>

የዛሬው (የ- UK) የኮሮና ክትባት ሙከራ!!! (ውብሸት ታዬ)

የዛሬው (የ- UK) የኮሮና ክትባት ሙከራ!!!

ውብሸት ታዬ
   ዩናይትድ ኪንግደም በዛሬው ዕለት በሰው ላይ የጸረ ኮርና ቫይረስ ክትባት ሙከራ ታደርጋለች።
ክትባቱ በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ እና በኢምፔሪያል ኮሌጆች የተዘጋጀ ሲሆን ለምርምር ሂደቱ 22 ሚሊዮን ፓውንድ ለእያንዳንዳቸው መመደቡን የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ማት ሐንኮክ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
   ሳይንቲስቶቹ ክትባቱን 80 በመቶ ተስፋ የተደረገበት እንደሆነ ቢገልጹም የጤና ሚኒስትሩ ግን በጉዳዩ ላይ ከውጤት በፊት እርግጠኛ የሆነ ምንም ነገር የለም(Nothing about this process is certain) ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
   ክትባቱ እንደተጠበቀው ስኬታማ የሚሆን ከሆነ መጀመርያ ተጠቃሚ የሚሆኑት ከ17 ሺህ በላይ ዜጎቻቸውን ያጡት የዩናይትድ ኪንግደም ሕዝቦች መሆናቸው ተገልጿል።
 
ለመሆኑ ኮሮናቫይረስን ለመፈወስ ተስፋ ያለው መድኃኒት የቱ ነው?
ከ150 ሺህ በላይ ሰዎች ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘ ህመም አልቀዋል። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ለቫይረሱ ተጋልጠው ይገኛሉ። እስካሁን ግን ከቫይረሱ እንደሚፈውስ የተረጋገጠለት መድኃኒት አልተገኘም።
ግን ግን ከኮቪድ-19 ጨርሶ የሚፈውስ መድኃኒት ለማግኘት ምን ያህል ተቃርበናል?
ከቫይረሱ የሚፈውስ መድኃኒት ለማግኘት ምን ተከናወነ?
በመላው ዓለም የሚገኙ ተመራማሪዎች ከ150 በላይ የሆኑ የተለያዩ መድኃኒቶች ላይ እየተመራመሩ ሙከራዎችን እያከናወኑ ይገኛሉ። ምርምር እና ሙከራ እየተደረገባቸው የሚገኙት አብዛኞቹ መድኃኒቶች በገበያ ላይ ያሉ ወይም ከዚህ ቀደም የሚታወቁ ናቸው።
የዓለም ጤና ድርጅት ‘ሶሊዳሪቲ ትሪያል’ የተሰኘ ለኮቪድ-19 ፍቱን የመሆን ተስፋ ያለውን መድኃኒት ለማግኘት ምርምር ላይ ይገኛል።
ዩናይትድ ኪንግደም በበኩሏ ከ5 ሺህ በላይ ታማሚዎች የሚሳተፉበት የዓለማችን በመጠኑ ሰፊ የሆነ የምርምር ሥራ እያከናወንኩ ነው ብላለች።
በርካታ የምርመር ማዕከላት ደግሞ ከበሽታው የዳኑ ሰዎችን ደም በመጠቀም ኮቨድ-19ን ለማከም ምርምር እያደረጉ ይገኛሉ።
ከበሽታው ሊፈውሱ የሚችሉት መድኃኒቶች ምን አይነት ሊሆኑ ይችላሉ?
ከበሽታው ሊፈውሱ የሚችሉ መድኃኒቶችን ለማግኘት እየተደረገ ያለው ምርምር በሦስት ከፍሎ መመልከት ይቻላል። እነዚህም፤
1.የመጀመሪያው ኮሮናቫይረስ ወደ ሰውነት ውስጥ ከገባ በኋላ የመቆየት አቅሙን የሚፈታተን ወይም በሰውነት ውስጥ መቆየት እንዳይችል የሚያስችል ጸረ-ተህዋሲ [አንቲቫይራል] መድኃኒት የማግኘት ምርምር አንዱ ነው።
2. በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ የሰውነትን በሽታን የመከላከል ሥርዓት ለኮሮናቫይረስ የተመጠነ ምላሽ እንዲሰጥ የሚያደርግ መድኃኒት ማግኘት ነው። ምክንያቱም የሰውነት የበሽታ መከላከል ሥርዓት፤ አካላችን በበሽታ ሲጠቃ ከመጠን በላይ ምላሽ ሲሰጥ ታማሚው በከፍተኛ ሁኔታ ስለሚታመም መድኃኒቱ ተዛማጅ ጉዳትን ለመቆጣጠር ይረዳል።
3. ሦስተኛው ደግሞ በላብራቶሪ የተዘጋጀ ወይም ከኮሮናቫይረስ ካገገሙ ሰዎች ‘አንቲቦዲ’ በመጠቀም ለኮቪድ-19 መላ መፈለግ የሚለው ነው።
ኮቪድ-19ን ሊፈውስ ይችላል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት መድሃኒት የቱ ነው?
የዓለም ጤና ድርጅት ባልደረባ ዶ/ር ብሩስ አለዋርድ ከቻይና ጉብኘታቸው በኋላ ኮሮናቫይረስን ያድናሉ ተብለው ከተሞከሩ መድኃኒቶች መካከል ውጤታማ ስለመሆኑ ምልክት ያሳየው ሬምዴሲቪር (remdesivir) ብቻ ነው ብለዋል።
ይህ መድኃኒት ከዚህ ቀደም ይውል የነበረው በኢቦላ
 የተያዘን ሰው ለማከም ነበር።
መድኃኒቱ ከኢቦላ በተጨማሪ ሌሎች የኮሮናቫይረስ አይነቶችን ለማከም በእንስሳት ላይ ተሞክሮ አመርቂ ውጤት አሳይቷል። በዚህም ኮቪደ-19ን ሊያክም ይችላል የሚል ተስፋ ተጥሎበታል።
አንድ ሾልኮ የወጣ መረጃ እንደጠቆመው በቺካጎ ዩኒቨርስቲ በተመራ የላብራቶሪ ሙከራ መድኃኒቱ በኮቪድ-19 የተያዘን ሰው ለማከም ውጤታማ መሆኑ ተደርሶበታል።
ይህ መድኃኒት የዓለም ጤና ድርጅት በ’ሶሊዳሪቲ ትሪያል’ ማዕቀፍ ውስጥ ከያዛቸው አራት መድኃኒቶች መካከል አንዱ ይህ ነው። የዚህ መድኃኒት አምራች የሆነው ጊሊድ የተሰኘው ተቋምም በመድኃኒቱ ላይ ምርምር እያካሄደ ይገኛል።
የጸረ ኤችአይቪ መድሃኒቶች ኮሮናቫይረስን ሊያክሙ ይችላሉ?
ሎፒናቪር (lopinavir) እና ሪቶናቪር (ritonavir) የተባሉ የጸረ ኤችአይቪ መድኃኒቶች በኮቪድ-19 የተያዘን ሰው ለማከም ይውላሉ የሚሉ መላምቶች በስፋት ቢኖሩም ለዚህ ማረጋገጫ አልተገኘም።
በላብራቶሪ ደረጃ መድኃኒቶቹ ውጤታማ ስለመሆናቸው ማረጋገጫዎች ቢኖሩም በሰዎች ላይ የተደረጉ የሙከራ ውጤቶች ግን አጥጋቢ ሳይሆኑ ቀርተዋል።
መድኃኒቶቹ በኮቪድ-19 ተይዘው በጠና ለታመሙ ሰዎች ቢሰጡም የመጨረሻ ውጤታቸው፤ ታማሚዎቹ ከበሽታው አላገገሙም፣ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥርም አልቀነሰም አልያም በሰውነት ውስጥ የሚገኘው የቫይረስ መጠን አልቀነሰም።
ጸረ-ወባ መድኃኒቶችስ ኮሮናቫይረስን መግታት ይቻላቸዋል?
የጸረ-ወባ መድኃኒቶች የዓለም ጤና ድርጅት እና ዩናይትድ ኪንግደም የሚያደርጓቸው ምርምር አካል ናቸው።
ክሎሮኪን እና ሃይድሮክሎሮኪን የተባሉ የጸረ-ወባ መድኃኒቶች ፕሬዝድነት ትራምፕ ኮቪድ-19ን ለማከም ሊውሉ እንደሚችሉ መጠቆማቸውን ተከትሎ መድኃኒቶቹን የመጠቀም ዝንባሌ በስፋት ተይቷል። ይሁን እንጂ መድኃኒቶቹ ከኮቪድ-19 ስለመፈወሳቸው ማረጋገጥ አልተቻለም።
የዓለም ጤና ድርጅትም የመድኃኒቶቹ ውጤታማነት ላይ እስካሁን ማረጋገጫ አልተገኘም ብሏል።
የበሽታ መከላከል አቅምን ከፍ የሚያደርጉ መድኃኒቶችስ?
የሰውነት የበሽታ መከላከል ሥርዓት ቫይረሱን ለመዋጋት ከተገቢው በላይ ምላሽ ከሰጠ፤ ሰውነታችን ይቆጣል። ኮቪድ-19ን ለመከላከል የሰውነት የበሽታ መከላከል ሥርዓት ላይ መመርኮዝ ጠቃሚ ቢሆም፤ ይህን ሥርዓት ከተገቢው በላይ ከፍ ማድረግ ግን አደጋ ሊያስከትል ይችላል።
የዓለም ጤና ድርጅት እያከናወነ ያለው ‘ሶሊዳሪቲ’ የተባለው ሙከራ ‘ኢንፌርኖ ቤታ’ የሚባል ኬሚካልን እየመረመረ ይገኛል። ‘ኢንፌርኖ ቤታ’ የንጥረ ነገሮች ስብሰብ ሲሆን ሰውነታችን በቫይረስ ሲጠቃ ቫይረሱን ለመከላከል በሰውነታችን ውስጥ ይለቀቃሉ። የሰውነት መቆጣትንም ይቀንሳሉ ተብሏል።
ዩናትድ ኪንግደም ደግሞ የሰውነት መቆጣትን የሚቀንስ የመድኃኒት አይነትን እየመረመረች ትገኛለች።
ከኮቪድ-19 ያገገሙ ሰዎች ደም በሽታውን ለማከም ይውል ይሆን?
ከኮሮናቫይረስ ያገገሙ ሰዎች ቫይረሱን የሚዋጋ አንቲቦዲ ይኖራቸዋል።
ሃሳቡ ከበሽታው ያገገመ ሰው አንቲቦዲ ያለበት ደም በመውሰድ በበሽታው የሚሰቃይን ሰው ለማከም ጥቅም ላይ ማዋል ነው።
አሜሪካ እስካሁን 500 ሰዎችን በዚህ መንገድ እክማለች። ሌሎች አገራትም የአሜሪካንን ፈለግ እየተከተሉ ነው።
መድኃኒት እስኪገኝ ምን ያክል ጊዜ እንጠብቅ?
በቅርቡ ከኮቪድ-19 የሚፈውስ መድኃኒት መቼ ተግባር ላይ እንደሚውል እንሰማለን።
ከዚያ በፊት ግን በቀጣይ ጥቂት ወራት የመድኃኒቶቹ ውጤታማነት ላይ የላብራቶሪ ግኝቶችን እንሰማለን። በትክክል መናገር የሚቻለው ግን ከክትባት ቀድሞ መድኃኒት ተግባር ላይ ይውላል።
ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ተመራማሪዎች እና ዶከተሮች የሚመራመሩበት ወይም ለታማሚዎች የሚሰጡት የመድኃኒት አይነቶች ደህንነታቸው የተረጋገጠና ከዚህ ቀደም የሚታወቁ ወይም የነበሩ መድኃኒቶች በመሆናቸው ነው።
ክትባት ለማግኘት ምርምር የሚያደርጉት ተመራማሪዎች ግን ሥራቸውን ከዜሮ ነው የጀመሩት፤ ይህም ምናልባት ወራትን ወይም ዓመታትን ሊጠይቅ ይችላል።
አሁን በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎች የሚታከሙት በየትኛው መድኃኒት ነው?
በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች በአሁኑ ጊዜ በሽታው ካልጠናባቸው በቤት ውስጥ እራሳቸውን ለይተው በመቀመጥ እረፍት እንዲያደርጉ፣ የህመም ማስታገሻዎችንና በርከት ያለ ፈሳሽ እንዲወስዱ ይመከራል።
በጽኑ የታመሙ ደግሞ በሆስፒታል አልጋ ላይ ሆነው ለመተንፈስ የሚያግዛቸው ቬንቲሌተር ተገጥሞላቸው እንደየ ሃገሩ መመሪያ መሠረት መድኃኒቶች ሊሰጣቸው ይችላል።
Filed in: Amharic