡ ለምኔ ብዬ? የኢትዮጵያን የማይቀር ትንሣኤ በተመለከተ ግን ካላንዳች ይሉኝታ ሁሉም የሚተፋፈርበትንና በግልጽ ቢናገር ወንጀልና ዘረኝነት የሚመስለውን የመፍትሔ ሃሳብ በግልጽ አወራለሁ – እውነትን ተናግሮ እመሸበት የማደር ያህል ነው፡፡ እውነትን መፍራት የትም እንደማያደርስ አየነው፡፡ በመተፋፈርና በይሉኝታ ብዙ ርቀት ተጉዘን ያተረፍነው ነገር ቢኖር ሀገርን እስከማሳጣት ያደረሰ ውድመትን ብቻ ነው፡፡

አንድ ሰው “በፍቅር እንሞትልሃለን!” ከሚሉት ሁለት ሴቶች ጋር ተኝቷል – ሌሊት ነው፡፡ ሃይማኖታዊ ፍልስፍናህን ለጊዜው ተወውና ዝም ብለህ አድምጠኝማ፡፡ ወንዱ የተኛው ታዲያን መሀል ነው፡፡ አንደኛዋ ሴት “ከሁለታችን ማንኛችንን ይበልጥ ትወዳለህ?” በማለት ያልጠበቀውን ዱብዕዳ ጥያቄ ትጠይቀዋለች፡፡ አፍ አውጥቶ “ትንቧለልን” ወይም “ጫልቱን” እንዳይል ከሁለት አንድኛቸው ሊቀየሙት መሆኑ ገባው፡፡ ሰውዬ ሆዬ ብልጥ ነበርና ተንጋሎ እንደተኛ ሁለት እጆቹን ወደሁለቱም ሴቶች ጭኖች በመላክ በአንድ ቅጽበት ሁለቱንም ቁንጥጥ አደረገና “አንቺን ነው!” ይላል፡፡ ያኔ ሁለቱም በእርካታ ውስጣቸው ይፍነከነካል፡፡ “ያቺኛዋ እንዳትነቃበት ነው እኔን ብቻ ቆንጥጦ እንደሚያፈቅረኝ በምልክት የነገረኝ!” በሚል እሳቤ ሁለቱም ተደሰቱ፤ ወደሌላ ጨዋታም አመሩ፡፡ ሰውዬው ግን በርግጥም ብልጥ ነው አይደል? አዎ፣ የሰውን ስሜት ሳይጎዱ በሁለት ወገን ለመፈቀር መሞከር ከተቻለና ዘላቂነት ካለው ክፋት የለውም፡፡  እንደውነቱ ግን ሁለት ተቃራኒ ኃይሎችን በአንዴ ማስደሰት ከባድ ብቻም ሣይሆን የሚቻል አይደለም፡፡ ሁለት እገር አለኝ ተብሎም ሁለት ዛፍ ላይ አይወጣም፡፡ ጥሩ አባባል ልጨምርና አንቀጽ ልለውጥ፡- “የዳኛ ልል ያማታል፤ የብልት ልል ያፋታል፡፡” ነጭና ጥቁር ኅብረት የላቸውም፡፡ የ binary opposition ህግ ይህን መሰሉን ወግቶ ይማርህ አስተኔ ኢ-ሥርዓታዊ ሥርዓት አይፈቅድም፡፡ 

ዶክተር አቢይ አህመድ ይህንን ሰው ይመስላል፡፡ ስለዚህም ማንንም ላለማስቀየም በሚያደርገው ጥረት (ይመስላል) ባሌና ደሴ ላይ የሚያደርጋቸው ንግግሮቹ ዐይንና ናጫ እየሆኑበት ክፉኛ ተቸግሯል – ክፉ ዕድሉ ከጠማማ ቀን ጋር ተዋውለውበት የነብር ጅራትና ሥልጣን ተፋጠጡበትና ከወረቱ ስንቁ ሳይሆንበት አልቀረም – አንዳንዴ በጣም ያሳዝነኛል፤ ከእርሱ ዕድል ይልቅ ሁለት ሙዝ በአንዲት ኮስማና የሦሥት ብር ዳቦ መሀል ከተው  ምሣቸውን “ግጥም አድርገው” በልተው ወደ ቀን ሥራቸው የሚገቡ “ቀምበሌዎች” ያስቀኑኛል፡፡ እርሱ በቦሌም በባሌም ብሎ የኖቤል ሽልማት ድጋፍም ተደርጎለት የያዘውንና ዕንቅልፍ ያሳጣውን ሥልጣኑን እስኪያረጋጋ ድረስ በተከታታይ በሚያጠፋቸው ጥፋቶች ምክንያት ሀገር ከአንጻራዊ መኖር ወደ ጨርሶ አለመኖር እየተጣደፈች ነው፡፡ አንደኛውን “ጠበኛየን” ገልጬ ጨረስኩ፡፡

አማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) አመሠራረቱ ቢገባኝም ከአማራ ወርድና ቁመት የማይመጣጠን ድርጅታዊ አወቃቀር የሚከተል ስለሚመስለኝ በቶሎ ይስተካከል፡፡ ይህ “ትዕዛዝ ነው”፡፡ “ትዕዛዜ” ቅቡልነትና ተዓማኒነት እንዲኖረው በግድ ከመምህር ግርማ ወንድሙ ወይም ከንግሥተ ነገሥታት ‹እኅተ ማርያም› ስንዱ የትብብር ደብዳቤ ማምጣት የለብኝም፡፡ አማራ፣ አማራ የምትሉ ወገኖቼ ትግሬ፣ ትግሬና ኦሮሞ፣ ኦሮሞ ከሚሉ የፖለቲካ ወያላዎች ክስረት መማር አለባችሁ – እውነት ነው ችግራችሁ ይገባኛል፡፡ ኮሮና ከመኝታ ቤቱ የወሸቀው ጃዋር “ኦሮሚያ” ከሚባል ምናባዊ “ትልቅ ሀገር” ውጡልኝ ይላቸው የነበሩ አማሮች ከገዛ ቀያቸው መውጣታቸውን ማረጋገጥ እንዳይችል በድሆች ደም የተገዛ ቤቱን ደጅ ማየት እንኳን ናፍቆታል፡፡ በስተርጅና የተበላሸው መረራ ጉዲናም አሁን የት እንዳለ አናውቅም፤ በቀለ ገሪባን የበላው ጅብም ካለፉት ሁለትና ሦስት ወራት ወዲህ አልጮኸም፡፡ ፕሮከሰር ሕዝቅኤልና የውሸት ዶክተር ፀጋየ አራርሳ እንዲሁም መምህራቸው ዲባቶ ገመቹ መገርሣ በየትኛው ማግለያ ጣቢያ እንደተጠለሉ አይታወቅም፡፡ ለዚህ ነው እንግዲህ በተረኛው መንግሥት የተማመነው ያ ሁሉ ዘረኝነት እግር አውጥቶ እስኪሄድ ድረስ በምስኪኑ ሕዝባችን ጫንቃ ላይ ይንጎማለል የነበረው – ሕዝብ አስተዳደር ጥበብንና አስተውሎትን ይጠይቃል፤ ጊዜ ሰጠኝ ብሎ በስሜት እምቡር እምቡር ማለት ሠላሣ ዓመታትንም ቢሆን ቆይቶ ትልቅ ዋጋ ያስከፍላል፡፡ (አውራ ዶሮው አሞራው እስኪያልፍ ከተደበቀ በኋላ ማለፉን አረጋግጦ “አምጭማ አምጭማ ጦሩን፤ ወንዙን ሳይሻገር እለውና ናላውን” ሲል እመት እናት ዶሮ “አንቱም አንቱም አይዋሹ፤ አሁን ቢመጣ አጥር ላጥር ሊሸሹ” አለችው አሉ፡፡ ሁሉም ታዬ፤ መንግሥት ተብዬው ይልቅ በጣም የተሻለ እንቅስቃሴ እያደረገ ነው – ምንም እንኳ ባለሥልጣናቱ የተጣባቸው የሙስና ደዌ አሁንም ተባብሶባቸው መቀጠሉ ቢነገርም፡፡ ሙስና ሱስ ነው፤ ካላስቀበረ የማይተው እጅግ አደገኛ ሱስ!)

አማራ ማን ነው? አማራነት ምንድን ነው? የተለዬ ነገር እንደምናገር የምትጠብቁ ካላችሁ እንዳትሳሳቱ አደራችሁን፡፡ አማራ ብሎ የተለዬ ዘር የለም፡፡ ፕሮፌሰር መስፍንና አንዳርጋቸው ጽጌ ይወቀሱበት የነበረውን “አማራ አለ፤ አማራ የለም” ተራ ክርክር አሁን እንርሳው፡፡ ካስፈለገም  “አማራ እያለ የሌለ መንፈስ ነው” ልበልና እኔ የሁለቱ አንጋፋ ሰዎች ተማሪ ላሻሽለው፡፡ አለ/የለም ብሎ መከራከር በመሠረቱ ሞኝነት ይመስለኛል፡፡ አማራ ከሌለ ጎጃምን፣ ጎንደርን፣ ወሎን፣ ሸዋን፣ ባሌን፣ አዲስ አበባን፣ ናዝሬትን፣ አዋሳን… ማን ሞላው? አማራ ካለ ኢትዮጵያን ምን በላት? ወዴት ገባች? ምን ዋጣት? 

አማራ እንደ አንድ ሕዝብ በአንድ ማኅበረሰብኣዊ ሥነ ልቦናና ማኅበራዊ ትስስር አናውቀውም፡፡ በተለመደው አገላለጽ አማራነት እንጂ አማራ አለ ማለት በምንችልበት ደረጃ የለም ወይም እስከቅርብ ጊዜ አልነበረም፡፡ “እኔ የአማራይቱ ልጅ!” ብሎ የሚፎክር አማራ ከተገኘ – አሁን በዚህ ዘመን እንኳን – ልቀጣ፡፡ በዞንና በጎጥ መፎከር ግን የነበረና ያለም ነው – “የመንዜይቱ ልጅ!” ዓይነት፡፡ በአማራነት መሳሳብ ግን አልነበረም፤ አማራ በመሆንህ ብቻ የሚያቀርብህ አማራ ካለ የወያኔ ትውልድ መሆን አለበት – እርሱም ከስንት አንድና አሁን አሁን፡፡ በትግሬነት ግን አለ – እስክንጠግብ አይተነዋል፡፡ በኦሮሞነትም አለ – እስኪያንገሸግሸን እያየነው ነው፡፡ አማራነት ላይ ተመሥርቶ ግና መቅጠርም ሆነ መሾምና ከቦታ ቦታ ማዛወር በበኩሌ አላውቅም፡፡ አማራነት በኢትዮጵያ ውስጥ ቀልጦ ወይም ሟሙቶ በመጥፋቱ አማራን ለይቶ ለማወቅ ራሱ አማራውም ተቸግሯል፤ አማራነትና ኢትዮጵያዊነት መሣ ሆነዋል – ይህም ነው አማራውን ያወከውና ጠላቶቹም ይህን ሕዝብ አጥፍተው ለመጨረስ ክፉኛ ያስቸገራቸው፡ የምለው ነገር ማንንም ግራ እንዳያጋባብኝ እፈልጋለሁ፡፡ አማራ የምለው አሁን አማራ ነኝ የሚለውን ወገን ነው፡፡ እንጂ አማርኛ ተናጋሪ የሆነ ሁሉ አማራ ላለመባል የሚጎድለውም ሆነ የሚከለክለው የለም፡፡ ለአማራ ውድቀት አሉታዊ አስተዋፅዖ ያደረጉ ነጥቦች ተመልሰው ለትንሳዔውም በአወንታዊነት ከፍተኛ ሚና የሚጫወቱ ይሆናሉ፡፡ ይህን ኗሪ የሚያየው ይሆናልና ከአማራ ጋር “የምትሳፈጡ” ይቅርባችሁ እላለሁ፡፡ ግልጽ ነው!

ቁጥርን በተመለከተ ብዙ ውሸት አለ፡፡ ጠባቦችና ጊዜ የሰጣቸው የላም አሸናፊዎች አማራን(ኢትዮጵያን) አሸነፍን የማለት ጀብዳቸውን አማናዊ ለማድረግ ከወሰዷቸው ድፍረት የተሞላባቸው እርምጃዎች አንዱ የአማራን ቁጥር በእጅጉ ቀንሶ መናገርና ማስነገር ነው፡፡ አሁን ስሙን የማላስታውሰው አንድ የትግሬ ምሁር እንዲያውም አማራን አናሳ ብሄረሰብ (minority) እንደሆነ በአንድ መጽሐፉ ያለአንዳች ሀፍረት ጽፏል፡፡  ከታወሩ አይቀር ደግሞ እንደዚህ ነው፡፡ እርግጥ ነው በፊት ሕወሓትም ሆነ አሁን ተረኛው ኦህዲድ አማራን አሳንሶ ለማሳየትና ዘሩንም ከምድረ ገጽ ለማጥፋት ያልፈነቀሉትና የማይፈነቅሉትም ድንጋይ የለም – “ኢትዮጵያዊ ነኝ” የሚልን በነሱ መለኪያ አማራ ያልሆነን ዜጋ ሳይቀር –  ጥላቻ እኮ ያሣውራል ወገኖቼ፡፡ ሆኖም አማራ ላጥፋው ብለህ እንደምታደማው የፊትና የሰውነት ኪንታሮት ባላሰብከው ፍጥነት እየተስፋፋ የሚሄድ ሕዝብ መሆኑን ባለፉት 30 ዓመታት አስመስክሯል፤ ባገር ውስጥ ስታጠፋው በውጭ ይባዛልህና በዕውቀትም በሀብትም ዳብሮ ጠፋልኝ ያልከው ሕዝብ ሲፋፋ ታየዋለህ፤ ተረግሞ የተመረቀ ሕዝብ፤ ተመርቆም የተረገመ የኢትዮጵያ አንዱ ፈርጥ፡፡ ስለሆነም ይህ ሕዝብ በአሁኑ ወቅት ከ50 ሚሊዮን ቢበልጥ እንጂ አያንስም፡፡ አማራ ሌላ የሚመካበት የጎሣም ሆነ የብሔር ማንነት የሌለው በመሆኑ በየትም ሥፍራ ሁሉም ዘመዱ ከመሆኑም በላይ ከሁሉም ጋር ተጋብቶና ተዋልዶ በሁሉም ውስጥ ተመሳስሎ የሚኖር ነፃ ሕዝብ ነው፡፡ ችግሩ ምልዓቱ ያስከተለበት መዘናጋትና ለበርካታ ዓመታት በጊንጦች የተፈጸመበትን ሤራና ተንኮል ለፈጣሪ ከመስጠት በዘለለ በኅብረት መታገል አለመቻሉ ነው፤ ይህ ነው የአማራ ትልቁ ጠላት – የአማራነት ሥነ ልቦና አዳብሮ ጠላቶቹን አለመጋፈጡ አማራን እንጦርጦስ አውርዶታል – ይሁን፤ ለበጎ ነው፡፡ አማራን አማራነቱ ቢያሰባስበው ኖሮ – ወልቃይትንና ራያን እንተዋቸው – ወያኔ አራት ኪሎን ይቅርና ቆቦና ወልዲያን መሻገር ህልም እንደሆነበት እዚያው ደደቢቱ ላይ በከሰመ ነበር – ይህንንም እውነት ወያኔዎች ራሳቸውም አሳምረው ያውቃሉ፡፡ ለዚህም ነው አማራውን በጥቅምና በተለያዩ ጥቃቅን ነገሮች የከፋፈሉት፡፡ አማራው ከሁሉም ዘር ጋር መሰባጠሩም ከቋንቋና ባህል መመሳሰል አኳያ ብዙ ጎድቶታል፡፡ ምክንያቱም አማራው ምንም እንኳን ተጠራጣሪ ቢሆንም ጥርጣሬው ግን እርስ በርስ እንጂ በሌሎች ላይ እስከዚህም በመሆኑ ቋንቋውን የሚናገሩ በረከት ስምዖንን የመሰሉ እፉኝቶች አማራ መስለው የጠላትን አጀንዳ ያስፈጽሙ ነበር – ሰዎች እየተቀያየሩ አሁንም ድረስ፡፡ ትንሹ አቢይ ሳይቀር ስንትና ስንት “ፊንታ” አማራው ላይ እየሠራ ነው፡፡

ሶማሊያውያን ገበሬዎች ስለአማራ ያሉትን ላስታውሳችሁ፡፡ ወያኔዎች አገር ምድሩን ሲቆጣጠሩና በዚያው ሰሞን “የአስተዳደር ጥበባቸው”ን በይፋ ማሳየት ሲጀምሩ ሶማሌዎች “አይ፣ አገር ማስተዳደሩንስ ለአማራ ተውት፤ እናንተ አትችሉበትም” ነበር ያሏቸው፡፡ ትልቅ ቁም ነገር ያዘለ አነጋገር ነው፡፡ ሰዎች የተለያዬ ክሂል አላቸው፡፡ ፍትሃዊነት፣ አድሏዊነት፣ ዳኝነት … ለሰዎች እንደተፈጥሯዊ መክሊት ከአምላክ የሚሰጡ ተውህቦዎች ናቸው፡፡ ንፉግነትና ቸርነት ራሳቸው “ተሰጥዖ” ናቸው፡፡ እነገሌ ለውትድርና፣ እነገሌ ለንግድ፣ እነገሌ ለአብራሪነት፣ … እነገሌ ለዶሮ ወጥ፣ እነገሌ ለክትፎ፣ እነገሌ ለጥልኆ… እየተባለ ብዙ ነገር እናውቅ የለምን? አዎ፣ ሸማ በየፈርጁ ይለበሳል፤ ክፋትም የለውም፡፡ በአንድ ወይም በጥቂቶች ብዙ ሰው መሰደቡ ያሳዝናል እንጂ ከዚህ በባሰስ እነገሌ ውሸታም፣ እነገሌ የሀሰት መስካሪዎች፣ እነገሌ ከሃዲዎች፣ እነገሌ ስስታሞች፣ እነገሌ ሌባና ቀጣፊዎች፣ እነገሌ ተልባዎች፣ እነገሌ ገለባዎች … እየተባለ ይነገር የለምን? የምን ይሉኝታ ነው! በየሀገራቱ ይህ ነገር አለ፡፡ ከፀሐይ በታች… 

አንድ አማራ የቢሮ ኃላፊ ቢሆን በሚቀመጡ መሥፈርት ለሥራው ብቁ የሆነ ሰው ከሁሉም አመልካቾች ፈትኖ ይቀጥራል እንጂ በስም ምንነት ታውሮ ስንሻውንና አምባቸውን አለሙያና ችሎታቸው በማግበስበስ ለነገ ሀፍረት ራሱን አያዘጋጅም – ከሽዎች አንድ የዚህ ዓይነት ብልግና የሚሠራ ይሉኝታቢስ ሰው ሊኖር ቢችል ከቁጥር አይገባም፡፡ በቀደሙትና በአሁን ግብዝ ተረኞች ያየነውና የምናየው ግን የተለዬ ነው፡፡ አሁን በየመ/ቤቱ የሚታየው ጉድ መነሻም ይሄው ነው፡፡ የነገዳቸውን ሰው ይጥቀሙ እንጂ ስለሀገርና ስለሥራ ስኬት ቅንጣት አይጨነቁም፡፡ ድፍን ቅል ራስ ሁሉ ከየጎጡ እየተጠራራ ሥራ እየተበለሻሸ ነው፡፡ ሰሞነኛ ምሣሌ ላቀርብ እችላለሁ – ከአዲሱ የሙሉና ጎደሎ የቤት መኪና ታርጋ ጋር በተያያዘ ስለወጣው ደምብ ከታዘብኩት ነው ፡- የዘንድሮ ባለሥልጣን መቼም በወያኔው ኮፒ-ፔስት ቅኝት ከሞላ ጎደል ሁሉም ደቻሣና ጉርሜሣ ሆኗልና አብዲሣ ያደቴ የተባለ መልከ መልካም የመንገድ ትራንስፖርት የሥራ ኃላፊ በቀደምለት እንዲህ አለላችሁ፤ “ህጉ የወጣው የሰዎች እንቅስቃሴን ለመገደብ ነው፡፡ በዚህ ደምብና ዐዋጅ ተጎዳሁ የሚል ባለመኪና ካለ ራይድ ጠርቶ መጠቀም ይችላል፤ በታክሲና አውቶቡስም በእግርም መጠቀም ይችላል…” (ቢሰማኝ ኖሮ ጉዴ ፈልፈቶ ነበር! ቀስ ብዬ ‹ደንቆሮ› አልኩታ!) የዚህን ሰው ጢሪሪም ጢሪሪም ስትሰሙ “እነዚህ ሰዎች በውነቱ ኢትዮጵያን እንዲገዙ የተሰጡን በምን ኃጢኣታችን ይሆን?” ብላችሁ መጨነቃችሁ አይቀርም – እናንተም በሽታው ካልተጠናወታችሁ ማለቴ ነው፡፡ አንድ ባለመኪና ቤተሰቡን ይዞ ወደ ግል ሥራው ቢሠማራ ይሻላል ወይንስ በታክሲና በአውቶቡስ እየተጋፋ በሽታውን ቢያዛምት? በቀላል ወጪ ኑሮውን ቢገፋ ይቀላል ወይንስ አምስት መቶና ስድስት መቶ ብር እየከሰከሰ ራይዶችን ቢመግብ ይሻላል? ሰዎቹ የራይድ መኪኖች ባለቤት ይሆኑ ይሆን? ምን ዓይነት የደደበ አስተዳደር ነው? ለዚህ ነው መንግሥትነት ከስሜት ይልቅ ለጥበብ ይቀርባል መባሉ፡፡

የሚያጽናናኝ ብዙ ነገር አለ፡፡ አንዱ አማራነት ተጋቦታዊ መሆኑ ነው፡፡ አማራነትን በምርጫ ማግኘት ይቻላልና ከየነገዱ በርካታ ዜጎች የአማራ ጠባይ የተጋባባቸው እንዳሉ እናውቃለን፡፡ ቋንቋና ሰው ባሕርያዊ ግንኙነት እንደሌላቸው የሚረዱ የየትኛውም ብሔርና ነገድ አባላት ወደጎሣዊ ማንነታቸው ሳይጨማደዱና ሳይኮማተሩ በኢትዮጵያዊነት ሸማና ኩታ ተውበው ዜጎቻቸውን በእኩልነትና በፍትህ የሚመሩ አሉ፡፡ ዘረኝነት ጥምባትና ግማት መሆኑን የሚገነዘቡ የየትኛውም ነገድ አባላት በቋንቋና በጎሣ ሲመጡባቸው ይጠየፋሉ፤ የሚጣልባቸውን የሥራ ኃላፊነትም በፍትህ ርትዕ ይወጣሉ፡፡ የእናት ሆድ ዥንጉርጉር ነው፡፡ እነዚህን መሰል ዜጎች የሀገራችን የወደፊት ተስፋና አለኝታ ናቸው፡፡ ይብዙልን፡፡

አማራንና አማራነትን ከሥልጣን ማባረር የዘመኑ ፋሽን የሆነው ኢትዮጵያን የሚጠሉ ኃይሎች የከፍታውን ቦታ ስለያዙ ነው፡፡ አሁንና ወደፊት ግን እነዚህ ኃይሎች በራሳቸው የቤት ሥራ ይጠመዳሉ፤ ብዙ ሀብትና ጫፍ የደረሰ ሥልጣኔም ምንም ማለት እንዳልሆነ ይረዳሉ – ሊያውም በቀላል ልምጭ፡፡ ስለዚህም እንኳንስ የኛን የወደፊት ዕጣ ሊወስኑ ስለራሳቸውም በብርቱ ይጨነቃሉ፡፡ ምልክቱንም በራሳቸው ግዑዝ ፍጡር ሰሞኑን እየታዘብን ነው – ወጥ በወጥ ሆነዋል፤ ይጨብጡትንና ይለቁትን አጥተዋል፡፡ የፓንዶራ ሣጥን የሚሏት ነገር ሳትከፈትባቸው አልቀረችም፡፡ የአንዳንዶቻችን ጸሎት ይሄው ነበር – ፈጣሪ ለጠላቶቻችን የቤት ሥራ እንዲሰጥልን – መጎዳታቸው ባያስደስተንም የኅልውና ጉዳይ ነውና ጸሎታችን ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ ነባር ብሂሉም እንዲህ ይላል፡- “አንቺም ጨካኝ ነበርሽ ጨካኝ አዘዘብሽ፤ እንደገና ዳቦ እሳት ነደደብሽ”፡፡ የዘመናት ጸሎታችን ሠምሯል፡፡ የእጃቸውን ሊያገኙም ሥፍሩ ተጀምሯል፡፡ ይዘገያል እንጂ ማንም ቢሆን በሠፈረው መሠፈር አይቀርም፤ ወያኔን ማየት በቂ ነው፡፡ 

አማራን በጥሬ ትርጉሙ እንርሳው፡፡ ነገ የትግሬ አማራ ይመጣል፡፡ ነገ የኦሮሞ አማራ ይመጣል፡፡ ነገ የሶማሊያ አማራ ይመጣል – አሁንም እንዳለ ሁሉ፡፡ አማራ ሀገሩ ኢትዮጵያ ትወለድለትና በገዛ ሀገሩ ሳይሸማቀቅ መኖር ይቻል እንጂ በአሁኑ ሁኔታ ለሥልጣን ያን ያህል እንስፍስፍ አይመስልም፡፡ ጽድቁ ቀርቶበት በቅጡ መኮነንን የሚሻ ነው፡፡ በቀትረ ቀላል ትናንሽ ሰው መሳይ ፍጡሮች ብዙ ተሰቃይቷልና የወደፊቱ ጊዜ የርሱና የርሱ መሰሎች ቢሆን ሲያንሰው ነው፡፡ ብዙ ስለተማረም የፍትህ መቅረዝ እንደሚሆን ይጠበቃል፤ ፍርደ ገምድልነት ምን ያህል ዋጋ እንደሚያስከፍልም ያውቃልና አይሞክረውም፡፡

ቋንቋን በተመለከተ አማርኛን ሊተካ የሚችል ሌላ ቋንቋ ኢትዮጵያ ውስጥ የለም፡፡ በትምክህትና በጉራ ማንም የትም አይደርስም፡፡ “አንድን ፈረስ አንድ ሰው ወደ ወንዝ ሊወስደው ይችላል –  ሃያ ሰዎች ግን በግድ ውኃ እንዲጠጣ ሊያደርጉት አይችሉም” የሚል ብሂል አለ፡፡ ብልጧ ወያኔ በ27 ዓመታት ፈረዖናዊ አገዛዟ ያልሞከረችውን ብሔራዊ ቋንቋን የመለወጥ ጉዳይ ዛሬ አንድ ጎሠኛ ተነስቶ የራሱን ላድርግ ቢል ለተወሰነ ጊዜ ግርግርና የሚያበሳጭ ሣቅን ከመፍጠር ውጪ የሚያመጣው ነገር የለም፡፡ ሀገርን ማስተዳደር የሚቻለው ከአፍ እስካፍንጫ በማያልፍ አስተሳሰብ ታውሮ የታሪክና የትውልድ መሣቂያና መሣለቂያ ለመሆን በመጣደፍ ሳይሆን አርቆ አሳቢ በመሆን ነው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ አማራና ኦሮሞ ብቻ ቢኖሩ ኖሮ እርግጥ ነው አማራውን በማስገደድ ኦሮምኛ  አስለምዶ የሚፈለገው ውጤት በተወሰነ የጊዜ እርዝማኔ ውስጥ ሊገኝ ይችል ነበር፡፡ አሁን ግን ለሽዎች ዓመታት በተካሄደ የቋንቋና ማኅበረሰብ ሽመና 86ቱ ጎሣና ነገድ በአማርኛ ተጠላልፎ እየተግባባ መኖርን ባህሉ ስላደረገ የወል መግባቢያን መቀየር በመሠሪ ቄሯዊ የዘር ፍጂት በቀን 86 ንጹሓን ዜጎችን እንደማስጨፍጨፍና በህግ ሳይጠየቁ በመናገሻ ከተማ ውስጥ እንደመፏለል ቀላል አይደለም፡፡ ይህን ማኅበረሰብኣዊ መደላድል ለመበታተን ባለፉት 30 ዓመታት የተደረገው ዓለም አቀፍ ጥረት እምብዝም የተሣካ አይመስልም፡፡ ለተወሰነ ጊዜ ልናታልላቸው ብንችልም ሰዎች የሚጠቅማቸውን ያውቃሉ፡፡ ራስህ ወግህን የምትጠርቅበትን የጋራ ቋንቋ ሌላው እንዳይናገረው ማገድ ክፋት ከመሆኑም ባሻገር ሰዎችን እንደኮቪድ 19 የቤተ ሙከራ ፍጡር መቁጠርም ነው፡፡ በነገራችን ላይ ለአማርኛ አዝኜ ወይ በኦሮምኛ ተከፍቼ አይደለም እንዲህ የምለው፡፡ እውነት ስለሆነ ነው፡፡ የጋራ መግባቢያችን አማርኛ በመሆኑ እንደ አንዳንድ የዋሃን ሥነ ልቦናዊ ጥቅም እንኳን አላገኝም፡፡ ሁላችንም ይህን ደካማ ሰውኛ ስሜት ማለፍ ብንችል ደስ ይለኛል፡፡ ቋንቋ መሣሪያ እንጂ የግል ንብረት አይደለም፡፡ በቋንቋ የሚራኮት ሰው፣ ሰው ለመሆን ገና ብዙ የሚቀረው ከእንስሳም ያነሰ ዝቃጭ ነው፡፡ …

የኢትዮጵያ ሕዝብ ደሙንና አጥንቱን ገብሮ ብዙ ተማረ፡፡ የሚጠቅመውን ከማይጠቅመው ለይቶ ዐወቀ፡፡ ያለፉት 30 እና 40 ዓመታት በተለይ በደምና በአጥንት ግብር ብዙ የተማርንባቸው ጊዜያት ናቸው፡፡ አሁን ወደ ጤናማ አማራነት፣ ጤናማ ኦሮሞነት፣ ጤናማ ትግሬነት … የምንጠጋበትና ሀገራችንን ከተደገሰላት ዘግናኝ የመበታተን ዕልቂት የምንታደግበት ወቅት ላይ ነን፤ ደግሞም ከፈለግን እንችላለን፤ ባንፈልግም አንዳንድ መልካም ነገሮች መምጣታቸው ታሪካዊ ክስተት ነው፡፡ እርግጥ ነው – ዛሬ ዘመነ ኮሮና ነው፡፡ ነገ ደግሞ ሌላ ቀን ነው፡፡ ዘረኞችና ጠባቦች እንዲሁም ትምክህተኞች ግን ፀሐያቸው ትጠልቃለች፡፡ በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ የሚታይን ብርሃን መናገር ነቢይነትን አይጠይቅም፡፡ ነገር እንዳበዛሁባችሁ ይገባኛል፡፡ በኮርዬ ምክንያት መሄጃ ስለሌለን ረጋ ብለን እናንብበው፡፡ የጋራ ችግር ነውና ጀርባችንን አንስጠው፡፡ የጋራንም ሆነ የግልን ችግር ጆሮ ዳባ ቢሉት እርሱ አይልም፡፡ ሰላም፡፡…

EMAIL: martyrof2011@gmail.com

Filed in: Amharic